ስዩም ተሾመ

ከዴሞክራሲ ቅፅበት ወደ አምባገነናዊ ፅልመት በ10 አመት

ከድጋፍና ተቃውሞ ባሻገር ሁላችንም የኢህአዴግ መንግስት የሚመራበትን መርህና መመሪያ በጥንቃቄ ማጤንና ማወቅ ይኖርብናል። ተወደደም-ተጠላ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ ነው። በመሆኑም፣ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ባህሪ ማወቅ አለባቸው። ምክንያቱም፣ አላዋቂ ደጋፊ መንግስትን ለውድቀት ይዳርጋል። አላዋቂ ተቃዋሚ ደግሞ የለውጥ እንቅፋት ይሆናል። ስለዚህ፣ ሁላችንም “የተወሰነም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት ለምን ተመልሶ አምባገነን ሆነ?” ብለን መጠየቅ አለብን።

በእርግጥ “እንዴ…ለመሆኑ የኢህአዴግ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ሞክሮ ያውቃል እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። “ለሰይጣንም ቢሆን የድርሻውን መስጠት ጥሩ ነው” ይባላል። የኢህአዴግ መንግስትም ቢያንስ በ1987 ዓ.ም ባፀደቀው ሕገ-መንግስት እና በ1997ቱ ምርጫ (እስከ ምርጫው ዕለት ማታ ድረስ) ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ጥረት ማድረጉ ሊታወስ ይገባል። ይሁን እንጂ፣ ከ1997 ዓ.ም በፊት “ሕገ-መንግስቱ ይከበር!” ሲል የነበረው የኢህአዴግ መንግስት በቀጣይ አስር አመታት ግን ሕገ-መንግስቱን የሚጥሰው እሱ ራሱ ሆነ።

የኢህአዴግ መንግስት በ2002ቱ ምርጫ 99.6%፣ በ2007ቱ ደግሞ 100% “አሸነፍኩ” ብሎ ተሳልቋል። ይህ “የይስሙላ ምርጫ” ግን በዴሞክራሲ መቃብር ላይ የበቀለ አረም ነው። የኢህአዴግ መንግስት፤ በፀረ-ሽብር ሕጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ በሚዲያና የመረጃ ነፃነት ሕጉ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሲቪል ማህበራትን አጥፍቷቸዋል።

የኢህአዴግ መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን የዴሞክራሲ ተቋማት ከማጥፋቱ በተጨማሪ፣ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን የራሱን አመራሮች “በሃይማኖት አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት ወይም ትምክህተኝነት” እየፈረጀ የተወሰኑትን ለእስርና ስደት ሲዳርጋቸው፣ የተቀሩት ደግሞ ሃሳባቸውን ከመግለፅ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል። በአጠቃላይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ እና የሲቭል ማህበራት ከሌሉ፣ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ከሌለው ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (Constitutional Democracy) አብቅቶለታል።

በአጠቃላይ በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ የታየው የዴሞክራሲ ቅፅበት ከአስር አመት በኋላ ሙሉ በሙሉ በአምባገነናዊ ፅልመት ተውጧል። በተለይ የፀረ-ሽብር ሕጉ ከወጣበት ግዜ ጀምሮ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ስር የተዘረዘሩት አብዛኞቹ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ተጥሰዋል። በተደጋጋሚ ጥሰት ከተፈፀመባቸው ውስጥ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 14፥ 15፥ 16፥ 17፥ 18፥ 19፥ 20፥ 21፥ 25፥ 26፥ 27፥ እና 28 ላይ የተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም በአንቀፅ፡- 29፥ 30፥ 31፥ 37፥ 38፥ 40 እና 44 ላይ የተደነገጉት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

“የሕዝብ ሉዓላዊነት” ወይስ “የብሔር ሉዓላዊነት”?

በመሰረቱ የኢሀአዴግ መንግስት እንደ መንግስት የተቋቋመው እነዚህን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር ነበር። ይሁን እንጂ፣ እነዚህን መብቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጥሰው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ ነው። ታዲያ፣ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተደጋጋሚ የሚጣሱበት ምክንያት ምንድነው? የኢህአዴግ መንግስት ለምን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር እንደተሳነው ለማወቅ በፅሁፌ መግቢያ ላይ እንደገለፅኩት መንግስታዊ ስርዓቱ የሚመራበትን መርህና መመሪያ በጥሞና ማጤን ያስፈልጋል።

ማንኛውም ሰው በራሱ አመለካከት ትክክል የመሰለውን ነገር ያደርጋል። ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ግን ከግል አመለካከታቸው ባለፈ ሥራና ተግባራቸው የሚመራበት ፖሊሲ፥ መርህና መመሪያ አላቸው። ለእነዚህ ደግሞ ዋና መሰረታቸው ሀገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ-መንግስት ነው። ምክንያቱም፣ የመንግስት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

በእርግጥ አምባገነናዊም ሆኑ ዴሞክራሲያዊ መንግስታት በሕገ-መንግስታቸው ውስጥ፤ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የሕግ-የበላይነት፣ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት፣ የዜጎች መብትና ነፃነት፣…ወዘተ የሚሉ መሰረታዊ መርሆች አሏቸው። ነገር ግን፣ በተለይ አምባገነን መንግስታት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማረጋገጥ በሚል ሰበብ የዜጎችን መብትና ነፃነት ሲጥሱ ይስተዋላል። ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት ሀገሪቷንና ሕዝቡን ሲያስተዳድር የነበረው የዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚገድቡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ነው።

ባለፉት አስር አመታት የታየው የኢህአዴግ መንግስት አስተዳደር ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ተፃራሪ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለምሳሌ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 12 መሰረት “የመንግስት አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት አለ” እንዳይባል ባለፉት አስር አመታት ሙስና እና ብልሹ አሰራር ምን ያህል እንደተንሰራፋ መንግስት ራሱ ጠንቅቆ ያውቃል። በአንቀፅ፡-11 መሰረት “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም” እንዳይባል በቅርቡ በእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ላይ የተፈፀመውን ግፍና በደል መጥቀስ ብቻ በቂ ነው። እንደ ማዕከላዊና ቅሊንጦ ባሉ እስር ቤቶች በፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣…ወዘተ ላይ የሚፈፀመውን የስቃይ ምርመራና እንግልት የሚያውቅ በአንቀፅ፡-10 መሰረት “የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች” በጭራሽ እንዳልተከበረ ይመሰክራል። በመጨረሻም፣ ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፀረ-ሽብር አዋጁ እየተዳኘ ባለበት ሁኔታ በአንቀፅ፡-9 መሰረት “የሕገ-መንግስቱ የበላይነት ተረጋግጧል” ሊባል አይቻልም።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከሕገ-መንግስቱ አምስት (5) መሰረታዊ መርሆች ውስጥ አራቱን ተግባራዊ እያደረገ እንዳልሆነ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡-8 ላይ የተጠቀሰውን “የሕዝብ ሉዓላዊነት” መርህ ግን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። በእርግጥ በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው የሕዝብን የስልጣን የበላይነት አያሳይም። ከዚያ ይልቅ፣ በንዑስ አንቀፅ 8(1) ላይ እንደተገለፀው፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መሰረታዊ መርህ፤ “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው” በሚል ተገልጿል። ቀጥሎ ባለው ንዑስ አንቀፅ 8(2) ደግሞ ሕገ-መንግስቱ (የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች) ሉዓላዊነት መገለጫ” እንደሆነ ይገልፃል።

በሕገ-መንግስቱ መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በተግባር “የብሔር ሉዓላዊነት” ነው። ምክንያቱም፣ የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች” እንጂ የሀገሪቱ ዜጎች አይደሉም። በእርግጥ ይህ መርህ ከተቀሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ጋር ይጋጫል። በመሆኑም፣ ባለፉት አሰር አመታት ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ከመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት፣ ከሕገ-መንግስቱ የበላይነት አንፃር ለተፈጠሩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ዋና መነሻ ምክኒያት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ከላይ የተጠቀሰው መርህ በሕገ-መንግስቱ ከተጠቀሱት መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር ይጣረሳል። በዚህ ምክንያት፣ መንግስት ይህን መርህ ለመከተል ጥረት ባደረገ ቁጥር የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ይጥሳል። በአጠቃላይ፣ በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ ዴሞክራሲ እንደ ተወርዋሪ ኮኮብ ለቅፅበት ታይቶ እንዲጠፋነና በምትኩ አምባገነናዊ ፅልመት የሰፈነው የኢህአዴግ መንግስት ከሌሎች የዴሞክራሲ መርሆች ይልቅ ይሄን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከሩ ምክንያት ነው።

ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። እነሱም፣ አንደኛ፡- “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ መሆኑ እና ሁለተኛ፡- ፖለቲካዊ ስርዓቱ በዚህ የተሳሳተ መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ናቸው። በሚቀጥለው ክፍል “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ብሔር ወይስ ግለሰብ?” በሚል የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 የተመሰረተበትን የተሳሳተ እሳቤ በዝርዝር እንመለከታለን።