እውነት ለዕውቀት ብቻ ተገዢ ነው!

ሀገራችንም ብሄራችንም ኬኒያ ናት። የምንፎካከረው ይህቺኑ ሀገር ለመለወጥ ነው እንጂ ለሌላ አይደለም። ስለዚህ ተቃዋሚም ሆንን ደጋፊ በጋራ መስራት ይኖርብናል። በውድድር አንዱ ማሸነፍ ሌላው መሸነፍ ያለ ቢሆንም ስላሸነፍናችሁ የምናጎድልባችሁ አንዳች ነገር አይኖርም። እኔ እጆቼን ወደ ተቀናቃኜም ሆነ ወደ ደጋፊዎቻቸው እዘረጋለሁ። ኑ ለሀገራችን በጋራ እንስራ!” – ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ

…..ከማክሰኞው የምርጫ እለት በኋላ ናይሮቢ አይኗን ጠራርጋ የነቃችው የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ማለዳ ወፍ ክንፉን ሳይታጠብ ብድግ ብለው “የምርጫውን ውጤት አንቀበልም፣ የተጭበረበረ ነው” ብለዋል በሚለው አስደንጋጭ ዜና ነበር።……. በዚህ ምክኒያት ላለፉት አራት ቀናት ከተማዋ ጸጥ ረጭ እንዳለች ቆየች።

አይኖች ሁሉ ወደ ቴሌቪዥን ቻናሎች አቅንተዋል። እውነታው ጎዳናው ላይ ሳይሆን የቴሌቪዥን ስክሪኖች ላይ ነው ያለው። ጎዳናውማ ሰው እንደናፈቀ አራት ቀኑ። ቴሌቪዢኖቹ ግን በየደቂቃው ዜና ያመነጫሉ፡፡

ይህ የተጠበቀ ነበር።…….ከወራት በፊት ነው ናይሮቢያውያን ሱፐርማርኬቶችን ሲያጨናንቁ የከረሙት። “ምርጫው ደርሷል በጊዜ አስቤዛችሁን ሸማምቱ!” የሚለው መልእክት የሁሉም ነበር።……. ምርጫው ምን ይዞ እንደሚመጣ አይታወቅማ!

…….ዛሬ ዛሬ ለአፍሪካውያን ምርጫ የሚሉት የስልጣን ማሸጋገሪያ ስርአት የጦርነት ያህል አስፈሪና የብዙዎችን ህይወት ለሞት፤ ገሚሱን ለእስር እንዲሁም ለስደት የሚዳርግ እየሆነ ነው።

አንድ አፍሪካዊት ሀገር ምርጫ ልታካሂድ ነው ሲባል ስጋት፣ ፍርሀት፣ ሽሽት፣ ጭንቀት ይነግሳል። ህዝብ ያልፈለገው ተቃዋሚ “እንዴት ሆኖ!” ሲል በአደባባይ ይፈክራል። ወንበር የያዘውም “ማን ባቀናው?” በሚል ንፉግነት የምርጫ ውጤቱን ወደ ጎን ገፍቶ የራሱን ሌላ መንገድ ይከተላል። በዚህም ሰበብ በሚነሳ ግጭት ተራው ህዝብ ለሞት ይዳረጋል።

……. አሁን መላ ኬኒያውያን ተሸብረዋል።……ዜናው ይቀጥላል። የተቃዋሚው ሁነኛ መሰረት የሆኑት በናይሮቢ የሚታወቀው “ኪቢራ” የተባለው መንደርና የ”ኪሱሙ” ክፍለ ግዛት ረብሽ ተነስቷል።…….. በተለይ ደግሞ የተቃዋሚው ደጋፊዎች “ራይላ ከሌለ ሰላም የለም!” የሚለው መፈክር ከተሰማ በኋላ ነገሩ እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ እንዳልሆነ ተገምቷል

……ይህ በሚሆንበት ወቅት ሁሉ የኬኒያ ሚዲያዎች በምርጫ ኮሚሽኑ አዳራሽ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሁነት በቀጥታ ስርጭት እንዲሁም ተቃዋሚዎች የሚሰጡትን መግለጫዎች በሰበር ዜና እግር ከእግር እየተከታተሉ ለህዝብ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። ….ጣቢያዎቹ የሙሉ ሰአት የዜና እወጃቸውን ሙሉ በሙሉ ሰርዘዋል። ህዝብ ለመረጃ ጆሮውን አቁሞ ሳለ ለዜና እንዴት ሰአት ይጠበቃል?

…… የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን….ወዘተ የሚሰጡት መግለጫና ማብራሪያ ሁሉ በየደቂቃው ለህዝብ ጆር ይደርሳል።……..የምርጫ ኮሚሽኑ ከአስር በላይ ጊዜ ለህዝብ መረጃዎችን ሲያቀርብ ጋዜጠኞች ከተቃዋሚዎችም ሆነ ከህዝብ የሰበሰቧቸውን ጥያቄዎችና ስጋቶች ለምርጫ ኮሚሽኑ እያቀረቡ ምላሽ እንዲሰጥባቸው አድርገዋል።…………. በአንዳንድ ቦታ ለታዩት የተቃውሞ ድምጾችም የጸጥታ ሀላፊው “በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞዋችሁን ማሰማት በህገ መንግስቱ የተፈቀደላችሁ መብት ነው።……” በማለት ዜጎች ከግጭት ይልቅ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ማንኛውንም የተቃውሞ ስሜታቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርገዋል።…በዚህም ምክኒያት የኬኒያ ሰላም በፍጥነት ወደ ቦታው ተመልሷል።

ኬኒያውያን ከዘር አስተሳሰብ ይልቅ ወደ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ከፍ ማለትን ያመላከተው የኡሁሩና የኦዲንጋ ውጤት (54/44)

********

በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካ የሚባለው (ሀገር የማስተዳደር ጥበብ) የሚዘወረው በፖለቲከኞቹ ዘር (ብሄር)( የትመጤነት) መሰረት ያደረገ ነው። ፖለቲከኞቹም በሚያቀርቡት የፖለቲካ መርህ፣ የጠራ ፖሊሲ ወይም የፖለቲካ ብስለት ይልቅ በህዝቦች መካለከል ያለውን (Group thinking, Group identity) መጠቀሚያ ያደርጉታል።……. ህዝቡንም “ምን ይዞልን መጣ?” ሳይሆን “ማን መጣ?” በሚል ጥያቄ ወደ ምርጫ ጣቢያ ይልኩታል።

…..በዚህ ደግሞ ሁሌም እንደ ምሳሌ ስትነሳ የኖረችው ሀገረ ኬኒያ ናት። የኬኒያ ፖለቲካ በዘር አስተሳሰብ (Race thinking) እንደሆነ ይነገራል።…

በዚህ የ2017 ሀገራዊ ምርጫ ግን (በኔ እይታ) ኬኒያውያን ጥያቄያቸው “ማን ነው?” ሳይሆን “ምንድነው?” የሚል እንደሆነ በምርጫ ድምጻቸው አሳይተዋል። ለተፎካካሪዎቹ የተሰጡት ድምጾች እንደሚያመለክቱት ሁለቱም የኔ ከሚሉት ጎሳ የተወሰኑ ድምጾችን እንዳጡና እንዲሁም ባልጠበቁባቸው ስፍራዎች የተሻለ ድምጾችን መሰብሰባቸው ነው።

……ዛሬ እለተ እሁድ ከቀኑ ስድስት ሰአት ሙዋንጊ ቲካ ሮድ በሚባለው (high way) እያሳበረ ወደ (Down-town) አሳፍሮኝ እየነዳ ነው።…… ሙዋንጊ ናይሮቢ ከገባሁ ጀምሮ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጠኝ ሾፌር ሲሆን ሰው ካልጠየቀው በስተቀር የማያወራ ዝምተኛ ሰው ነው።…… ላወራው ፈልግያለሁ።….

“What is your opinion? ስለምርጫው ምን ታስባለህ?” አልኩት።…… “You know, election comes and go but Kenya, ምርጫ ይመጣል ይሄዳል። ከኒያ ግን ሁሌም ትኖራለች።” አለኝና ዝም አለ…….

“About the result?” ትንሽ ገፋ አድርጌው የልቡን እንዲያወራኝ ፈለኩ። “ውጤቱን እንዴት አገኘሀው?” …….. “You know, there is always another day, another chance…”

ሙዋንጊ የመረጠውን እንዳላገኘ አውቅያለሁ። ነገር ግን ደግሞ ያልመረጠውን እንደተቀበለና ለነገው ደግሞ ተስፋ እንዳለው አነጋገሩ ይናገራል።……

የኬኒያ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነበር?

ይህ ጥያቄ ሊመለስ የሚገባው “ከማን ጋር ሲነጻጸር?” የሚለው ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ ነው። ከየትኛው ሀገር ምርጫ ጋር ሲነጸጸር ነው ኬኒያውያንን እና የኬኒያን የመንግስት መዋቅር ማመስገን የሚገባው

እንደ አንድ የሌላ አፍሪካ ሀገር ታዛቢ ስመለከተው …..ይህ ሁሉ የምርጫ ታዛቢ፣ ይህ ሁሉ ገለልተኛ የሚዲያ ተቋም፣ ይህ ሁሉ የአደባባይ ላይ መረጃ፣ እንዲህ ያለ ትእግስተኛና መፍትሄ አፈላላጊ ፖሊስና መከላከያ፣ ይህ ሁሉ ……. የትኛው የአፍሪካ ሀገር ነው ያለው? ከዚህ የተሻለ ያለው ሀገር ያለ እንደሆን ያኔ ስለ ኬኒያ ምርጫ ኢዴሞክራሲያዊነት እናወራ ይሆናል! እስከዚያ ግን ብልህ ከጎረቤቱ ይማራልና ከዚህ ሁሉ አንዱም የሌለን እኛ ልክ እንደ ጀማሪ፣ ዛሬ እንደተሰራ ሀገር፣ ሶስት ሺህ አመታት መንግስት እንዳላየን ከባለ ሀምሳ አመት እድሜዋ ኬኒያ እንማራለን!! እናም የኬኒያ 2017 ህዝባዊ ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ነበር!!!

<p style=”border:0;outline-color:initial;outline-style:initial;vertical-align:baseline;background:transparent;margin-right:0;margin-bottom:0;margin-left:0;padding:0;”>

Asanteni Sana!! ካሪቡ ኬኒያ!!

ተፈጸመ!–

Ethiopian Think Tank Group