August 15, 2017

ኢትዮጵያዊነት:: የዘውጌ ብሄርተኞች የጥቃት ኢላማ

ሰሞኑን የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች በብሔራዊው ጀግና አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ላይ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ የዚህ በኃይሌ ላይ የተከፈተው የማጠልሸት ዘመቻ ሰበብ የሩጫ ውድድር ስናደርግ በ”ኢትዮጲያዊ መንፈስ” ይሁን ማለቱ መሆኑ ደግሞ ነገሩን በልዩ ትኩረት እንድንመረምረው ያደርጋል፡፡ ዘውገኞች ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን በሚያጎሉና ርዕዮቱን በሚያራምዱ ግለሰቦች ላይ ሰብዕናን የመግደል ዘመቻ ሲያካሂዱ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በተጠራች ቁጥር፣ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ባለ ቁጥር የሚቀሰቀስ ህመማቸው መገለጫ ነው፡፡

የዘመቻውን ዳራ በጥቂት ምሳሌዎች

ይህ ዘመቻ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ባሉ የርዕዮተአለም ወንድማማቾች ቅንጅት፣ በስልጣን ላይ ባለው መንግስትና ስልጣን ካለመያዛቸው በቀር ከአገዛዙ ጋር አንዳችም ልዩነት በሌላቸው የኦሮሞ ብሄርተኞች ጥምረት የሚካሄድ የተደራጀ ክንውን ነው፡፡ ይህም የተቀናጀ ክንውን በተለያየ ጊዜ እራሱን ከስቷል፡፡

1. ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ጥቁር ሰው የተሰኘውን ዘፈን በማውጣቱና አስተሳሳሪ መልእክቶችን በማዜሙ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን እንዳያቀርብ ለማደናቀፍና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የገባው የስራ ስምምነትና ውል እንዲቋረጥ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡

2. የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሀይሌ ላሬቦ በኢሳት ቴሌቪዥን ቀርበው ለዘውገኞቹ ከፋፋይ ርዕዮት የማይስማማ፣ ነገር ግን በማስረጃ የበለጸገ የታሪክ ትንተና ማጋራታቸውን ተከትሎ፣ ስማቸውን የማጠልሸትና ሰብዕናቸውን የማቆሸሽ እኩይ ተለምዶአዊ ተግባራቸውን በመገናኛ ብዙሀኖቻቸውና በየማህበራዊው ድረገጽ ከማጧጧፋቸውም በላይ፤ ከሚያስተምሩበት ከታዋቂው ኮሌጅ እንዲሰናበቱ የሚጠይቅ ማመልከቻ ተፈራርሞ እስከመላክ ደርሰው ነበር፡፡

3. አሁንም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ላይ በመፈጸም ላይ ያሉት የዚሁ ተግባራቸው ተቀጥላ ነው፡፡ ወደ ኃይሌ ገብረስላሴ ፊታቸውን ያዞሩት አስቀድመን እንደጠቆምነው ተወዳዳሪ አትሌቶችን ሰብስቦ ስንሮጥ ኢትዮጵያን እያሰብን በኢትዮጵያዊ መንፈስ ይሁን ሲል በመናገሩ ነው፡፡ ኃይሌ ነፍጠኛ የሚል ጫማ አሰርቷል ይሉትን በሬ ወለደ ያመጡትም ለዚህ እኩይ ዘመቻቸው ድጋፍ ነው፡፡ አንድም ተጨባጭ ማስረጃ ግን የለም፡፡

ነፍጠኛነት

በማንኛውም ስፍራና ዘመን አገር በመስራት ሂደት ውስጥ መሪ ተሳታፊ የሆነና ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞቹን የሚያስጠብቅ ማናቸውም ቡድን፣ አገዛዝ፣ መንግስት፣ አካል ወዘተ በዚህ በነፍጠኝነት ብየና ውስጥ ይወድቃል፡፡ በአገራችን አውድ ቃሉን ብንመለከተው ደግሞ ነፍጠኝነት አገር ሰሪነትና አቅኚነት ነው፡፡ በጭብጨባ የተሰራ ሃገር የለም፡፡ ደም ፈስዋል፡፡ አጥንት ተከስክስዋል፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ ተፈራርቀዋል፡፡ አገር መስራትና አገር ማቅናት ደግሞ ኩራት ነው፡፡ ነፍጠኝነት የብሄር ማንነት የለውም፡፡ ነፍጠኝነት አንዱን ብሄር ይበልጥ የሚመለከት ሌላኛውን ደግሞ የማይነካ አይደለም፡፡ ዘውገኞቹ እንደሚያደርጉት በማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችልን ታሪክ የካደና የራሱን አዲስ ተረት የፈጠረ ካልሆነ በቀር፣ ኢትዮጵያ እንድትሰራ ያልተካፈለና ያልሞተ የለም፡፡

ኢትዮጲያ ኢትዮጲያ በሚሉ ሰዎች ላይ የሚዘምቱት ለምንድነው?

ለዘውገኞቹ አጥር መስራትና በልዩነት ስንጥቆች ላይ ሽብልቅ መክተት የህልውናቸው ዋስትና ነው፡፡ የርዕዮተአለም እስትንፋሳቸው ያለአጥርና ልዩነት፣ ያለጠብና ክስ፣ ያለሰለባነት ምሬትና ጥላቻ እራሱን ችሎ አይቀጥልም፡፡ ውህደት ያጠፋቸዋል፡፡ ስምምነት ይውጣቸዋል፡፡ ፍቅር ይኮሰኩሳቸዋል፡፡ ጌጥና መልካችን የሆነውን ብዙነት እንድንፈራራበት፣ እርስ በእርስ እንድንጠራጠርበት ካላደረጉ የግል ጥቅማቸውንና የጨነገፈ ርዕዮታቸውን ከግብ ማድረስ እንደማይችሉ ተገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም፣ ይህ ለእነርሱ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን ጥላቻ ለማግለብለብ ጭዳ የሚያደርጓቸው አገር ወዳድ ግለሰቦች ያስፈልጓቸዋል፡፡

በትርክታቸው ትላንት ተፈጸመ የሚሉት ጭቆናና ግፍ ከፍተኛውን ስፍራ ቢይዝም፣ እነርሱም ከአስተሳሰባቸው የተለየን ሁሉ ከመደፍጠጥ የማይመለሱ፣ ሌላ የማሰብ መንገድን የማይታገሱ፣ የተለየ የሀሳብ ስስ ነፋስ ሽው ሲል እንኳ የሚያምማቸው ጨፍላቂና አምባገነን ናቸው፡፡ ሞግቶ የሚረታ፣ ተከራክሮ የሚበልጥ አተያይ የላቸውምና አማራጭ ሀሳብ በማሳው እንዳይበቅልና ፖለቲካዊ መሰረታቸውን እንዳያሳጣቸው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል መልእክት በየቦታው የማሰራጨት መብትን ለእራሳቸው የሸለሙ፣ ሌላው ግን ስለውድ ሀገሩና ስለሚኮራበት ዜግነቱ ሲናገር ስልጣን ላይ ያሉት በመሳርያ፣ ስልጣን ያልያዙት በኢንተርኔት ዘመቻ ሊያፍኑ እንቅልፍ የላቸውም፡፡ እናም፣ በቅንጣት አመክንዮና በጥቂት ማስረጃ ትርክታቸው እንደሚተንን ያውቃሉና፤ ኢትዮጵያዊነትን ማንነቱ ያደረገ ግለሰብ ያስደነብራቸዋል፡፡ ስለሆነም፣ የማሳደዳቸው ኢላማ ነው፡፡ ቅስታቸው በግለሰቡ ሰብዕና ላይ ቢሆንም አብይ የጥቃት ኢላማቸው ግን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው፡፡

በውስጣቸው ያለውን ክፍፍል ለማረቅም ይህንን ስልት ይጠቀሙበታል፡፡ እውስጣቸው ላሉት የበዙ የፍላጎትና የጥቅም ግጭቶች ማርገብያና ህብረቱን አጣብቆ ለማቆየት የሚያቆራኝ ጠላት ይፈበርካሉ፡፡ ይህም የአምባገነኖችና የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች ተዘውታሪ ዘዴ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ዘውገኞቹ የሰልፋቸውን ወጥነት ለማረጋገጥና ከወደውስጥ የሚጠዘጥዛቸውን የእርስ በእርስ ልዩነት ለማስታመም ለኢትዮጵያዊ ማንነት የቆሙ ግለሰቦችን የመስዋእት በግ ማድረግ እንዳለባቸው ያምናሉ፤ ይተገብሩታልም፡፡

ይህንን ሆይሆይታ በመስጋትም ሌሎች ግለሰቦች በአደባባይ ስለኢትዮጵያ እንደሀገርና ስለኢትዮጵያዊነት እንደብሄራዊ ማንነት እንዳይናገሩ የማሸማቀቅ አላማም አለው፡፡ እናም፣ በፖለቲካው ምህዳር ህይወት ያለው መስሎ እንዲታይ የሚሹት ከጨለማና መለያየት በቀር፣ ከልዩነትና ፉክቻ በቀር ሌላ የማይታየው የማነስ መነጽራቸው ነው፡፡

መፍትሄዎች

ዘውገኞቹ በእነዚህ ስለኢትዮጵያ በሚናገሩና ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅኑ ግለሰቦች ላይ በሚዘምቱበት ወቅት በተቀናጀ መልኩ መከላከል ሌሎችም አንገታቸውን እንዳይደፉ ያስችላል፡፡ ጥቃቱ እየተፈጸመ ያለው በግለሰቦቹ ላይ ሳይሆን በኢትዮጵያዊ መንፈስና ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ነው፡፡ ለሀገሬ ፍቅር አለኝ የሚል ሁሉ ይህንን ክቡር ማንነት በመከላከል የዜግነት ግዴታውን ቢወጣ ግልጋሎቱ ትልቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ወይም ኢትዮጵያዊ ማንነት ለዘመናት የተሰራና ላብ፣ ደምና ጥበብ የፈሰሰበት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም፣ ይህ የዘመናት ስራ ተከታታይ ጥበቃና ክብካቤ ካላገኘ ቀላል የማይባል ጉዳት እንደሚደርስበት ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ የሆኑ መገናኛ ብዙሀን ኢትዮጵያዊነትን መስበክ የመፈጠራቸው ምክንያትና የሁልጊዜ ትኩረታቸው እንዲያደርጉት ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ከሚያደርጉት መንግስትን በተለያዩ ቃላት ከማውገዝና ከፕሮፖጋንዳ በተሻገረ መልኩ ብሄራዊ ስሜትን ለማጠናከርና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጥበቅ የሚበጁ በማንም ሊደመጡ የሚችሉ ዝግጅቶችን ማሰራጨት ይገባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው ርዕዮቱ በህዝብ መሀል ስሩን እንደሰደደ እንዲዘልቅ አንድን ድምጻዊ ወይም በሌላ ሞያ የተሰማራ ሰው አሸማቅቆ ይቅርታ ከማስጠየቅ ፋይዳ ቢስ ተግባር ተላቅቆና አድጎ፣ የሀገርን ነገ በሚያሳምር እንዲህ ባለ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ከዘውገኞች ጥቃት በመከላከል ላይ ቢሳተፍ እንደሚበጅ እናምናለን፡፡ ፕሮፌሰር ሀይሌ ላሬቦን መሳ ለመሳ ተሟግቶ የሚከላከል ድርጅትም ሆነ የመገናኛ ብዙሀን አለመኖር፣ አሁንም አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴን ኢትዮጵያዊ መንፈስ በማለቱ ከሚደርስበት ጥቃት የሚታደግ ወገን አለመኖር ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው የሚጠበቅበትን አለማከናወኑን ያመለክታሉ፡፡

ኢትዮጵያችንን የትኛውም ዜጋ፣ በብሄሩ፣ በኢኮኖሚያዊ ደረጃው፣ በሀይማኖቱ፣ በቆዳው ቀለም፣ በጾታው ወዘተ የማይገለልባት፣ ነጻነትና ዲሞክራሲ የሚያብቡባት እንድትሆን ለማድረግ ካለንበት የፖለቲካ ርዕዮትም እየተሻገርን ጭምር የጋራ የመጫወቻ ሜዳ እንፈጥር ዘንድ ተምኔትና ጥሪያችን ነው፡፡

አሁንም እንላለን፣ በሩጫ ውድድር ስንሳተፍ፣ በህክምና፣ በምህንድስና፣ በመምህርነት፣ በውትድርና፣ በኪነጥበብ ና በሌላ በማንኛውም ሞያ ስንሰማራ፣ በህግ ማስከበር ሜዳ ስንገኝ፣ በጋዜጠኝነት በካሜራና ማይክሮፎን ፊት ስንቆም፣ የፖለቲካ ስራ ስናከናውን በኢትዮጵያዊ መንፈስ እና በኢትዮጵያዊ ርዕዮት ይሁን፡፡

Source: http://www.mereja.com/amharic/542196