ጀርመን የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲን በመጥቀስ ዊኪ ሊክ አሜሪካና የአዉሮፓ ሕብረት የአሰብ ጉዳይ መፈታት እንዳለበት ለኢትዮጵያ መንግስት ማሳሰባቸውን ግልጿል። በሌላ በኩል፣ በአሜሪካ የሕግ ፕሮፌሰር የነበሩት እውቁ ኢትዮጵያዊ የሕግ ሰው ዶር ያእቆብ ሃይለማሪያም፣ የሕግ ባለሞያና የቀድሞ የአየር ሃይል አዝዥ የሆኑት ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖትን ጨመሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ፣ የአሰብ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደሚቻል በመገልጽ፣ በርካታ ፣ አሳማኝ ዝርዝር ጽሁፎች አውጥተዋል።

“የአሰብን ወደብ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማስመለስ ይቻላል የሚሉ ወገኖች አሉ። በርግጥ ይሄ መንገድ አለ ወይ ? ካለስ ኢሕአዴግ በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን ግልጽ አቋም አይዝም” በሚል በኢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የቀድሞ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “ከሕግ አኳያ ስንሄድ  ወደብ የሌላቸው አገሮች የሌላ አገር ወደብ ይወስዳሉ የሚል አለም አቀፍ ሕግ የለም።ሊኖር ይችላል ብሎ መገመት መሐይምነት ነው” ሲሉ የምሁራኑን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ዝብ የሚጠቅም አስተያየት አጣጥለዉታል። እንግዲህ እናስበው እነ ዶር ያእቆብን ነው አቶ መለስ መሐይም ብሎ ሲሳደቡ የነበሩት።

አቶ መለስና የሕወሃት  ጓዶቻቸው፣  “ሶማሊያን እና ሲዊዘርላንድ እንደ ምሳሌ በመጥቀስም፣ ወደብ የሌላት ሲዊዘርላንድ ስታድግ፣ ወደቦች ያላት ሶማሊያ ግን የትም አልደረሰችም” በማለት የወደብ አስፈላጊነትን በማሳነስ፣ ኢትዮጵያ አግራችን ላለፉት 25 አመታት ባህር አልባ ሆኖ እንድትቀር ነው ያደረጉት።

ያ ብቻ አይደለም፣ አሰብና ምጽዋ በኤርትራ ስር ሆነዉም፣ ለጅቡቲ ከሚከፈለው በተሻለ ወጭ በኤርትራ በኩል እቃዎችን ማስገባትና ማስወጣት ይቻል ነበር። ሕወሃት ከሻእቢያ ጋር  ባለው እልህና አፍራሽ ፖለቲካ ምክንያት፣ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ፣  “No war ;  no peace”  የሚል ለማንም የማይጠቅም ፖሊሲን በመዘርጋት፣ በታሪክ፣ በባህልና በሁሉም መስፈርቶች አንድ የሆነዉን ከመረብ በስተደቡብና በስተሰሜን ያለውን ሕዝብ ባላንጣ እንዲሆን ተደረጎ፣ አካባቢዉ የጦርነት ቀጠና ሆኖ፣   ከጀቡቱ በጣም የተሻለ ክፍያ በመከፈል ፣  በጣም ቅርብ የሆኑ አሰብን እና ምጽዋን ኢትዮጵያ መጠቀም እንዳትችል የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው።

ሕወሃት/ኢሕአዴግ  በአሁኑ ጊዜ በአመት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር (ወይም ሃያ አራት ሚሊዮን ብር ) ለጅቡቲ የሚከፍል  ሲሆን ፣ የጅቡቲ ወደብ በቂ ሆኖ ስላልተገኘም፣ እንደ ፖርት ሱዳን ያሉትን በስፋት ለመጠቀም እያሰበ ነው። “ሕወሃቱ” አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በሱዳን በቅርቡ ባደረጉት ጉብኘት “አሁን ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የጅቡቲ ወደብ ከአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የራቀ በመሆኑ ለትራንስፖርት ተጨማሪ ወጪ እየዳረጋት ነው። በመሆኑም ይህን ችግር ለማቃለል የሱዳን ወደብን መጠቀም የተሻለ አማራጭ ነው” ሲሉ በይፋ እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል።

አሁን ኢትዮጵያ ከምንም ነገር በላይ ለአገር ጥቅም የሚያስብ መንግስት ነው የሚያስፈልጋት። አገር በግትርነት አትመራም። የእልህ፣ የጥላቻ፣ የጠብ ፖለቲካ የትም አያደርስም። እርግጥ ነው ያለ ኤርትራ መኖር ብንችልም ኤርትራ ብትኖር ግን የበለጠ እንጠቀማለን። ኤርትራ ታስፈልገናለች። በመሆኑም ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግር በመፍታት ኢትዮጵያ አሰብንና ምጽዋን በቀዳሚነት የምትጠቀምበት መንገድ መፈለግ አለብት።

ምጽዋና አሰብ፣ እንዲሁም ሌላዋ የጅቡቲ ወደብ ታጁራ እያሉ ፖርት ሱዳንን መጠቀም ለኢትዮጵያ አያዋጣም። (ምን አላባት ሕወሃትቶች ሱዳንን ለመጥቀም ካልፈለጉ በስተቀር) አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ”የጅቡቲ ወደብ ከአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የራቀ” ያሉትም አባባል በጣም የተሳሳተ ነው። ለምሳሌ ከፖርት ሱዳን መቀሌ ሃያ አምስት ሰዓት ሲፈጅ፣ ከምጽዋ አምስት፣ ከአሰብ አሥራ ሁለት፣ ከታጁራ አሥር  እና ከጅቡቲ አሥራ ሁለት ሰዓት ነው በመኪና የሚፈጀው። ከፖርት ሱዳን ጎንደር አሥራ አምስት፣ ከፖርት ሱዳን ባህር ዳር አሥራ ስምንት ሰዓት ሲፈጅ ከምጽዋ ጎንደር አሥራ አምስት፣ ከምጽዋ ባህር ዳር ደግሞ አሥራ ሰዓት ነው የሚፈጀው።

እንግዲህ የሕወሃት ፖለቲካ ይሄ ነው። የአገርን ጥቅም በመሸጥ የደረሰውን ጉዳት ተረድቶ፣ ስህተትን በማመን የተሻለ አማራጮችን ከመፈለግ፣  ስህተትን ማድበስበስ፣  አላስፈላጊ ወጭ በማውጣት አገርን ማክሰር፣ ተተኪዉን ትውልድ እዳ ዉስጥ መዝፈቁን ነው ሕወሃት አሁን የተያያዘው። አምስት ሰዓት ወይስ ሃያ አምስት ሰዓት የሚፈጅ መንገድ ይሻላል ? ሲባል እኛ አምስቱን ስንል ሕወሃቶች ግን ሃያ አምስቱን ነው እያሉን ያሉት።

አቶ መለስ የሰጡት አስተያየት

https://www.youtube.com/watch?v=lTyS9bPHr9I

የዊኪ ሊክ ዘገባ

http://hornaffairs.com/2011/02/20/us-eu-on-ethiopia-meles-economics-assab-port-and-election-leaked-cable-of-us-embassy-berlin/