19 Aug, 2017 By ብርሃኑ ፈቃደ

50 በመቶ የወጪና የገቢ ንግድ በፖርት ሱዳን ሊስተናገድ ይችላል ተብሏል      

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሱዳን ለሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች ማስተናገጃ ለመገንባት የሱዳን መንግሥት ለኢትዮጵያ ቦታ መስጠቱ ተገለጸ፡፡

በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና በሌሎች ሁለትዮሽ ግንኙነቶች ዙሪያ ካደረጓቸው ውይይቶችና ስምምነቶች አንዱ የአገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ለማስተናገድ ፖርት ሱዳን አማራጭ ከመሆን ባሻገር፣ ወደቡ ለኢትዮጵያ ሸቀጦች ማስተናገጃ ለመገንባት የሚያስችል ቦታ ማቅረቡን፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ አምባው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ሚኒስትር ዴኤታው ሱዳን ለኢትዮጵያ ያቀረበችው የቦታ መጠን ስፋቱ ምን ያህል እንደሆነ ባይጠቅሱም፣ ሌሎችም አማራጭ ወደቦች ላይ ተመሳሳይ አካሄድ ለመከተል እንቅስቀሴ መኖሩን አልሸሸጉም፡፡ ይሁንና በየትኞቹ አገሮች ውስጥ መንግሥት ኢንቨስት ያደርጋል የሚለው ገና ይፋ እንዳልተደረገ አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል፡፡ ምን ያህል ገንዘብ ለኢንቨስትመቱ እንደሚመደብም ይፋ አልተደረገም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የአገሪቱ 50 በመቶ የገቢና የወጪ ንግድ በፖርት ሱዳን በኩል ሊስተናገድ እንደሚችል በሱዳን ጉብኝታቸው ወቅት ገልጸዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ለወደብ ማስተናገጃ ግንባታው የሚውል መሬት የሱዳን መንግሥት አዘጋጅቷል ተብሏል፡፡

አገሪቱ አማራጭ ወደቦችን ከመጠቀም ባሻገር በሌሎች አገሮች ውስጥ ኢንቨስት በማድረግ የተጠቃሚነት ወሰኗን ለማስፋት የሚያስችላትን ሐሳብ ማንፀባረቅ የጀመረችው ከሁለት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ በውጭ ኩባንያዎች ጥናት የተካሄደበት ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ሰነድም በዚሁ ወቅት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ከፖርት ሱዳን በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሌላንድ የበርበራ ወደብን በአማራጭነት የመጠቀም ፍላጎቱን አንፀባርቋል፡፡ በወደቡ ማስፋፊያም ኢንቨስት የማድረግ ሐሳብ እንዳለው ይነገራል፡፡ ይሁንና የዱባዩ ዲፒ ወርልድ የበርበራ ወደብን ለ30 ዓመታት በሚቆይ የሊዝ ስምምት መሠረት በ442 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ መግዛቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የሶማሌላንድ መንግሥት የ35 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ በወደቡ አስተዳደራዊ ሥራዎች ውስጥ እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ የኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚነት ድርሻ እስከ 19 በመቶ እንደሚሆን መገለጹም አይዘነጋም፡፡ ይሁንና የሪፖርተር ምንጮች ይህ መጠን ወደ 30 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ይህ እየተገለጸ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ከ95 በመቶ የሚበልጠው የአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ ከሚስተናገድበት ከነባሩ የጂቡቲ ወደብ ባሻገር፣ የጂቡቲ መንግሥት ያስገነባቸው አራት ተጨማሪ ወደቦች ወደ ሥራ መግባታቸው አይዘነጋም፡፡

ወደቦቹ በአመዛኙ የኢትዮጵያን ሸቀጦች ለማስተናገድ የተገነቡ መሆናቸው ቢታወቅም፣ መንግሥት ወደ ሱዳንና ሶማሌላንድ አልፎ ተርፎም ወደ ኬንያ ሞምባሳ ወደብ እያማተረ ነው፡፡ በዚሁ መሠረትም ፖርት ሱዳን ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ መጠኑ በየጊዜው እየጨመረ የመጣ የኬሚካል ማዳበሪያ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲሞከርበት ቆይቷል፡፡        

Source   –   Home