የአማራና የትግራይ ክልሎች፣ የ”አሸንዳ” በዓልን በዩኔስኮ ሊያስመዘግቡ ነው፤ “መሠረቱ ሃይማኖታዊ ነው፤”/ቤተ ክርስቲያን/

  • “በአከባበር ኹኔታውና ድምቀቱ ልዩነት ቢኖርም፣ በኹሉም አካባቢዎች የሚከበረው በዓል መሠረቱ ሃይማኖታዊ ነው፤ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት ነው፤”
  • “የአገራችንን አንድነትና ነጻነት፣ የሕዝባችንን አብሮነትና የእርስ በርስ መተሳሰብ፣ እግዚአብሔርን የመፍራትና ድንግል ማርያምን የመውደድ፣ ሃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን አዳብሮ ጥሩ ሰብእና ያለው ማኅበረሰብን ያፈራ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ባህል ነው፤ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሀገራዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ዅሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡”

(የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን)

  • ኹለቱም ክልሎች፣ የጥናት ውጤታቸውን ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በየፊናቸው የሚያስገቡ ሲኾን፤ ባለሥልጣኑ ትክክለኛና ቱባ የባህሉን ገጽታዎችና ይዘቶች ለይቶ ለዩኔስኮ ያመለክታል፤ ተብሏል፡፡

 

(አዲስ አድማስ፤ ዓለማየሁ አንበሴ፣ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13 ቀን 2009 ዓ.ም.)

 

በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ የሚከበረውን የአሸንዳ/አሸንድዬ በዓል፣ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች

 

በየፊናቸው፣ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እያደረጉ እንደኾነ አስታወቁ፡፡

የትግራይ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ፣ ዘንድሮ በኹሉም የክልሉ አካባቢዎች ከነሐሴ 16 እስከ 24 የሚከበረውን የአሸንዳ በዓል፤ በተለየ ሥነ ሥርዓት ለማከናወን መታቀዱንና ለዚኽም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽንን(EBC) ጨምሮ በዋልታ እና በኢኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ የበዓሉን አከባበር በቀጥታ ሥርጭት ለሕዝብ ለማድረስ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ ሥነ በዓሉን፣ የአሜሪካው ሲኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሽፋን ይሰጠዋል፤ ተብሎ እንደሚጠበቅም ሓላፊው አክለው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ እንደየአካባቢው የበዓሉ ስያሜ እንደሚለያይ የጠቆሙት አቶ ዳዊት፤ በአኵስም አካባቢ “ዓይኒ ዋሪ”፣ በክልሉ ምሥራቃዊ ዞኖች ደግሞ “ማርያ”፣ በተንቤንና መቐለ አካባቢ “አሸንዳ” በሚሉ ስያሜዎች ይታወቃል፤ ብለዋል፡፡ የአሸንዳ በዓል አከባበርን አስመልክቶ፣ የክልሉ መንግሥት ጥናቱን አጠናቅቆ፣ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ማስረከቡንና በዩኔስኮ ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ ቅድመ ኹኔታዎች በሙሉ ተጠናቅቀው ውጤቱ እየተጠበቀ እንዳለ ሓላፊው አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በክልሉ በተለይም በሰቆጣ፣ ላስታ ላሊበላ እና በራያ ቆቦ አካባቢዎች በስፋት የሚከበረውን የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል በዓል አከባበርን፣ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ አስፈላጊው ጥናት ተከናውኖ መጠናቀቁን ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡

በቀጣይ ዓመት በዓሉን በክልሉ ኹሉም አካባቢዎች እንዲከበር ለማድረግ መታቀዱን የገለጹት የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊዋ ዶ/ር ኂሩት ካሣው፤ የዘንድሮውን በዓልም በዓውደ ጥናቶችና በተለያዩ የበዓል ትዕይንቶች ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡ የዘንድሮ በዓልም፣ ከማክሰኞ ነሐሴ 16 እስከ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚከበር ተጠቁሟል፡፡

ኹለቱም ክልሎች የጥናት ውጤታቸውን፣ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በየፊናቸው የሚያስገቡ ሲኾን፤ ባለሥልጣኑ ትክክለኛና ቱባ የባህሉን ገጽታዎችና ይዘቶች ለይቶ፣ መዝገቡን ለዩኔስኮ ያመለክታል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊ፣ አቶ ዳዊት ኃይሉ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ በስፋት “አሸንዳ” በሚል፣ በአማራ ክልል ሰቆጣ፣ ላስታ ላሊበላና ቆቦ አካባቢዎች፣ “ሻደይ/አሸንድዬ” እየተባለ የሚከበረውን በዓል በተመለከተ ማብራሪያ የጠየቅናቸው፣ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሰባኬ ወንጌል ሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን አገዘ በሰጡት ምላሽ፤ “በኹሉም አካባቢዎች የሚከበረው በዓል መሠረቱ፣ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት ነው፤ አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው እንደመኾኑ ልዩነት የለውም፤” ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ “ምናልባት በዓሉን በድምቀት ለማክበር በሚደረገው ጥረት ላይ ወይም በልጃገረዶች አለባበስና የፀጉር አሠራር ረገድ ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ መሠረቱ ግን አንድ ነው፤” ሲሉ አስረድተዋል፤ ሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን፡፡

የጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሱባዔን መጠናቀቅ ተከትሎ የሚከበረው የአሸንድዬ/አሸንዳ በዓል፣ የአገራችንን አንድነትና ነጻነት፣ የሕዝባችንን አብሮነትና የእርስ በርስ መተሳሰብ፣ እግዚአብሔርን የመፍራትና ድንግል ማርያምን የመውደድ፣ ሃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን ዅሉ አዳብሮ ጥሩ ሰብእና ያለው ማኅበረሰብን ያፈራ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ባህል እንደኾነ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በሱባዔው ዋዜማ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ገልጸዋል፡፡

ለሃይማኖታችን መጠበቅ፣ ለአገር ልማትና ለቱሪዝም ክፍለ አኮኖሚ መበልጸግ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ በመኾኑ፤ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሀገራዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ኢትዮጵያዊ የኾነ ዅሉ የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል

SOURCE  –