ሐራ ዘተዋሕዶ

  • በመናፍቃኑ ደባ ምክንያት፣ የማይግባባ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ እንደኾነ ተጠቁሟል
  • በስፖርትና በርዳታ ስም ሕፃናትን እያሰባሰቡ በኑፋቄ መበከል አንዱ ስልታቸው ነው
  • የቅ/ፍሬምናጦስ ኮሌጅ ስመ ተማሪዎችና የአስኳላ መምህራን፣ ዋና አስፈጻሚ ናቸው
  • ኮሌጁ፣ በስመ ተማሪና መምህር የኑፋቄ ወኪሎች ላይ ፍተሻውን ሊያጠናክር ይገባል
  • አጋዥ፥የካህናት፣ የምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተጠየቀ
  • ከግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ወደትግርኛ ተተርጉሞና ታትሞ እንዲሠራጭ ቢመቻችልን
  • ጥያቄያችን መልስ ካላገኘሕጋዊ ሰላማዊ ሰልፍ እንደምናደርግ እንገልጻለን”/ምእመናኑ/

 

የመቐለ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና የሚገኝባትና የሊቃውንቱ ማእከል የኾነችው የማኅደረ ስብሐት ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም(ማርያም ጉግሳ) ቤተ ክርስቲያን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ቢታተምም፣ የቤተ ክርስቲያናችንን መሠረተ እምነት የሚፃረር ኾኖ የተገኘው የተሳሳተ የትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳይሠራጭ ቋሚ ሲኖዶስ ያገደ ሲኾን፤ አተረጓጎሙና ይዘቱም በሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር አዘዘ፡፡

ኅትመቱ እንዳይሠራጭና እንዲታገድ ሲቃወሙ የቆዩት የመቐለ ከተማና አካባቢዋ ሊቃውንትና ምእመናን፤ ከግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም በ2000 ዓ.ም. ከግእዝ ወደ አማርኛ ከተመለሰው 81ዱ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በቀጥታ ተተርጉሞና ታትሞ የሚመሠራጭበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፤ መቐለን ጨምሮ በመላዋ ትግራይ፣ በኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችና ሕፃናት ላይ ውስጥ ውስጡን የከፋ ደባ እየፈጸሙ ያሉትን መናፍቃንና ወኪሎቻቸውን ለማጋለጥና ለመከላከል፣ አህጉረ ስብከቱ የኖላዊነት ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በ2007 ዓ.ም. ያሳተመው የትግርኛ ትርጉም፤ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ከካቶሊካዊትና ወንጌላውያን ኅብረት ጋራ እንዳሳተመችው በመግቢያው ቢጠቅስም፤ ትግራይን ጨምሮ በማንኛውም አህጉረ ስብከት እንዳይሠራጭ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለማኅበሩ ማስታወቁ ተገልጿል፡፡ የቋንቋ አጠቃቀሙ፣ አተረጓጎሙና ይዘቱ፣ በቤተ ክርስቲያናችን የሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር ቅዱስ ሲኖዶሱ ያዘዘ ሲኾን፣ “ውጤቱ ታይቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ኅትመቱ የታገደ መኾኑ እንዲታወቅ ለሚመለከተው ኹሉ ይገለጽ፤” ሲል መወሰኑ ታውቋል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በትግርኛ ቋንቋ መተርጎሙ፣ ለኅብረተሰቡ አስፈላጊ እንደኾነ ቢታመንበትም የተዛባ መኾን እንዳልነበረበት በአቤቱታቸው የተቹት ሊቃውንቱና ምእመናኑ፤ በመላዋ ትግራይ መለያየትና ሁከት እየፈጠረ እንደኾነና ወደ ወረዳዎች የተበተነው የኅትመቱ ቅጅ እንዲሰበሰብ ወይም ማስተካከያ ደብዳቤ ወደ ኹሉም ወረዳዎች እንዲጻፍ፣ ካለፈው ግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡

ይኸው የ2007 ዓ.ም. ትግርኛ ትርጉም፣ ከቤተ ክርስቲያናችን መሠረተ እምነት በተፃራሪ፡- የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚክድ(ሮሜ 8፥ 26 – 34)፤ የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያዛባ (ዘፍጥረት 18)፤ ሥልጣነ ክህነትን የሚሽርና የማይቀበል(ያዕቆብ 5፥14)፤ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምበትን ፊደል፣ ቁጥርና አቆጣጠር የማይቀበል እንደኾነ የሚያሳዩ አስረጅዎች፣ በመጽሐፍ፣ በምዕራፍና ቁጥር እየተለዩ በአቤቱታው ተዘርዝረዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸውን 81ዱን ቅዱሳት መጻሕፍት ወደ ጎን በመተው 66 መጻሕፍትን ብቻ መያዙም በአቤቱታው ተተችቷል፡፡

“በምድራችን፣ ዕድሜ ጠገብ መጽሐፍ ቅዱስ (the oldest bible in the world) የሚገኘው በክልላችን ባለው በአቡነ ገሪማ ገዳም ነው፤” ያሉት ሊቃውንቱና ምእመናኑ፣ የትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም በ2000 ዓ.ም. ከግእዝ ወደ አማርኛ ከተመለሰው 81ዱ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ተተርጉሞና ታትሞ የሚመሠራጭበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ነው፣ በአቤቱታቸው ያመለከቱት፡፡

ከ92 በመቶ በላይ የክልሉ ሕዝብ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በኾነበት፣ አተረጓጎሙ ለሌሎች የክርስትናው እምነቶች አስተምህሮ እንዲመችና መሠረታዊ ዶክትሪኗን በሚፃረር መልኩ መታተሙ፣ “ቤተ ክርስቲያናችን፣ ከማኅበሩ ከምትጠቀም ይልቅ የምትጎዳበት እያመዘነ እንደመጣ ያመለክታል፤” ብለዋል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍቱን ይዘትና ትርጉም፣ በጥንቃቄ የሚመረምር የሊቃውንት ጉባኤ በሀገርና በአህጉረ ስብከት ደረጃ ማጠናከርና ራሷን የምትችልበት የዲጅታል ኅትመት ተቋም እንድታቋቁምም አዘክረዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ በመቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅና በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች፣ የቤተ ክርስቲያናችንን የእምነት ነጻነት የሚጋፉ መናፍቃንና ምልምሎቻቸው፣ በተለያዩ ስልቶች ኑፋቄን እየዘሩ፣ ምእመኑን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ለመለየት አደገኛ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲኾን፣ በሀገረ ስብከቱ ችላ የተባለው የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት እንዲጠናከርና የዐቂበ ምእመናን ሓላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በመቐለና አካባቢዋ ማኅበረ ምእመናን 162 አመልካቾች ስም፣ ሙሉ አድራሻና ፊርማ ተደግፎ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የቀረበው አቤቱታ እንደሚያስረዳው፤ መናፍቃኑ፣ ዋነኛ የእንቅስቃሴያቸው ማእከል ያደረጉት፣ የቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅን ነው፡፡ ተቋሙ፣ “እንደ አባቶቻችን እንደነቅዱስ አትናቴዎስና ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ያሉ ደቀ መዛሙርትን ያፈራል ብለን ስንጠብቀው፣ የሉተራውያን መናፍቃን መናኸርያና መፈንጫ በመኾን፣ ጥቂት የማይባሉ የኮሌጁ ተማሪዎች፣ በመቐለና በአካባቢው ያሉ ምእመናንን በኑፋቄያቸው ከእናት ቤተ ክርስቲያን እየለዩ ይገኛሉ፤” ብሏል፡፡

በሻሂ፣ በቡና፣ በምግብ ቤቶችና በግለሰቦች መኖርያና በመሳሰሉት እየዞሩ፣ “የመንፈሳዊ ኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ነን፤” በማለት ይተዋወቁና ቆይተው ኑፋቄያቸውን በመዝራት መጠመዳቸው ሲታይ፤ የኮሌጁ አስተዳደር፣ ደቀ መዛሙርቱ ትምህርታቸውን በአግባቡ ስለመከታተላቸው፤ መምህራኑም ትምህርቱን በአግባቡ ስለመስጠታቸው ይከታተላል ወይ? የሚል ጥያቄ እንዲያነሡ አስገድዷቸዋል፤ ማኅበረ ምእመናኑን፡፡

በኵሓ፣ በፈለገ ዳዕሮ፣ በሓውሰዋ፣ በደንጎላትና በሌሎች የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አካባቢዎች፣ የኑፋቄው እንቅስቃሴ ኹለት መልኮች እንዳሉትና ዋነኛው፣ ከመንፈሳዊ ኮሌጁ በተመለመሉ ስመ ተማሪዎች የሚፈጸመው ሲኾን፤ ሌላው ደግሞ፣ የዘመናዊ ትምህርት መምህራንን አሠልጥኖ ማሠማራት እንደኾነ በአቤቱታቸው አስረድተዋል፡፡

በየአካባቢው አዳራሾችን በመሥራት በስፖርትና በርዳታ ስም ሕፃናትን እያሰባሰቡ በኑፋቄያቸው መበከል ሌላው ስልታቸው ነው፡፡ በመቐለና አካባቢዋ ብቻ፣ ከ50 በላይ አዳራሾች እንዳሏቸው ተጠቅሷል፡፡ እነዚኽን በመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች ወጣቶችንና ሕፃናቱን እየበረዙና እየከለሱ፣ አይችሉም እንጅ ቤተ ክርስቲያናችንን ሊያጠፏት ቀንና ሌሊት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በዚኽም ሳቢያ፣ በአኹኑ ወቅት በትግራይ፣ በሃይማኖት ምክንያት የማይግባባ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ እንደኾነና ይህም፣ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ለአገርም አለመረጋጋት እንደሚፈጥር አሳስበዋል፡፡

በቅዱሳን አባቶቻችን ተጋድሎና በሊቃውንት አበው አመክንዮ ተጠብቃ የኖረችውን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ለመበረዝና ለመከለስ የተነሡ መናፍቃን የዓመታት ዕቅድ በማውጣት፣ በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በከፍተኛ ደረጃ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ እኛ ምልከታ በክልላችን ትግራይ እንቅስቃሴው የከፋ ነው፡፡… በሰላምና በፍቅር ተከባብረን መኖር ማለትኮ፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ዶግማና ዶክትሪን፣ ትውፊትና ቀኖና፣ የቀደመው ኣስተምህሮኣችንና እምነታችን መበረዝ ማለት ኣይደለም፡፡


እያገባደድነው ባለው የ2009 ዓ.ም. ብቻ፣ የመንፈሳዊ ኮሌጁ 12 ተማሪዎች፤ ባለፈው 2008 ዓ.ም. ደግሞ 2 ተማሪዎች፣ በኑፋቄው እንቅስቃሴ ተገኝተው መባረራቸው፣ በተዘረጋው የኑፋቄ አሽክላ(ኔትወርክ) ላይ፣ ሰፊና ጥልቅ ዳሰሳ ሊደረግበት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል፤ ብለዋል ማኅበረ ምእመናኑ፡፡ ከዚኽም ጎን ለጎን ሊሠሩ ይገባሉ ያሏቸውን፣ ተጽዕኖውን የመግታትና የመከላከል ርምጃዎች እንደሚከተለው ጠቁመዋል፡፡

በመቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ከመኾኑ የተነሣ ለሚከተሉት የመፍትሔ ሐሳቦች ከፍተኛ አጽንዖት ተሰጥቷቸው ቢታዩልን፤

  1. አኹን እየተማሩ ያሉ ተማሪዎች፣ ሃይማኖታቸው በጥልቀት ተጠንቶና ተመርምሮ የመናፍቃን አራማጅ የኾኑትን መለየት፤ ተመክረው የሚመለሱት ቢመለሱ፣ የማይመለሱ ተወግዘው ቢለዩ፤ ለዚህም ከመቐለ አድባራትና ገዳማት ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች አጣሪ ኮሚቴ ቢቋቋም፤
  2. የመንፈሳዊ ኮሌጁ አስተዳደርና መምህራንም በጥልቀት ቢጠኑ፤
  3. በ2010 ዓ.ም. እና ከዚያ በኋላ ወደ ኮሌጁ የሚገቡት ተማሪዎች ምዘና ጠንከር ቢል፤ ለምሳሌ፡- በዶግማዊ ፈተና፣ በሃይማኖት ጽናት፣ በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በአገልግሎት ጥንካሬ ተመርምረው እንጅ ለኮታ ማሟያ ባይኾን፤
  4. ይህ ኹሉ የመናፍቃን እንቅስቃሴ ሲደረግ፣ ሀገረ ስብከቱና ሊቀ ጳጳሱ፣ ምእመናንን ትምህርተ ወንጌል ለማስተማር ያደረጉት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በዘርና በጎሳ በመለያየት በሁከት ያሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ምእመናኑን ከነጣቂ ተኩላዎች ለመጠበቅ የሚተጉ አባቶች ቢመደቡልን፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤም፣ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. የሀገረ ስብከቱን ውሳኔ አጥንቶ የወሰነው ተግባራዊ ይደረግልን፤
  5. በጠቅላይ ቤተ ክህነቱም፣ የቤተ ክርስቲያን አካላትና ምእመናን የሚያቀርቡትን አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችና አቤቱታዎች አጥንቶ መፍትሔ የሚሰጥ፤ የመናፍቃኑን እንቅስቃሴ የሚገታ አካል የለምና በጥልቀት ቢታይ፤ የሚሉት ናቸው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለመንፈሳዊ ኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ምረቃ፣ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በመቐለ በተገኙበት ወቅት፣ እነኝህን አቤቱታዎች ለማሰማት፣ የምእመናኑ ተወካዮች ከጠዋት እስከ ማታ ቢጠይቁም፣ “በጋርድ እየተከለከሉ” ማቅረብ እንዳልቻሉ፣ ማኅበረ ምእመናኑ አማርረዋል፡፡

ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡት እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው በመኾኑ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ መክረው መፍትሔ እንዲሰጧቸው ተማፅነዋል፡፡ “ጥያቄያችን መልስ የማያገኝ ከኾነ ግን፣ ሕገ መንግሥታችን በሚፈቅደው መሠረት፣ ሕጋዊ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የምንገደድ መኾኑን እንገልጻለን፤” ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሔደው መደበኛ ስብሰባው፣ ተቃውሞ የቀረበበትን የ2007 ዓ.ም. የተሳሳተ የትግርኛ ትርጉም በተመለከተ፣ የእግድ ውሳኔና ተጓዳኝ መመሪያዎች በማስተላለፍ፣ ከማኅበረ ምእመናኑ አቤቱታዎች ለአንዱ ምላሽ የሰጠ ሲኾን፤ ሌሎቹም ጥያቄዎቻቸው በሚመለከታቸው የጠቅላይ ጽ/ቤቱና የሀገረ ስብከቱ አካላት ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል፡፡

SOURCE   –