ታላቁ ሣይንቲስት አልበርት አንስታይን ሣይንስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ «ሣይንስ ማለት ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን፣ የየቀኑ የአስተሳሳብ ጥራት ነው» ብሎናል። አዎ! የሰው ልጅ በየዘመኑ፣ በየዓመቱ፣ በየወሩ እና በየቀኑ ስለዓለም፣ ስለተፈጥሮ፣ ስለአካባቢው፣ ትክክል ወይም ትክክል አይደሉም ብሎ ተቀብሏቸው ስለነበሩ ጉዳዮች፣ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት እና የእምነት ለውጥ በማድረግ የተጓዘና በመጓዝ ሂደት ውስጥም እንዳለ ይታወቃል። ለውጡም በአስተሳሰብ ጥራትና ትክክለኛነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ዓለም በማያቋርጥ የውለጥና የዕድገት ግሥጋሴ ውስጥ እንድትጓዝ አድርጓታል። በዓለማችን ላይ ያሉ የሣይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገቶችና ግኝቶች በየቀኑ በሚከናወኑ የሣይንስ የአስተሳሰብ ለውጦች ውጤቶች ናቸው። ግዙፍ አካላትን ተሸክሞ በውቅያኖሶች ላይ መንሳፈፍ፣ በአየር ላይ መብረር፣ ከአንደኛው የዓለም ዳርቻ ቆሞ ወደ ሌላኛው ዳርቻ በቅጽፈት ውስጥ መነጋገር ወይም መልዕክት ማድረስና መቀበል መቻል፣ በጥቅሉ በመገናኛ፣(የባሕር፣ የየብስ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ ራዲዮና ቴሌቪዥን፣ ኮምፒውተር፣የኢሜይል፣ የፌስቡክ፣ የቲዊተር)፣ የሕክምና፣ የመከላከያ፣ የፎቶ ግራፍ፣ የዓለም አመለካከት(ፍልስፍና) እና የሕዝቦችና የመንግሥታት ግንኙነቶች ወዘተ የየቀኑ የሰው ልጅ  የአስተሳሰብ ጥራት የወለዳቸው ተጨባጭ ግኝቶች መሆናቸውን ማስተባበል አይቻልም።

የየቀኑ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ መሠረቱም፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት ሲል ከተፈጥሮ  እና ከራሱ ጋር በሚያደርጋቸው መስተጋብራዊ ግንኙነቶች የሚወልዱ ውሕደቶችና ግጭቶች የሚፈጥሩዋቸው ግኝቶች ናቸው። እነዚህ ግኝቶች ግን ምናባዊ ሳይሆኑ፣ በእጅ የሚዳሰሱ፣ በዓይን የሚታዩ፣ በአፍንጫ የሚሸተቱ፣ በጀሮ የሚሰሙ ናቸው። ይህ ነባራዊ ኅልውናቸውም ነው ሣይንስ ያሰኛቸው። ሣይንስ የየቀኑ የአስተሳሰብ ጥራት መሆኑ ማሳያውም ሂደቱ የማያቋርጥና ተከታታይ ሆኖ፣ የሰው ልጆች ፍላጎት ማሟያ የሚሆኑ ተጨባጭ ግኝቶች መሆናቸው ነው። ይህም ሂደት የረጋ ወይም የቆመ ሳይሆን፣ ተንቀሳቃሽ፣ ተለዋዋጭና በተሻለ መልኩ ዳባሪ በመሆኑ፣ የየቀኑ የአስተሳሰብ ጥራት የሚገኝበትን ደረጃ አመልካች ነው። የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ጥራት በየጊዜው እየዳበረና እየተለወጠ ባይሄድ ኖሮ፣ የታቆረ ውኃ እንደሚገማ ሁሉ፣የሰው ልጅም አጠቃላይ ኑሮ ከእንስሳት ኑሮ የተለየ ሊሆን አይችል እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም የአስተሳሰብ ጥራትና ለውጥ፣ የሰው ልጅ አጠቃላይ የሕይዎት ቅመም ከመሆኑም በላይ፣ የዕድገት ተከታታይነትንና የየዘመኑን የአስተሳሰብ ጥራት ገላጭ ነው።

የአስተሳሰብ ጥራት ስንልም ትናንት ትክክለኛ ነው ወይም ትክክል አይደለም ብለን ተቀብለን እናራምደው የነበረውን አስተሳሰብ፣ እምነት፣ አሠራር ፣ግንኙነት ወዘተ ያ እምነታችንና አመለካከታችን በየቀኑ የነባራዊ ሁኔታዎች ለውጥ ሂደት የተነሳ፣ትክክል ነው ወይም ትክክል አይደለም ብለን እናራምደው የነበረውን እምነት፣ አሠራር፣ ግንኙነት ወዘተ ከመሬት ላይ በተጨባጭ ባለው ግኝት ላይ በመመሥረት  ሂደቱ ተገቢ እና ትክክል እንደሆነ ያረጋገጠልንን ስንከተል ነው። በሌላ አባባል የየቀኑ ነባራዊ ሁኔታ ያስገኘውን ዕውነታ የአስተሳሰባችንና የዕምነታችን መሠረት ማድረግ ማለታችን ነው። ነባራዊ ስንልም ዕውነት የሆነ ማለታችን ነው። ሣይንስ የየቀኑ የአስተሳሰብ ጥራት የሚሆነውም፣ የሰውን ልጅ የገጠሙትንና ሊገጥሙት ይችላሉ የሚባሉ ችግሮችን ሊፈታባቸው የሚችሉ ዘዴዎችን ማመንጨት፣ ውሸቱን ከዕውነቱ ማበጠሪያ ስልቱንና ማወቂያ መንገዱን ማሳየት መቻሉ ነው። ይህ አጠቃላይ ዕይታ ነው። እስቲ ይህን አጠቃላይ ዕይታ ከዚህ በላይ በገለጥነው ሣይንሳዊ መርሕ አኳያ፣ ዛሬ ኅብረተሰባችን የደረሰበትን የለውጥና የአመለካከት ዕድገትን በመመዘን ተቃዋሚው ኃይል ቢያውቅበት፣ በዘረኛው የትግሬ-ወያኔ ላይ ባለድል ሊሆን የሚያስችለው ወሣኝ ወቅት ላይ መድረሱን እንፈትሽ።

በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ድባብ ውስጥ ሁለት ታላላቅ የኃይል አሰላለፎች ጎልተው ይታያሉ። አንደኛው ኃይል በትግሬ-ወያኔ የበላይነት የሚመራው ኢሕአዴግ እና አጋር ድርጅቶች የሚባሉትን የሚያካትተው የፀረ-ኢትዮጵያ  ስብስብ ነው። የዚህ ስብስብ ማኅበራዊ መሠረቱ እንደየ ድርጅቶቹ ዕድሜ፣ እንደ አደረጃጀታቸውና ከሕዝቡ ጋር እንዳላቸው ቀረቤታ ቆመንልሃል ከሚሉት ነገድ የሚገኙት ድጋፍና ታማንነት የተለያየ እንደሆነ ቢታመንም፣ ቋሚ መሠረታቸው ነገዳቸው መሆኑ ግልጽ ነው። የተደራጁት በነገዳቸው ስም ነውና!

የዚህ ስብስብ አውራ የሆነው የትግሬ-ወያኔ ቡድን ማኅበራዊ መሠረቱ  በኢትዮጵያዊነትና በዐማራው ነገድ ላይ የጥላቻ አመለካከትና እምነት ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ትግሬዎች እንደሆኑ ይታወቃል።  ያለፉት 26 ዓመታት የትግሬ ወያኔ አገዛዝ የዕለት ተዕለት ጉዞ እንዳሳየን፣ የዚህ ኃይል የፖለቲካ አመለካከት በነገዶች፣ በተለይም በዐማራና በኦሮሞ ነገዶች መካከል አንድነትና መተማመን እንዳይኖር የሚያደርግ በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የጎሣ ፖለቲካ ነው። የወያኔው መሪ መለስ ዜናዊ «የዐማራውና የኦሮሞ ነገዶች አብረው መቆም ከጀመሩ ድርጅቴ ሕወሓት ያኔ ማቅ ትለብሳለች። የትግራይ ሕዝብ ኅልውና በዐማራውና በኦሮሞው ነገዶች ፍቺ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ላፍታም መዘንጋት የለብንም። ዐማራውና ኦሮሞው መልሰው ጋብቻ የሚፈጥሩበት አጋጣሚ ካገኙ ሕወሓት በይፋ ያከትምለታል።» ሲል የተናገረው  የትግሬ ወያኔ የርዕዮቱ እና የኅልውናው መሠረት  በዐማራውና በኦሮሞ ነገዶች መካከል ቋሚ የልዩነት ግንብ መገንባት እንደሆነ በቅኔ ሳይሆን በግልጽና በቀላል አማርኛ ነግሮናል። ይህም አንድን ነገድ የበላይ ሌሎችን የበታች አድርጎ የሚመለከት የዓለም ምልከታ፣ ዓለም ካስተናገደቻቸው ርዕዮተ-ዓለሞች አንዱ የሆነው የናዚዝም-ፋሽዝም ርዕዮተ-ዓለም ነው። ይህን ርዕዮተ-ዓለም የናዚ ጀርመን እና የሞሶሎኒው ፋሽስት ጣሊያን  ሕዝቦች ቀላል የማይባለው ቁጥር እንደ ትክክለኛ የዓለም አመለካከት ወስደው(ተቀብለው) ለተወሰኑ ዓመታት ተመርተውበታል። በርዕዮቱም  የዓለም ሕዝብ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት እንዲያስተናግድ እንዳስገደዱት የሚዘነጋ አይደለም። ሣይንስ የየቀኑ የአስተሳሰብ ጥራት ውጤት በመሆኑ፣ ይኸውና የፋሽስት የዓለም አመለካከት በዘረኛነት መልኩ፣ እስከ 1980ዎቹ መባቻ ድረስ በደቡብ አፍሪካ እና ከ1983 ዓም ጀምሮ በወያኔ በምትገዛው ኢትዮጵያ ከመከሰቱ በቀር፣ በዛሬዋ ዓለም ውስጥ የጨካኞችና የአረመኔዎች አገዛዝ መገለጫ ከመሆን ያለፈ ሚና የሌለው መሆኑ ይታወቃል።

የዘረኛው የወያኔዎች ቡድን የሚያራምደው በዘር ላይ የተመሠረተ የዓለም አመለካከት፣ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛው ብሔርተኛና የሥልጣን ጥመኛ የሆነው የየነገዱ ክፍል እንደ ትክክለኛ የዓለም አመለካከት አድርጎ ተቀብሎት እንደነበርና ዛሬም በዚህ አመለካከት ተውጠው የቀሩ እንዳሉ ይታመናል። ሆኖም ሣይንስ፣ የየዕለቱ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ጥራት በመሆኑ፣ የወያኔ ማኅበራዊ መሠረት ከሆነው ከትግራይ ሕዝብ ጀምሮ፣ በአጃቢነት የተሰለፉት የኦሕዴድ፣ የብአዴን እና የደኢሕዴግ እንዲሁም የአፋር፣ የቤንሻጉል-ጉምዝ፣ የጋምቤላ፣ የሶማሊያና የሐረሪ ድርጅቶች አባሎች የትግሬ ወያኔ ኅልውና መሠረት ከሆነው የዘረኝነት አመለካከት እያፈነገጡ መሆኑን በየአካባቢው በሚነሱት ሕዝባዊ እንቢተኝነት እንቅስቃሴዎች የሚሰሙ ድምፆች በጉልህ እያሳዩ ነው። ይህም በሂደት ስለትግሬ ወያኔ ዕውነተኛ ማንነት፣ ለምንስ ዓላማ እንደቆመ ከመረዳት የመጣ የሀሳብና የአመለካከት ጥራትና ጥልቀት የተገኘ ዕውነታ ነው።

ሁለተኛው ኃይል፣ ወጥ አመለካከት የሌለው፣ የጠነከረ ድርጅታዊ ብቃት ያልገነባ፣ ነገር ግን፣ በዘመኑ የብዙኃን መገናኛዎች አለን የሚሉ ቡድኖችን ያቀፈ ነው። የዚህ ኃይል ማኅበራዊ መሠረት ቆመንለታል የሚሉት ነገድ አባሎች ናቸው። በአሰላለፍ ደረጃ ይህ ኃይል በሚጽፏቸውና በፕሮግራማቸው ፀረ-ወያኔ መሆናቸውን ያሳውቁ እንጂ፣ በተግባር የወያኔ ፀርነታቸውን ያሳዩት እጅግ ጥቂቶች ናቸው።  ይህን ኃይል በራሱ የውስጥ አሰላለፍ በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል።

የመጀመሪያው፣ የየራሳቸውን ነገድ ከኢትዮጵያ ገንጥለን አገር እንፈጥራለን የሚሉት (ምሳሌ እንደ የኦጋዴን ነፃአውጭ ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወዘተ ያሉ)  የያዘው ነው። ሁለተኛውና በቁጥሩም ቀላል ነው የማይባለው ብሔርተኝነትን ዋነኛ የመታገያ ሜዳው አድርጎ በየነገዱ ስም የተደራጀው በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኘውን ክፍል የያዘው ነው። ሦስተኛው ወገን በኅብረ-ብሔር ስም የተደራጀውን ክፍል የሚያካትተው ነው። የዚህ ክፍል አመራር አካሎች በወሳኝነት የሚገኘው ካገር ውጭ ነው።

ይህ የወያኔ ተቃዋሚ ኃይል ነኝ የሚለው ብሔርተኛውና ገንጣይ ቡድኖች፣ በእሳካሁኑ ጉዞአቸው ወያኔን በቃል እንቃወማለን ይበሉ እንጂ፣ የአስተሳሰብ ጥራታቸው ከወያኔ ያልተለዩ፣ የወያኔን ዓለማ የሚያራምዱ በመሆናቸው፣ በስም ካልሆነ በተግባር ወያኔን ይቃወማሉ  ለማለት አያስደፍርም። እንዳውም አንዳንድ ጊዜ ወያኔ የተቃዋሚውን ኃይል ለመከፋፈል ሆን ብሎ ያደራጃቸውና የሚመራቸው የሚመስሉ ናቸው። ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነት የጋራ ዕሴቶች አያምኑም፤ የዐማራውን ነገድ ወራሪና ጨፍጫፊ፣ ገዥና አስገባሪ፣ ነፍጠኛና ጨቋኝ ነው ብለው የሚያምኑ በመሆኑ ፣ በአመለካከት የወያኔው ቀጥተኛ ቅጂዎች እንጂ፣ ተቃዋሚዎች ናቸው ለማለት የሚያስችል የዓላማ፣ የዕራይ፣ የተልዕኮና የግብ ልዩነት የላቸውም። ይህን ኃይል ከወያኔ የሚለየው በጥቅም፣ በሥልጣንና ከወያኔ እኛ ለብሔር/ብሔረሰቦች የተሻልን አማራጮች ነን በማለታቸው ብቻ ነው።

ኅብረ-ብሔርተኛው ቡድን በዓለም አመለካከቱ አብዛኛው የግራው ዘመሙ የዓለም አመለካከት ምርኮኛ የሆነው ትውልድ በመሆኑ፣ የአመለካከት ጥራት ብቻ ሳይሆን፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ በኢትዮጵያዊነት የጋራ ዕሴቶች ዙሪያ ራሱን ያላደራጀ፣ ኢትዮጵያውያን በረጅም ጊዜ  የታሪክ ፍሰት የገነቡትን የጋራ ማንነት ለአንድ ነጠላ ነገድ የሰጠና ሌሎቹን ባይተዋሮች እንደሆኑ ቆጥሮ፣ ሁሉም እርሱ ባይተዋሮች ብሎ የሰየማቸው ነገዶችና ጎሳዎች በአንዱ ነጠላ (ዐማራ) ነገድ ላይ ተባብረው ክንዳቸውን እንዲያሳርፉበት የሰበከና አገሪቱ ዛሬ ለምትገኝበት የጥፋት ጎዳና በር የከፈተ በመሆኑ በወጣቱ ትውልድ በከፍተኛ ጥርጣሬ የሚታይ ነው። በሌላ በኩል፣ የዚህ ቡድን አባሎች የነበሩ ፣በጊዜ ሂደት የአመለካከትና የአስተሳሰብ ጥራት ያገኙት ከቡድኑ የዓለም አመለካከት በመውጣት  ጣታቸውን በሌሎቹ ላይ የሚቀስሩ በመሆኑ፣ ወጥ አመለካከት አልባ ነው። ይህ ቡድን  ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታና የአስተሳሰብ ደረጃ ጋር ራሱን ማዛመድ የተሳነው በመሆኑ፣ ከነባሩ የራሱ ትውልድም ሆነ ከወጣቱ ትውልድ ጋር የሚያገናኘው ድር ሰላላ መላላ ወይም ምንም በመሆኑ፣ በወያኔ  ላይ ማድረግ የሚጠበቅበትን ጫና ሁሉ፣ ጊዜንና ቦታን ባገናዘበ መልኩ እያደረሰነው የሚባል አልደለም። በመሆኑም ይህ ቡድን ከፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ባለፈ የወያኔ የሥጋት ምንጭ ነው ሊባል የሚችል አይደለም።

ከጥንካሬ አንፃር ከተቃዋሚው ይልቅ ወያኔና አጋሮቹ አንፃራዊ ጥንካሬ አላቸው። የጥንካሬአቸው መሠረቱም የዓለም አመለካከት ወጥነት፣ የዓላማ አንድነትና ትክክለኛነት ኖሮአቸው አይደለም። በሕዝብ ተፈቃሪና ተወዳጅ ሆነውም አይደለም። ሰላምና ዕኩልነት፣ ዕድገትና ብልጽግናን አስፍነው፣ ፍትሕንም አረጋግጠው አይደለም። የጥንካሬአቸው ምንጭ በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት የሚያዙ በመሆኑ፣ የልዩ ልዩ  የመጨቆኛ መሣሪያዎች ማለትም፣ የጦር ሠራዊቱ፣ የፖሊሱ፣ የጸጥታ/የደህንነት/ ሠራተኛው፣ የፍርድ ቤቱንና የወህኒ ቤቱ አዛዦችና ተቆጣጣሪዎች መሆናቸው ነው። የእነዚህ ተቋሞች ወሣኝ ቦታዎችና  የሠራተኛው አብዛኛውን ቁጥር የያዘው በትግሬ-ወያኔ አመለካከት ተኮትኩተው ያደጉት ትግሬዎች መሆናቸው ነው።

ይህ ሲባል ግን ይህ ኃይል፣ የዓላማ፣ የራዕይ፣ የተልዕኮ እና የአመለካከት የጠጠረ አንድነትና ጥንካሬ ያለው አይደለም። የወያኔ ቡድን ጥንካሬ የፀጉራም ውሻ ዓይነት ነው። አለ ሲሉት የሚሞት ነው። አንድነቱ በነቀዝ የተበላ የብሳና ግንድ ነው። ሥርዓቱ ከራስ እስከ እግር ጥፍሩ በሙስና የተበከለ ነው። ሙስና  ፈጣንና ተላላፊ በሽታ ከመሆኑም በላይ ሊያጠፉት የማይቻል የሥርዓቱ ካንሰር በመሆኑ ገዥውንና ሠፊውን ሕዝብ ላይገናኙ ፊት አዟዙሮ ያቆመ ማኅበራዊ ተውሳክ ነው። ይህ ማኅበራዊ ተውሳክ የሆነ ወረርሽኝ ክፉኛ በመዛመቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ልትወጣው ከማትችለው አዘቅት ወስጥ እንድተገባ አድርጓታል። የኢኮኖሚው ማሽቆልቆል በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ በመሆኑ፣ ሕዝቡ ያላንዳች አደራጅ በራሱ አሰሳሽነት አደባባይ በመውጣት ቁጣውንና ምሬቱን እንዲገልጽ አስገድዶታል። ይህም  ጥንትም አገር ለመዝረፍ እንጂ፣ ለመከፋፈል ባልተስማሙት ዘራፊ  ቡድኖች  መካከል  የማይታረቅ የጥቅም ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ወያኔ ሕዝቡ ላነሳቸው  የፍትሕ፣ የዕኩልነት፣ የሃይማኖት፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ መስጠት የተሳነው ብቻ ሳይሆን፣ ባሕሪውም ያልሆነው የዘራፊው ቡድን፣ የታችኞቹ ወደ ላይኞቹ ሲያጎኑት፣ የላይኞቹ ደግሞ  ወደ ታችኞቹ መልሰው ከመወርወር በተጨማሪ፣ የሙስናውን አቀባባይ ቅርጫፎች ጭዳ ለማድረግ በሕግ ሽፋን ወደ ዘብጥያ እየላኳቸው ይገኛሉ።  ይህም ቅራኔው ከግጭት አልፎ ለጊዜው ባለጉልበቱ ጉልበተ ወናሳውን እያሳደደ ወህኒ እየወረወረው መሆኑን ከማሳየቱም በላይ የገዥው ቡድን አባሎች ከማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ የገቡ እንደሆነ በገሐድ እየታየ ነው። ይህም የድክመት እንጂ፣ የጥንካሬ መገለጫ አይደለም። የወያኔው ቡድን በሥልጣን ላይ ያለው በተቃዋሚው ድክመት እንጂ፣ በራሱ ጥንካሬ አይደለም የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም።

ገዥው ቡድን ከጥቅም ቅራኔውና ግጭቹ ባሻገር፣ አደረጃጀቱ «እናንተ እና እኛ» በሚል የተቃኘ በመሆኑ፣ ከመሠረቱ የፈጠሩት አንድነት ነባር ማንነትን፣ ባህልን፣ ሃይማኖትን፣ አሠራርን፣ ግንኙነትን፣ የወል እሴቶችን ወዘተ ለማጥፋት እንጂ፣ በነበሩ መልካም ማንነቶችና የወል ዕሴቶችን ለመገንባት ባለመሆኑ፣ መጋጨታቸውና መለያየታቸው የባሕሪያቸው መሆኑ ይታወቃል።  ለዚህም ነው ዛሬ በብአዴንና በሕወሓት፣ በኦሕዴድና በሕወሓት፣ በደኢሕዴድና በሕወሓት፣ እንዲሁም በኢሕአዴግና በጋር ድርጅቶቹ መካከል መናቆርና «እናንተ እነማን ናችሁ?» የሚል ጥያቄ በሕወሓቶች ላይ ከየአቅጣጫው መሰንዘር የጀመረው። ኦሕዴዶች በሻዕቢያና በሕወሓት ምርኮኞች አንመራም ሲሉ፣ ብአዴኖችም ዐማራ ባልሆኑትና የወያኔ ምርኮኞች በሆኑት፣ በረከት ስምዖን፣ ታደሰ ጥንቅሹ፣ ካሣ ተክለብርሃን፣ ሕላዊ ዮሴፍ፣ አዲሱ ለገሠ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ ዓለምነው መኮንን — ወዘተ አንመራም፤ «ብአዴን» በዐማራው ሕዝብ ልብ ያልገባው መሪዎቹ የራሱ ልጆች ስላልሆኑ  ስለሆነ፣ እነዚህ ሰዎች ይነሱልን ሲሉ በአደባባይ ጥያቄአቸውን  የማቅረባቸው ጉዳይ፣ በወያኔ አገዛዝ ገዥ ቡድኖች መካከል የከረረ ቅራኔ የተነሳ ብቻ ሳይሆን፣ ቅራኔው ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ለውጥ ጠሪ እና ወያኔ በአሁኑ ሰዓት በሥልጣን ላይ ያለው ወደ መቃብሩ የሚከተው ጠንካራ ተቃዋሚ በማጣቱ ብቻ መሆኑን አመልካች ነው። ባጭሩ የወያኔ አገዛዝ ቀንቅኗል። በስብሷል።

ተቃዋሚው ጎራ ከፍ ሲል በተጠቀሱት ምክንያቶች ልዩነት እንዳለው ሁሉ፣ የወያኔው ጎራም ከተቃዋሚው በበለጠና በከረረ ልዩነት የተሞላ ነው። ከፍ ሲል ለማብራራት እንደተሞከረው፣ የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶች የሚባሉት ከላይ ስማቸው የተገለጸው ድርጅቶች፣ የድርጅት ነፃነት የሌላቸው በመሆኑ «ያንተ ነን» የሚሉት ሕዝብ አመኔታና ከበሬታውን የቸራቸው አይደሉም። ሕዝቡ የሚያያቸው በወያኔ አሽከርነት እንጂ፣ የእኛ ጥቅምና ፍላጎት አስከባሪዎች ናቸው ብሎ የተቀበላቸው ባለመሆናቸው ኅልውናቸው የተያያዘው ከወያኔ ጋር ነው። በመሆኑም ወያኔን አስደስቶ ለመኖር፣ ከሕዝቡ ፍላጎት ውጭ የሆኑ ተግባሮች ስለሚፈጽሙ ከሕዝቡ ጋር ዓይና ናጫ ናቸው። ባንድ ቃል ከ1997 ዓም ወዲህ ወያኔ በሥልጣን ላይ የቆየው በተቃዋሚው መልካም ፈቃድ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ሲባል ተቃዋሚው ወዶና ፈቅዶ ወያኔ በሥልጣን እንዲቆይ አደረገ እያልን አይደለም። እያልን ያለነው፣ ተቃዋሚው ኃይል ከትናንት እንስ ከዛሬ ወያኔን ከሥልጣን ሊያስወግድበት የሚያስችለውን የዕለት ተዕለት የሀሳብ ጥራት፣ የአመለካከት ወጥነት፣ የአደረጃጀት ጥንካሬ፣ በሕዝብ መሀል ገብቶ የማደራጀትና የመምራት፣ በነባሯ ኢትዮጵያ አንድነትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ በሕዝቡ አንድነት፣ ዕኩልነት፣ ሉዓላዊነት፣ የሕግ የበላይነት ወዘተ ወጥና ተመሳሳይ አቋምና አመለካከት አልያዘም ነው። ይህንም ባለመያዙ ጥካሬና የማድረግ ብቃቱን አሳጣው። ጥንካሬ እና የማድረግ ብቃት የሌለው ኃይል ደግሞ ባይወድም ተገዶ በሚጠላውና በሚንቀው ኃይል መገዛቱ ዕውነት ነው። ለዚህም ነው ፕሌቶ«ራሳችን ከፖለቲካ ባገለልን ወይም ባራቅን ቁጥር፣ በምንበልጣቸው ሰዎች በመገዛት እንቀጣለን» ያለው። ዛሬ ከብት ጠብቀው ባላደጉ፣ በምንንቃቸውና በምንጠላቸው የትግሬ ፋኖ ወያኔዎች የምንገዛው፣ ተቃዋሚው ወገን ተቃውሞውን የሚገልጸው በተናጠል በየጎጆ ተሸሽጎ እንጂ፣ በአደባባይ በኅብረት ወጥቶ ባለመሆኑ ነው። የወጣውም የተከፋፈለ ነው። ለመከፋፈሉ ዋናው ምክንያትም በአገሪቱ ከተዘራው መጥፎ የዘር ፖለቲካ እንዴት መውጣት እንደሚቻል ከየዕለቱ ተጨባጭ የሕዝቡ እንቅስቃሱና ዕውነተኛ ፍላጎት የመነጨ የአስተሳሰብ ጥራት መጨበጥ አለመቻሉ አንዱ ነው። ሁለተኛውና ገዝፎ የሚታየው ችግር፣ የፖለቲካውን መድረክ ጮሌዎች በመቆጣጠራቸው፣ ልምዱና ችሎታው ያላቸው ሰዎች በይሉኝታ፣ ወይም ተገፋን፣ አልተፈለግንም በሚል ስሜት ራሳቸውን ከመድረኩ በማራቃቸው፣ መድረኩን አል-ባሌ ሰዎች በመቆጣጠራቸው፣ በምንጠላቸውና በምንቃቸው ሰዎች በመገዛት የቅጣት ዘመናችን ማራዘማችን ነው።

ተቃዋሚው በሚንቃቸው ሰዎች ከመገዛት ቅጣት ለመዳን እስከ ዛሬ የሙጥኝ ብሎ ከያዘው ሃይማኖታዊ ከሚመስል የዕለት ተዕለት አመለካከት ራሱን ማጽዳት አለበት። «ሳይንስ የየዕለቱ የአስተሳሰብ ጥራት ነው» ሲል አልበርት አንስታይን የገለጸልንን ሐቅ የእንቅስቃሴአችን መመሪያ ለማድረግ እንጣር።  የጥረታችን መጀመሪያም የፖለቲካ ሣይንስ ሀ ሁ በሆነው «በፖለቲካ ቋሚ ጥቅም እንጂ፣ ቋሚ ጠላት የለም» የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ምንነት አፍታተን ምንነቱን እንረዳና እንዴት ወዳጃችን ጠላት፣ ጠላታችን ወዳጅ ሊሆን እንደሚችል በተጨባጭ እንረዳ ። ቀጥሎ የፖለቲካ ትግል ማለት በሂደት «የጠላት የሆነውን ሁሉ የራሳችን ማድረግ» የሚለው ምን ማለት እንደሆነ በቅጡ መገንዘብና ያን በሥራ ለማዋል ከጣርን፣ በእርግጥም የጠላት የነበረው የእኛ ይሆናል። በሌላም በኩል በድርጅቶችና በድርጅት አባሎች መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት አበጥሮ ማወቅ ይኖርብናል። የምንታገለውን ጠላት በምንፈልገው ፍጥነት ለማስወገድ ከውጭ በሚደረግ ግፊት ብቻ ልንጥለው የማንችል መሆኑን ማወቅ ብልኅነት ነው። ጠላታችን በምንፈልገው ፍጥነት ለማስወገድ የምችለው ግፊቱን ከውስጥም ከውጭም ስናጠናክር ነው። የውስጡ ገፊ ኃይል ማንም ሳይሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወያኔ ባደራጃቸው ድርጅቶች ውስጥ ያሉ አባሎቹን የተቃዋሚው ጎራ ዓላማ አራማጆች ማድረግ ሲቻል ነው።

በዚህ ረገድ ከወያኔ ማዕቀፍ ውጭ ሆኖ በተቃዋሚነት በየጎሣው የተደራጀው ኃይል፣ ወያኔ ባደራጃቸው የነገድ ድርጅቶች ውስጥ ሰርጎ ለመግባት የሚያግደው አንዳችም ነገር የለም። አስፈላጊው ተቃዋሚው ዓላማውን፣ ተልዕኮውን፣ ራዕዩን፣ ግቡንና የትግል መርሆዎቹን በግልጽ ቋንቋና አቀራረብ የማስረዳትና የማስረጽ አቅሙን ማጎልበት ነው። ቀጥሎ ወያኔ በአገርና በሕዝብ የሚያደርሰውን በደል በተጨባጭ መረጃ ማሳየት ነው። ተቃዋሚው የሚቃወመው፣ አገዛዙንና የሚመራበትን የዘር ፖለቲካ እንጂ፣ ለመኖር ሲሉ ወደውም ሆነ ተገደው የወያኔ ድርጅቶች አባል የሆኑትን ግለሰቦች አለመሆኑን በማያሻማ ቋንቋ በተደጋጋሚ ማስረዳት ለነገ የሚባል ተግባር መሆን የለበትም።  ከወያኔ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች የወገኑ ሰዎችና ቡድኖች፣ ተቃዋሚው ጎራ የእኛ ጠላት አይደለም፣ ጠላትነቱ የአገዛዙ አውራ ቡድኖች እና የሚያራምደው አመለካከትና በዚሁ አመለካከት ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎች ናቸው ብለው እንዲያስቡና እንዲያምኑ የማድረግ ሥራ በተከታታይ ሊሠራ ይገባል። ይህ ሲሆን የጠላት የሆነውን ሁሉ የእኛ አደረግን ማለት ነው። የጠላት የነበረው ሁሉ የእኛ ከሆነ፣ የድሉ ቀን ይቃረባል።

ስለሆነም በተቃዋሚው ጎራ የቆሙ የኦሮሞ፣ የዐማራ፣ የጉራጌ፣ የአፋር፣ የሶማሊ፣ የሲዳማ፣ የጋምቤላ፣ የሐዲያ፣ የከመባታ፣ የወላይታ ወዘተ የነገድ ወይም የኅብረ-ብሔራዊ ድርጅቶች አውራ ጠላታቸው የትግሬ ወያኔ አገዛዝና የሚያራምደው ሥርዓት እንጂ፣ ከወሣኝ አመራር ሰጪዎች በታች ያሉት ተራ አባሎች ከመሪዎቹ ጋር ዕኩል ጠላት አድርገው መመልከት የትግሉ ዘመን ከማራዘም ውጪ፣ ለድሉ መቀላጠፍ የሚያስገኘው ጥቅም ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። በመሆኑም ተራ የብአዴን፣ የኦሕዴድ፣ የደኢሕዴድ፣ የሐረሪ፣ የሶማሊያ፣ የጋምቤላ፣ የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የከምባታ፣ የሲዳማ ወዘተ አባሎችን ከማስፈራራት ማበረታታት፣ ከመራቅ መቅረብ፣ ከጥላቻ ፍቅር፣ ከመግፋት ማቀፍ፣ ወዘተ ማሳየት በተቃዋሚው ጎራ ከተሰለፉ የየነገዱ ሰዎች በተናጠልና በቡድን፣ በግለሰብና በድርጅት ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ አንፃር የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(ዐኅኢአድ)፣ የተደራጀው የዐማራን ብሔርተኝነት ለማቀንቀን አይደለም። የተደራጀው ባለፉት 26 ዓመታት ዘረኛው ወያኔ በዐማራው ላይ ያደረሰውን ተከታታይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ድርጊት ለማስቆም ቀርቶ፣ ድምፅ ለማሰማት የቻለ ኅብረ-ብሔራዊም ሆነ ብሔራዊ ድርጅት ባለመኖሩ፣የዐማራውን ኅልውና ለማስጠበቅና ድምፅ ለመሆን የተደራጀ መሆኑ ወዳጅም ጠላትም በግልጽ ሊያውቀው ይገባል። በመሆኑም የዐኅኢአድ ቀዳሚ አጀንዳ የዐማራውን ኅልውና ማስጠበቅ ነው። ተከታዩ አጀንዳው፣ በኢትዮጵያዊነት የወል ዕሴቶች፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል አለባት፣ ኢትዮጵያ በውስጧ ለዘመናት በኖሩና ወደፊትም በሚኖሩ ነገድና ጎሣዎች የጋራ ሥሪት ናት፣ ባለፉ መልካም የጋራ ዕሴቶች ላይ እየጨመርን ኋላቀሮቹን በሂደት እያስወገድን፣ ለሕዝቡ አንድነትን፣ ሰላምን፣ ብልጽግናን፣ ዕኩልነትን፣ ፍትሕን፣ መቻቻልን፣ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርና የሕግ የበላይነትን እናስፍን ብለው ከሚያምኑ ድርጅቶችና ቡድኖች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን አንድነት የማስጠበቅ ዓላማን አንግቦ የተደራጀ ድርጅት ነው።

ይህም በመሆኑ፣ ዐኅኢአድ በትግሬ ነፃ አውጭ ድርጅት እና በተራ አባሎቹ፣ በብአዴን እና በተራ አባሎቹ ፣ በኦሕዴድና በተራ አባሎቹ፤ በደኢሕዴድ እና በተራ አባሎቹ፣ በጥቅሉ በኢሕአዴግና በተራ አባሎቹ መካከል ሠፊ የአመለካከት፣ የእምነት፣ የዓላማና የተልዕኮ ልዩነቶች እንዳሉ ይረዳል። ለተያያዘው ዓላማም ዳር መድረስ የራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ሕይዎት ለማቆየት ሲሉ የብአዴን አባል የሆኑ ሰዎችን በጠላትነት አይመለከትም። ጠላቱ ድርጅቱ እንደ ድርጅትና የድርጅቱ ዓላማ፣ ራዕይ፣ ተልዕኮና ግብ ቀያሾች፣ አመራር ሰጭዎች እና መሥራቾች ናቸው። በጥቅሉ በብአዴን እና በአባሎቹ መካከል ሠፊ ልዩነት እንዳለ ዐኅኢአድ ጠንቅቆ ያውቃል። ይህን ልዩነትም በግልጽ በብአዴን ምክር ቤት ስብሰባ፣ በዐማራ ክልል ተብየው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግሮች ስብሰባ ላይ የተገኙ የወረዳ እና የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ ሹሞች፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የክልሉ ኃላፊዎች የዐማራው ክልል ሆን ተብሎ  በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር የልማት ሥራዎችን እንዳይሠራ መደረጉን አጋልጠዋል። ከሁሉም በላይ በተናጠል በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የዐማራው ልጆች የሆኑ፣ግን ደግሞ የብአዴን አባሎች የሆኑ የድርጅቱን ገመናና የትግሬ ወያኔ አሽከር መሆኑን፣ ብአዴን የዐማራው ዕውነተኛ ተወካይ አለመሆኑን፣ አገዛዙ በዐማራው ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ሁለገብ ችግር ማንንም ሳያፍሩና ሳይሸማቀቁ ሐቁን በግልጽ ቋንቋ እየተናገሩ ነው። ስለሆነም ዐኅኢአድ እንደነዚህ ያሉትን የዐማራ ልጆች በጠላትነት አይመለከታቸውም። በአንፃሩ ችግራቸውን በመጋራት ወያኔንና አገዛዙን አሽቀንጥሮ ለመጣል በሚደረገው ትግል የበኩላቸውን ሚና መጫዎት እንዲችሉ አስፈላጊውን መሰናዶ ማሟላት እንዳለበት ያምናል።

በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ዐኅኢአድ ፣በኢትዮጵያ አንድነት፣ በሕዝቡ ዕኩልነት፣ ነፃነት፣ ሰላም፣ ፍትሕና ዲሞክራሲ ከሚያምኑ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባሎችን በጠላትን አይመለከትም። ሣይንስ የየዕለቱ የአስተሳሰብ ጥራት ነውና፣ ድሮ የነበራቸውን የፖለቲካ አቋም ቀይረው፣ አሻሽለው ወይም አዳዲስ ሀሳቦች ጨምረው በኢትዮጵያ አገራዊነት ከሚያምኑ ድርጅቶች ጋርም ቢሆን ተቀራርቦ ለመወያየትና አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታ ለማመቻቸት በሩ ዝግ አይደለም። ይህን ስናደርግ አስተሳሰባችን እየጠራ፣ ትግላችን ለፍሬ ይበቃል ብለን እናስባለን።

የዐማራ ኅልውና መጠበቅ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው።

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(ዐኅኢአድ)፣