ከሰሞኑ አንዱ የኦነግ ርዕዮተ አለም ተጋሪ ከወደ ጀርመን «አማራ ጫነብን» ፤«ሃይማኖታችን ዋቄ ፈና እንጂ ክርስትናን አማራ የጫነብን ሃይማኖት ነው» በማለት ኦነግ በፕሮግራም ሲታገለው የኖረውን ክርስትናን ለኢትዮጵያና ለአለም ለማስተማር ሲሞክር ተስተውሏል። ይገርማል። ፓስተር ነኝ የሚለው በንቲ ቴሶ ከጀርመን በተማረው ኢትዮጵያን የማጥፋት ትምህርት ታግዞ ክርስትናን «ከጳጳሱ ቆሱ» እንዲሉ ለኢትዮጵያና ለአለም እንዳዲስ ጽፎ ሊያስተምር እንደሆነ ነገረን።

ኢትዮጵያ የክርስትና አስተማሪ እንጂ የክርስትና ተማሪ ልትሆን አትችልም!

 

ዛሬ የሚጠሉትን ኢትዮጵያ  የሚለውን  ስም ከመጽሕፍ ቅዱስ ለመደምሰስ የተነሱት እነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪሎች ነገ አንዱ ሰላቶ ተነስቶ በቅዱስ ቁራዓንም ተጠቅሶ የሚገኘውን ኢትዮጵያ የሚለውን ስምም ይቀየር እንደማይል እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ምንም እንኳ ማህበራዊ ሚዲያውን በሕዝባችን ባጠቃላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ለማሳወቅና ያ ትውልድ ያጠፋውን ታሪካችንን እንድናውቅ ለማድረግ ብንጠቀምበትም አገርና የሃይማኖት አባት ስለሌለን ታሪካችና ባለም ላይ ኢትዮጵያ በክርስትናም በእስልምናም ያሳረፈችው አሻራ ሲደለዝ ዝም ብለን ልናይ አንችልምና ይህንን ከትበናል።

ኦቶማን ቱርክና ግብጽ አስራ ሁለት ጊዜ፣መዲስቶች ሶስት ጊዜ፣ ጥሊያን ሁለት ጊዜ፣ እንግሊዝ አንድ ጊዜ ሞክረው ውርደት ተከናንበው ሽንፈት ቢጋቱም በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን ቁርሾና ቂም ግን በኢትዮጵያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪል በሆነው በፋሽስት ወያኔ አማካኝነት እየተወጡ ናቸው። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ በቀጥታ ሞክረውት ኢትዮጵያውያን አክሽፈውት የነበረው የጠላት ፕሬግራም በፋሽስት ወያኔ ግን ያላስፈጸመ አንዳች ነገር የለም። የሆነው ሆኖ ዛሬ ኢትዮጵያ የሚለው ስም እንዲጠፋ የተፈለገው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሆነ ስለክርስትናና ኢትዮጵያ ታሪክ የተወሰነ ነገር ልናወሳ ተገደናል። ነገው ሌላ ቀን ነውና የማይተኙልን ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ከቅዱስ ቁርዓን ለማለያየት ሲመጡብን ዝምና ያኔም በድጋሚ በሀይማኖቶችና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው ግንኙነት እውነቱን እንናገራለን።

ከአንድ አመት በፊት በምኖርበት አገር ከአንድ የአገሩ ክፍለ ሀገር ከተማ ወደ ሌላ ክፍለ ሀገር ከተማ በባቡር ተጉዤ መሄድ ወደፈለግሁበት ቦታ ደርሼ ከባቡር ጣቢያው ወርጄ የእግር መንገድ ስጓዝ ከፊት ለፊት በር ላይ ቆሞ አንድ የምዕራብ አፍሪካ ተለላጅ የሆነ አፍሪካዊ በእጁ የያዘውን ፓምፕሌት እየበተነ ከባቡር ጣቢያው ከሚወጣው ሰው የቻለውን ያህል በመከተል «ጌታን ተቀብለሀል?» እያለ ይጠይቀ ነበር። ተራው የኔ ሆኖ እኔ ጋር ሲደርስ አልፌው ወደ መዳረሻዬ ሳቀና ሶስት አራት እርምጃ እየተከተለ «Excuse we sir, do you have a moment to talk about Jesus Christ?» የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ እያከታተለ አቀረበ። እኔም ጥሪውን ሰምቼ ዘወር ብዬ እንዳየሁት «Oh you are Ethiopian, wow… beautiful!» አለኝና «Have you accepted Jesus as your personal savior? በማለት «ጌታን ተቀብለሀል ወይ?» ሲል አጥብቆ ጠየቀኝ።

እኔም ለጠየቀኝ ጥያቄ መልስ ከመስጠቴ በፊት ከአነጋገሩ የአገሩ ተወላጅ እንዳልሆነ ስለተረዳሁ ከየት አገር እንደመጣ ጠየቅሁት። ከናይጀሪያ መሆኑን ነገረኝ። ከዚያ «ጌታን ተቀበል» ብሎ ለጠየቀኝ ጥያቄ Don’t you know that Ethiopians have accepted Jesus Christ and his mother and dedicated their life to Christ and to the Father and the Holy Spirit two thousand years before you and the rest of the world does? ስለ መለስሁለት። ሰባኪው ናይጀሪያዊ መልሴን በሰማ ጊዜ ቀንዷን እንደተመታች ላይ ዙሮ ሳያየኝ «Yes I know that brother» ብሎኝ ከፊቴ ጠፋ። ለናይጀሪያዊው ማስተላለፍ የፈለግሁት መልዕክት ስለክርስትናና እየሱስ ክርስቶስ እኛ ኢትዮጵያውያን አለምን እናስተምራለን እንጂ ከኛ ከሺ አመታት በኋላ ክርስትናን የተቀበለው አለም ሊያስተምረን አይችልም የሚል ነበር። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ ክርስትን የምናውቀው በስሚ ስሚ ወይንም ሰባኪ ነግሮን ሳይሆን ከፈረሱ አፍ ከክርስቶስ ኃዋርያ ከፊፒጾስ ነውና። ነገሩ እንዲህ ነው።

የኃዋርያት ስራ ምዕራፍ ስምንትን ያነበበ ሁሉ እንደሚገነዘበው እየሱስ ክርስቶስ ሞቶ በተነሳ በአመቱ በ34 ዓ.ም. ኃዋርያት አለምን ለማስተማር ሲበተኑ ኃዋርዋው ፊሊፖስ በጋዛ አቅጣጫ አድርጎ ሲሄድ በሰረገላ ላይ ተቀምጦ ወደ እየሩሳሌም ሊሳለም በመሄድ ላይ የነበረውን ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ የንግስት ህንደኬን አቃቤ ንዋይ የኢሳያስን መጽሐፍ [ትንቢት] ሲያነብ አግኝቶት የትንቢቱን ፍቺ ካስረዳው በኋላ አዲሱን ሃይማኖት ለመከተል «እመንና ተጠመቅ» ባለው መሰረት ወደ ወንዝ ወርደው ጃንደረባው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃዋርዋያ በፊሊጶስ ተጠምቆ ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች መካከል እንደሆነ እንረዳለን።

ልብ በሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ኃዋርያ የሆነው ፊሊጶስ ጃንደረባውን ሲያጠምቅ የተጠመቀው አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባው ብቻ አይደለም። ምክንያቱም የንግስቲቷ ልዑክ መሪና የኃብቷ ኃላፊ ወደ እየሩሳሌም በሰረገላ ሲሄድ ብቻውን አይሄድም። ይህ ማለት ጃንደረባው ወደ እየሩሳሌም በሰረገላ ሲሄድ ብዙ አጃቢና ጋሻጃግሬ አብሮት ይኖራል ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ «እንደንጉሱ አጎንብሱ» በሚባልበት ዘመን ደግሞ የልዑኩ መሪ ጃንደረባው ሲጠመቅ ልዑኩ ባጠቃላይ ይጠመቃል ማለት ነው።

እነዚህ ከአለም አስቀድመው ክርስትናን የተቀበሉት ኢትዮጵያውያዊው ጃንደረባና ወደ እየሩሳሌም አብረውት ሄደው የተጠመቁት የልዑክ ቡድኑ አባላት ከእየሩሳሌም ጉብኝት በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ጃንደረባው ዘመዶቹንና በስሩ ያለውን ሕዝብ፤ ባለሟሎቹም ዘመዶቻቸውንና ተከታዮቻቸውን ሁሉ እንዲጠመቁ ያደርጋሉወይንም ያስተምራሉ ነው። ይህ ማለት ባጭሩ ክርስትና ኢዛና የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሲሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የገባ ሃይማኖት አይደለም ማለት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በክርስትና ታሪክ የኢዛናን ዘመን ለየት የሚያደርገው ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት መሆኑ ብቻ ነው እንጂ ኢዛና የመጀመሪያው ክርስቲያን ንጉስ ከመሆናቸው ከሶስት መቶ አመት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ [ሙሉ በሙሉ ባይሆንም] ክርስቲያን የነበረና ክርስትናን የሚያስተምሩ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖቱ መምህራን ነበሩ ማለት ነው።

የጀርመኑ ፓስተር በንቲ ቴሶ ክርስትናን የተማረባት አገር ጀርመን ክርስትናን የተማረችው ሲልቲክ የሚባሉ ሕዝቦች የሚኖሩበትን የምዕራቡን የጀርመን ክፍል የግዛቷ አካል አድርጋ ታስተዳደር ከነበረችው ከሮማን ኢምፓየር ነው። ኢትዮጵያውያን ክርስትናን ተቀብለው ላልተጠመቀው ኢትዮጵያዊና ለቀሪው አለም ክርስትናን በሚያስተምሩበት ወቅት የሮም ቄሳሮች በክርስትናና በክርስቲያኑ ላይ ሲቀልዱ ነበር። ከዚህም አልፎ የሮማ ቆሳሮች የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያዎች የሆኑትን ጴጥሮስና ጳውሎስን በአደባባይ ሰቅለዋቸዋል።
ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን በአለም ላይ ከክርስትና ቀደምት አስረማሪዎች የምንመደብ ነን እንጂ የክርስቶስ ኃዋርያት የሆኑትን ጴጥሮስና ጳውሎስን የሰቀሉ ቄሳሮች ክርስትናን ካስተማሯቸው የክርስትና ተማሪዎች ክርስትናን አንማርም።

ከዚህ በተጨማሪ በአለም ላይ ካሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጅዎች ሁሉ እጅግ ጥንታዊውና የተሟላው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘው በግዕዝ ፊደል የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኝው የግዕዝ መጽሕፍ ቅዱስ እውነትም ጥንታዊና በአለም ላይ ከሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ሁሉ የተሟላ እንደሆነ አውሮፓውያን ሳይቀር አረጋግጠናል ብለው ነግረውናል። በዚህ ጥንታዊ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በደማው ቀለም ሰፍሮ የሚገኘውን «ኢትዮጵያ» የሚለውን ቃል በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተሰናዳው የእንግሊዙ ንጉስ የንጉስ ጀምስ መጽሕፍ ቅዱስ ቅጂ ሊለውጠው የሚችልበት የሞራል ልዕልና የለውም። ምን ይሄ ብቻ! አይደልም ከንጉስ ጀምስ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስትናን የተማረው ፓስተር በንቲ፤ ፓስተር በንቲ የተማረበትን መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ እንዲዘጋጅ ያደረገው የእንግሊዙ ንጉስ ጀምስ ራሱ ክርስትና ከኢትዮጵያ ይማር እንደሆነ እንጂ ለኢትዮጵያ ክርስትና ሊያስተምራት አይችልም።

እንግሊዞች ኢትዮጵያን አቢሲኒያ ይሏት ነበር። አውሮፓውያን የሆኑት ግሪኮች ደግሞ የቅድመ ክርስቶስ ልደት በፊት ኢትዮጵያን ኩሽ ይሏታል። ከነዚህ አገራት ሁሉ ግን ቀድመው ኢትዮጵያውያን ክርስትናን ተቀብለዋል። የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስም በነዚህ አገራት ቋንቋዎች ከተጻፈው በጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ እጅጉን ጥንታዊ ነው። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስላሉት የቦታ ስሞች ማመሳከሪያ ሊሆን የሚችለው ቀድሞ የነበረውና ጥንታዊ የሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ኦነጋውያን ግን የእውቀት ጾመኞችና በኢትዮጵያ ጥላቻ የናወዙ ስለሆነ የሚፈልጉትን ታሪክ ለመጻፍ አለም የተቀበለውን ጥንታዊውንና ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘው የግዕዝ መጽሕፍ ቅዱስ ማውገዝ እንጂ መጥቀስ አይፈልጉም። ከሰሞኑም ከሆነው ይሄ ነው።