የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
Ethiopian People’s Congress for United Struggle (Shengo)
www.ethioshengo.org shengo.derbiaber@gmail.com
ነሃሴ ፲፬ ቀን ፪ ሺህ ፱ ዓ. ም
August 20, 2017
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) አራተኛ ጉባዔውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቀቀ
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) አራተኛ ጉባዔውን ከነሃሴ ፲፪ እስከ ፲፬ ቀን ፪ ሺህ ፱ ዓ. ም (August 18 – 20, 2017) በአሜሪካን አገር፣ በቨርጂኒያ ግዛት፣ በአሌክሳንደሪያ ከተማ ውስጥ አካሂዷል። ጉባዔው በሦስቱ ቀናት ውስጥ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይቶችን አካሂዶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
የረጅም ዘመን ታሪክ ያላትና የሰው ልጅ መገኛ የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ወራሪ የፋሽስት ሠራዊትን በጦርና በጎራዴ አይቀጡ ቅጣት ቀጥታና አዋርዳ ነፃነቷን ያስከበረችና ለአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ሆና የኖረች ሀገር በአሁኑ ወቅት ከምን ጊዜውም በላይ ኅልውናዋ ከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያውያን በአኩሪ ታሪካችን ኮርተን በገዛ አገራችን በነፃነት የመኖር መብታችንን ተገፈን እንደ ዜጋ መኖር ያልቻልንበት አስከፊ ጊዜ ላይም እንገኛለን።
ኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታችን ተረግጦ በአፈና፣ እስራት፣ ግድያና የሽብር ኑሮን እየገፋን እንገኛለን። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በሥራ አጥነት፣ በኑሮ ውድነት፣ በረሃብና በበሽታ እየተሰቃዩ፣ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነው ኑሮን እንዲገፉ የተገደዱበት ድረጃ ላይ ተደርሷል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የወደፊቱ የአገሪቱ ተስፋዎች የሆኑ ወጣቶች እንደዜጋ በሀገር ውስጥ መኖር ካልቻሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው፣ የተሳካላቸው የስደት ኑሮን ሲያያዙት፣ በርካታዎቹ ግን በቀይ ባህርና በሜዲቴራኒያን ባህር ውስጥ እየሰጠሙ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ሆኗል። የተወሰኑትም የሰሃራ በረሃን ሲያቋርጡ በአክራሪ ቡድኖች በመስዋዕትነት ተሰይፈዋል። በተጨማሪም እራሳቸውን በማኖር ዘመዶቻቸውን ለመርዳት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ሴቶች እህቶቻችን ስብዕናቸው ተገፎ የዘመናዊ ባርነትና የውርደት ኑሮን እንዲገፉ ተዳርገዋል።
ሀገራችን አሁን ለምትገኝበት ውጥንቅጥ ችግር ዋናው መንስዔ በጠብ–መንጃ ኃይል የሥልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጠው ሽበርተኛና አምባገነን የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነው። በመሆኑም አገዛዙ በስፋት እያካሄደ ያለው አፈናና ግድያ ያስመረረው ሕዝባችን፣ ከስቃይ ኑሮ ለመላቀቅ ለብዙ ወራት የዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳያግደው በአራቱም ማዕዘናት መብቱን ለማስከበር ትግሉን እያጧጧፈ ይገኛል። ሕዝባችን የነፃነት አየር ለመተንፈስና ሀገራችንን በዕድገትና ብልጽግና ጎዳና ላይ እንድትጓዝ ለማድረግ ከፍተኛውን መስዋትነት በመክፍል እያካሄደ ያለውን የሞት የሽረት የሀገር አድን ትግል፣ ሸንጎ ከልብ ይደግፋል። ይህ ትግልም እንዲጠናከርና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እንዲቀጣጠል፣ ብሎም ጎሰኛውንና ጎጠኛውን የግፍ አገዛዝ በተባበረና በተቀናጀ መልኩ ታግሎ ለማስወገድ እንዲቻል ሸንጎ አቅሙ በፈቀደ መጠን ድጋፉን ይሰጣል፣ ሁለንተናዊ የሆነ ጥረት ማድረጉንም ይቀጥላል።
ሸንጎ በሦስት ቀን ጉባዔው ካሳለፋቸው በርካታ ውሳኔዎች ውስጥ አንኳር እንኳሮቹ፦
1. ጉባዔው የሸንጎውን የሁለት ዓመት ዘገባ አዳምጦና በዘገባው ላይ ውይይት አካሂዶ ዘገባውን አጽድቋል።
2. ጉባዔው እስካሁን ድረስ በአገዛዙ እየደረሰባቸው ያለውን መጠነ ሰፊ አፈና ተቋቁመው ሥርዓቱን እየታገሉ ካሉ የተለያዩ ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነቶች የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የተቀነባበረ የጋራ ትግል እንዲካሄድ ወስኗል።
3. አራተኛው ጉባዔው ሦስተኛው ጉባዔ ያፀደቀውን የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ዕድልን ከጥፋት ለመታገድ የሚመረጠውና የተሻለውን የሰላምና ዕርቅ አማራጭ እንደገና መርምሮ አሸባሪውንና አምባገነኑን አገዛዝ የሚወጥሩ ሁኔታዎችን በመፍጠር በማስገደድ ወይም በማስወገድ የሥርዓት ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ አጠናክሮ ሕዝብን ያማከል ትግል መቀጠል እንዳለበት ተስማምቷል።
4. ሸንጎ ትግሉን ይበልጥ ኣጠናክሮ ለመቀጥል፡–
ሀ) የሸንጎን አምስት መሠረታዊ መርሆዎች ማለትም
1. በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የሕዝቡ የሥልጣን ባለቤትነት የማያወላውል ዕምነት መኖር፤
2. የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች ማክበር፤
3. በሀገራችን የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን መታገል፤
4. በኢትዮጵያ ሕዝብ መካክል በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች አድሏዊነት ሳይኖር ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ዜጎች መሆናቸውን ማመንና በተግባር ማረጋገጥ፣
-
የህወሓት/ኢህአዴግን ሥርዓት ማስወገድና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካት ናቸው።