Wednesday, 23 August 2017 12:34
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የአማራና ቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ጀመረ። በዚህ መሠረት ቦርዱ የሕዝበ ውሳኔው መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ በማቀድ የአፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡
ቦርዱ የአማራና ቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው የሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት በማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች መጀመሩን በቅርቡ በአምባሳደርነት የተሾሙት የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና መግጳቸውን ከቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ባሳለፍነው ወር የቦርዱ ፅ/ቤቱ የቴክኒክ ጉዳዮችን ለመመርመር አንድ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የቅድመ ዝግጅት ዳሰሳ ጥናት ማካሄዱንና ስንት ምርጫ ጣቢያዎች ማቋቋም እንዳለበትና ስንት የምርጫ አስፈፃሚዎችና የሕዝብ ታዛቢዎች ማሰማራት እንዳለበት መለየቱን ቦርዱ አሳውቋል።
የአሁኑ ስብሰባም በሕዝበ ውሳኔ አፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ/ ረቂቅ ላይ ለመመካከርና የአማራና ቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖርባቸው 12 ቀበሌዎች በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የአፈፃፀም ማብራሪያ ላይ ከክልሉ መስተዳድር አካላት እና በክልሉ የተዋቀሩ የሁለቱ ሕዝቦች የጥምር ኮሚቴ አባላት ጋር ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክርቤት አፈ ጉባዔ አቶ ይርሳው ታምሬ በአካባቢው የነበሩትን ጥያቄዎች አብዛኛዎቹ ከሕዝብ ጋር በመወያየት፣ በመግባባት እና በመተማመን የተፈቱ መሆናቸውን በማስታወስ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄድባቸው 12 ቀበሌዎች ግን በሕዝብ ውሳኔ መፍትሄ እንዲያገኙ በሁለቱ ወገኖች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ መቅረቡን አስታውሰው፤ ምርጫ ቦርዱ በነዚህ አካባቢዎች ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንደሚደረግና ሕዝበ ውሳኔው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እምነት እንዳላቸው ተናግሯል። በመቀጠልም የሁለቱ ህዝቦች በሠላም አብሮ የመኖር ታሪካቸውን የሚያጠነክርና የሚያጎለብት ሕዝበ ውሳኔ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጿል።
በሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀውን ተቻችሎና ተግባብቶ አብሮ የመኖር ግንኙነትና ዝምድና የሚጠናከርበት፣ ችግሮች ተወግደው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማታቸው የሚጎለብትበት፣ የሕዝቦቹ ዘላቂ ሠላምና ብልፅግና የሚረጋገጥበት ሕዝበ ውሳኔ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 እና በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. መሠረት የተቋቋመ ተቋም እንደሆነና፤ ቦርዱ ግዙፍ ሕዝባዊና ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት ተሸክሞ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በየአምስት ዓመቱ በተከታታይ የሚካሄዱ ምርጫዎችን የጠቅላላ ምርጫ አምስት ጊዜ፣ የአካባቢ ምርጫ አምስት ጊዜ እንዲሁም በተለያዩ ደረጃ የምርጫ ዓይነቶች ማለትም የማሟያ ምርጫ፣ ድጋሜ ምርጫ እና ሕዝበ-ውሳኔዎችን ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ ሆነው እንዲጠናቀቁ በማድረግ በርካታ ልምድ ያካበተ ተቋም ነው።
ሕዝበ ውሳኔ ማለት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት ሲወሰን የህዝብ ፍላጎትን ለመለካት እና የሕዝብን ውሳኔ ለማወቅ ድምፅ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው። በዚሁ መሠረት ቦርዱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሕዝበ ውሳኔ ምርጫዎችን በብቃት በማካሄድ የህዝቦችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነትን አረጋግጧል። ለአብነት ለመጥቀስ የቤጊ ሕዝበ ውሳኔ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ ቀበሌዎች፣ እንዲሁም በኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች አዋሳኝ በሆኑት ቀበሌዎች ላይ የተካሄዱ ሕዝበ ውሳኔዎች ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቃቸውን ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የአማራና የቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖርባቸው 12 ቀበሌዎች ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አፈፃፀም ያጸደቀው የጊዜ ሰሌዳ እነሆ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የአማራና የቅማንት ሕዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ
ነሐሴ 2009 ዓ.ም
ተ.ቁ |
ክንውን |
ቀን |
1 |
በህዝበ ውሳኔው የጊዜ ሰሌዳ እና የህዝብ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ማብራሪያ ላይ ውይይት የሚደረግበት፤ | ነሐሴ 10 ቀን 2009 ዓ.ም |
2 |
ለህዝበ ውሳኔው አስፈፃሚዎች ስልጠና የሚሰጥበት፤ | ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2009 ዓ.ም |
3 |
ለህዝበ ውሳኔው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ የሚካሄድበት፤ | ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም |
4 |
ስለህዝበ ውሳኔው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ለህዝቡ ገለፃ የሚሰጥበት፤ | ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም |
5 |
ለህዝበ ውሳኔው ድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ የሚከናወንበት፤ | ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም |
6 |
የህዝበ ውሳኔው የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ክፍት ሆኖ የሚቆይበት፤ | ከመስከረም 4 እና 5 ቀን 2010 ዓ.ም |
7 |
የህዝበ ውሳኔው ቅሬታ በየደረጃው የሚቀርብበት እና ውሳኔ የሚሰጥበት፤ | ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም |
8 |
የህዝበ ውሳኔው የድምፅ መስጫ ዕለት፤ |
መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት |
9 |
ድምፅ አሰጣጡ እንደተጠናቀቀ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ቆጠራ የሚጀመርበት፤ | መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ |
10 |
የህዝበ ውሳኔው የድምፅ ቆጠራ በድምፅ መስጫ ጣቢያው በይፋ የሚገለፅበት፤ | መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም |
11 |
የህዝበ ውሳኔው የድምጽ ቆጠራ ውጤት ተጠናቅሮ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የሚላክበት፡፡ | መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም |