August 25, 2017 13:42

አሸንዳ፤ አሸንዳዬ
ማሬ ነሽ ወለላዬ።
አሸንዳ አሸንዳ ሙሴ
እርግፍ በይ እንደ ቀሚሴ
እም እም ሰብራ አንገት፤ እምም ሰብራ አንገት


እያሉ የጎንደር ወገራ አካባቢ ልጃገረዶች ሲሽከረከሩ ማየት “እምምምምም” ያሰኛል። ተሽከርከሩበት!!!። አሸንዳ የባህል ጨዋታ ስያሜውን የወሰደው አሸንድዬ ከሚባል ቅጠሉ ሰፋፊ ከሆነ የተክል ዓይነት ነው። የባህል ጨዋታው በከፊል ጎንደር ፤ በከፊል ወሎ እና በከፊል ትግራይ ውስጥ የሚከበር የልጃገረዶች የጨዋታ ዓይነት ነው። በአሉ የሚከበረው ከነሃሴ 15- 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ይህንን የልጃገረዶች ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ደርግ ወደ ስልጣን በወጣበት ወቅት ከተወለድኩበት ከጎንደር ከተማ ወደ እናቴ  ሃገር ወገራ አያቶቼ አካባቢ በሄድኩበት ወቅት ነበር። ይህንን ባህላዊ ጨዋታም የራሴን መለስተኛ የፈጠራ ዜማና ግጥም በመጨመር ለመጀመሪያ ጊዜ በጎንደሩ የፋሲለደስ ባህል ቡድን ለመድረክ እንዲበቃ አድርጌ ነበር። በወቅቱ ተወዳጆቹ ድምጻውያኖች አሰፉ ደባልቄ እና ሰላማዊት ነጋ ተጫውተውታል።

ታዲያ ዊንዲጎው ወያኔ ለምን የአሸንዳን ባህል የግሉ ለማድረግ ተውተረተረ? ከመቼ ጀምሮ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንደ አንድ ኢትዬጵያዊ ይመለከተኛል ብዬ ስላሰብኩ ጥያቄዎቹን በመንተራስ ከአንባቢዎቼ ጋር ለመካፈል ወደድኩ።  መቼም ነውጠኞቹ የዘመኑ ገዥዎቻችን በዘመን መካከል ከተዘገቡ መንግስቶቻችን ጋር ማነጻጸር በእጅጉ ቂል ያሰኛል። አነሳሳቸው ፤ አካሄዳቸው እና አደራረሳቸው? ዘውጉ ሌላ ነውና ። እነርሱ በጭካኔያቸው፤ በስግብግብነታቸው እና በውሸታቸው ፋሽዝምንም፤ አፓርታይድንም ከዚያም ሲልቅ ዲያብሎስን ያስናቁ የሴዖል ጀግኖች ናቸውና ከማን ጋር እናመሳስላቸው?። እንደእኔ እምነት የክፋታቸውን ከፍታ እና ጥልቀት ሰውኛው ቋንቋ ሊገልጠው አቅም ያጥረዋል። ለዚህ ጽሁፌ ማጣቀሻ ይሆነኝ ዘንድ ግን አንድ የአሜሪካ ህንዶችን ትርክት ላነሳ ወደድኩ ስለ ዊንዲጎ!።
ዊንዲጎ በመላው አሜሪካና በካናዳ በታላቁ የባህር ክልል ውስጥ በወቅቱ በስፋት የሚታወቅ ግማሽ ሰውና ግማሽ አውሬ ነው። ሰው ነው ስትሉት አውሬ ነው ፤ አውሬ ነው ስትሉት ሰው ነው። ህወኃትንና ጀሌዎቻቸውንማ አስተውሉልኝ እንዲህ ያለ ገጸ ባህሪ አይታያችሁም?። ለማንኛውም ይህ ሰው መሰል አውሬ  በመላው አሜሪካና በደቡብ ካናዳ አካባቢ ይኖሩ በነበሩ ህንዶች ህይወት ላይ ተጽዕኖ የፈጠረ አካል ነበር። ይህ ሰው መሰል አውሬ  በማህረሰቡ መካከል እየተገለጠ  በማስገደድና በማስጨነቅ የሚፈልገውን ሁሉ ያለርህራሄ ይወስድ ነበር። እናም ማህረሰቡ ዊንዲጎ ከመገለጡ በፊት የሚያቀርቡትን ስጦታ አስቀድመው አዘጋጅተው ነው የሚጠብቁት። ስጦታውን  የሚያቀርቡለት ስለሚወዱት አይደለም በጭካኔው ስለሚፈሩት እንጅ!።
እናም አንድ ቀን በአካባቢው ታላቅ ርሃብ ይከሰታል። ህዝቡ በዚህ ታላቅ ርሃብ ምክኒያት እንኳንስ ለዊንዲጎ የሚሰጠው ራሱን የሚያቆይበት አቅም አልነበረውም። እናም ርሃቡ ነገሮችን ከቁጥጥር ውጭ ማውጣቱ ብቻ ሳይሆን በህዝቡና በዊንዲጎ መካከል የነበረውን የፍርሃት ግንብም አፈራረሰው አንዳንድ ጊዜ “ለመልካም ነው” የሚባለው ለዚህ አይደል። በዚህ ርሃብ ምክኒያትም የዊንዲጎ የመጀመሪያ ልጅ በሞት ይቀጠፋል ዊንዲጎም ከልጁ ሞት በኋላ ራሱን ለማቆየት ያሚያስችል መልቲ ምክኒያት ፈጥሮ ሚስቱንና ቀሪዎቹን ልጆቹን ቆረጣጥሞ ይበላቸዋል።
ዊንዲጎ በአሜሪካውያን ህንዶች የጭካኔ፤የስግብግብነት ተምሳሌት ነው። ባላገሮቹ አሜሪካዊ ህንዶች ነጮቹንና መጤዎቹን አሜሪካዊያኖችን በሽሙጥ ዘይቤአዊ አነጋገር ዘመናዊዎቹ ዊንዲጎዎች እያሉ ይሸነቁጧቸዋል ለምን? ሲባሉ ሁሉንም ወስደው እንደዊንዲጎ አይረኩም ሲያሻቸውም የራሳቸውን ሰዎች ይበላሉ ይሏቸዋል። አሜሪካዊውንና በኢትዬጵያ ጋምቤላ ውስጥ  በአውሮፕላን አደጋ የሞቱትን ሚኪሊላንድን ሳስታውስ  ራሳቸውን ይበላሉ ወይ? ብዬ….ህምምም እላለሁ። የኛው ዊንዲጎ ህወኃትም እንዲህ ነው ስግብግብ ነው። ያለውን ሁሉ ዘርፎ አይረካም የብር ፤ የታሪክ፤የሃሳብ ፤የደንበር…ሌባ ነው እያጋፈፈ አይጠረቃም። ከዚያም ሲያልፍ ነገ ቀውጢ ቀን ሲመጣ  በለመደው ውሸቱ  ዛሬ ቆሜለታለሁ የሚለውን  የትግራይን ህዝብ ቆርጥሞ እንደሚበላው ምንም ጥርጥር የለኝም። ትላንትና እነ ኃየሎምን፤ክንፈን እና ሌሎችን ሺህዎችን የበላ ህወኃት ለነገ ለትግራይ ህዝብ ምን ዋስትና አለው?። ልብ ያለው ልብ ይበል ህወኃት የጤነኞች ሰዎች ስብስብ አይደለም። እንደዊንዲጎ ሰው ሲሏቸው አውሬ፤ አውሬ ሲሏቸው ሰው የሚሆኑ እሥስቶች ናቸውና።
ባለፉት 26 የመከራ ዓመታት  ሁላችንም የየራሳችን አስገራሚ ነገሮች እንደሚኖረን ባምንም ሁለት ገጠመኞቼን  ለአንባቢዎቼ ላካፍላችሁ። አንደኛው ገጠመኝ አንድ ጊዜ ከጅማ ወደ ሚዛን ተፈሪ እየተጓዝኩ ነበር። ከጎኔ ከተቀመጡት ሁለት የህወኃት ካድሬዎች መካከል አንደኛው የኢትዬጵያ አየር መንገድ የሚያሳትመውን “ሰላምታ” መጽሄትን ያገላብጣል። በመጽሄቱ ውስጥ ያሉትን የአክሱምን ፤ የላሊበላን፤ የፋሲልን ግንብ  ፎቶግራፎችን እየተመለከተ “አይ ትግራይ”  እያለ ይደነቃል። ከጎናቸው የተቀመጠው አንድ ምስኪን ኢትዬጵያዊ “ይህ ሁሉ ትግራይ ውስጥ ነው ያለው?” ብሎ ይጠይቀዋል። እርሱም ያለ ምንም ሃፍረት አዎ በማለት ይመልሳል እኔም አላስቻለኝምና  “ ምን ማለትህ ነው የጎንደር ፋሲል ግንብ፤ የወሎው ላሊበላ ሁሉ ትግራይ ውስጥ ነው የሚገኘው?”  አልኩት ካድሬው ኃፍረት ቢጤ ይወረው ጀመረ። “ቆይ ቆይ” በተሳስቻለሁ ዓይነት ለማደናገር ይሞክራል……….. ዊንዲጎው ህወኃት!።
ሁለተኛው አጋጣሚ አንድ  ውይይት ታክሲ ላይ ከፒያሳ አራት ኪሎ ተሳፍረን ስንጓዝ አንድ የትግራይ ወጣት የባህርዳሩን ግሼ ዓባይንና ጣናን፤ የጎንደሩን ፋሲል ግንብ፤ የወሎውን ላሊበላ፤ትግራይን ሙሉ በሙሉ ያካለለ ካርታ ያለበት ቲሸርት ለብሷል በካርታው ላይም  “ The queen of Sheba”  የሚል ጽሁፍ አለበት። ምንድነው ብዬ ጠየቅሁ ጥያቄዬ ያላስደሰተው ወጣት “እንግሊዝኛ አታነብም አንዴ?” አለኝ። ጽሁፉን አንብቤ “ምን ማለት ነው ለማለት ፈልጌ ነው” አልሁት “ትግራይ ማለት ነው” ብሎ ተረጎመልኝ………….. ስግብግቡ ዊንዲጎው ህወኃት!።
ሁለቱን አጋጣሚዎቼን ማካፈል የፈለግሁበት ዋና ምክኒያት ሃሳቦቹን ካስተዋልን የህወኃትን የዕብደት ምኞት ወለል አድርጎ ያሳየናል። በሌላ በኩል  ወያኔ ይህንን ያክል የአሸንዳ ጉዳይ ለምን ይወዘውዘዋል? ለሚለው ጥያቄ እነዚህ ሰዎች የምኞታቸው ዳራ ገደብ አልባ መሆኑንና እንደ ዊንዲጎ ስግብግቦች መሆናቸውን መግቢያ በርም ይሆነናል ብዬ በማሰብ ነው። የአሸንዳን በዓል የእኛ ነው ሲሉንም የአማራን ክልል ለመውረስ ካላቸው ክፉ ምኞት መነሻነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በዊንዲጎዎቹ ህወኃቶች አስተሳሰብ ሁሉም ነገር የትግራይ ነው።
ወያኔ የአሸንዳን በዓል በብቸኝነት በያዘው ሚዲያ መወትወት የጀመረው ከመቼ ጀምሮ ነው ? ስለሚለውም ትንሽ ልበል። ወቅቱ 1998 ነሃሴ ወር ላይ ጀምሮ ነው። ከዚህ በፊት ስለአሞራው ሙዚቃዊ ድራማ ጽፌ ነበር። ተውኔቱን የፃፍኩት ከ1997ቱ ምርጫ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ነበር። ተውኔቱን ያዘጋጀሁበት ዓቢይ ምክኒያትም በወቅቱ ለተከታታይ ወራት በሬዲዮ ፋና በሚተላለፍ ፕሮግራም የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ የማጠልሸት ስራ በሰፊው እየተሰራ ስለነበር ነው። የሬድዮው ዘመቻ ቅስትም ታሪክ የጀመረው ዛሬ ነው ዓይነት ነገር ልክ እንደ ማሪያኒቲ ፍልስፍና የደንበር አልባውን አፄ ትዕቢትን ወናፍ በማናፋት ነበር።   ጋዜጠኛ የተባሉቱም ያለምንም መሸማቀቅ ሰንካላውን የውንብድና ፍልስፍና በሰንካላ ቃላት ይቸፈችፉት ይሸፈሽፉት ይዘዋል። ያኔ ነው እንግዲህ ይህንን ሃሳዊ የወያኔ ልፍለፋ እንዴት መመከት ይቻላል? በሚል እሳቤ ተውኔቱን ያዘጋጀሁት፤ በወቅቱ ላደርገው የምችለው ይህንኑ ብቻ ነበርና። ተውኔቱ ከዝግጅት ጊዜው ጀምሮ ለመድረክ እስከበቃበትና ከዚያም በኋላ በገዥው ኃይላት ስለተደረገው ዘመቻ ራሱን የቻለ ተውኔት ወይም ሲኒማ ይወጣዋልና በዚህች አነስተኛ ጽሁፌ ለመንካት አልሞክርም።
ወደ ጽሁፌ ዋና ነጥብ ስመለስ በዚህ “አሞራው” በተሰኘው ሙዚቃዊ ድራማ ውስጥ  ከተካተቱት ዜማዎችና ውዝዋዜዎች መካከል አንዱ አሸንዳ ነበር። “አሞራው”  የሚለው ስያሜም የጀግናው ራስ ውብነህ ተሰማ የአርበኝነት ስም ነው። ውብነህ በጎንደር ክ/ሃገር በወገራ አውራጃ ቆላ መረባ በ1884 ተወልደው በአካባቢው ባህልና እምነት መሰረት ተኮትኩተው ያደጉና በኢትዮጵያዊነት ተጠምቀው ለኢትዮጵያውያን የኖሩ ስመ-ጥር ጀግና ናቸው። ‘አሞራው’ የሚለውን ስያሜ ያገኙትም በፈጠራ  የእውሸት ድርሰት ተጀቡነው ሳይሆን ሃገራችን ኢትዮጵያ በፋሺስት ወረራ ስር በወደቀችበት በዚያ የጭንቅ ወቅት እንደወርቅ በእቶን ውስጥ በዕውነት አልፈው ነው። እኒህ ጀግና የተወለዱት ቆላ ወገራ ነው መረባ “አሸንዳ”ም  የአካባቢው ልጃገረዶች የባህል ጨዋታ በመሆኑ በሙዚቃዊ ድራማው ውስጥ እንዲካተት የተደረገውም ለዚህ ነበር ።
ወያኔን በተውኔቱ ውስጥ ሁለት ነገሮች ቆጥቁጠውታል። አንደኛ የአሸንዳ ጨዋታ ሲሆን ሁለታኛው ደግሞ  አሞራው  የሚለውን አርበኛ ስም ናቸው የወያኔ የወቅቱ የዘመቻዎቹ አንኳር ሃሳቦች ሆነውም ወጡ። በወቅቱ የግል ጋዜጣ አሳታሚዎች በሙሉ እስር ቤት የገቡበት ጊዜ ነበርና ወያኔ በግላጭ አገኘን በብቸነት በያዘው ሚዲያም አሞራው ማን እንደሆነ እና አሸንዳም የማን እንደሆነ አጥብቆ መለፈፉን ተያያዘው።
ተውኔቱ ወደ መድረክ እንዳይወጣ ከተደነቀሩት መሰናክሎች መካከልም ተውኔቱ ለህዝብ እይታ ከመቅረቡና የማስታወቂያ ስራ ከመሰራቱ በፊት የተውኔቱ ጭብጥ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ለመሆኑ የታሪክ ምሁራን ማረጋገጫ መስጠት አለባቸው ተባልኩ። ይህንን ለማረጋገጥ ወደ አዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የታሪክ ክፍል /Department/መሄድ ነበረብኝና  በወቅቱ የክፍሉ ኃላፊ ከነበሩት ከዶ/ር ተክለሃይማኖት ገ/ ስላሴ ጋር በዪኒቨርሲቲው ውስጥ  የግል ውይይት አደረግን።ራስ አሞራው የትግራይ ሰው ናቸው የሚለውን የዶ/ሩ ብዥታ ላይ ጋል ያለ ክርክር አድርገንና አጥርተን፤ አርበኛውም ጎንደሬ ለመሆናቸው ተማምነንና ዶ/ር ተክለሃይማኖትም ቲአትር ቤት ድረስ በመምጣት ከተመለከቱ በኋላ ለተውኔቱ የነበራቸውን አድናቆት ገልጸው በአዲስ አበባ የታሪክ ትምህርት ክፍል /Department/ ስም ደብዳቤ ጽፈውልናል ደብዳቤው አሁንም በእጄ ይገኛል። አትዘንጉ አሸንዳም አለች።
እዚህ ላይ የሰውየውን የግል ስእብና ሳላደንቅ ባልፍ ህሊናዬ ይከሠኛል ሰውዬው በውይይት የሚያምኑ የተረጋጉ ሰው መሆናቸውን መመስከር አለብኝ በስመ ህወኃት ሁሉም የትግራይ ልጆች መጨፍለቅ የሌለባቸውም ለዚህ ነው። በነገራችን ላይ ይህን ተውኔት ትግራይ ድረስ በመውሰድም እንዲታይ አድርጌአለሁ። ከታዬ በኃላም ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የትግራይ ሰዎች ምኝታ ቤታችን ድረስ በመምጣት ያላቸውን  አድናቆት ከመግለጽ  ባሻገር ለታሪካቸው ያላቸው ቁጭትም እፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር። አትዘንጉ “አሸንዳ” የምትለው ጨዋታም አብራ ትዞር ነበር። ስጠቀልለው አሸንዳ ወያኔ እንደሚለው የትግራይ ብቻ ሳይሆን የጎንደርም የወሎም ነውና የአካባቢው ልጃገረዶች ተነሱ “አሸንዳዬ አሸንዳ ሙሴ በሉ” ባህሉ የናንተም ነውና!። አበቃሁ።