ዘመኑ ተናኘ’s blog

 

(ከግራ – መለስ አለም፣ ማርቆስ ተክሌ እና አበበ አይነቴ

የኢትዮጵያ አዲሱ የወደብ ፖለቲካ

23 Aug, 2017

By ዘመኑ ተናኘ

 

ኢትዮጵያ የባህር በር ከሌላቸው አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ አገሪቱ ያለ ባህር መኖር ከጀመረች ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ተቆጥሯል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ስትሄድ የአሰብንና የምፅዋን ወደቦች ይዛ በመሄዷ ወደብ አልባ አገር ሆናለች፡፡

የባህር በር ወይም ወደብ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለወታደራዊ አገልግሎት ያለው ጥቅምም ከፍተኛ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ጂቡቲ ከአራት በላይ ወደቦች አሏት፡፡ ይህች ትንሽ አገር ተፈላጊነቷ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ሆኗል፡፡ ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ እንዲሁም ከአሜሪካ እስከ እስያ ድረስ ያሉ አገሮች ዓይናቸውን እንደጣሉባት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የተወሰኑ አገሮች ቻይናን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በዚች ትንሽ አገር ወታደራዊ ቤዝ ገንብተዋል፡፡ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ የበለፀጉ አገሮች በብዛት ምርጫቸው እንድትሆን አድርጓል፡፡

እነዚህ አገሮች ወደዚች ትንሽ አገር መጥተው ወታደራዊ ቤዝ እንዲኖራቸው ካስፈለጓቸው ምክንያቶች ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ የዚህ አካባቢ ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያና ግብፅ በወደብ ስም በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ኤርትራ በመሄድ በዚህ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ሲያጠኑና ሲከታተሉ ይታያሉ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ከአሰብ ወደብ ከፊሉን ከኤርትራ በሊዝ ገዝታ ለብዙ ዓመታት ለማስተዳደር ፈቃድ አግኝታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት የአሰብና የምፅዋ ወደቦች ለግመል ውኃ መጠጫነት ከማገልገል የዘለለ ፋይዳ እንደሌላቸው ሲነገር ቢሰማም፣ የዓረብ አገሮች በተደጋጋሚ ጊዜ ወደዚህ አካባቢ ሲሄዱና ወታደራዊ ሠፈር ሲያቋቁሙ ታይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጂቡቲ ወደቦች በሁለት ሳምንት የሚያንቀሳቅሱትን ያህል በዓመት ማንቀሳቀስ እንደማይችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አሁንም ድረስ ግን ተፈላጊ መሆናቸው የማይካድ ነው፡፡
የጂቡቲን ወደቦች ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ይጠቀሙባቸዋል፡፡ እነዚህ አገሮች የጂቡቲ ወደቦችን የኢትዮጵያን ያህል የሚጠቀሙ ባይሆንም፣ በአካባቢው ላይ ያላቸው ፍላጎትና ዝንባሌ ግን ከፍተኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት ለወደብ ኪራይ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለጂቡቲ እንደምትከፍል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወጪና ገቢ ንግዷን የምታካሂደውም በጂቡቲ ወደቦች ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የጂቡቲ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የወደብ ማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡

የጂቡቲ መንግሥት ከቻይና ባገኘው ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍም አዳዲስ ወደቦችን እየገነባና እያስፋፋ ነው፡፡ ይህን የወደብ ማስፋፋት ፕሮጀክት ሲያከናውን በዋናነት ተሳቢ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ደግሞ ኢትዮጵያን ነው፡፡

በሌላ በኩል ንብረትነቱ የሶማሌላንድ የሆነው የበርበራ ወደብ ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ወደብ የማስተዳደር 19 በመቶ ሥልጣን ቢኖራትም፣ በዋናነት የሚተዳደረው ግን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት ነው፡፡ ሶማሌላንድ 35 በመቶ፣ ኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፣ 46 በመቶ ወደቡን የማስተዳደር ሥልጣን የኤምሬትስ መንግሥት ነው፡፡

በዚህ የአፍሪካ ክፍል በተለይም በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን የባህር በር በቅርብ ሆኖ ለመከታተል፣ እንዲሁም አማራጭ ወደብ ለማግኘት በማለት የተለያዩ አገሮች በእነዚህ ወደቦች ላይ ፍላጎት ያሳያሉ፡፡
ኢትዮጵያም በበኩሏ የባህር በር የሌላት አገር ከመሆኗ አንፃር የጂቡቲ ወደቦችን በመከራየት የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴዋን ስታካሂድ ቆይታለች፡፡ ከጂቡቲ ወደቦች ባሻገር በአማራጭነት ሌሎች ወደቦችንም ስትጠቀም ኖራለች፡፡ አገሮች የወደቦች ሽሚያ በሚመስል ውድድር ውስጥ በመግባት የባህር በርና ወደብ ወዳላቸው አገሮች ፊታቸውን እያዞሩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከሱዳን መንግሥት ወደብ በመከራየት የአገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ ለማካሄድ ዕቅድ እንደያዘች ሰሞኑን ተነግሯል፡፡

ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ኃይል አላቸው የሚባሉት ኢትዮጵያና ኬንያም ይህን የኃይል ሚዛን ለማስጠበቅ ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ፡፡ የእነዚህን አገሮች የበላይነት ሊገዳደሩ የሚችሉ አገሮች ብቅ ማለት እንደጀመሩ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም የባህረ ሰላጤው አገሮች ስብስብ ወደ ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ መምጣት፣ የእነዚህ አገሮችን ኃያልነት ሊገታ እንደሚችል ፍርኃታቸውን ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ፖርት ሱዳን የመሄዷ ጉዳይም ይህ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

ተንታኞች ይህን ይበሉ እንጂ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ጄኔራል ዳይሬክተር አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ (ዶ/ር) ይህንን  ሐሳብ ይቃወማሉ፡፡ ኢትዮጵያ የወደብ አማራጯን እያሰፋች የመጣችው የጂቡቲ ወደብ ከመጠን በላይ እየተጨናነቀ በመምጣቱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የበርበራ ወደብንም ሆነ የፖርት ሱዳንን ከጁቡቲ ወደቦች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለመጠቀም ስታስብ፣ አሁን እያደገ የመጣውን የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በተቀላጠፈ መንገድ ለማከናወን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የውጭ ግንኙነት ጥናት ኢንስቲትዩት የጂኦፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪና ተንታኙ አቶ አበበ ዓይነቴ በዶ/ር ማርቆስ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አቶ አበበ፣ ‹‹ከየትኛውም አገር ወደብ የምናገኘው በኪራይ ነው፡፡ በአገሪቱ የውጭ ግንኙነትና ደህንነት ፖሊሲ ላይ ከሁሉም አገሮች ልናገኝ የምንችለው አገልግሎት በግልጽ ሠፍሯል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ኬንያ፣ ሶማሌላንድ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲና ሌሎች አገሮች ወደብ ብንከራይ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ላይ እንደተቀመጠው ለኢኮኖሚያዊው ፋይዳው እንጂ ለፖለቲካ ይዘቱ አይደለም፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ ፖርት ሱዳን መሄዷ አማራጭ ወደብ ፍለጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮች እንዲኖራት ትፈልጋለች፣ በጎረቤት ያሉ ወደቦችን መጠቀም ትፈልጋለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሱዳን በሄዱበት ጊዜ እንደተናገሩት ካለፈው ዓመት በተሻለ ፖርት ሱዳንን ዘንድሮ ተጠቅመንበታል፡፡ ለቀጣዩም አጠቃቀማችንን ከፍ ለማድረግ ፍላጎት አለን፤›› ብለዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ ፖርት ሱዳን መሄዷ ጂቡቲን ቅር ሊያሰኛት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ጂቡቲ ይህንን ሁሉ ወደብ የምታስፋፋው በዋናነት ኢትዮጵያን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ በመጠቆም፣ ኢትዮጵያ 50 በመቶ የሚሆነውን የወጪና ገቢ ንግዷን በፖርት ሱዳን ለማካሄድ መፈለጓ ሌላ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ አይስማሙም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋምም ይህ እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ሌላ አገርን ለማስደሰት ብሎ የሚያደርገው የወደብ አጠቃቀም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ አቶ አበበ ወደቦችን ስንጠቀም የሚወስደውን ጊዜ እንጂ ሌላ የፖለቲካም ሆነ ሌላ ይዘት እንደሌለው ይከራከራሉ፡፡
ዶ/ር ማርቆስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ፖርት ሱዳንን 50 በመቶ ለመጠቀም መወሰኗ ትክክል እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲገልጹም ጂቡቲ በአሁኑ ወቅት ወደቦቿን እያስፋፋች በመምጣቷና ለዚህም ኢትዮጵያን ዋነኛ ተዋናይ አድርጋ በማቀዷ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት አማራጭ ውስጥ መግባቷ ጂቡቲ በተደጋጋሚ የምትጨምረውን የወደብ ኪራይ ሊቀንስ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

አቶ መለስ ኢትዮጵያ 50 በመቶ የወጪና ገቢ ንግዷን በፖርት ሱዳን ልታደርግ አቅዳለች የተባለው የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ጠቅላይ ሚነስትሩ በንግግራቸው ወቅት ግማሽ የሚሆነውን የአገሪቱን ገቢና ወጪ ንግድ በፖርት ሱዳን ለማካሄድ ማቀዷን ግልጽ አድርገዋል፡፡ በርበራም ሆነ በፖርት ሱዳን፣ እንዲሁም በጂቡቲም ሆነ በሞምባሳ ወደቦች ላይ ኢትዮጵያ ያላት አቋም የሽሚያ ሳይሆን የአማራጭ ጉዳይ መሆኑን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህሩ ግን ይህንን ሐሳብ ይቃወማሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌሎች ወደቦች መሄድ መጀመሯ የገልፍ አገሮች በአካባቢው ላይ እያሳደሩት ያለውን ወቅታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ አቶ አበበ ግን ኢትዮጵያ ሌሎች የወደብ አማራጮችን የፈለገችው በአገሮች መካከል የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠርና ተጠቃዋሚነትን ለማዳበር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ዶ/ር ማርቆስ ግን የመምህሩን ሐሳብ ይደግፋሉ፡፡ ‹‹ይህ እውነት ነው፡፡ ይህ አካባቢ ስትራቴጂካዊ ነው፡፡ ጂቡቲ ላይ እየሆነ ያለው ይህ ነው፡፡ ለምሳሌ ከቻይና ጀምሮ ጦራቸውን በጂቡቲ ላይ እያሠፈሩ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ይህ አካባቢ ጂኦግራፊያዊ ጠቀሜታው ዝቅ ያለ ሆኖ ቢቆይም አሁን ተመልሶ አንሠራርቷል፡፡ በብዙ ምክንያቶች የተነሳ ይህ አካባቢ ለጂኦፖለቲካም ሆነ ለወታደራዊ አገልግሎት ጠቃሚ ስለሆነ ሁሉም አገር ድርሻውን ለመያዝ እየታገለ ነው፤›› በማለት ያብራራሉ፡፡ ዶ/ር ማርቆስ እንደሚሉት ኤርትራ እንኳ ካለችበት እስር ቤት ወጥታ ወደዚህ ውድድር እየገባች ነው፡፡ ኢትዮጵያም ዝም ብላ ቆይታ አሁን ማሰብ መጀመሯም የሚደገፍ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አቶ መለስ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደተለያዩ አገሮች በመሄድ አማራጭ ወደቦች እንዲኖራት ማቀዷ ከፖለቲካም ሆነ ከወታደራዊ አገልግሎት ጋር እንደማይያያዝ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አቋም በየጊዜው የሚቀያየር ሳይሆን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ የተመረኮዘና በጋራ ተጠቃነት ላይ ያተኮረ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ መምህሩ ግን ኢትዮጵያ ወደ ሱዳን መሄዷ ሌላ ፖለቲካዊ ጫና ውስጥ መግባቷን የሚያሳይ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸውን ሲያብራሩ፣ ሱዳን ተደጋጋሚ የሆነ ጥያቄ ማቅረብ በመጀመሯ አገሪቱ በግድ ወደዚህ እንድትገባ እንደተገደደች እንደሚያምኑ ያስረዳሉ፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች ሱዳን ግብፅን ትታ ወደ ኢትዮጵያ ልትመጣ የምትችለው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ብቻ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለጂቡቲ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለወደብ ኪራይ ትከፍላለች፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ቢሊዮን ዶላሩን ለሱዳን የምትከፍል ከሆነ ሌላ ይዘት ይኖረዋል ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ ፖለቲካዊ ጉዳይ ሊያመጣ እንደሚችል በማስረዳት፡፡

የጂቡቲ መንግሥት እንደሚለው በዓመት 35 ሺሕ የተለያዩ አገሮች መርከቦች በጅቡቲ በኩል ያልፋሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ጂቡቲ በዓመት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ታገኛለች፡፡ በእነዚህ ወደቦች በዋናነት ኢትዮጵያ የምትጠቀም ቢሆንም ኡጋንዳና ኬንያም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

የሶማሌላንድ የበርበራ ወደብም ዓለም አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ አካባቢ ከወደብ አገልግሎት ባሻገር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ለአብነት ያህልም በዚህ አካባቢ የኤምሬትስና የኳታር ወታደሮች ይገኛሉ፡፡ በተለይ የገልፍ አገሮች ይህንን አካባቢ እንደሚፈልጉት አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በዚህ አካባቢ እየተፈጠረ ያለውን ወታደራዊ አሠላለፍና ጫና በቅርብ ሆኖ ለመከታተልና አካባቢውን አሳልፎ ላለመስጠት፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ፊታቸውን ወደዚያ እንዳዞሩ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡

አቶ አበበ የኢትዮጵያ ወደ ፖርት ሱዳንና በርበራ መሄድ ለሌላ ፖለቲካዊ  ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸው፣ አሁን ያለው በተለይ ከዓረቡ አብዮት በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበረው የኢኮኖሚ ትስስር ትንሽ እየራቀ እንደመጣ አመልክተዋል፡፡  አሁን የአገሮች ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው በላይ ስትራቴጂካዊ ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱን ያብራራሉ፡፡ ለዚህ ጉዳይ እንደ ምክንያት ብለው ያስቀመጡት ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ነው፡፡

እንደ ቻይና ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው እየጨመረ በመጡ አገሮች አማካይነት የፖለቲካ ምኅዳሩ እየተቀየረ መምጣቱንም ይጠቅሳሉ፡፡ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የገልፍ አባል አገሮች (34 አባላት) ወታደራዊ ኅብረት ፈጥረው እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው፣ በዚህ አካባቢ የወደብም ሆነ የወታደራዊ ቤዝ ፍለጋ ሽሚያ እንደሚመስል ይገልጻሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ እንደ አገር ከዚህ ርቃና ተገልላ መኖር እንደማትችል ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገሮች የራሷ የሆነ ጠንካራ ወታደራዊ ቤዝ ቢኖራት እንደሚመረጥ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ማርቆስ ኢትዮጵያ የፖርት ሱዳንን የመጠቀም ጉዳይ መዘግየቱ ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህን ሐሳብ አቶ አበበም ይጋሩታል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ ለመግባት ሙከራ መደረጉን እንደ ጥሩ ጎን ይወስዱታል፡፡

ኢትዮጵያ ከዛሬ 30 እና 40 ዓመታት በፊት የራሷ በሆኑ ወደቦቿ ስትጠቀም ቆይታ ዛሬ ወደብ የሌላት አገር ሆናለች፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ኪሳራ እየደረሰባት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በዓመት ለወደብ ከምትከፍለው ኪራይ በተጨማሪ ለደኅንነቷ አሥጊ የሆኑ ጉዳዮች በአካባቢው እየተፈጠሩ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በወደብ ስም የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ወደ ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ጠረፎች እየተጠጉ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች እየተስፋፋ የመጣ የአሸባሪነት ድርጊትም አገሪቷን ሊጎዳት እንደሚችል ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ሆነ ለፖለቲካ ደኅንነት ወደ እነዚህ አገሮች በመሄድና ወደብ በመከራየት አካባቢውን መቃኘት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹ የባህር በር ለሌላት ኢትዮጵያ ወደብ የአማራጭ ብቻ ሳይሆን የሽሚያ ጉዳይም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (ለዚህ ዘገባ ብርሃኑ ፈቃደ አስተዋጽኦ አድርጓል)

 

ምንጭ – ሪፖርተር )