August 26, 2017 13:48

የብሔርተኝነት እና የአንድነት አቀንቃኞች ስለ ኢትዮጲያ ታሪክ ያላቸው ግንዛቤ ውስንና ተመሳሳይ ነው። በእርግጥ ሁለቱ ወገኖች የሚያውቁት ወይም ያነበቡትና የሰሙት ትርክት ለየቅል ነው። ነገር ግን፣ የሁለቱም የታሪክ ዕውቀትና ግንዛቤ ከምክንያታዊነት (objectivity) ይልቅ ግላዊነት (subjectivity) የበዛበት ነው። ለምሳሌ፣ ዘወትር ስለ አደዋ ድል እና የኢትዮጲያ አንድነት የሚያቀነቅኑት ብሔርተኞች በዚያ ምክንያት ከስምጥ ሸለቆ በስተምስራቅ በሚገኙ ማህብረሰቦች ላይ ስለተፈፀመው ግፍና በደል በቂ ግንዛቤ የላቸውም። በተመሳሳይ፣ ዘወትር በማህብረሰባቸው ላይ ስለተፈፀመ ግፍና በደል የሚናገሩ ብሔርተኞች ስለ አደዋ ድል እና ስለ አንድነት ፋይዳ ያላቸው ግንዛቤ በጣም ውስን ነው።

ግላዊ (subjective) የሆነ የታሪክ ዕውቀትና ግንዛቤ በመግባባት ላይ ለተመሰረተ ውይይት ዋና ማነቆ ነው። ብሔርተኞች በራሳቸው ብሔር ላይ የደረሰን ግፍና በደል ከመዘርዘር ባለፈ በሌላ ግዜ፥ ቦታና ምክንያት በሌሎች ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ላይ ከተፈፀመው ግፍና በደል ጋር አያይዘው አይመለከቱም። በሌላ በኩል፣ የኢትዮጲያን አንድነትና ነፃነት የተረጋገጠው የተለያዩ ሉዓላዊ ግዛቶችን በኃይል በመጨፍለቅ እንደሆነ አይገነዘቡም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሁለቱም ወገኖች የኢትዮጲያ ታሪክ እና አመሰራረት ከሌሎች ሀገራት ታሪክና አመሰራረት ጋር አያይዘው አይመለከቱም። ለምሳሌ፣ በአኖሌ ስለ ተፈፀመው ግፍና በደል የሚያውቅ የአንድነት አቀንቃኝ በኩራት የሚያወድሰው የኢትዮጲያ አንድነትና ነፃነት ያስከፈለውን ዋጋ ይገነዘባል። በተመሳሳይ፣ ስለ ሌሎች ሀገራት አመሰራረት የሚያውቅ ብሔርተኛ ከአኖሌ በደል ይልቅ የአደዋ ድልን ማስታወስ ይመርጣል።

ስለዚህ፣ የብሔርተኝነት እና አንድነት አጀንዳ የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ልሂቃን ላይ የሚስተዋለውን የግንዛቤ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የኢትዮጲያ ዘመናዊ ታሪክን ከሌሎች ሀገራት ታሪክ ጋር አንፃር መመልከት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የፈረንሳይ እና ኢትዮጲያ ታሪክን በንፅፅር መመልከት በጉዳዩ ዙሪያ የላቀ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል። ምክንያቱም፣ የሁለቱ ሀገራት ታሪክና አመሰራረት ተመሳሳይ ከመሆኑ በተጨማሪ ተያያዥነት አለው።
ፈረንሳይ በምዕራባዊያን ዘንድ ቁልፍ ሚና ያላት ሀገር ናት። በተለይ እ.አ.አ. በ1789 ዓ.ም የተካሄደው የፈረንሳይ አብዮት በምዕራቡ ዓለም በእኩልነት እና ነፃነት መርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት እንዲዘረጋ አስችሏል። በእርግጥ ከፈረንሳይ አብዮት በፊት ቀድሞ የተካሄደው የአሜሪካን አብዮት ነው። ነገር ግን፣ የአሜሪካ አብዮት በራሱ የምዕራብ አውሮፓ ምሁራን፣ በተለይ ደግሞ የፈረሳይ አብዮተኞች የሙከራ ውጤት ነው። የፈረንሳይ አብዮተኞች ትግላቸውን የጀመሩት በአሜሪካ የነፃነት ትግል ላይ በመሳተፍ ነው። ለምሳሌ፣ የፈረንሳይ እብዮት መሪ የነበረው “Marquis de la Fayette” የፈረንሳይን አብዮትን ከመምራቱ በፊት የአሜሪካ የነፃነት ጦርነት ተጀምሮ-እስኪያልቅ ከአሜሪካኖች ጎን ቆሞ ተዋግቷል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በኒውዮርክ ከተማ የሚገኘውና በአሜሪካኖች ትልቅ ግምት የሚሰጠው የነፃነት ሃውልት (statue of liberty) ከፈረንሳዮች የተበረከተ ስጦታ መሆኑ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። በአጠቃላይ፣ በምዕራቡ ዓለም የነፃነት እና እኩልነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትጠቀሰው ሀገር ፈረንሳይ ናት።

ልክ እንደ ፈረንሳይ ኢትዮጲያም በአፍሪካዊያን፣ እንዲሁም በመላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ የነፃነት እና እኩልነት ተምሳሌት የሆነች ሀገር ናት። ጥቁሮች ከቅኝ-አገዛዝ እና የነጮች ጉልበት ብዝበዛ ነፃ ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል ከፊት ሆና የመራች ሀገር ናት። ይህ የሆነው ደግሞ በአደዋ ድል አማካኝነት ነው። ኢትዮጲያ በ1889 ዓ.ም የኢጣሊያን የቅኝ-አገዛዝ ወረራ በመመከት የተቀዳጀችው አንፀባራቂ ድል በመላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ የነፃነት እና እኩልነት ትግል እንዲቀጣጠል በማድረግ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ፈረንሳይ ለነጮች፣ ኢትዮጲያ ደግሞ ለጥቁሮች የነፃነትና እኩልነት ተምሳሌት ናቸው። ይህ ግን የሀገራቱ ከፊል ታሪክ ነው። ምክንያቱም፣ ሁለቱም ሀገራት የተመሰረቱት የተለያዩ ጎሳዎችን፥ ብሔሮችን፥ ብሔረሰቦችን፥ ሕዝቦችን፥ ወይም ራስ-ገዝ ግዛቶችን በኃይል፥ በጦርነት በመጠቅለል ነው። ስለዚህ የሁለቱም ሀገራት አመሰራረት በአስከፊ ጦርነት እና ጭካኔ (war and brutality) ላይ የተመሰረተ ነው።

ልክ እንደ ኢትዮጲያና ፈረንሳይ ሁሉም የዓለም ሀገራት የተመሰረቱት በአስከፊ ጦርነት እና ጭፍጨፋ ነው። እንደሚታወቀው የአሁኗ ኢትዮጲያ የተመሰረተችው በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመን ሲሆን አብዛኛው የሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በአስከፊ ጦርነትና ጭፍጨፋ የተጠቃለለ ነው። ይህ ግን ከየትኛውም ሀገር ታሪክና አመሰራረት የተለየ አይደለም። “What is a Nation?” በሚለው ፅሁፍ የሚታወቀው ፈረንሳዊ የታሪክ ምሁር “Ernest Renan” ሁሉም ሀገራት በአስከፊ ጦርነትና ጭፍጨፋ የተመሰረቱ መሆናቸውን ይገልፃል፡-

“All nations, even the most benevolent in later practice, are founded on acts of violence, which are then forgotten. Unity is always achieved by brutality: the joining of the north of France with the center was the result of nearly a century of extermination and terror. ….No French citizen knows whether he is a Burgundian, an Alan, a Taifale, or a Visigoth, yet every French citizen has to have forgotten the massacre of Saint Bartholomew, or the massacre that took place in the South in the thirteenth century.”  Ernest Renan, “Qu’est-ce qu’une nation?¨, conference faite en Sorbonne, le 11 Mars 1882.

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ እያንዳንዱ ሀገር እንደ ሀገር የተመሰረተው በአስከፊ ጦርነት እና ጭፍጨፋ ነው። “ለምን?” የሚለው ከሀገር አመሰራረት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የፈረንሳይ እና ኢትዮጲያ አመሰራረትና ታሪክን ዋቢ በማድረግ በቀጣይ ክፍል ሰፋ ያለ ትንታኔ ይዘን እንቀርባለን።