የእልቂት ማስጠንቀቂያ ደወል

ነሃሴ 20-2009 (27-08-2017)

ከሁለት ቀናት በፊት የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት ለዜጎቹ ባወጣው የማስጠንቀቂያ መልእክት ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ውጊያ ልትገባ እንደምትችል የሚያመላክትና ለዚያ መንደርደሪያ የሚሆኑ ግጭቶች በያቅጣጫው መከሰታቸውን፣በስልጣን ላይ ያለውም እብሪተኛ የጎሰኞች ቡድን ሁኔታውን መቆጣጠር ተስኖት ይበልጥ ቀውሱ እንዲቀጣጠል የሕዝቡን ተቃውሞና ጥያቄ በማፈን አነጣጥሮ ተኳሾችን በማሰማራት ሁኔታው እንዲባባስና ከእጅ እንዲወጣ በማድረግ ላይ የተሰማራ መሆኑን ሳይደብቅ ይፋ አድርጓል።የካናዳና አንዳንድ የአውሮፓ አገሮችም ለዜጎቻቸው ተመሳሳይ መልእክት አስተላልፈዋል።

«ማን ይናገር የነበረ፣ማን ያርዳ የቀበረ» ነውና አሜሪካኖች ከወያኔ መራሹ መንግስት ጋር ካላቸው ቅርበት በአገሪቱ ውስጥ ምን እንዳለና ምንስ ሊፈጠር እንደሚችል ከቅርበት የማየትና የማወቅእድላቸው ከፍተኛ ነው።ስለሆነም ይህን ይከሰታል ብለው በይፋ የገለጹትን አደጋ ለዜጎቻቸው በቅድሚያ ማስገንዘብና ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲመረምሩና በአገሪቱም ውስጥ የሚገኙት ከአደጋው ለመትረፍ ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል፤በተጨማሪም አድራሻቸውንና የቴሌፎን ቁጥራቸውን በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኘው ኤምባሲ ቢሮ እንዲገልጹ፣ የኢንተርኔት ግንኙነትም ላይኖር ስለሚችል በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ግንኙነት ለማድረግ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ በጥብቅ አሳስቧል።

ይህንን የመሰለ ጥሪና ማስጠንቀቂያ ከተለያዩ አገሮች መንግስታት ቢሮ በተለይም ከአሜሪካኖቹ በኩል በቀላሉ የሚሰጥ ሳይሆን የአደጋውን ደረጃና አይነት በስፋት ከዘረጉት የስለላና የመረጃ ሰንሰለት ግኝት በመነሳት አውጥተውና አውርደው ያሳለፉት የፖለቲካም ይዘት ያለው ውሳኔ ነው።

ታዛቢና አሳቢ መንግስት ያለው ዜጋ ከሚመጣው አደጋ እራሱን እንዲጠብቅና እንዲድን ይህን የመሰለ ጥረት ሲደረግለት ስንሰማ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። አደጋ ውስጥ ያለውንም ዜጋቸውን ለማትረፍ የጦር ሃይል ሳይቀር ሊያሰማሩ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ የታዬ ድርጊት ነው።ታዛቢና አሳቢ መንግስት የሌለው እንደውም በራሱ መንግስት የሚጠቃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ለጭዳ ወደ ቄራ እንደሚነዳ ከብት ለአደጋ ሲጋለጥ የሚከላከልለት ሃይል አላገኘም።ሁሉም በየፊናው እልቂቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኖ የተቀመጠ ይመስላል።ያማ ባይሆን ኖሮ በጎሳ ተከፋፍሎ በሚያደርገው የተበታተነ ትግል ውስጥ አይሰማራም ነበር፤ተሰባስቦ አንድ ጠንካራ ሃይል በፈጠረ ነበር።

ምንም እንኳን በአገር ውስጥ ባለው የመንግስት ተጽእኖና በጎሰኞች ጫጫታ ሕዝቡ አንድ ወጥ ትግል ለማካሄድ ተስኖት ለአደጋው የተጋለጠ ቢሆንም አንዳንድ ተስፋ ሰጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎችም ብቅ ብቅ እያሉ መጥተዋል።እነዚህን ትግሎች ማያያዝና ማጠናከር የአገር ወዳዱ ድርሻና አላፊነት ነው። በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በመሰባሰብ በአንድ ድምጽ ያንዣበበውን አደጋ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቅ ያለበት ጊዜው አሁን ነው። የእርስ በርሱ ውጊያ ከተቀጣጠለ በዃላ ለማቆም መሯሯጥ ከንቱ ልፋት ይሆናል፤የሶሪያን፣የየመንን፣የሶማሊያንና የሌሎቹንም እያዩ ከዚያ መማርና መረዳት ይቻላል።ሰዓቱ እረፍዶ ወደ ምሽቱ እያቆለቆለ መሄዱን ልብ ልንለው ይገባል።

በአንድነት ጎራ የተሰለፉትንም የተለያዩ ስብስቦች አንድ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ አጀንዳ ይዘው በአገር አድኑ ትግል ዙሪያ ተሰባስበው እንዲንቀሳቀሱ ማስገደድ ይኖርብናል።የፖለቲካ ልዩነታቸውን ከአገር ከማዳኑ ትግል በኳላ ማድረግ እንደሚችሉ ሊገነዘቡት ይገባል።ቦታና ጊዜውም ያ ነው።

በጎሳና በጎጥ ተደራጅተው የኢትዮጵያን ህልውናና ታሪክ የማይቀበሉትን፣ ሕዝቡን በክልል ከፋፍለው የሚያፋጁትን ቡድኖች ወግዱ ልንላቸው ይገባል።በየዋህነት ወይም ለማያዋጣ ትብብር በመለሳለስ ከዓላማችን ልናፈገፍግ አይገባም፤ ያን ማድረግ ኢትዮጵያን ለጥፋት አሳልፎ መስጠት ይሆናል።

ለሚፈራው የእርስ በርሱ ጦርነት ዋና ተጠያቂው በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ቢሆንም እርሱ የቀደደውን የጥፋት ጎዳና ተከትለው በየከልሉ በቋንቋ ላይ መሰረት ያደረገ ጥላቻና ጥቃት በሌላው ላይ ያደረሱትና በማድረስም ላይ ያሉት በጎሰኝነት በሽታ የተለከፉትም በተቃዋሚ ስም የሚንቀሳቀሱት ጭምር ተጠያቂዎች ናቸው። ሃይማኖትንም የልዩነትና የግጭት ምክንያት
አድርገው ለመጠቀም የሚሹም የባእዳን አገሮችና ተላላኪዎች እንዳሉ መካድ አይገባም። ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ የሃይማኖት አክራሪዎችም ሆኑ ጎሰኞች በሃይማኖትና በጎሳ መብት ጭንብል በዚህ ግርግርና የእርስ በርስ እልቂት እንጠቀማለን ብለው ካሰቡ ሞኝነት ነው።በዚህ መንገድ ሁሉም ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ የሚሆን የለም። በጎሳው መካከል የተለያዩ እምነት ተከታዮች እንዳሉ መርሳት አይገባም።ምናልባት ተጠቃሚ ቢኖር መሳሪያ ሻጩና አትዮጵያን ተሰባብራ ማየት የሚሹ ጠላቶቻችንና የነሱ ቅጥረኞች ናቸው።የደፈረሰው መጥራቱ አይቀርም! ብሩህ ቀን ለኢትዮጵያ ሲወጣ ሁሉም በታሪክ ሚዛን ላይ ተቀምጦ ይመዘንበታል።

ይህን የአሜሪካኖቹን የአደጋ ማስጠንቀቂያ ቀይ መብራት የተረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ)ለህዝባችን ደህንነት፣ለአገራችን ሰላምና አንድነት፣ለፍትህና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን የቆሙት ሁሉ ሃይላቸውን አስተባብረው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ አስቸኳይ ጥሪ ያደርጋል። የአገርና የሕዝብ አደራ ለመወጣት ዝግጁና ብቃት ያላቸው የፖለቲካና
የብዙሃን(የሙያ) ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የሕግ ባለሙያዎች አማራጭ ሆነው ለመቅረብና ክፍተቱን ለመሙላት ተቀራርበው ውለው ሳያድሩ የጋራ መመሪያ መንደፍ እንደሚኖርባቸው፣በሕዝቡም ውስጥ ሰፊ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ፤ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊና አገር አድን ትግል ድጋፍና አመራር እንዲሰጡ ሸንጎ አጥብቆያሳስባል፣ጥሪም ያደርጋል።

በተጨማሪም የገዢው ቡድን ማምለጫ መንገድ የሚሆነውን ስልት ይዞ ብቅ ማለቱ አይቀርም ብሎይገምታል።

ሊከሰቱ ከሚችሉትም ውስጥ አንዱ ቡድን ሌላውን በይምሰል መፈንቅለ መንግስት(ኩዴታ) አሶግዶ ስርዓቱ እንዲቀጥል ማድረግ።ወይም በውጭ ሃይሎች የሚረዳ ቡድን ስልጣን ላይ እንዲወጣ ማመቻቸት፤ወይም ስልጣኑን እንደሰንበቴ ለባለተረኛ ጎሳ አሳልፎ መስጠት።የመሳሰሉት ናቸው።እነዚህም ሆኑ ሌሎቹ ካለ ሕዝብ ፍላጎትና ተሳትፎ የሚመጡ የስልጣን ዝውውሮች በመሆናቸው ዘላቂ ሰላምና መፍትሄ ሊያመጡ አይችሉም።ለውጡ የጅራፍና የገራፊ ለውጥ ነው።

አሁን በስልጣን ላይ ያለው ቡድን አገሪቱ ከገጠማትና ሊገጥማትም ከሚችለው ቀውስ ለመውጣት የሚያስችላትን አስተማማኙን መንገድ መምረጡ የሚጠቅመው እንጂ የሚጎዳው አይሆንም።በያዘው ከቀጠለበት ግን እወክለዋለሁ የሚለውን ማህበረሰብ ጭምር ከአደጋ ውስጥ የሚከተው ይሆናል።የሕዝብ ደህንነትና የአገሪቱ ሰላምና አንድነት የሚያሳስበው ከሆነ በሰላም

ስልጣኑን ሁሉንም ላካተተ ለብሔራዊ አገር አቀፍ የሽግግር መንግስት ማስረከብ ይኖርበታል ብሎ ሸንጎ ያምናል።ይህ ሲባል እራሱ ለሚመርጣቸውና ሕገመንግስቱን ለሚቀበሉለት ሳይሆን የችግሩ ሁሉ መነሻ የሆነውን ሕገመንግስቱን የሚቃወሙትንም ሁሉ የሚያካትት ሊሆን ይገባዋል።የሽግግር መንግስቱም አንዱ ስራው ሕዝቡን ያሳተፈ ሕገመንግስት ማርቀቅ ነው።

የስርዓቱ ደጋፊዎችም አገሪቱ ያለችበትን አደጋ ተገንዝበው የሚደግፉት መንግስት የሚፈጽመውን፤ ወንጀልና አገር አጥፊ ተግባር ሊቃወሙት ይገባቸዋል።የለውጡ ጎርፍ ከስርዓቱጋር ጠራርጎ እንዳይወስዳቸው ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ከሚጠቃው ሕዝብ ጎን መሰለፍ ይኖርባቸዋል።የእነሱም አገር ናትና ለኢትዮጵያ በአንድነት መኖር ሊጨነቁና ሊጠበቡ ይገባል።በቅርቡ በጎንደር ዳኞች የተወሰደው በመንግስት ባለስልጣኖች ትእዛዝ ሕጉን ጥሶ የመፍረድን ተግባር መቃወም ሁሉም እንደ መጀመሪያ የእምቢባይነት ምሳሌ አድርጎ ሊወስደውይገባል።በሌላውም ቦታ ያሉ ዳኞችና ሕግ አስከባሪዎች ለሕጉ ማደርና በሃቅ ህዝቡን ማገልገል እንዳለባቸው እንደ ጎንደር ዳኞች በድፍረት ማሳየት ይኖርባቸዋል።ፍርደገምድልነት እምቢሊሉ ይገባል።በሌላውም የስራ ዘርፍ የተሰማራው ሁሉ እንዲሁ ለመብቱና ለነጻነቱ መታገል አለበት።በመካሄድ ላይ ያለው የስራ ማቆም አድማ ከግብር ቅነሳ ጥያቄ በላይ ከዴሞክራሲ ስርዓት መስፈንና ከአገሪቱ አንድነት ማስከበር ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆን ይገባዋል።

ሸንጎ በየአቅጣጫው የተጫረው ጎሳ ተኮር እንቅስቃሴ አደገኛነቱን እያስጠነቀቀ፤ ለጋራ ድሉ መብቃት ቀጣይነት ያለው፣የተያያዘና ሕብረብሔራዊ ይዘት ያለው የጋራ ትግል መሆን እንደሚኖርበት ያሳስባል።

ያንዣበበውን የእልቂት አደጋ ተባብረን እናሶግድ!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ)