የትግራይ ነጻ አውጭ ቡድን የሆነው ህወሓት፣ ከኢሬቻ በዓል ጭፍጨፋ ጋር በተገናኘ ያቆመው ሐውልት ብዙዎችን አስቆጣ፡፡ እየተገባደደ ባለው ዓመት መስከረም ወር ላይ የኢሬቻን በዓል ለማክበር ቢሾፍቱ በተገኘው ህዝብ ላይ የተኩስ እሩምታ ከፍቶ ብዙዎችን የገደለው ህወሓት፣ ዛሬ አዛኝ መስሎ ሐውልት ማቆሙ እንዳስቆጫቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ለተፈጠረው እልቂት ዋነኛ ተጠያቂ የሆነው ህወሓት፣ ራሱን ከደሙ ንጹህ አድርጎ ለመታየት እየተጫወተ ያለው የፖለቲካ ጨዋታ የትም እንደማያደርሰው ታዛቢዎች ያስገነዝባሉ፡፡

በወቅቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዓሉን ለማክበር በተገኙበት ቢሾፍቱ፣ በወታደሮቹ አማካይነት ለከባድ የጦርነት ፍልሚያ የሚውል ዘመናዊ ታንክን ጨምሮ ሌሎች ከባባድ መሳሪያዎችን ይዞ በቦታው የተገኘው ህወሓት፣ ከሰማይ ደግሞ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮችን በሄሊኮፕተር ጭኖ የበዓሉን አካባቢ ጦር ሜዳ አስመስሎት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ባዶ እጁን በወጣው የበዓሉ ተሳታፊ ህዝብ ላይ በቀጥታ በመተኮስ ብዙዎች ገደል ገብተው እንዲያልቁ ያደረጉት የህወሓት ታጣቂ ወታደሮች፣ እንደ ዓይን እማኞች ገለጻ በወቅቱ በርካታ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል፡፡

ለዚህ ሁሉ እልቂት ተጠያቂ የሆነው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ እንደ ሎሌ በሚያዛቸው የኦህዴድ አመራሮች አማካይነት ሐውልት ማቆሙ፣ ከፍተኛ ድፍረት ነው ይላሉ-ታዛቢዎች፡፡ ለደረሰው መቼም የማይረሳ ታሪካዊ እልቂት፣ የህወሓት የጦር አዛዦች፣ ከፍተኛ የፌደራል ፖሊስ አመራሮች፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አዛዦች ሊጠየቁ እንደሚገባም ታዛቢዎቹ ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ በዓሉን ሲያከብር የነበረው ህዝብ ከመሬት ተነስቶ ገደል ገብቶ እንደሞተ እያስመሰለ የሚገኘው ህወሓት፣ በወቅቱ ለተፈጠረው እልቂት ምክንያት የሆነውን ድርጊት ሲገልጽ ‹‹መረጋገጥ›› ብሎታል፡፡ የተፈጠረውን እልቂትም ‹‹ድንገተኛ›› ሲል ጠርቶታል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት ትላንት በቢሾፍቱ የተመረቀው ይኸው ሐውልት፣ በሚቀጥለው መስከረም ወር መጨረሻ ከሌሎች ዝግጅቶች ጋር በድጋሚ ታስቦ እንደሚውል ተነግሯል፡፡

(BBN News 8/28/17)