August 29, 2017 06:11

ነሃሴ 20, 2009 ዐ.ም. አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ

በዕብራይስጥ “ዐም” ማለት “ሕዝብ” ማለት ሲሆን “ሐራ” ማለት ደግሞ “ነፃ” ማለት ነው። ስለዚህ “ዐማራ” የሚለው ቃል ትርጒሙ “ነፃ ሕዝብ” ማለት ነው። የአማራ ምንጩ በቀጥታ ከአክሱም እንደሆነ ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ ያስረዳሉ። አማራወች የአክሱም ከተማን ዋና መናገሻ እንድሁም የአዶሊስ ወደብን ዋና በር አድርገው የቀይ ባህር እና የአካባቢዉን ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ እንደተቆጣጠሩት ሓሪ አትክንስ ቁልጭ አድርጎ ጽፎታል።
ከወደ ሶርያ የመጣው ፍሬምናጦስ በአትናቲወስ, አባ ሰላማ, ተብሎ ተሹሞ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ እስከገባበት ጊዜ ድረስ አማራወች የኦሪት እምነት ተከታይ ነበሩ። የአክሱም ንጉስ የሆኑት ንጉስ ኢዛና የክርስትና እምነትን ተቀብለው ኦፊሻላዊ የመንግስት ሃይማኖት እንድሆን አወጁ። በዚህም አብዘሃኛው አማራ ክርስትናን ሲቀበል የተወሰኑ ማህበረሰቦች ክርስትናን ሳይቀበሉ በኦሪት እምነታቸው ቀጠሉ። ከእነዚህ ህዝቦች መካከል አሁን ቅማንት እየተባሉ የሚጠሩት ህዝቦች ይገኙበታል።

በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆነ በአለም ዘንድ የክርስትና ሃይማኖት እየተስፋፋ ሲሄድ አብዘሃኛው የአማራ ማህበረሰብ ክርስትናን እየተቀበለ መጣ። ለዚህም ጥሩ ምስክር የሚሆኑት የአገው-አማራወች የዛጉዬ ስረወ-መንግስትን መስርተው እንደ ላሊበላ ያሉ እስከዛሬ ድረስ የክርስትና እምነት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ አብያተ- ክርስቲያናትን አነጹ። በዚህ የሃይማኖት መስፋፋት ደስተኛ ያልሆኑት እና ክርስትናን መቀበል ያልፈለጉት ቅማንት- አማራወች ከመንግስት ጋር ግጭት ዉስጥ ገቡ።

የአማራ መንግስት ግዛቱን ከአክሱም ወደ ጎጃም፣ ቤተ-አማራ (የዛሬይቱ ወሎ)፣ በጌምድር (ጎንደር) እና ሸዋ ሲያስፋፉ (ምስል 1) ቅማንት-አማራወችም በሂደት ክርስትናን እየተቀበሉ መጡ። የተወሰኑት ደግሞ የኦሪት እምነታቸዉን እንደያዙ ዛሬ ወንበርማ በሚባለው የጎንደር አካባቢ ተሰባስበው መኖር ጀመሩ። ዛሬ ላይ ምንም እንኳ የቅማንት ማህበረሰብ በጭልጋ እና ላይ አርማጭሁ በብዛት ቢገኙም ክርስትናን ቀድመው ከተቀበሉት ሌሎች የጎንደር አካባቢ ነዋሪወች ጋር ተጋብተው ተዛምደው አንድ ሆነው ለዘመናት ሲኖሩ ቆይተዋል። ቅማንት እና አማራ የዘር ሃረጋቸው አንድ ነው።

ክርስትናን መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት አብቅቶ በትረስልጣኑ ወደ ወታደራዊ የደርግ ስርአት ሲዞር ዛሬ ላይ ህወሃቶች በእነርሱ ዘመን የተጀመረ አስመስለው ታሪክን እያዛቡ የሚያቀርቡትን የብሄር ጥያቄ ደርግም ይጠቀምበት ነበር። በዚህ “ብሄሮችን እዉቅና የመስጠት ሂደት” ቅማንት እራሱን የቻለ አስተዳደር እንድመሰርት ተሞክሮ ነበር። የቅማንት ማህበረሰብ የሰጡት ምላሽ ግን አጭር እና ግልጽ ነበር፣ “አርፋችሁ ተቀመጡ!” ለዚህም ምስክር በአበቅ የለሽ ጠጅ ቤታቸው የሚታወቁት እማሆይ አበቅ የለሽ ናቸው። “የጎንደር ህዝብ አንድ ነው! ቅማንት እና አማራ እያላችሁ አትከፋፍሉን ሁላችንም የአንድ ሰው ልጆች ነን” ነበር ያሉት እማሆይ አበቅ የለሽ።

ዘረኛዉ የህወሃት አገዛዝ መሰረቱን ጸረ-አማራ አድርጎ በትረ-ስልጣኑን በያዘ ማግስት አማራን መከፋፈል እና ማዳከም ጀመረ። ለምሳሌ በከሚሴ አካባቢ የሚኖሩትን በቁጥር ዉስን የሆኑትን ኦሮሞወች የራሳቸው ዞን ፈጥሮ ኦሮሞ ሲላቸው ከ70% በላይ አማራ የሚኖርባቸዉን እንደ ናዝሬት እና ደብረዘይት ያሉ ከተሞችን ግን አማራ ሊላቸው አልፈለገም። ይባስ ብለው የአማራ ነገስታት መናገሻ የነበረችውን አዲስ አበባ ለኦሮሞ አሳልፈው ሰጡ። ይህ አማራን የማዳከም ሴራ በመቀጠል አገዉ ራሱን የቻለ አስተዳደር እንኖረው ሲደረግ የቅማንት አማራ ግን ፈቃደኛ አልሆነም። ይህ የቅማንት እና አማራ አንድነት ያስደነገጠው ህወሃት ስልቱን ቀይሮ ሶስት ሴራወችን ሸርቦ መጣ።

ቅማንትን ከብአደን እና ከጎንደር ህዝብ ጋር ማጋጨት እና እራሱን የቅማንት ተቆርቋሪ አስመስሎ መቅረብ፤ የህወሃት የትሮይ ፈረስ የሆነው ብአደን የተለያዩ በደሎችን በቅማንት ህዝብ ላይ እንድፈጽም እና የቅማንት

ማህበረሰብ እየበደለን ያለው የአማራው ብአደን ነው የሚል ስሜት እንድፈጠር ማድረግ። ለዚህም ለአብነት ያክል የቅማንት የማንነት ጥያቄ ያነሱትን የጭልጋ እና አርማጭሆ ግለሰቦች ቅማንት ወደማይኖርበት ዳባት ወስዶ ማሰር እና ያሰራቸሁ አማራ እና የአማራ ፖሊስ እንደሆነ ነገሯቸው። በዚህም ወረዳወች እና ቀበሌወች ተጋጩ፣ ብዙ ህዝብም አለቀ።

አወዛጋቢው የህዝብ ቆጠራ በቅማንት ማህበረሰብ፤ በ1997አ.ም በተካሄደው ህዝብ እና ቤት ቆጠራ ህወሃት ቅማንትን ከአማራ ነጥሎ የራሱ ቁጥር ሰጠው። ከ10 አመት በኋላ በ2007 አ.ም በተካሄደው ቆጠራ ደግሞ መልሶ ዜሮ አደረገው። ይህ ነገር ሆን ተብሎ ቅማንት ጠፍቷል የሚል ስሜት እንድፈጠር እና ቅማንቶች ከአማራ ተለይተው ጥያቄ እንድያቀርቡ የተጠነሰሰ ሴራ ነበር። እንዳቀዱትም የቅማንት ማህበረሰብ ጥያቄዉን አነሳ፣ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴም ተቋቋመ። እዚጋ ልብ ማለት ያለብን የቅማንት ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ የቅማንት ህዝብ ቁጥር ለምን ዜሮ ሆነ እንጂ የራሳችን አስተዳደር ይሰጠን የሚል አልነበረም። በወቅቱ ፕሮፌሰር ግዛው አንድ ስብሰባ ላይ እንድህ ብለው ነበር “ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንደት ዜሮ ታደርጋላችሁ? ቢያንስ እኔን እና ቤተሰቦቼን የት ጣላችሁን?”፤ ዛሬ ላይ ህወሃት የዚህን ጥያቄ አጀንዳ ቀልብሶ ቅማንት አማራ አይደለም የሚል አጀንዳ ዋና መሪ ሆኖ ጽ/ቤቱን መቀሌ ላይ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ተራ ቁጥር 1 እና 2 ከተሳካ ወደ ህዝበ-ዉሳኔ እንድሚኬድ ቀድመው ያቀዱት ህወሃቶች ቀደም ብሎ በወንበርማ አካባቢ የሚኖሩ አማራወችን በኢንቨስትመንት ስም እና በገንዘብ በመደለል አካባቢዉን ለቀው ወደ አርማጭሆ እንድሰፍሩ ተደረጉ። በተጨማሪም የትግራይ ተወላጆች ቅማንት በሚበዛበት አካባቢ እንዲሰፍሩ ተደረገ። አሁን ወደ ድምጽ መስጠት ከተገባ አላማቸው እንደሚሳካ አረጋግጠዋል።

እንደማጠቃለያ:

ሀ. በቅማንት ስም አማራን እየከፋፈለ ያለዉን ህወሃት ስንቃወም የቅማንት ወንድሞቻችንን እንዳናስቀይም ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል። አንዳንድ ሰወች ቅማንትን ገንጥለው ወደ ትግራይ ሊወስዱት ነው የሚል ስጋቻ ይገልጻሉ። ይህ ቢያንስ ሶስት ምክንያቶች ፈጽሞ ሊሆን አይችልም።

ቅማንት መቸም ቢሆን የአማራ ስለ-ልቦናዉን አይቀይርም። በአንዳንድ የህወሃት ተላላኪወች የቅማንትን ህዝብ መፈረጅ የለብንም።

ከታች በካርታው እንደሚታየው (ምስል 2) ቅማንት በብዛት የሚኖርባቸው የጭልጋ እና ላይ አርማጭሆ አካባሚወች ከትግራይ ጋር ምንም አይነት ድንበር የላቸዉም። ዙሪያዉን በመተማ፣ በታች አርማጭሆ፣ ወልቃይት ጸገዴ፣ ዳባት፣ ወገራ፣ ደምብያ እና ጣቁሳ የተከበበ ነው። (ካርታው ላይ ወልቃይት አይታይም)
ከትግራይም ብቻ ሳይሆን ከሱዳንም ጋር ምንም አይነት ወሰን የለዉም። ዙሪያዉን በጎንደር ወረዳወች እና ቀበሌወች የተከበበ ነው። ይህም አይደለም ወደትግራይ መዉሰድ የእራስ አስተዳደር የሚለዉን ጥያቄ ዉድቅ ያደርገዋል።

ለ. እንደሚታወቀው የአካባቢው ነዋሪወች በነፍጠኝነታቸው የታወቁ ጀግና ህዝቦች ናቸው። ለዚህም ፡ ወልቃይት ጸገዴ ሰሜን አርማጭሆ ቦታዉም ያስፈራል እንኳን ጥይት ጭሆ:: ተብሎላቸዋል።

የህወሃትንም መንግስት በተደጋጋሚ ድባቅ ሲመቱን አይተናል። ይህ ተደጋጋሚ መራራ ሽንፈት የሰለቸው ህወሃት አሁን እነዚህን ጀግና ህዝቦች እርስበርስ ሊያጫርሳቸው እያሴረ ነው። ይህን ተዋዶ እና ተዋልዶ ያለምንም ድንበር የኖረ ህዝብ ለሁለት መክፈል እጂግ አደገኛ ነው።

መ. የቅማንት ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ፣ “የህዝብ ቁጥራችን ለምን ዜሮ ሆነ?” ሊመለስ ይገባል? የዚህ ጥያቄ መልስ ግልጽ ነው፣ የቅማንትን ብሎም የሰፊው አማራን ህዝብ እያጠፋ ያለው ህወሃት ነው! ስለዚህ የቅማንት ህዝብ ነጻነቱን የሚያገኘው ከህወሃት ነጻ ሲወጣ ብቻ ነው።

ሰ. በመጨረሻም ቅማንት መስለው አማራን ሲያጠለሹ ከሚዉሉ የፌስቡክ ሰራዊቶች እንጠንቀቅ። አብዛሃኞቹ ስለ ቅማንት የሚጽፉት ግለሰቦች ፈጽመው ቅማንትን የማይወክሉ ትግሬወች እና የህወሃት ተላላኪወች ናቸው።

ረ. የመጨረሻ መጨረሻ ወልቃይት እና ወልቃይትን ያሉ ነጻ ይዉጡ!

 

 

ዳምጠው ነፍጠኛው (PhD)