(ሪፖርተር) በአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ሙሉዓለም ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሰሜን ጎንደር ዞን ወደ ሦስት ዞኖች ማለትም መሀል ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደርና ምዕራብ ጎንደር ይፈከላል፡፡ በእነዚህ ዞኖች የሚካተቱ ወረዳዎችን ዝርዝርም ለሪፖርተር ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ መሠረት ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው ዞን ዋና ከተማው ጎንደር ነው፡፡ የሚያካትታቸው ወረዳዎችም ጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ ምዕራብ በለሳ፣ ምሥራቅ በለሳ፣ ወገራ፣ ጠገዴ፣ ታች አርማጭሆ፣ ማሰሮ፣ አለፋ፣ ጣቁሳ፣ ምዕራብ ደንቢያና ምሥራቅ ደንቢያን ያካተተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይኼ ዞን አሥራ አንድ ወረዳዎችንና 331 ቀበሌዎችን የሚያካትት እንደሆነ አቶ አየልኝ ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ ሰሜን ክፍል ወይም ሰሜን ጎንደር ተብሎ የሚጠራው አዲሱ ዞን ደግሞ በስምንት ወረዳዎችና በ176 ቀበሌዎች የተከፈለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ዞን ዋና ከተማው ደባርቅ ሆኖ፣ ወረዳዎችም ዳባት፣ ደባርቅ፣ ደባት ከተማ አስተዳደር፣ ጃን አሞራ፣ በየዳ፣ አደረቃይ፣ ጠለምትና ደባርቅ ከተማ አስተዳዳር እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

Gonder | File Photo

ምዕራብ ጎንደር ዞን ተብሎ የሚጠራው አዲሱ ዞን ደግሞ በሰባት ወረዳዎችና በ98 ቀበሌዎች የተካተተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዚህን ዞን ዋና ከተማም ገንዳ ውኃ ሆኖ ወረዳዎችም መተማ፣ ቋራ፣ ምዕራብ አርማጭሆና በከተማ ወረዳ ደግሞ ገንዳ ውኃ፣ መተማ ዮሐንስና ምድረ ገነት እንደሆኑ ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ተቃውሞና አመፅ በከፍተኛ መጠን ተሳታፊ ከነበሩ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሰሜን ጎንደር ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የሰው ሕይወትና በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት መውደሙም ይታወሳል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሰሜን ጎንደርን ወደ ሦስት ዞኖች ለመክፈል ያስፈለጉበት ምክንያቶች ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛ ዞኑ ሰፊ የሆነ ቆዳ ሰፋት ስላለው፣ ሁለተኛ የሕዝቡ ቁጥር ከፍተኛ መሆንና ሦስተኛ የመሬት አቀማመጡ አስቸጋሪ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቅርብ ሆኖ ሕዝቡን ለመምራትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ አስቸጋሪ ሆኖ እንደነበረም አስረድተዋል፡፡

አቶ አየልኝ እንደሚሉት በራስ ዳሽንና በደባርቅ አካባቢ ያሉ ወረዳዎች በምግብ ዋስትና እጥረት የሚሰቃዩና በዕርዳታ የሚኖሩ ናቸው፡፡ በምዕራብ በኩል ያለው አካባቢ ደግሞ ሊለማ የሚችል መሬትና በርካታ ወንዞች ያሉት ነው ብለዋል፡፡ ይህ አካባቢ በቅርብ ርቀት ከኤርትራ ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ከዚያ የሚመጣ የሻዕቢያ ተላላኪ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር እያደረገ መሆኑንና ከሱዳን ድንበር ጋር ተያይዞም የሕገወጥ መሣሪያ አዘዋዋሪዎች ሰለባ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ጣና ዙሪያንና ጎንደርን ማዕከል ያደረገው አካባቢ ደግሞ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ የከርሰ ምድር ውኃ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ አየልኝ፣ ‹‹የሰሜን ጎንደር ዞን ወደ ሦስት ዞኖች መከፈልን ከግርግሩ ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ ከአራት ዓመት በፊት የተወሰነ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ ሰሜን ጎንደር ዞን እንዲከፈል ጥያቄዎች ከሕዝቡ ሲቀርቡ የነበረው ካለፈው ዓመት በፊት እንደነበር የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፣ አሁኑ የመንግሥት አቅም እየተሻሻለ በመምጣቱና የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ ዞኑን ለመክፈል እንደተወሰነ አስረድተዋል፡፡ በዞኑ ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች ውይይትና ክርክር በማድረግ ሕዝቡ ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም 98.5 በመቶ የሚሆነው የዞኑ ሕዝብ የዞኑን መከፈል የሚደግፍ እንደሆነ መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት በዞኑ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ አንስተውት የነበረውን ጥያቄም ለመፍታት አስተዳደሩ ሌት ከቀን እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በ2009 ዓ.ም. ለ150 ሺሕ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ110 ሺሕ ወጣቶች ዕድሉን መፍጠር እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡