August 31, 2017 01:39

ወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማኅበር
Wollo Ethiopian Heritage Society
‘ወሎየነት መለያችን፣ኢትዮጵያዊነት ማንነታችን!’

ሕዝባዊ መግለጫ
የወያኔ መንግስት የሰሜን ጎንደር ዞንን ለመከፋፈልና የምዕራብ ጎንደርን መሬት ለመቀራመት ያወጣዉ እኩይ እቅድ አገር አጥፊ ነው!
በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንድምንሰማዉ የወያኔ አስተዳደር የሰሜን ጎንደር ዞንን ለሶስት ለመክፈል እንደወሰነና ለዚህም ምክንያቱ ላለፉት 26 አመታት ለልማት ምቹ ስላልሆነ ነው የሚል ነዉ። የአማራን መሬቶች የትግራይ ለማድረግ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራና ቅማንት ማኅበረሰብ ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ነውም ተብሏል። ይባስ ተብሎ የ“ታላቋ ትግራይን” ሕልም ለመተግበር ሕወሃቶች ጎንደርና ጎጃም ከሱዳን እንዳይዋሰኑ ለማድረግ ትግራይን እስከ ጋምቤላ ለማስፋፋት ያዘጋጁት ሚሥጥራዊ ካርታ በቅርቡ ይፋ ወጥቶ ለማየት በቅተናል።

ቅማንትና አማራ በሚለዉ ክፍፍል ያልሰራለት ወያኔ አሁን ደግሞ ለ3 ዞን ከፍሎ የሰሜኑን ጫፍ ወደ ትግራይና ሱዳን፣ መካከሉን ቅማንት ለሚባል ከዋናዉ ወገኑ የተለየ በግጭት ሁልጊዜ የሚኖር አካባቢ ለመፍጠር፣ ሶስተኛዉ የአማራ ዞን በማለት 3 እርስ በእርሳቸዉ እንደ እስራኤልና ፍልስጥኤም ዘወትር በስጋት የሚኖሩ ማህበረሰቦችን በመፍጠር ጎንደሬን እርስ በእርሱ በማስተላለቅ ወያኔ የቀበሮ ዳኛ የሚሆንበትን ስርአትና ሁኔታ ምቹ ለማድረግ የታሰበ ስንኩል እቅድ መሆኑ ግልጽ ነው። የመሬት ቅርምቱም ስልጣን ካጣን ትግራይን ነጻ እንገነጥላለን ከሚል ቅዠት የመነጨ ነው።
ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት እንደሚባለዉ፣እስካሁን በአካባቢዉ ምንም አይነት ልማት ያልተካሄደዉ አካባቢዉ ስላልተከፋፈለ ሳይሆን ወያኔ በአማራ ህዝብ ላይ ባለዉ የተንሸዋረረ አስተሳሰብ ምንም አይነት ልማት ወደ አካባቢዉ እንዳይሄድ ስላደረገ ነዉ። በወልቃይታና በጠገዴም የታየው የዘር ማጽዳት፣መሬት መቀራመትና፣ የአማራን ማንነት አትፍቶ በትግሬ ማንነት ለመተካት የተፈጸመው ድርጊት የዚህ ታላቅ ሴራ ሌላው ምልክት ወይንም መንስዔ መሆኑን ማንም አያጣውም።
የሕዝብ መከፋፈልና መሬት መቀራመት የሚያለማ ቢሆንማ ገና በጥዋቱ ወሎን ለ6 ከፍሎት አልነበር እንዴ? ወሎን ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ከሚሴ፣ አፋር፣ ዋግ ህምራ እና ወደ ትግራይ ቆርሶ የወሰደዉ ራያን በመሸንሸን አንዱ ላንዱ ችግር እንዳይደርስ አድርጎ አዳክሞ ምንም አይነት መሰረተ ልማት እንዳይደርስ በማድረግ አዳክሞ ወደ መጥፋት ደረጃ አድርሶታል።
ሁላችንም በየግቢያችን ችግሩን ተረድተን አብሮ ለመስራት ተስፋ እየታየ በመሆኑ ጎንደሬዎች በህብረት ቁማችሁ የምትታገሉበት እንጂ የምትለያዩበት ወቅት አይደለም። ከድል በኋላ ራሳችሁ ቁጭ ብላችሁ እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች ወንድሞቻችሁ በተገኙበት ችግራችሁን እስከምትፈቱበት ጊዜ ድረስ በትእግስትና  ነገሮችን በጥሞና ማየቱ እጅግ አስፈላጊ ነዉ። የገዢው ፓርቲ ደባም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በቀጥታ የሚመለከት ነው።
በኛ አስተያየት የጎንደርና የወሎ ሕዝብ በደም፣ በባህልና በታሪክ መንታ ነው። ከዚያም በላይ ኢትዮጵያዊነታችን ያስተሳስረናል። ስለዚህ “ወሎ የኢትዮጵያ ዉርስና ቅርስ ማህበር” ከጎናችሁ በመሆን ትግሉ የሚጠይቀዉን መስዋእትነት አብሯችሁ ለመክፈል ዝግጁ ነዉ።

ያገር አድን ክተት ጥሪ ለሁላችንም ነው!!
ድል ለተባበረው የኢትዮጵያ ህዝብ!!