ኢትዮጵያ ፈርሳ ኦሮሚያ ልትኖር ትችላለችን ?!

( ዘርዓያዕቆብ ጌታቸው ጉዲና )

በተደጋጋሚ እንደ ሰማነው አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ኦሮሚያ ክልል የራስን እድል በራስ የመወስን መብቱን ተጠቅሞ መገንጠል አለበት ይላሉ ግን ዋናው ነገር የውሳኔው ባለቤት ጥቂት አክቲቪስቶች ሳይሆኑ መላው የኦሮሞ ህዝብ መሆኑ ነው። በእርግጥ ህዝቡ የሚበጀኝና የሚመቸኝ መንገድ መገንጠል ነው ብሎ ከወሰነ በኤርትራ ጉዳይ እንዳየነው የትኛውም ኃይል ሊያቆመው አይችልም

ግን ለኦሮሞ ህዝብ የሚበጀውና የሚሻለው ትክክለኛ መንገድ መገንጠል ነው ወይስ በኢትዮጵያ ጥላ ስር መቀጠል ?,… ኦሮሚያ ተገንጥላ ሃገር ለመመስረት ብትሻ በቀላሉ ይቻላልን ?!,… አሁን ላይ ላለው የኦሮሞ ህዝብ ችግር ኦሮሚያ የሚባል ሃገር በመመስረት ይቀረፋል ?,… ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ አንድነቱን ማስጠበቅስ ይችላልን ?

በዚህ ዙሪያ ብዙ ቢባልም ለተሻለ አመለካከትና ለጋራ ጥቅም መወያየት አይከፋምና በግልፅነት ብንወያይ ጥሩ ይመስለኛል!

በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ሳትኖር ኦሮሚያ የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም እላለሁ! ኦሮሚያ ብትገነጠል ሊያጋጥማት የሚችለው ውዝግብና ችግር መቼም የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ነው የሚከታት! ይህን እውነታን የመገንጠልን ካርድ እየመዘዙ እንደ ማስፈራሪያ የሚጠቀሙ አብዛኛው የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም ጠንቅቀው ያውቁታል!
ከነዚህ ችግሮች ውስጥ

#1ኛ በየአቅጣጫው ዙሪያውን በድንበሮች ላይ የሚነሱ የይገባኛል ጥያቄዎች!

ለምሳሌ በቅርቡ የተከሰተው የሶማሌ ልዩ ፖሊስ በምሥራቅ ኦሮሚያ ከ5 ዞኖች በ17 ወረዳዎች ላይ ያካሄደው መጠነ ሰፊ ወረራ ከ1200 በላይ የኦሮሞ ተወላጆችን ሂወት ቀጥፏል። ይህ የሚያመላክተን ሁለት ነገሮች አሉ (1) ኦሮሚያ ሃገር ከሆነች ከኢትዮጵያ—ሱማሌም ሆነ ከግራንድ ሱማሊያ ጋር በመሬት ይገባኛል ውዝግብ መቼም የማይቆምና የማያባራ ጦርነትና መጨፋጨፍ ውስጥ መግባቷ አይቀሬ መሆኑ። (2) ከአፋር ፣ ከአማራ ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ፣ ከጋንቤላ ፣ ከደቡብ ክልል ዙሪያውን የሚነሱ ተመሳሳይ ጥያቄዎችና ግጭቶች የሚያስከትሉት ጉዳትን ማሰብ እራሱ በጣም ይዘገንናል!

#2ኛ ለብዙ ዘመናት የተለያዩ ብሄሮች መኖሪያ በሆኑ እንደ አዲስ አበባ ፣ ድሬዳዋ ፣ ሃረር ፣ ሻሸመኔ አይነት ከተሞች የሚነሱ ውዝግቦችና ከነዋሪዎቹ ጋር የሚከሰተው ግጭት የማያባራና እጅግ ከባድ ነው።

#3ኛ የደቡብ ሱዳን አይነት እጣ ፋንታ

በ1983 እ.አ.አ የተዋቀረውና በሟቹ የነፃነት ታጋይ ጆን ጋራንግ ይመራ የነበረው ‘SPLA‘ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር ከ30 አመት በላይ ከሱዳን መንግስት ጋር ተዋግቷል በስተመጨረሻ በ2005 በተደረገው ስምምነት መሰረት የደቡብ ሱዳን ህዝብ የስልጣን ተካፋይ እንዲሆንና ሰላም እንዲወርድ ሁለቱ ካሎች (የሃገሪቷ መንግስትና SPLA) ተስማምተው ነበር ሆኖም ግን ታላቁ የነፃነት ታጋይ ጆን ጋራግ ለዘመናት የታገሉለትን የነፃነት የሰላም የእኩልነት አላማቸው ከግብ ካደረሱ በኋላ የሰላሙን ፍሬ ብዙም ሳያጣጥም በድንገት ሞተ የጋራንግን ሞት ተከትሎ ስልጣኑን የያዘው ሳልቫ ኬር ከሰሜን ሱዳኖች ጋር መስማማት ተስኖት በምእራባዊያን ግፊት የራስን እድል በራስ ወስኖ ደቡብ ሱዳንን ከሱዳን ገነጠለ። ጁባ ከካርቱም መገንጠሏ ችግሮቿን ሁሉ የሚቀረፍ መስሏት ነበር ግን አልሆነም!
በተለያዩ የከርሰ ምድር ሃብት ፣ በነዳጅ በውሃና በእርሻ መሬት የታደለችው ደቡብ ሱዳን እነሆ በጋራ ተባብረው በገነጠሏት ሃገር ዛሬ ልጆቿ ዲንካና ኑየር ተከፋፍለው እርስበርስ በገጀራ እየተፋጁ ህዝቡ ለአንድ ቀን እንኳ ሰላም ተስኖት ከ400ሺ በላይ ዜጎቿ ወደ ጎረቤት ኢትዮጵያ ለመሰሰደድ ተገደዋል

ነገ ኦሮሚያ ተገንጥላ ነፃ ብትወጣ ሸዋ ፣ ወለጋ ፣ አርሲ ፣ ኢሊባቦር ፣ ጅማ ፣ ከፋ ፣ ሃረርጌ ፣ ባሌ ፣ ቦረና አዋሽ/ባቢሌ/ድሬዳዋ ወዘተ በአመለካከትና በአቅዋም ባይስማሙ አንዱ ከሌሎቹ ተነጥሎ የራሱን እድል በራስ የመወሰን መብቱን ተጠቅሞ እስከመገንጠል የመዝለቅ መብት ይኖረዋልን ?! ማጆሪቲ ሙስሊም የሆነባቸው የደቡባዊውና ምስራቁ ክፍል እስላማዊ ፓርቲ ለማዋቀር ቢሹ ክርስቲያን ማጆሪቲ የሆነባቸው እንደ ሸዋና ወለጋ እጣ ፋንታ ምን ይሆናል ?! ያን ያለመቀበልም ሆነ የመቃወም አቅሙስ ይኖራቸዋል ?! በዞን በዘር በአመለካከትም ሆነ በኃይማኖት የመከፋፈል እጣ ፋንታ ሊከሰት ይችላል ይህ ማለት ኦሮሚያ ብዙ ቦታ የመከፋፈልና እንደ ደቡብ ሱዳን እርስበርስ የመጋጨት እጣ ፋንታ በጣም ያሰጋታል።

የኦሮሞ አክቲቪስቶች ማወቅ ያለባቸው ሁለት ነገሮች
#አንደኛ የከርሰ ምድር ሃብት ብቻ ስላለ ሰላምና እድገትን ማግኘት የሚቻል ቢሆን ደቡብ ሱዳን የት በደረሰች ነበር!
#ሁለተኛ አንድ ቋንቋ በመናገር ብቻ አንድነትን ማስጠበቅ የሚቻል ቢሆን ሱማሊያ አንድ ቋንቋ አንድ እምነት እና አንድ በሃል እያላት እንዲህ ባልተበታተነች ነበር።