September 4, 2017
ከሙሉነህ ዮሐንስ
(ነሃሴ 29 2009) በራሰ ተነሳሽነት የአርማጭሆ፣ የደንቢያ እና የጭልጋ ህዝብ ተጠራርቶ የወያኔን ጎንደርን የማፈራረሰ የቀቢፀ ተስፋ እኩይ ሴራ ለማክሸፍ በአንድነት እንደሚመክቱና ጎንደርን እንደሚታደጓት ስምምነት ተደርሷል። ስብሰባው የህዝብ ተወካይ ሽማግሌወች፣ የጎበዝ አለቆችና ብዛት ያለው ወጣት ህዝብ የተሳተፈበት ነው። የስብሰባው ሂደትና እጅግ ስሜት ቀስቃሽ ከሆኑ ግጥሞች ጋር እጃችን ገብቷል። ነገር ግን የህዝቡን ዝርዝር ሚስጥራዊ ስምምነት ለጠላት አሳልፎ ላለመስጠት፣ የተሰብሳቢውን ህዝብ ማንነት ላለማጋለጥ ስንል የስብሰባውን ልዩ ቦታና የድምፅ ፋይሉን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበናል።
የስብሰባው ዋና የስምምነት ነጥቦች ግን በመግለጫ መልኩ ስለመጡ አጋርተናል፦
1) ጎንደር አትከፋፈልም። ህዝባችንን ባልጠየቅነው አዲስ ዞኖች መከፋፈል አጥብቀን እናወግዛለን አንቀበለውም። ይህ ከሃገር ተለይቶ ለምን ጎንደር ላይ ለምን በዚህ ሰአት ቢባል ዋናውን የነፃነት ጥያቄያችንን ለማዳፈን እኛን ከፋፍሎ ለማዳከም የታለመ የትግሬ ወያኔ ሴራ ነው።
2) የጎንደር ህዝብ በቅማንትና በአማራ ተብሎ አይከፋፈልም አንቀበለውም። ያልጠየቅነውን የህዝበ ውሳኔ የጫነው ከፋፋዩ የወያኔ ቡድንና ሆድ አደር ተላላኪወቹ ናቸው።
3) ሰፊውን ከሱዳን ድንበር ጋር የሚያዋስነውን በጎንደርና በጎጃም ያለውን ደንበራችንን ለረዥም አመታት በተግባር እየቆራረሰ ሲሰጥ የቆየው ወያኔ የመጨረሻ ደረጃ እቅዳቸው የሆነውን ጎንደርን ሙሉ ለሙሉ ከሱዳን ድንበር ነጥሎ በቤንሻንጉል ስም ሰይሞ ወደ ትግራይ ለመጠቅለል ያሴሩትን ሴራ ያጋለጠ ካርታ ሰሞኑን በይፋ በቴሌቪዥን አይተን እጅግ ተቆጥተናል። እልፍ አእላፍት ወገኖቻችን ባሻ ጥጋቡን ጨምሮ ህይወታቸውን የሰጡትን ድንበራችንን! የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አሳልፈን አንሰጥም።
4) የተፈጥሮ ድንበራችንን ተከዜን ተሻግሮ ጊዜ ሰጠኝ ብሎ ወያኔ በማናለብኝነት የወሰዳቸውን የሁመራ፣ የወልቃይት፣ የጠገዴና የጠለምት መሬቶች ወደ ታሪካዊ የጎንደር ግዛት እንዲመለሱ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። ወልቃይት መሬቱ የጎንደር ህዝቡም አማራ ነው!
5) የኢትዮጵያ ህዝብ ለፀረ ወያኔ ትግሉ በሚያደርገው እርብርቦሽ በጋራና በህብረት መሰራቱ ከመቸውም ጊዜ አሁን ወሳኝ ምእራፍ ላይ ነንና በጋራ እንታገል የሃገራችንን መፃኢ እድል አብረን እንወስን እያልን ጥሪያችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን።
ስብሰባውን የነሃሴ ገብርኤል ጨርሰናል። ይህ መግለጫ በጣምራ ኮሚቴ አመራሩ የነሃሴ መድሃኒአለም እለት ለህዝብ ተልኳል።
የግርጌ ማስታወሻ…የአቋም መግለጫውን ከቦታው ያደረሱን የህዝብ ተወካዮች ተከታታይ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል እኛም ወደ ህዝቡ መልእክቱን እናደርሳለን።