04 Sep, 2017

By ታምሩ ጽጌ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 57 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ

የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ቁጥር 115 ደርሷል

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አምስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዓርብ ነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ኃላፊዎች ድርጅቱን ለረዥም ጊዜያት ሲመሩና ሲያገለግሉ የነበሩት የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ ስብሃት፣ የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ፣ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት ተፈራ፣ የፕላንና ቢዝነስ ልማት መምርያ ኃላፊ አቶ ሲራጅ አብዱላሒና የፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መላኩ ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሕዝብና መንግሥት የጣለባቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተውና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል ለጊዜው ያልተገለጸ ጉዳት በሕዝብና በመንግሥት ላይ ማድረሳቸውን፣ የፌዴራል ዋና ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡ ከዋና ኦዲተር የኦዲት የምርመራ ሪፖርትና ከሕዝብ በተገኘ መረጃ መሠረት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ቢሮ ክትትል በማድረግና ማስረጃዎችን በመሰብሰብ ከፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ አውጥቶ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋሉም ታውቋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለማስፈቀድ በ48 ሰዓት ውስጥ ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንደሚያቀርባቸውም ተጠቁሟል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ባገኘው የኦዲት ሪፖርት፣ ባደረገው ክትትልና ባገኘው መረጃ መሠረት፣ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረዋል ያቸውን 57 የሥራ ኃላፊዎችና በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩ ሠራተኞችን በቁጥጥር ሥር አውሎ በምርመራ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በአስተዳደሩ ሥር በሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተለያየ ኃላፊነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ ከነሐሴ 23 ቀን እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተጠርጣሪዎችን ስምና የሚሠሩበትን ተቋም መግለጽ ያልፈለገ ቢሆንም፣ ሪፖርተር ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ለማረጋገጥ  እንደቻለው ተጠርጣሪዎቹ ከመሬት አስተዳደር፣ ከፅዳት ውበትና መናፈሻ፣ ከቤቶች ልማትና ከተለያዩ ተቋማት ናቸው፡፡

ከጉለሌና ከቦሌ ክፍላተ ከተሞች መሬት አስተዳደር ቁጥራቸው በዛ ያሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ለማወቅ  ተችሏል፡፡ የመንግሥት ቤት ወደ ግል በማዘዋወር የተጠረጠሩ፣ ከተገልጋዮችና ከባለሀብቶች ላይ ጉቦ የተቀበሉ ተጠርጣሪዎች እንደተካተቱም የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ከፅዳት፣ ውበትና መናፈሻ ግን በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የተጠርጣሪዎችን ስምና የሥራ ድርሻ በተመለከተ ከኮሚሽኑ መረጃ ለማግኘት ጥረት የተደገ ቢሆንም አልተሳካም፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ግን አስታውቋል፡፡