September 4, 2017

ሙሉቀን ተስፋው

የቅማንት ጉዳይ በጣም ቀላል ቢመስልም ሕወሓቶች በሚገባ ለማወሳሰብ ጥረዋል። በነገራችን ላይ የትግራይ ተስፋፊዎች ሊያውቁት የሚገባ ነገር አለ። እሱም የፈለገውን ያክል ቢደክሙ ይህን ትውልድ ማታለል እንደማይችሉ ደጋግመን መንገር ይጠበቅብናል። ቀበሮ የበሬውን … ይወድቃል ብላ ስትከተል ዋለች እንደሚባለው፤ የዐማራ ሕዝብ በየትኛውም መልኩ ፈተና ቢበዛበት ጠላቶቹን መቅጣት ይችልበታል። እንደ ቀበሮዋ ሲከተሉ ከመዋል ውጭ የቅማንት ወንድሞቻችን ለብዙ ሺህ ዓመታት አብረውን እንደኖሩ ወደ ፊትም አብረን እንኖራለን። ቅማንትን እንወክላለን በሚል በጎንደር ዩንቨርሲቲ መሽገው የወያኔን ሴራ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎችን ሳንጨምር ማለቴ ነው።

ከአራት ዓመታት በፊት አባ ወንበሩ መርሻን ቅማንት ማለት ምን ማለት ነው? ስላቸው ‹‹እናት አባት፣ አያት፣ ቅድመ አያት፣ ቅም-አያት፣ ቅማንት… እያለ ይሔዳል፤ ስለዚህ እኛ ከዚህ ቀድሞም የነበርን ሕዝብ ነን›› ነበር ያሉኝ። እሳቸው ይህን መልስ የሰጡኝ የቅማንት አምልኮ ከአይሁዳውያን ጋር መመሳሰሉን ጭምር አንስቼላቸው ስለነበር ጭምር ነው።

ባለፈው ለመግለጽ እንደሞከርኩት የተለየ የቅማንት የሚባል ባህል በአካባቢው ማግኘት የሚከብድ ቢሆንም ‹‹ቅማንት ነኝ›› ብሎ የሚያምን ሕዝብ ግን አለ። ቁጥሩ የትኛውንም ያክል ይሁን በማን አጋፋሪነትም ጥያቄው ይቀንቀን ቅማንት ነኝ የሚል ሕዝብ ካለ አይደለህም ማለት አይቻልም። ሊጠፋ ያለውን ቋንቋ ማዳን (ከባድ ቢሆንም) ጉዳት የለውም።

ሆኖም የአንድን ሕዝብ መብት ለማክበር የሌላውን መርገጥ ደግሞ ወንጀል ነው። እኔ እስከማውቀው ቅማንት ብቻውን የሚኖርበት ቀበሌ አላውቅም። ነገር ግን ባለፈው ዓመት በ2007 ዓ.ም ከጭልጋና ከላይ አርማጭሆ የተውጣጡ 42 ቀበሌዎች ለቅማንት ወረዳ ተሰጡ። በዚህም ሳያበቃ በ‹ክልሉ› ምክር ቤት ሳይመከርበት ተጨማሪ 21 ቀበሌዎች በሕወሓት ትእዛዝ ወደ ቅማንት ወረዳ እንዲጨመሩ ተደረገ። አሁን እንደገና 12 ቀበሌዎች ለማካተት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ የወያኔ ምርጫ ቦርድ አዟል።

በዚህ መካከል ቀደም ሲል ለቅማንት ከተከለሉ ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ ሰዎች አስቀድመው ሪፈረንደም ይደረግባቸዋል ወደሚባሉት ቀበሌዎች እየሄዱ የቀበሌ መታወቂያ በማውጣት እንደመራጭ ሆነው መመዝገብ ጀምረዋል።

ሌላው የሕዝበ ውሳኔው ችግር ደግሞ ለሕዝበ ውሳኔ የቀረቡት ቀበሌዎች ከአዲሱ የቅማንት ወረዳ ጋር በ50ና በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ መኖራቸው ነው። በሰሜን ጎንደር የደጋማው አካባቢ ሕዝብ ክረምት ላይ ሞፈር ዘመት በሚል ወደ ቆላማው አካባቢ ይሔዳል። በዚህም በዚያው ለምዶ የሚቀር ወይም የሚመለስ ይኖራል። ከጭልጋ በሞፈር ዘመትነት ሂደው የቀሩ ጥቂት ቅማንቶች ያሉባት ከሱዳን ድንበር ያለች በቋራ አንዲት ቀበሌ ለምርጫ ቀርባለች። ከሌላው ጋር ለመገናኘት በትንሹ ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ያስፈልጋል።

አሁንም አንባቢ እንዲያውቀው የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢኖር ከሁለት ቀበሌዎች ውጭ ሕዝበ ውሳኔው በሚካሔድባቸው 10ሩ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ነዋሪው ዐማራ ነው፤ እንደ ብላጂግ ያሉት ሁለቱ ቀበሌዎች እንዲያውም የጎንደር ከተማ አካል ናቸው። የተወሰኑት ደግሞ ቀደም ሲል የቤተ እስራኤላውያን መኖሪያ የነበሩ ናቸው።

በመሠረቱ ሕዝበ ውሳኔ መደረግ የነበረበት በሁሉም በተጠየቁ ቀበሌዎች ነበር፤ ማለትም አንድም ቀበሌ እንደዚህ ነህ የሚል ውሳኔ ከመስጠት በፊት በግልጽ በሁሉም አካባቢዎች ነበር ሕዝበ ውሳኔው መካሔድ የነበረበት። ይህ ቢሆን የሕዝቡን ትክክለኛ ስሜት ከማወቃችንም በላይ በፍላጎት ላይ የተመሠረተ አስተዳደር መመሥረት ይቻል ነበር፤ ሆኖም በእኛም እንዝላልነት አገዛዙም ቀድሞን የፈለገውን አደረገ።

በመጨረሻም ሳይጠቀስ የማይታለፍ ጉዳይ አለ። እሱም አብረን ለዘመናት ኖረን ሳለ ድንበር ለማበጀት ምርጫ ምረጡ እንዴት ይሉናል በሚል በርካታ ሰዎች የምርጫ ካርድ እንደማያወጡ እየተናገሩ ነው። ያላወጡም በርካቶች ናቸው።

ችግሩን ይህን ያክል ከዘረዘርን የመፍትሔ ሐሳብ የሚባሉትን ማካፈል አስፈላጊ ይመስለኛል። አሁን ለጊዜው መነጋገር የምንችለው ከፊታችን በአጪር ቀን ውስጥ ስለሚደረገው ሪፈረንደም ብቻ ነው።

በአንድ በኩል ከሌላ ቦታ መጥተው የምርጫ ካርድ ለማውጣት የሚሹ ሰዎች ሲበዙ የአካባቢው ሕዝብ ደግሞ ላለመለያየት ካርድ አናወጣም በሚል ቸልታ ውስጥ የገቡበት ሁናቴ ሁለቱም የሚጠቅም አይደለም። ካርድ ሁሉም ሰው ሊያወጣ ይገባል፤ በፍላጎቱ መካለል ይገበዋል፤ ከሌላ ቦታ መጥተው ካርድ የሚወስዱትን ሰዎች ደግሞ ልናስቆማቸው ይገባል እላለሁ።