September 5, 2017 16:01

 


1ኛ/ ልደት፣ መንፈሳዊ ትምህርትና አገልግሎት በአጭሩ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቅድመ ሊቀ ጵጵስና  መምህር አባ ዘሊባኖስ ፋንታ/ቆሞስ/ በመባል ይታወቃሉ። የተወለዱት በጎንደር ክፍለ ሀገር ሲሆን የትውልድ ሐረጋቸው እስከ ጎጃምንም ድረስ ይሳባል። አባ ዘሊባኖስ ፋንታ በተወለዱበት አካባቢ አዘውትሮ እንደተለመደው ወደ ያሬዳዊ መንፈሳዊ ትምህርት የጀመሩት ገና በልጅነታቸው ሲሆን፤ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ደረጃ በደርጃ ብቃት ባለው ሁኔታ ተከታትለዋል። ጸዋትዎ ዜማ፣ ቅኔ ከነሙሉ አጋገባቡ፣በሕረ ሐሳብ፣ መጽሐፍተ ሐዲሳትና ሊቃውንት፣ አቋቋም፣ዝማሬ መዋስዕት በመምህርነት፣ ቅዳሴ በመምህርነት፣ ድጓ መምህርነት ደርጃ  ቢሚገባ አጠናቀው ተምረዋል።

ይህን ታሪክ ያስታዎሱት በአውሮፓ ኗሪ የሆኑ የታላቁ ሊቅ የአለቃ ቀለመወርቅ ዘደብረታቦር ደቀ መዝሙር እና እውቅ የተክሌ አቋቋም የአብነት መምህር ናቸው። አረጋዊ ሊቅ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ቅዱስ አባታችን አቡነ መርቆሬዎስን ከአንዳቤት ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ድረስ በቅርብ የማውቃቸው አባቴ ናቸው። በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ይህ ቀረህ ያማይባል የተሟላ ዕውቀት ያላቸው ሊቅ ናቸው። ዜማ ካፋቸው አይለይም፤ በጣታቸው ጽፈው ያስመሰከሩትን ድጓ በዓይኔ አይቸዋለሁ። ሊቃውንት ያመሰገኑት የተዋጣለት ድጓ ነው። ቁም ጽፈታቸው እጅግ የተዋበ ነው። በአንድ ወቅት አንዳቤት እያለን አንድ ተማሪ ዚቅ እንዲጽፍለት ጠየቋቸው፤ አሥራ አምስት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መጽሐፉን ጽፈው አመልክተው አጠናቀው ሰጡት። እጅግ ትዕርምተኛና የጸሎት ሰው ቁጡብና የተረጋጉ ናቸው። የማዳመጥና የመረዳት ችሎታቸው ከፍተኛ ሲሆን የሚናገሩት ግን የተመጠነ ነው። ከሊቃውንት ጋር ያደጉ በመሆናቸው  በንግግራቸው መካከል በአብዛኛው ገላጭ ኃለ ቃላትና ምሳሊያዊ አነጋገርን የመጠቀም ባሀልና ባህሪ አላቸው። በማለት ይገልጿቸዋል።

መምህር አባ ዘሊባኖስ ፋናታ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት በተወለዱበት አካባቢ በዐት አጽንተው ወንበር ዘርግተው ጉባዔ አስፍተው ብዙ ደቀመዛሙርትን አስተምረዋል። ከዚያም ወደ ጎጃም ባህርዳር በጣና ሀይቅ ገዳማት ቆይተዋል። ቀጥሎም ቀድሞ ከልጅነት እድሜያቸው ጀምሮ በነበራቸው መንፈሳዊ ፍላጎት መሠረት እንደ ቀደሙት አባቶቻቸው የተወለዱባትን ደብር መምህር ሆነው ለመምራትና ለማስተማር ፈላጎት አድሮባቸው ይህንኑ ለማጸደቅ ወደ አዲስ አበባ መጥተው መነበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  በእንግድነት ተቀምጠው የመምህርነት ደርጃቸውን አስጠብቀው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለመመለስ ቤተ ክህነት ደጅናት ጀመሩ።
ሆኖም በእንግድነት በቆዩበት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአገልግሎት ቀድመው የሚገኙና ስብሐተ ነግሁን፣ ዘይነገሱ፣ አቋቋሙን የፆመ ድጓውንና የድጓውን ቅኝት ሁሉ ያለመጽሐፍ የሚያንበለብሉ ሊቅ ከመሆናቸውም በላይ መንፈሳዊ ትህትናቸው በማኅበረ ካህናቱ ዘንድ የተወደደና የተመሰገነ መሆኑ ታምኖባቸው፤ እኒህ አባት በካቴድራሉ ቢቀጠሩ የሚሰጡት አገልግሎት እጅግ ጠቃሚና መንትያ መሆኑ በማኅበረ ካህናቱ፣ በወቅቱ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተማርያም ወርቅነት የአሁነ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሊቀ ጳጳስ እና በቤተ ክህነቱ አስተዳደር በኩል ዝናቸው በስፋት ተሰማ። ከዚያም  በመምህርነት እንዲቀጠሩ የተወሰነ ቢሆንም፤ መምህር አባ ዘሊባኖስ ወደ ትውልድ ሀገራቸው የመመለስ እንጅ አዲስ አበባ የመቅረት ፍላጎታቸው ባለመሆኑ ውሳኔውን ሳይቀበሉ ቆይተው ከብዙ ልመናና ምልጃ በኋላ የካቴድራሉ የአብነት መምህር ሆነው ተቀጥረው አዲስ አበባ ለመቅረት ችለዋል።
መምህር አባ ዘሊባኖስ ፋንታ የዘመናዊ ትምህርት በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ገብተው በጥሩ ደርጃ እየተከታተሉ ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ የነበሩ ቢሆንም ለምነው ለተማሩት ብዙ ለደከሙበት ለዜማውና ለመንፈሳዊ ትምህርቱ አገልግሎት ከፍተኛ ትኩረትና አድልዖ በመስጠት የዘመናዊዩ ትምህርት ያሳሰባቸው ባለመሆኑ ብዙም እርቀው ለመሄድ ፍላጎታቸው አልነበረም።

2ኛ/ የስተዳዳሪነትና የማዕረገ ሊቀ ጵጵስና ሹመት፤

መምህር አባ ዘሊባኖስ ፋንታ በመንበረ ጸባዎት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በአብነት መምህርነትና ሁለገብ በሆነ መልኩ ሲያገለግሉ ቆይተው፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፈቃድ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። በዚህ ውቅት ቤተ ክርስቲያኑን ለማሠራት እጅግ ከፍትኛ ድካም ያደረጉ ከማኅበሩና ከሊቃውንቱ ጋር ተግባብተው ሲያገለጉሉ ቆይተው፤ ብቃት ባለው የአብነት መምህር ዕውቀታቸው፣ በትዕርምታቸው፣ ገዳማዊና መንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ በቅዱስ ሲኖዶድስ ሙሉ ድምጽ በቀዳሚነት ለኤጴስ ቆጶስነት ተመርጠው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አንብሮተ ዕድ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ሊቀ ጳጳስ ሆነው መጀመሪያ ወደ ድሬደዋ ሀገረ ስብከት የተሾሙ ቢሆንም፤ ጎንደር አቡነ እንድርያስ  ከሻለቃ መላኩ ተፈራ ጋር ተጣልተው ከቦታው ተነስተው ስለነበረ፤ አቡነ እንድርያስ የታወቁ የብሉያትና የሐዲሳት መምህር እንደመሆናቸው መጠን እሳቸውን የሚተካ፣ የጎንደርን አራት ዓይና ሊቃውንት የሚመጥንና ቃለ እግዚብሔር የሚመክቱ ትህትና ያላቸው ተግባብተው ሊያገለግሉና ሊያስገለግሉ ይችላሉ በሚል ግምገማና ጥናት የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ።
ከዚያም በተለይም የመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ድካሙን ውጣ ውረዱንና እንግልቱን በቅርብ የሚያውቁት በመሆናቸው ለጉባዔ ትምህርት ቤቶች ለአብነት መምህራን ትኩረት በመስጠት የመማር ማስተማሩ ሄደት በተቻለ መጠን በመደጎም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ይትባህል መሠረት የቤተ ክርስቲያኗ ትውፊት የሊቃውንቱ መፍለቂያ ታላቁ ጎንደር ቀዳማዊ የትምህርት ማከዕልነት ታሪክ እንደተጠበቀ ጉባዔያት እንዳይፈቱ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። አዳዲስ አቢያተ ክርስቲያናትን ባርኮ በመክፈትና እንዲሁም መነፈሳዊ አስተዳደር ብቃት ባለው ውሳኔ ሰጭነት በሊቃውንቱ ዘንድ የተመሰገኑ ሆነው ሀገረ ስብከቱን በሊቀ ጳጳስነት እየመሩ በስፋት ሲያገለግሉ በነበሩበት ወቅት፤ ባህታዊዩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት በ1979 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ በወቅቱ የቅዱስ ፓትርያርኩ እንደራሴና ልዩ ረዳት ስለነበሩ ወዲያውኑ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው እንዲቆዩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ።

3ኛ/ የብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ሲመተ ቅዱስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ፤

ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ከቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት በኋላ ለምርጫ ፓትርያርክነት መመዘኛውን አሟልተው በአንድኛ ደራጃ በአብላጫ ድምጽ እጩ ሆነው ከቀረቡት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ በወቅቱ በተለይም በመንፈሳዊ ትምህርት ደረጃ እሳቸው ያቀረቡትን የመምህርነት ማስረጃ አሟልቶ ያቀረበ ባለመኖሩ፤ በትክክለኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግጋት መሠረት የምርጫ መመዘኛውን በሚገባ አሟልተው በቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ድምጽ በመንበረ ጽባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ በተደረገው ሥነ ስርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ቅዱስ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በተሟላ የመንፈሳዊ ትምህርት ብቃት በተለይም በድጓ  የአብነት መምህርነት ደረጃ ያላው ፓትርያርክ ሲመረጥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ናቸው። በቅርብ የሚያውቋቸው ሊቃውነት እንደሚናገሩት ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ከመሆናቸው በፊት፤ እንደ ሌሎች መነኮሳት የሌሊቱ ማኀሌት አልቆ ሲነጋ ለኪዳንና ለቅዳሴ የሚመጡ ሳይሆኑ፤ ከሊቃውንቱ ጋር ቆመው የተክሌ አቋቋሙን አሳምረው የሚዘሙ፣ ቅኔ የሚቀኙ፣ በወርሃ ዐብይ ፆም ጥርት ባለ ዜማ ድጓና ጾመ ድጓ የሚቃኙ ሊቅ መሆናቸውን ይመሰክራሉ፤
ቅዱስነታቸው ምንም እንኳን በአዲስ አበባ ፓትርያርክ ሆነው የቆዩበት ዘመን አጭር ቢሆንም ወድያውኑ እንደተመርጠው መንበሩን በአባትነት እንደተረከቡ ቀዳሚ ትኩረታቸውን በቤተ ክርስቲያንዋ ሕልውና ላይ አድርገው እጅግ የሚበጅና መሠረታዊ  መመሪያዎችን አስተላለፉ፤
ሀ/ ጥንታዊ የአብነት ትምህርት ቤቶችና መምህራን የቤተ ክርስቲያን የደምስርና እስትንፋስ መሆኑን አርቆ በማሰብ፤ መምህራን በችግር ምክንያት ጉባዔውን ፈትተው ተማሪዎቻቸውን አሰናብተው እንዳይሰደዱ፤ ብዐት አጽንተው፣ ወንበር ዘርግተው ጉባዔ አስፍተው የሚያስተምሩ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአብነት መምህራን በሙሉ በያሉበትና በሚያስተምሩበት ደመወዝ እንዲከፈላቸው፤
ለ/ በአድባራትና በገዳማት የሚሾሙ አስተዳዳሪዎች ሊቃውንቱን የሚመሩ እንደመሆናቸው መጠን ከቤተ ክርስቲያኑቱ የጉባዔ ትምህርት ቤቶች ማለትም በመጽሐፍት ትርጓሜ፣በአቋቋም/ዜማ፣ በቅኔ እንዲሁም በቅዳሴ በአንዱ መምህርነትን ያስመሠከረ ወይም የመምህርነት ደረጃ ያላቸው ብቻ እንዲሆኑ፤
ሐ/ ለሊቀ ጳጳስነት የሚታጩ ቆሞሳት እንደዚሁ ከጥንታዊ የመንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች የመምህርነት ምስክር ያላቸው፣ ገዳማዊ ሕይወት ያሻቸው ከነበሩበት ገዳም በአገልግሎታቸው ብርታት በሃይማኖታቸው ጽናት ለቤተ ክርስቲያን ያላቸው ታማኝነት ማስረጃ የሚያቀርቡ መሆናቸው የተመሠከረላቸው ወይም በተላላቅ አድባራትና ገዳማት ያለ ወቀሳና ከሰሳ እረጅም ጊዜ የአስተዳደሩ የታወቁ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ  እንዲሆን፤
መ/ በየአድባራቱ የሚመደቡ ሰባክያነ ወነጌል እንዲሁ በቤተ ክርስቲንኗ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የታሹና የስብከተ ወንጌል ችሎታቸው በሊቃውንት ጉባዔ የተመሠከረላቸው ብቻ እንዲሆኑ የሚሉ ወሳኝነት ያላቸው ተቀዳሚ መመሪያዎችን በማስተላለፍ የፓትርያርክነት መንፈሳዊ ተግባራቸውን ጀመሩ፤
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሀገር ውስጥ ሳሉ ከተሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት ሁሉም በጥንታዊ የቤተ ክርስቲያንዋ መንፈሳዊ ትምህት የታሹና አብዣኛዎቹ የመምህርነት ደርጃ ያላቸው ናቸው። በአስተዳዳሪነት ደረጃም በተለይም በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ይሾሙ የነበሩት የአብነት የመምህርነት ደረጃ የነበራቸው ነበሩ ለመሳሌ፦ በቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል እነ ሊቀ ሥልጣናት ዳኔል ባሳዝነው የቅኔ መምህር/ጎጃም/፣ በማህደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን እነ መልአከ ስብሐት ተስፋ መርሻ የድጓ መምህር/ሸዋ/፣ እነ መልአከ አርያም ይትባረክ፣ እነ መልአከ ብርሃናት ናሁሰናይ የድጓ መምህር/ጎጃም/፣ እነ መልአከ ስብሐት ተስፋ ጀንበሬ የአቋቋም መምህር/ጎንደር/፣ እነ መልአከ ኃይል አባ ዋካ ድንግል የቅዳሴ መምህር/ወሎ፤ በግፍ የተንገላቱ አረጋዊ አባት//፣  እነ መልአከ አርያም ዘላለም እሰይ የአቋቋም መምህር የመሳሰሉት ሊቃውንት በየአድባራቱ በችሎታቸው ብቻ እየተመዘኑ መሾም ጀመሩ።
አዳዲስ አድባራትም ለማሰራት የመሠረት ድንጋይ አኖሩ፣ ለምሳሌ የቦሌ መድኅኒዓለም ወመጥምቁ ዩሐንስ፣ የጎፋ ቤዛ ብዙኃን ኪዳነምህረት፣ የአስኮ ቅዱስ ገብርኤል አቢያተ ክርስቲያናት የመሠረት ድንጋይ የተጣለው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ነው።
የቤተ ክርስቲያንኗ ጥንታዊ ክብር በዚህ መልኩ እየተጠበቀና ሰፊ እንቅስቃሴ ላይ በነበረበት ወቅት በሻቢያ ሲቆሰቆስ የቆየው ፍም እሳት ቀስ በቀስ ወያኔ የሚባል እረመጥ ወልዶ ቀን በቀን የጎሳና የዘር መድሎ እየተመገበ በጣባብነት፣ በአንድ ጎሳ የበላይነትና ተስፋፊነት በጭካኔና በተንኮል በከፋፍይነት በገንጣይ አስገንጣይነት አስተሳሰብ በጫካ ተክኖ  በተሳሳተ የወጪ መንግሥታት የፓለቲካ ግምገማ ስኬት እየገሰገሰ መጣ፤

4ኛ/ የወያኔ አዲስ አበባ መግባትና በቅዱስ ፓትርያርክ ላይ ያደረገው ሴራና የአድማ፤

ይህ በዘርና በጎሳ በጠባብ ብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳብ  ተመርዞ በሻብያ ሞግዚትነት ያደገው ከበረኽኝነት የወንብድና ተግባር አልፎም፤ መጥረጊያ እየሸጠ ብጥስጣሽ ቆርቆሮ እየለቀመ ደርግ አምኖ በሾማቸው ሁሉ ውስጥ ውስጡን ሰርጎ ደርጎች በሚስቶቻቸውም በቁባቶቻቸው እየተሰለሉ ሥርዓቱ እየተነቃነቀ መጣ። የበላይ አመራሮቹ በሀገር አንድነት በሕዝብ እኩልነት መርህ ላይ የተመሠረተውን ብሔር ብሔርሰብ አቀፍ የሀገር መከላከያ ጦር በአመራር እጦት እያደከሙት ሄዱ። በመጨረሻ አካባቢ በበረሃ ካለው ጥቃት ይልቅ በውስጥ ያለው ሸፍጥኝነት ጥፋቱን ሁሉ በአንድ ሰው ላይ ደፍድፎ እጁን እንደ ጲላጦስ ታጥቦ ለመቀመጥ የሚያደርገው የውስጥ መርመጥመጥ  ከሁሉም  በላይ የሲ.አይ.ኤ፣ የእነ ካርተርና የኸርማንኮን በጠቅላላው የአሜሪካን ከፍተኛ የተሳሳተ ፓለቲካ ጫና ተደምሮበት ገና ለንደን ላይ የተሰየመው በነክቡር ተስፋየ ዲንቃ ይመራ የነበረው ልዑክ የተኩስ አቁም   ድርድሩ ሳይጠናቀቅ ወያኔና ሻብያ በአሜሪካን ትእዛዝ አዲስ አበባን መግባት ቋመጡ። የሀገሪቱ አመራር አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀ፤ የቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊና ቀኖናዊ ህልውና ለሁለተኛ ጊዜ አደጋ ተጋረጠበት።
ማሀሉን ያገራችን ክፍል እንወክላለን የሚሉ በውስጥ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና በወጪ  መሰል መኳንንት ነን የሚሉ  መሐል ሰፋሪ አድመኞችና የፓትርያርክ ምኞት ያላቸው ባለ «ንግርተኞች» የተለመደ አድማቸውን ሲያደርጉ፤በሌላ አግጣጫ ደግሞ ታዛዥ ቀራቢ ሆነው የነበሩት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዩች የትግራይ ተወላጆችም «ዘመኑ የእኛ ነው» በሚል ምንም ባልበደሏቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ላይ  ቀሚስ እየለበሱ በገቡ መሰል መነኮሳት እየተረዱ አንገታቸውን ማቅናት ማን ይነካናል በሚል ይንጠራሩ ጀመር ።
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፈቃድ በካርቱም የሚገኘውን በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተተከለውን የመድኅኒ ዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲያስተዳድሩ የተሾሙት መምህር ሀበተማርያም ተድላ/ትግሬ/ በስተ ሽምግልና የተሰጣቸውን ሹመት ክደው  ወያኔን ተቀላቀሉ ቅዱስ ፓትርያርኩንም እጅግ ቅሌት በተሞላው ቃላት መዝለፍ ጀመሩ።

በሌላ አቅጣጫ ከላይ እንደተጠቀሰው መሀሉ ሀገራችን ክፍል እንወክላለን የሚሉ መሃል ሰፋሪዎችም  አቡነ መርቆሬዎስን አውርዶ የፓትርያርክነት ሥልጣኑን የመያዝ ንግርት አለኝ የሚሉትን ለማሾምና በሚገኘው በረከት ግብረ በላ ለመሆን አያ በሬ ሆይ ሣሩን አየህ እንጅ ገደሉን ሳታይ እንደተባለው ውስጥ ውስጡን ወደፊት ስማቸውን በምንጠቅሳቸው ሊቃነ ጳጳሳት አመራር ሰጭነት፣ እነ መልአከ ሰላም ቀሲስ ዳኛቸው፣ እነ መምሬ ፍርስሐ ተበጀ በቅጽል ስማቸው መምሬ ወርቁ ይሏቸዋል፣ እነ አቶ ደርቤ፣ እነ ኃይለጌዎርጊስ ዳኘ፣ እነ መዘምር ኪነጥበብ… በአራት ኪሎ በዐታ ለማርያም ገዳምና በመንበረ መንግሥት ግቢ ቅዱስ ገብርኤል አካባቢ ያሉት ጥቂት ካህናትን ጨምረው አድማው ማቀጣጠል ጀመሩ። ይህ ድርጊት ለወያኔ ስለተመቸው በተናጠል እየያዘ ትሾማለችሁ በሚል ተስፋ አድማው እንዲ ጠነክር ከፍተኛ ግፊት አደረገ።
ቅዱስነታቸው በየቦታው የሚደረገው አድማ እንቅስቃሴ በሁሉም አቅጣጫ እነማን እንደሚያደርጉት ይሰሙ ነበር። በተለይም ቀሲስ ዳኛቸውን በንቃታቸው በአንደበተ ርቱዕነታቸው ይወድዋቸው ስለነበረ፤ ዳኛቸውም አለበት ሲባሉ፤ «አሁን ዳኛቸውን ምን አድርጌው ነው፤ ወይ ጉድ! አረምና ጠላት ሳይዘሩት ይበቅላል» ብለው እንደተናገሩ ውስጥ አዋቂ ሰዎች በቤተ ክህነቱ አካባቢ በጨዋታ መልክ ያስታውሱታል። ቀሲስ ዳኛቸው ከአሁን በፊት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ አድመዋል ተብለው በወቅቱ ቅዱስ ፓትርያርኩ አስቀርበው ሲጠየቁዋቸው፤ ይቅርታ አባታችን!! አድጦኝ ነው ብለው ሲመልሱ፤ ፓትርያርኩም «ታዲያ እኮ ቢያድጥህ ቁልቁል እንጅ ሽቅብ ያድጥሀል እንዴ» ብለው እንደገሰጿቸው በቤተ ክህነቱ ውስጥ ቀደም ያሉ ሰዎች በምሳሌ መልክ ሲናገሩ ሰምተናል። ያው ታሪክ እራሱን ይደግማል ነው እንግዲህ። መልአከ ሰላም ዳኛቸው አንደበተ ርዕቱ  ሰባኪ፣ ብቃት ያለው ተናጋሪና ጥሩ ፐሮግራም መሪ ሲሆኑ የሰብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ ሆነው እረጅም ግዜ  ቤተ ክርስቲያኗን ያገለገሉ ቢሆንም በአድማ የሚያክላቸው የለም እየተባሉ ይተቻሉ።
ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ እድገታቸውም ኑሯቸውም ከቃለ እግዚአብሔር ጋር በእጅጉ የተቆራኙ፣ መንፈሳዊ የጸሎትና ፍጹም የቤተ ክርስቲያን ሰው እንጅ የነገርና የተንኮል ሰው ስላልሆኑ፤ በወቅቱ ወያኔ ተገን አድርጎ ከየአቅጣጫው የሚነጉደው የፓሮፓጋንዳና የስም ማጥፋት ዘመቻ ነጎድጓድ መንፈሳዊ ተግባራቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ተብትቦ ያስጨንቃቸው ጀመር። ብዙም ሳይቆይ የሀገሪቱ መሪ ፕረዘዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ተሰደዱ። ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሻቢያና ወያኔ በሳሉት በሁለት በኩል ስለት ባለው ሰይፍ ለፍሪዳ ቀረበች። ወያኔም በሻቢያ ታዝሎ አዲስ አበባ ገብቶ ንጉሠ ነገሥት ምንሊክና ዓይናማዋ ንግሥት እቴጌ ጣይቱ ያቀኑትን ቤተ መነግሥት ተቆጣጥረ፤ ቅማል የፈላበትን የሱዳን ሽርጥና አቡጀዲድ ቤተ መንግሥት አጥር ላይ አጥባ ማስጣት ጸጉርዋን መከርከም ገላዋን መታጠብ ጀመረች። ጽድቁንም ሀጥያቱንም በሀገር ወዳዱ በታሪክ ባለአደራው ፕረዘዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጭነን እኛ እንደ ጲላጦስ እጃችን ታጥበን ከደሙ ነጻ እንሆናለን ብለው ያሰቡት ጀነራሎችና ምኒስትሮች ከጀኔራል ኃይሌ መለሰ /እራሳቸውን አደራጅተው እንደገና ወያኔን ለመመከት  ከፋኝ በኋላም አርበኛች ግንባር የሚባለውን ካአቋቋሙት/ በስተቀር ሁሉም በጀምላ ለወያኔ  እጃቸውን ሰጥተው  ዘብጥያ ወረዱ። አንዳንዱቹም በስደት ወደ እንግሊዝና ወደ አሜሪካን ሀገር ተሰደው የመኖር እድል ገጥሟቸው ዛሬ በየአቢያተ ክርስቲያኑ ጣልቃ እየገቡ በማያውቁት ነገር ውቂው ደብልቂው ሲሉ ይውላሉ።
ከዚያም ቅዱስነታቸውም ነገሩን በማለሳለስና በማለዘብ ለመያዝና መንፈሳዊ ድርሻቸውን የተወጡና እንደዚሁም ወያኔ ህሊና ያለው መስሏቸው አከታትለው በየአድባራቱና ገድማቱ ምህላ እንዲደረግ መመሪያ ከመስጠት ጋር ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም እንዲወርድ ጸሎተ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን በሬዴዎ ቢያስተላልፉም፤ በየገዳሙ መነኩሴ ሆኖ ቆብ እየደፋ፣ አስቀድሞ የራሱን ፓትርያርክ አጭቶ የመጣው ይሉኝታ የሌለው ወያኔ ገና ከሕጻንነቱ ጀምሮ የሚጠላውን ከአማራ እና ኦርቶዶሳዊ እምነቱን የሚሰማበት ጀሮ ሆነ ጊዜ  ሳይኖረው ቀጥታ ሳያፍር በድፍረት ፓትርያርኩን ባልተገራ እና ሥርዓት በሌለው አንደበት ማዋከብ ማሳቀቅ ጀመረ፤

5ኛ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በወያኔዎች የደረሰባቸው ከፍተኛ ወከባ፣ ዘለፋና ዛቻ፤

ወያኔ በበርሃ እያለ ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን አባቶች በጀምላ የደርግ ጳጳሳት እያለ ሲዘልፍ እንዳልነበረ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ መሀል ሰፋሪ አድመኛችን ክሳሽ አድርጎ ያለ የሌለ የጥላቻ ኃይሉን በፓትርያርኩ ላይ አነጣጠረ። ከላይ የተጠቀሰውን ለማጠናከር፤ በውስጥ መካከለኛውን የሀገራችን ክፍል እንወክላለን የሚሉ ጥቂት አድመኛች፤ እንዲሁም ጊዜው የእኛ ነው ብለው በተመኩ ሥልጣን ፈላጊ የትግራይ ተወላጆች ሊቃነ ጳጳሳትና ካህናት  ውስጥ ውስጡን  በተናጠል በሥልጣን እያባበለ መቀስቀስ ጀመሪ። በቤተ ክህነቱ አካባቢ ቁምጣ የታጠቁ አማረኛ የማይሰሙ እንዲሁ ድንገት «ጠጠው በል» «ቁም» እያሉ በሚያስፈራሩና የስነ ልቦና ጫና የሚያደርሱ የወያኔ ወታደሮች ተሰማሩ።
ቀጥሎም፤ አቶ አባይ ፀሐይዩ የሚባለው ቀንደኛ ወያኔ በወቅቱ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እንደራሴ አቡነ ዜናማርቆስና ልዩ ጸሐፊ ለነበሩት ለብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ ደውሎ፤ አንተ ብሎ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጋር በፈጹም እንደማይሡሩ ከማስጠንቀቂያ ጋር መልዕክት አስተላለፈ። ከዝያም እነ ታምራት ላይኔ፣ እነ ክንፈ ገብረመድኅን፣ እነ ኃያሎም የመሳሰሉት ሁሉ እየደወሉ የቅሌት ስድብ የሚቀናቸው ወያኔዎች ከመጠን የዘለለ ያልተገራና ያልታረመ ቃላት እየተጣቀሙ ቅዱስ ፓትርያርኩን  አዕምሮዋቸውን ማወክና ማዋከብ ጀመሩ። ሌላው ተላላኪው ጭምር እየታዘዘ እንዲሁ ስሙን በባለሥልጣናቱ ስም እየቀየረ አንደበቱን የተግራኛ ቅላጼ እያደረገ ፓትርያርኩን ማጨናነቅ ተረባርቦ የማስወገድ ሥራ ተጀመረ። በቀን ተቆጥሮ የማያልቅ የስልክ ጎርፍ ይወርድባቸዋል። በክርስቶስ ወርኅ ስቅለት… ወተማከሩ ሊቃነ ካህናት… እንዲል መጽሐፍ የውስጥ አርበኛች ሊቃነ ጳጳሳቱን በየጉሬው እያደሙና እያሴሩ ነገሩን ያጦዙት ጀመር። ቅዱስነታቸው ይህን ሁሉ የመከራ ቀንበር በብቸኝነትና በአኮቴት ወይም በአርምሞ በፀጋና በጽናት ተቀበሉት።
ከዚያም በመምህር ሀበተማርያም ተድላ አስተባባሪነት እነ ቀሲስ ዳኛቸው፣ እነ ደክተር ማርቆስ/ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የነበሩ/ እነ አቶ ደርቤ፣ እነ መምሬ ፍስሐ ተበጀ /መምሬ ወርቁ/ አቀነባባሪነት ወያኔ በገባ በወሩ ሰኔ 28 ቀን 1983 ዓ.ም ፓትርያርኩን የሚከስ የሐሰት ደብዳቤ አርቅቀው ለወያኔዎች አቀረቡ። ከዚያም በተጨማሪ ምቹ ጊዜን ፈልጎ ቅዱስ ፓትርያርኩን ከመንበራቸው ጎትቶ የሚያስወጣ የወያኔ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ነበር። ሆንም ያሰቡት ዓላማ የሚያዛልቅ አለመሆኑ ስለተመከረበት በውጭ ሆነው አድማውን ያራግቡት ጀመር።
በሌላ አቅጣጫ በቤተ ክርህነቱ ሠራተኞች እንዲሁም በባህታዊ አምኃሥላሴ የሚመራ ከፍተኛ ቁጥር የነበረው ምዕመናን  ለቅዱስ ፓትርያርኩ የነበረውን ድጋፍ አሰማ። በተለይ በመነበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ባህታዊ አምኃሥላሴ የሚመራው ከፍተኛ የምዕመናን ቁጥር በተከታታይ በማታው ስብከተ ወንጌል እየተገኙ ግቢውን በማጨናነቅ ቅዱስነታቸውን ይጠብቅ ነበር። ባህታዊ አምኃሥላሴም በተለይም ሊቃነ ጳጳሳቱ በመንፈስ ቅዱስ አባታቸው በቅዱስ ፓትርያርኩ ላይ የሚሸርቡት ሸፍጥ፣ ከላይ የተጠቀሱት የመሃል ሰፋሪዎች አድማ በትምህርት መልክ በልበ ሙሉነት ስሜት በሰላ አንደበት በማጋለጥ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዳይደፈር መሪር ተጋድሎ አደረጉ። በአዲስ አበባ ያደረጉት ጥረት አልሳካ ሲል እንደገና ጉዳዩን ወደ ጎንደር በመውሰድ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለሊቃውንቱ ለሕዝቡም በማስረዳት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር። በዚህ አጋጣሚ ባህታዊ አምኃሥላሴ ሃያ ሰባት ዓመት ወያኔን ግንባር በግንባር በመጋፈጥ እስር ቤት ደረስ የተቀጠቀጡ እና እንደ ወርቅ በሳት የተፈተኑ የቤተ ክርስቲያኗ ልጅ፣ ባህታዊ፣ አርበኛ መሆናቸውን መዘከር ግዴታ ነው።
ቅዱስነታቸው ቅዱስ ሲኖዶስን ቢሰበስቡም፣ወደፊት ስማቸውን የምጠቅሳቸው የወያኔ ገባር በመሆናቸው፤ ማነን አምነው ምን ይናገሩ፤ ምንስ ያስወስኑ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ወደቁ። ለጊዜው እንደራሴው ብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ ሲኖዶሱን እንዲመሩት ቢደረግም ወያኔ ለአቡነ ዜና ማርቆስ ፓትርያርኩን ያሰናብቱ እያለ ያዋክባቸው ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ አሰናብተው ባያሳውቁን ኃላፊነቱን ይወስዳሉ እያለ ግራ ሲያጋባቸው፤ በአድማ የሰከረውን በሴራ የተመረዘውን አባላት እንደመከረው ቅዱስ ፓትርያርኩ በፈለጉት ቦታ ማረፍያ ተሰጥቷቸው እንዲቀመጡ የሚል ደብዳቤ በማብረር ከወያኔ ወከባ ሊገላገሉ ቻሉ። ነበሩ ሁሉ ቅዱስነታቸውም ውስብስብ ሆነ። የሴረኛው ክፍልም የቤተ ክርስቲያንኗ የወደፊት እጣፋንታ ስያስታውል ወያኔን ተገን አድርጎ እጣቱን ስለቀሰረባቸው በስውር ተጉዘው ለጊዜው ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ ወደሚገኝ ዘመድ እረፍት አደረጉ።

6ኛ/ የወያኔ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አዲስ ሥራ አስኪያጅ መሾም፤

ወቅቱ የወያኔ መንግሥት ያልተረጋጋበት ሥራዎችንም በተገቢው የአስተዳደር ብቃት ተክቶ ለመሥራት በረኽኞቹ ትምህርትም ችሎታም የሌላቸው ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞዎቹ አማርኛውንም ያዳምጣሉ እንጅ መናገር፣ መረዳትና መጽሐፍ የማይችሉ በመሆኑ በወቅቱ ሁሉንም የመንግሥት ተቋማት እንዳሁኑ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ስላልቻሉ፤ አንዳንድ የደርግ ሹመኛችን በአሉበት ማቆየት የግድ ያለበት ጊዜ ነበር። በሌላ አቅጣጫ እነሱ እራሳቸውም ሆነ የእነሱን አለዋቂነት ተጠቅሞ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይደረግ እንደነበረው ዘረፋ ሁሉ በተለይም በቤተ ክህነቱ ልማት ኮሚሽን በሚባለው አካባቢ ለዕርዳታ የመጡ ንብረቶችን እየዘረፍና አያዘረፉ ለመርካቶ ነጋዴ የሚቸበችቡ ሙስና የዕት ተዕለት ተግባር ሆነ በጠቅላላው የቤተ ክህንቱ  አጠቃላይ አስትዳደር  የዋዥቀበት መሪና ተመሪ የጠፋበት ውቅት ተፈጠረ።
በዚህን ወቅት ወያኔ አድስ ሥራ አስኪያጅ መሾም እንዳለባት ተረዳ። በዚህ አጋጣሚ ከደርግ ባለስልጣናት ጋር ተጣልተው ወደ አንድ ዓመት ገደማ ከርቸሌ ታስረው በኋላ ግን የተፈቱት አቶ ዘመነ ሕላዊ በሥራ አስኪጅነት ተሾሙ። አቶ ዘመነ ሕላዊ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከአለቃ ጥበቡ ገሜ እስከ ቅኔ ድረስ የተማሩ፤ በቤተ ክህነቱ አካባቢ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስሊዮስ እንደራሲና አማካሪ ከነበሩት አያታቸው እክታላቁ ፀባቴ ገብረሥላሴ ያሳደጓቸው፤ ወደ አሜሪካን አሀገርም ተልከው በሳንፍራንሲስኮ ዩንቨርስቲ በወንጀል መከላከል ሳይንስ ማስተርስ ድግሪ የሠሩ ቢሆንም በተፈጥሮዋቸው በኃይል የመጠቀም፣ ትግሥት የሌላቸው ፈሊጥ የጎደለው ቁጡነት የሚበዛው በህሪ ያላቸው በመሆኑ፤ በዚያን የትርምስ ውቅት የነገር ብልት ሲሰነጥቁ የሚውሉ የቤተ ክህነቱን አድመኞች በየጎሬው በሚያድሙበት ውቅት ለቤተ ክህነቱ አስተዳደር ተመራጭ ሰው እንዳልነበሩ የሚታወቅ ሃቅ ቢሆንም፤ አቶ ዘመነ የቤተ ክርስቲያኗን ሕልውና ከማስጠበቅ አንጻር ብፁዕ ቅዱስ ፓትርያርኩን ወደ መነበራቸው መመለስ ወይም መጥራት አስፈላጊ መሆኑን ለወያኔ መንግሥት አበክረው አሳስበው ነበር። ከዚህም ጋር በተያያዘ ብፁዕ ውቅዲስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ፣ መንፈሳዊ የአባትነት ተግባራቸውን ለማከናወን የሚያግዳቸው አንዳችም የጤና የመንፈስም ችግር እንደሌለባቸው በመግለጽ ለቅዲስ ሲኖዶስ በአድራሻ  ለመለስ ዜናዊ በግዜው የሀገሪቱ ሽግግር መንግሥት ፕረዘዳንት እና ለሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት መሥሪያቤቶች ደብዳቤ አስተላለፉ።
ይህን የሰማው የመካከለኛው ቡድን ውስጥ ውስጡን በወያኔ እየተገፋ፤ ጎንደሬ ሥራ አስኪያጅ ሹማችሁ ፓትርያርኩን ወደ መንበራቸው ሊመልሳቸው ነው በማለት አድማውን እንደ ጉድ አጦዘው። በተለይም በልማት ኮሚሽን ውስጥ በአቡነ ጤሞቴዎስ፣ እና አቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የትግራይ ተወላጆች እነ ንቨረዕድ ኃይለልዑል ወልደገሪማ ጨምሮ  ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው ማሀል ሰፋሪዎች በፓትርይርኩ ላይ ብቻ  ሳይሆን በአዲሡ ሥራ አስኪጅ ላይ ከፓትርያርኩ ባልተናነሰ  አጧጧፋ። በአድማ ጠቅላይ ምንስትሩ ታምራት ላይኔ ቢሮ ገብተወ ይህ ሥራ አስኪያጅ ካላነሳችሁ እክናችሁ ቆባችን ተረከቡን እስከማለት ተናግረው፤ ሥራ አስኪያጁን  ያስተዳደር በደል አድርሰዋል በሚል በታምራት ላይኔ ፊርማ አስነስተው ደብዳቤውን ፎቶ ኮፒ እያደረጉ በአራት ኪሎ አካባቢ አባዝተው በየበሩና በየስል እንጨቱ አስለጠፉት።

7ኛ/ በቅዱስ ፓትርያርኩ ላይ ሸፍጠኝነቱንና አድማውን ያንቀሳቀሱት ሊቃነ ጳጳሳት፤

ወደኋላ ታሪክን ማስታወስ ለአዲስ ታሪክ መሪና በንጽጽር ለማየትና የኅሊና ዳኝነት ለመስጠት ይረዳል። ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴውፍሎስ በደርግ መንግሥት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ብለወ ከፈረሙት አባቶች መካከል በቅዱስነታቸው ማዕረግ ሊቀ ጵጵስና ከተሰጣቸው ዋናው ብፁዕ አቡነ መቃሪዎስ የሚባሉ የተንቤን ትግራይ ተወላጅ ነበሩ።  በኃላም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፈቃድ በጎጃም ክፍለሀገር ላይ በሊቀ ጵጵስነት ተሹመው አማራውም ማኅበረሰብ በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ በሰሩት ከፍተኛ በደል ቂም በቀል ሳይዝ አባቴ ብሎ ተቀብሎ እረጅም ጌዜ በጎጃም መሬት ላይ በተድላ ቆይተዋል። በአጭሩ ይህን ታሪክ ለዝክረ ነገር አስታውሰን ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለሳለን።
እንደሚታወቀው ወያኔ በቀዳሚነት አማራ የሚባለውን ማኅብረሰብ ማዳከም፣ ቤተ ክርስቲያኗንም የአማራ ናት በሚል የተሳሳተ የማጥቃት አስተሳሰብ ከማፍረስ በተጨማሪም በራሱ ታመኞች መቆጣጠር ከርበርሃ መርሪ ዕቅዶስቹ ውስጥ አንዱና ዋነኛው እንደመሆኑ፤ ይህን አፍራሽ አስተሳሰብ የተጋሩ ነገር ግን አማራ እና ኦሮሞ በአንድነት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ያቀና ለአንድነት መስዋትነት ከፍሎ በባንዲራው መግነዝነት በአንድ ጉድጓድ የተቀበረ መርሆኑ ያልተርዱ ጥቂት የአሮሞ ተወላጆች ጭምር አሳስቶ  ሁሉም አባቶቻችን ያቀኗትን ቤተ ክርስቲያን በጠላትነት በመመልከት ፕሮቴስታንትነት መረጡ።
ወያኔ በቤተ ክህነቱ አካባቢ ያሉትን ውልደ ትግራይን ሊቃነ ጳጳሳትንና ካህናትን በማሳደም፤ ከበረሃ ተከትለውት የመጡ መሰል መነኮሳትን በሰላይነት በቤተ ክህነቱ ውስጥ በማሰማራት ከፍተኛ አድማ ቅስቀሳ ሲያደርግ፤ የመካከለኛው ሀገርን እንወክላለን የሚሉት ደግሞ ወያኔ የመንግሥት ሥልጣንን ከያዘ የቤተ ክህነቱን ለኛ ይለቅልናል በሚል የሞኝ ተስፋ በመንፈስ ቅዱስ አባታቸው በቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ እንዳይመለሱ አድማውን ያራግቡት ጀመር አድመኞቹ ሊቃነ ጳጳሳት ከዚህ የሚከተሉት ናቸው።

ከዚህ በላይ ስማቸው የተጠቀሰው 1ኛ/ ብፁዕ አቡነ መቃሪዎስ /ትግሬ/ 2ኛ/ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ/ ሸዋ/ ሁለቱም በሕይዎት የሉም ነፍሳቸውን በገነት ያሳርፍ/ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን አሳልፈው ለደርግ ሰጥተው ቤተ ክርስቲያንዋን ገድለው ያስገደሉ ሲሆኑ፤ ወያኔ ሲመጣ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴውፍሎስን ሰማዕት ብለው የሰየሙ ናቸው። እነዚህ ከትናንት ስህተታቸና  ከደረሰባቸው ወቀሳ ሳይማሩ እንዲያውም በዚህ ገበርተ አመጻ ጎዳና ሌሎችንም አጥምቀውና አሳምነው እራሳቸው በድምጽ ብልጫ የመረጧቸውን ፓትርያርክ ከተመረጡ ሦስት ዓመት ያልሞላቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጊዘውን ተጠቅመው ለወያኔ ሰይፍ አሳልፈው የሰጡ፤ ቤተ ክርስቲያንዋን አደጋ ላይ የጣሉ የከፈሉ እንድትከፈልም አስተዋጽዖ ያደርጉ ናቸው።
የሚገርመው በተራ ቁጥር በ3ኛ/ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት አቡነ ጤሞቴውስ/ትግሬ/ በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ምንም በደል ያደረሰባቸው ይልቁንም ለቤተ ክርስቲያንዋ የውጭ ዕርዳታ የሚያስገባው የለማትና ክርስቲያናዊ ተራድዖ ኪሚሽን የሚባለው ትልቁ መምሪይ ኃላፊ ሆነው በብቸኝነት ብዙ ጌዜ የኖሩ በዚህ መምሪያ ውስጥ በሙሉ ትግረኛ ተናጋሮዎች በቻ በኃላፊነት በሰራተኝነት የነብሩበት፤ ዛሬ ባለ ጥምር ምሌነሩ አቶ ጸጋየ በርሄ የሚባለው ከፍተኛ ገንዘብ ያጋበሱበት መምሪያው ሥር በሕጻናት አስተዳደግ ክፍል እነ አቶ ሊላይ የመሳሰሎ በመኖፓል ይዘው ይጠቀሙበት በአብዛኛው የትግራ ሕጻናት ይረዱበት እንደነበረ እየታወቀ ምንም በደል ሳይደርስባቸው ግዜ ሲያገኙ አድብተው ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ግፍን የሠሩ ሰው ናቸው።
በ4ኛ/ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ብፁዕ አቡነ  ቀውስጦስ ዛሬ ወያኔ አንዳንድ መቃኞ ቤተ ክርስቲያንን ሲያፈርስ እየየ እያሉ ሲያለቅሱ ይሰማሉ፤ ማልቀሱ ማዘኑ መልካም ነው። ዛሬ ሰው ከነሕይወቱ በሚቀበርበት፣ ሀገር እየፈረሰች ፣ ሰባት ሚሊዮን የቤተ ክርስቲያን ተከታይ ያለ ጠያቂ ደብዛው በጠፋበት ወቅት ያለ አረጋዊ አባት የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ከመጀምሪያው ግን መንፈሳዊ አንደበታቸውን እየተጠቀሙ የቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና እንዲጣስ የመንፈስ ቅዱስ አባታቸው ያውም እንደሳቸው በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ለምኖ በመብላት የተንገላቱ ወንድማቸው ፓትርያርኩ በአድማ እንዲፈናቀሉ አስተዋጽዖ ካአደረጉት መካከል ዋናው ናቸው። ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጥሶ ፓትርያርክ ሲሰደድ ያልተሰማቸው አባቶች፤ ሊቃውንቱ በባዶ እግራቸው በግል ልብሳቸው፣ጣፍና የክሰል ጥቀርሻ በጉሮሯቸው እየደረቀ የጉም እንባ እያናቡ ለሊት በማኅሌት ሲነጋ በቅዳሴ ያለምንም ደጎማ  ያቀንዋትን ቤተ ክርስቲያንና የቀኖና ጥሰት ዘንግተወ….. ውፍ ዘራሽ ጠገኛ ሆኖ የቤተ ክርስቲይንን ደም የሚመጥ የካህናትን መቁንን የሚሻማ ማኅበረ ቅዱሳን ሲነካ …ይህ ቤተ ክርስቲያንን በድጅኖ ማፈርስ ነው ብሎ መስበክ እንዲሁም ቅዱስ ዳዊት  «ወጽድቅከኒ በማኅበረ ቅዱሳን» በማለት ለፈጣሪው የዘመረውን ለመደዴ ከተሜዎች ዝና ማዋልና በእግዚአብሔር ቃል ላይ መሳለቅ በእውነት ከፍርድ ተጣያቂነት ነጻ ያደርጋል የሚል ግምት የለንም። በርግጥ ማልቀሱ ውጤት ያመጣል። መጽሐፍ  «…. እንግዲህ በዋይታና በልቅሶ ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ ተመለሱ ማለቱን አሳምረው  አብራርተውና ተርጉመው የሚያውቁና የሚረዱ ጥሩ  መምህር በመሆናቸው በከቱን ጽቁን አስቀድሞ መለመን ተገቢ መሆኑን ያውቅቃሉ።
እንደገና በ8ኛ/ ተራቁጥር  የተጠቀሱት አቡነ ገብርኤል በወቅቱን ተጠቅመው በፓትርያርኩ ላይ ካደሙት አባቶች መካከል አንዱ ሆነው ሳለ፤ ለይስሙላ በትደረገወ የምርጫ ሂደት ውስጥ አቡነ ጳውሎስንም ለማስመረጥ  «ዶክተሩን ምረጡ»  እያሉ በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋጻዖ ማድረጋቸው በግልጽ እየታወቀ ፤እንደገና በኋላ  ሲጣሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን  ማስመረጣቸው እጅግ ትልቅ ስህተት መፈጸማቸውን እና መጸጸታቸውን በሕዝባዊ መገናኛ ብዙኃን አረጋግጠዋል። ከአቡነ ጳውሎስ ጋር በተጣሉበት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በሕጋዊ ፓትርያርክነት እቀበላለሁ ቅዱስ አባት ናቸው። እያሉ ሲያስተምሩን ቆይተው፤ እደግና ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው፤ ወያኔ በፓለቲካ በሁልም አጣጫ ኪሳራ የደረሰበት መሆኑን ለመጠገን ወይም ካድሬ ቭዲዩ ቀራጮች የገቢ ምንጭ ለመፈጠር ይሆን በለሌላ ፤ በአለቀ ጊዜ በድጋሜ ክህደት ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን አመልክተው ነው የለቀቁ…. ሌላም ሌላም ተገቢ ያልሆነ ቃላት ሲናገሩ  በስተሽምግልና ሲሳለቁ፤ ሰው  ትላንት ምን እደተናገሩ እውነቱን የማያውቅ  የማይታዘባቸው ይመስላቸዋል። ይህ የሃያ አምስት ዓመት ታሪክ ነው፤ ጀሮአችን እየሰማ ዓይናችን እያየ የሆነውን ነገር፤ ገና ሊቀ ጳጳስ ነን ሰው እኛን ይሰማል በሚል ግንዛቤ ቃልን እየለዋወጡ እየተገለባበጡ እወነተኛውን ታሪክ ለማጨለም  መሞከር ትዝብት ነው ትርፉ። ይህ የልሳን ከዳተኝነትና ተለዋዋጭነት አቋም ማጣት በአንድ ወቅት የቤተ ክህነት ሊቃውንት ከዲቁና እስከ ጵጵስና በክህደት ጎዳና ብለው የጻፉትን  የትንቢት ያክል ተመልሰን  እንደ አዲስ እንድናስታውስ አስገድዶናል።
ከነዚህ ከላይ ክተዘረዘሩት ኮር አድመኞች በተቃራኒ ከዚህ ቀጥሎ ስማቸው የተጠቀሰው ሊቃነ ጳጳሳት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አይጣስም፤ በሙሉ ድምፅ የመረጥናቸው ፓትርያርኩ አይወርዱም ብለው የተቃወሙ በሀገረ ውስጥም በስደትም የሚገኙ ይኖሩ እነሱ የነብሩ ያሉበት ሲሆኑ እነሱም።

ከላይ ስማቸው ከተጠቀሰው አበው ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ አንድ መረሳት የሌባቸው ግን ሆን ተብሎ ማንነታቸው የተደበቀ የእረፍተ ዜናቸው እና ታሪካቸው ያልተወሳ ሊቀ ጳጳስ ነበሩ። ሊቀ ጳጳሱ  በ7ኛ ተራቁ የተጠቀሱት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የምስራቅ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩ ሲሆን። እኒህ አባት እጅግ የሚያስፈራ ግርማ ያላቸው፤ ረጅም ቁመት ጥርት ያለ ብሩህ ገጽታ የነበራቸው ሲሆኑ፤ የአቡነ ጳውሎስን ምርጫ ፓትርያርክ ሳይቀበሉ፣ መስቀላቸውንም ሳይሳለሙ፤ የቅዱስ ሲኖድስ አባላትንም «ከአሳዳጆች ጋር አልሰብሰብም» እያሉ እንደረገሙ ከአንዳቸውም ጋር ሳይነጋገሩ በቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ ተቀምጠው ባልታወቀ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ  ቆራጥ አባት ናቸው። በእውነት በዚህ አጋጣሚ በውጭ  ያለው ሲኖድስ የእኒህን ጠንካራ አባት  ዜና መዋዕል በአዲስ መልክ መዘገቦ ለትወልድ ማስተዋወቅ እንደሚገባው በዘህ አጋጣሚ እያሳሰባለን።
በ8ኛ ተራቁጥር የተጠቀሱት አንጋፋውና ቀድሰው የማይደክማቸው እረጅም እድሜ ያገለገሎት በመጨረሻም በአንድ መቶ ሰባት ዓመታቸው በሰላም ያረፉት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፤ ምንም እንኳን በሲኖዶስ ስብሰባ ተሳታፊ ቢሆኑም፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለክብራቸው ሳይጨኑቁ በእግራቸው የሚጓዙና ብዙ ሕዝብ የሚያውቃቸው በመሆናቸው፤ አቡነ ጳውሎስን በመቃወም በጎልበት የተያዘ ፓትርያርክነት፤ ቤተ ክርስቲያን ተዘረፈች እያሉ አበክረው በተናጠል መልክት ያስተላልፉ ነበር።
ሌላው መታውስ ያለባቸው ሊቀ ካህናት ኃይለሥላሴ ዓለማየሁ  የትግራይ ተወላጅ ሲሆኑ፤ በመቀሌ፣ በሰላሌ እና በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከታት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሠሩ በመጨረሻም፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መመሪያ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ እጅግ የተወደዱና የተመሰገኑ የአስተዳደር ችሎታ ያላቸው፣ የሰከነ አስተዋይ ልቦና መልካም ባህሪ ያላቸው ካህን ናቸው። በአንድ ወቅት በአሜሪካን ድምጽ የማርኛው ፕርግራም/ቪ.ኦ.ኤ/ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው «ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የተገፉ አባት ናቸው። በማለት ምስክርነታቸውን በጽንዖት የገለጹ ሲሆን፤ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ባላቸው ቃራኔም ከአንድ ዓመት በላይ ከሥራና ከደመወዝ ታግደው ከእነ ቤተሰቦቻቸው እጅግ የተንገላቱ ሲሆን በጋጣሚ የአሜሪካ ቪዛሎተሪ ወጥቶላቸው በአሁኑ ጊዜ ኑሯቸውን በአሜርካ ያደረጉ ሲሆን፤ ቀደም ሲል የአባቶች እርቅ ጉዳይ ለሽምግልና ተመርጠው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ቢላኩ በዚህ ቂም የያዙት ወያኔ፣ ማኅበረ ቅዱሳንና የአቡነ ጳውሎስና የአድማ ከዳሚዎቹ ተባብረው ከአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ከደረሱ በኋላ ወዲያውኑ ወደ አሜሪካን ሀገር እንዲመለሱ ተደረጎ፤ ከትወልድ ሀገራቸው ወደ የአሜሪካን ዲፓርት ተደረጉ። የአሜሪካ ዜጋ መሆናቸው አዳናቸው እንጅ ወያኔ ዘብጥያ ያስገባቸው ነበር።

8ኛ/ የፓትርያርኩ እንደራሴ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ መሰደደ፣ የአቡነ ያዕቆብ አቃቤ መንበር ሆነው መመረጥ፤

ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ከሥራ አስኪያጁ ጋር በመሆን ቅዱስ ፓትርያርኩን ወደ መንበረ ክብራቸው ለመመለስ ጥረት ቢያድርጉም አድማው እየሰፋ፤ ወያኔም በስልክ እየደወለ በአካል እየተገኘ ከሚያስተላልፈው ዘለፋና ወረፋ አንጻር መቋቋም የማይቻል መሆኑን አረጋገጡ። ሥራ አስኪያጅም በታምራት ላይኔ ወደያውኑ የአስተዳድር በደል አድርሰዋል ተብለው ተነሱ። አቡነ ጤሞተዎስ ይህን ተከትለው ሲቪል በለበሱ ወያኔዎች ታጅበው በእብሪትና በትዕቢት በማን አለብኝነት የቤተ ክህነት ቢሮችን ማሸግ ጀመሩ። የቤተ ክህነቱ የባንክ ሒሳብም እንዳይነቀሳቀስ ታገደ። በዚህን ግዜ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ውጥቶ በመሀል ሀገር አድመኛችና በወያኔ ድጋፍ  ጊዜውን በተመኩ የትግራይ ተወላጆች ቅንጅት በተለይም የቤተ ክህነቱ በነበሩት በጎንደር ተወላጆች  ላይ ያነጣጠረ ከአቅም በላይ የሆነ ደባ መሆኑን የተረዱት ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ፤ አስቀድመው ወደ ውጭ ሀገር ተሰደዱ።
ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ የት ወደቁ ይሙቱ ይዳኑ የሚለው ሳያስጨንቃቸው፣ በእውነት እጅግ በሚሳዝን መንፈሳዊነት በተለየው ሽኩቻ፤ አዲሱን የወያኔ ዕጩ ፓትርያርክ ለማስቀመጥ ይጣደፉ ጀመር። በዚህን ወቅት ኤርትራ ተግንጣላ የራስዋን ፓትርያርክ ከግብጽ ለማስመጣት ዝግጅት እያደረገች ባለችበት ወቅት ከላይ ከተጠቀሱት የአድማው ኮር አባላት ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ በ7ኛ ተራ ቁጥር የተመዘገቡት ሙሉ ለሙሉ የኤርትራ ተወላጅ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ወደ ኤርትራ መሄድ ሲገባቸው፤ በወቅቱ በፓለቲካው ውስጥ መለስ ዜናዊ ለሻቢያም ለወያኔም በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሆኖ ይሠራ እንደነበረ ሁሉ፤ እኒህ አባትም ሻቢያንም ወያኔንም ወክለው በቀጥታ መመሪያ እየተቀበሉ በቤተ ክህነቱ ውስጥ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሆነው አቡነ ጳውሎስ ፓትርያክ  ሆነው እንዲመረጡ ከፍተኛ ሚና የተጫዎቱ ናቸው። በእዚህ ወለታቸውና አገልግሎታቸው ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሁነው እስከ ኢትዮ-ኤርትራ የባድመ ጦርነት ድረስ በሥልጣን ላይ ነበሩ። በመጨረሻም እራሳቸው የትግራይ ተወላጆች ማጉረምረም ሲጀምሩ  የክብር አሸኛኘት ተደርጎላቸው የአውሮፕላን ትኬት ተቆርጦላቸው ከታላቅ ምስጋና ጋር ወደ ሀገራቸው ኤርትራ ገቡ ሆኖም ብዙ ሳይቆዩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ ፈጣሪ በገነት ያሳርፋቸው።

9ኛ/   የአዲስ የፓርያርክ ምርጫ አቡነ ጳውሎስና አቡነና ማትያስ ሽኩቻ፤

ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎውፍሎስ አንብሮትረ ዕድ ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሾሙ ሲሆን በደርግ ዘመን እነ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀበተማርያም ወርቅነህ የአሁኑ አርጋዊ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ  ቀዳማዊ ጋር ለሰባት ዓመታት ታስረው ከስር ከተፈቱ በኃላ የጀመርኩትን ትምህርቴን መጨረስ አለብኝ በሚል ምክንያትና ፈቃድ በሊቀ ማዕምራን አበበው ይገዛው ድጋፍና ዕርዳታ በሰላም ወደውጭ ሀገር የወጡ  የአደዋ/ ትግራይ ተወላጅ ናቸው። ብፁዕ አቡነ ማትያስ /የአሁኑ ቅዱስ ፓትርያርክ/ ጎንደር በተማሪ ቤት ያደጉ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አንብሮተ ዕድ ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሾሙ የተመሰገኑ ተወህቦ ክህነት ያላቸው ጥሩ ካህን ሲሆኑ፤ ከቅዱስነታቸው አቡነ ተክለሃይማኖት ጋር ተጣልተው ወደ አሜርካን ሀገር የወጡ የተንቤን/ትግራይ ተወላጅ ናቸው። ሁለቱም በአሜሪካን ሀገር ከአስር ዓመታት በላይ የቆዩ ሲሆን፣ ወቅቱን ተጠግተው ንፋሱን ገምግመው ወደ ሀገራቸው ገቡ።
አቡነ ጳውሎስ ከቤተ ክህነት እስከ መለስ ዜናዊ የአድዋ ተወላጅ የሽግግር መንግሥቱ ፕረዘዳንት ድረስ በጣም ሥር የሰደደ ድጋፍ ሲኖራቸው፤ አቡነ ማትያስ ግን በቤተ ክህነቱ በኩል የተንቤን ተወላጅ የሆኑት አቡነ ጤሞቴዎስ በስተቀር ብዙም የተጠናከረ ኃይል አልነበራቸውም፤ ሆኖም ሁለቱም በወያኔ ዓይን ሚዛን ውስጥ ገብተው ነበር።
በእርግጥ ቤተ ክርስቲያኗ ሕጓ ይጠበቅ ሥርዐቷ  ይከበር የሚል ተቆርቋሪ ቢኖር በአድማ ላይ የተሰማሩት የሊቃነ ጳጳሳት ጭፍንነት አንዱን አስወግዶ ሌላውን ለመሾም እሩጫና ሽሚያ ባይኖር የሰከነ ማስተዋል ቢኖር፤ ሁለቱም ከአሥር ዓመታት በላይ ከቅዱስ ሲኖዶስ ማኅበረ አንድነት ተለይተው ሁለቱም የራሳቸው ለእራሳቸው ብቻ የሚያዙበት ቤተ ክርስቲያን በአሜሪካን ሀገር አቋቁመው የቆዩ በመሆናቸው ትክክለኛ ግምገማና ጥናት ቢደረግ፤ ከሀገር ውስጥ ከነበሩትና በቅዱስ ሲኖዶስ ታቅፈው ሲያገለግሉ ከቆዩት ቀድመው የፓትርያርክነት የበለጠ ድርሻ የሚሰጣቸው አልነበሩም። ሆኖም ጊዜው የወያኔ ሙሉ ለሙሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጁን ያስገባበት የመሀል ሀገር አድመኛችም በተስፋ የጎመጁበት ወቅት ሲሆን ሚዛኑ ግን ለአድዋው ተወላጅ ለአቡነ ጳውሎስ እያደላ መጣ። ይህን የተረዱት ብፁዕ አቡነ ማትያስ የአሁኑ ብፁዕ ውቅዱስ ፓትርያርክ ሁኔታው ስላማራቸው ይቅርብኝ ብለው ወደ አሜርካ ከመመለስ በስተቀር በሀገር ቤት መቆየቱን አልፈለጉትም ነበር።
ከዚያም ለይስሙላ አስመራጭ ኮሚቴ ተመርጦ፤ ለይስሙላ ተወዳዳሪዎች የዋህና መናጆ ናቸው የሚባሉት እነ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በስመ ጎንደር አስቀድመው በወያኔ ዓይን ውስጥ ከታጩት ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ዕጩ ፓትርያርክ ሆኑ። ከዚያም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሀገር ውስጥ እያሉ፤ ፓትርያርክ በሕይዎት እያለ ሁለተኛ ፓትርያርክ በአንዲት ሀገር ውስጥ  በአንድ ዘመን አይሾም የሚለው የማያሻማ ትርጉም ያለው አርቶዶክሳዊ የቤተ ክርስቲያን ሕግ በአማጽያነ ክህነትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተጥሶ ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሆነው ተሾሙ።

10ኛ/ የተጣሰው ኦርቶዶክሳዊ ፍትሕ መንፈሳዊ ሕገ ቤተ ክርስቲያ፤

እዚህ ላይ ታሪክን ማስታወስ ተገቢ ነው። የመጀመሪያው ፓትርያርክ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ባስሌዎስ በእርግና ምክንያት አይናቸው ገርሞ፣ ሕመም ጸንቶባቸው ጉልበታቸውም ደክሞ አልጋ ላይ ውለው ነበር። በውቅቱ የፓትርያርኩ እንደራሴ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በኃላ ፓትርያርክ፤ የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ባስሊዮስ ፓትርያርክነት እስከ ዕለተ ሞታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እንደራሴው ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ  የቅዱስ ፓትርያርኩ ምስለኔ ወይም እንደራሴ ሆነው በሙሉ ኃላፊነት በግንባር ቀደምነት እየሠሩ መንበሩን ጠበቁ እንጅ፤ ፓትርያርኩ ታመዋል፣ ደክመዋል ወይም ሌላ ምክንያት ፈልጎ የመንፈስ ቅዱስ ሹመት ነው ተብሎ የሚታመንበትን የፓትርያርክነት ሹመት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስሌዎስ  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ላይ አልተነሳም ነበር።
ይህም ፓትርያርክ እያለ ፓትርያርክ አይሾምም፤ በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት ፓትርያርክ አይሾም፤ ከተሾመም ለመጀመሪያው ይጽና ለሚለው ሕግ ተገዥ በመሆን፤ በመንፈስ ቅዱስ ሹመት ላይ፣ በቤተ ክርስቲያኗን ሕግን ጥሶ ለሹመት መሽቀዳደምን በፓትርያርክ ላይ አመጽ ማስነሳትን የሃይማኖት ጥሰትና ግድፈት ያክል እጅግ በጣም ጥንቃቄ ከማደረግ የተፈጸመ መሆኑን  እሩቅ ሳንሄድ ሃምሳ ዓመት ያልሞላው የአባቶቻችን መንፈሳዊ የታሪክ አሻራ ያስገነዝበናል።
በአጭር አገላለጽ ፓትርያርክ የሚሻረው የሚለወጠው በሃይማኖቱ ህጸጽ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ግድፈት/ብልግና፣ አደፍ ጉድፍ ተገኝቶበት ለቤተ ክርስቲያዋ ሕልውና ሥጋት ሲጥል ብቻ በማስረጃ ተረጋግጦ በምላተ ቅዱስ ሲኖድስ ጉባዔ ሲወሰን ብቻ ነው።ያ ካልሆነ ፓትርያርክ ሹመት የእድሜ ልክ ነው። ፓትርያርኩ እንኳን በፈቃዱ ልውረድ ቢል በፍጹም የመንፈስ ቅዱስን አድራ አቃሎ መውረድ መተላለፍ አይችልም። ሥልጣኑን እራሱ በራሱ ያገኘው ሳይሆን መለኮታዊ አደራ ጠባቂነት በመሆኑ እስከ ዕለተ ሞቱ የአባትነት አደራ የርሱ ብቻ ነው።
የፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ በሕይዎት መኖር እንዲሁም ፓትርያርካዊ ማዕረጋቸውን ተጠቅመው ሐዋርያዊ ተግባራቸውን በስደት ሀገር ሲኖዶስ አቋቁመው በመምራታቸው ፤ የአቡነ ጳውሎስን የፓትርያርክ ሕልውናቸውንና ታሪካቸውን እጅግ አውዛጋቢ ስላደረገው፤ በእርግጥም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በጠበንጃ ኃይል መጣሱን ስለሚአያረጋግጥ፤ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለውን ስርዋጽ አካል በአስፈጻሚነት ተጠቅመው በተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፤ እጅግ በሚቀፍና በሚያሳዝን ታሪክ ሊታገሰውና ይቅር ሊለው በማይገባ ሁኔታ አዲስ ታአምረ ማርያም አሳትመው፤ መንጋውን በትኖ የሚሰደድ ፓትርያርክ ይነሳል፤ እግዚአብሔር ግን ጳውሎስ የሚባል አባት ያስነሳል እሱም ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል ያስጠብቃል የሚል እጅግ ጸያፍ ድፍረት፣ ንፍቅና እና ክህደት አስገብተው በተኑ። ይህ ብቻ ሳይሆን ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አሸባሪ እጃቸውን በደም የታጠቡ የቋራ ተወላጅ እንደነበሩ እና ብዙ ደም እንዳፈሱሱ እግዘብሔር ግን ኢትዮጵያን ለማጽናት የሰኅለሥላሴን የልጅ ልጅ ምንይልክን ብቻ እንደመረጠ አድርገው ተአምረ ማርያም አሳትመው አሰራጩ።
መቸም ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው የገንዘብ ድርጅት ነጠላ እየዘቀዘቀ ተመሳስሎና ተቆርቋሪ ሆኖ ቤተ መቅድስ ድረስ ዘልቆ በመግባት እንዴት ቤተ ክርስቲያንን እንዳ አግማማት፣ እንደዘረፋት፣ እንደከፋፈላት ወደፊት በስፋት በዝርዝር የሚጻፍ ሲሆን፤ ለግዜው አቶ ስብሐት ነጋ  የሚባሉ አንጋፋ የወያኔ መሪ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲይኗ ሸክም ኣና ዕዳ ነው ሲሉ የተናገሩት  እወነትነት ስላለው ሳንወድ በግድ ለመጥቀስ እንወዳለን።
ከቤተ ክርስቲያን ሕግ አንጻር የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ የደርሰባቸውን ወከባ፣ አድማ፣ ጠባብ የጎሰኝነት ጥላቻ ጊዜውን የተመኩ ሰዎች እብሪትና ትዕቢት፣ የስልጣን ጥበመኞች ስግብግብነት ካልሆነ በስተቀር፤ በቤተ ክርስቲያኗ ማንኛውም መንፈሳዊ መመዘኛ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን የሚያስንቅ ሊቅ፣ መንፈሳዊ አባት፣ ትዕርምተኛ በቅዱስ ሲኖድስ ሙሉ ድምጽ ያለምንም ተቃውሞና ትችት የተመረጡ መሆናቸውን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ምስክርነታቸውን ያረጋግጣሉ።

11ኛ/ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ለስደት መዳረግ፤

ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፤ ወደ መንበሬ ልመለስ መንፈሳዊ አደራየን ለመወጣት ምንም ዓይነት የአካልም ሆነ የመንፈስ ችግር የለብኝም ብለው ለቅዱስ ሲኖዶስና ለመንግሥስት ተብየው በወቅቱ ካሳውቁ በኃላ ያለወን ወከባና የሚወረወረውን ያልታረመ ያልተገራ የቃላት ናዳ አልፎም ሊደርስ ከሚችለው አደጋ ለመጋረድ ብሥራተ ገበርኤል አካባቢ ወደሚገኝ የቅርብ ዘመዳቸው ተጠግተው ፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሰራውን ድራማና እንቆቅልሽ አንድ በአንድ በትዝብት ይከታተሉ ነበር።
ቀጥሎም የቅዱስነታቸውን መገለል የማይፈልጉ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በእነ ባህታዊ አምኅ ኢየሱስ የሚመራው የምዕመናን ክፍል፣ በቤተ ክህነቱና በየሀገር ስብከቱም ያሉ ሥራ አስኪአያጆች እንቅስቃሴ፤ በጠመንጃ የሚታገዘውን ወያኔንና የወያኔን ሹመኛ መካከል የሚነሳውን አደጋ በመሥጋት በርሳቸውም ላይ ሊደርስ የሚችለውን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እጣ ፋንታ በማስታወስ ከዚያም በላይ ክርስቶስ ለሥጋው አደላ እንደሚባለው ሁሉ ሥጋ የለበሱ ሰው እንደመሆናቸው መጠን፤ ወጣት ማሀሪ የሚባል የቤተ ክህነት መደበኛ ሹፌር ታዛዥና ቅን አገልጋይ የነበረ፣ እንዲሁም በዚያን ጊዜ ሊቀ ዲያቆናት ልሳነወቅ ወቤ የአሁኑ ቀሲስ  አስከትለው፤  ያአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሆነች ሰማያዊ ማርሴድስ መኪና ይዘው እስከ ጠረፍ ድረስ ተጓዙ። ከዚያም የሄዱባትን መኪና በአደራ አስቀምጠው፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የእርድ አንስሳትን ከጠረፍ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ከተማ በሚያስገባ የጭነት መኪና ውስጥ ከተጫኑት ከብቶች ጋር ጎንለጎን ሆነው የእንሳቱ ግሳት ምግብ እስትንፋሳቸው ኃይልና ጉልበት ሆንዋቸው ለሁለት ቀናት እህል ባፋቸው ሳይገባ ውሃ እየተጉመጠመጡ አውርዱኝ ለቀመጥ ልነሳ ሳይሉ ጸሎት ከአንደበታቸው ሳይለይ ከግራም ከቀኝም ያለምንም የጠረፍ ጠባቂ ጥያቄ የኢትዮጵያ ደንበር አልፈው ቆላማውን ሰፊውን የጠረፍ አዋሳኝ ተሻግረው በሰላም ኬንያ ናይሮቢ ገቡ።
ኬንያ እንደ አጋጣሚ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ከባቡር ሀዲድ የጠነከረ አቋም ለነበራቸው ለፕረዘዳንት መንግሥቱም እንዲሁም ነጋ ጠባ ቃለ እግዚአብሔር የማይለያቸው ፣ ለሊቃውንቱና ለቤተ ክርስቲያን ከማሰብ ወጪ ሌላ ተልዕኮ ላልነበራቸው ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ  የስደት ኑሮ መሸጋገሪያ ድልድይ የሆነች ሀገር ነች። የኢትዮጵያ አምላክ የሀገር መሪውም ፕረዘዳንቱ መንግሥቱ፤ የታላቋ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሕይወት ኑረው ጽድቁን ሀጥያቱንም አላፊወንም ጠፊውንም በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሠራውን ቁማር ሁሉንም በዓይነ ህሊና በአንቃዱ ልቦና እንዲታዘቡ አደረገ። ሞት ሁላችንም የሚያደባ ጠላት ቢሆንም ሀገር በማፈረስ ሕዝብን በጎሳ በመበታተን የባህር ወደብ በማዘጋት ይበልጥ ከሚታወቀው መለስ ዜናዊ እና በመንፈስ ቅዱስ ና በቆብ ወንድማቸው ውደቀት መሳደድ ላይ ተመሥርተው ወያኔንና መሀል ሰፋሪዎችን ተጠግተው ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ  ሁለቱም የአድዋ ተወላጆች በአንድ ዘመን በወር ልዮነት ከዚህ ዓለም በሞት እንዲለዩ ያደረገበትን ምክንያት ጥበቡን መመርመር እጅግ ከአቅማችን በላይ ነው።
ይህ በራሱ እጅግ በጣም አስገራሚ ተአምር መሆኑ አልተሰበከም። ወደፊት ግን ጊዜ አንስቶት እወነተኛ ሃማኖተኖች መምህራኖች  ሲነሱ ይሰበካል የሚል ግምት አለን።  ነገርን ነገር ያነሳዋል እንደሚባለው፤ በዚህ አጋጣሚ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ባለቤት እመቤት ውባንች ብሻው የታላቁ ሀገር ክፍል የጎጃም ተወላጅ እጅግ ሲበዛ አማኝ፣ጭምት፣ ጸሎተኛና ቅሩበ እግዚአብሔር መሆናቸውን የንስሐ አባታቸው የነበሩት በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ከስልሳ ዓመታት በላይ በክህነት ያገለገሉ ሊቀ ትጉሃን መመሬ ከበደ የሚባሉ እጅግ ሲበዛ ደግ የሆኑ ካህን የመንዝ ተወላጅ ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአካል አጫውተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ኬንያ ናይሮቢ እንደገቡ ሕጋዊ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መሆናቸውን ገልጸው በጠመንጃ ኃይል ከመንበረ ክብራቸው እንደ ተፈናቀሉ በወጭ ሀገር የመገናኛ ብዙኃን በወቁቱ ግልጽ አድርገዋል።
ይህ ሲሰማ በአዲሱ ተመራጭ በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ላይ ከፍተኛ የሆነ ብስጭት አስከትሎ፤ ወድያውኑ የቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ መርቆረዎስ ሦስት እራሳቸውን ሆነው የቤተ ክህነት መኪና ይዘው ከድተው ወደ ኬንያ ገብተዋል። መንግሥት እንዲህ ያለ ነገር ሲፈጸም የጠረፍ ጥበቃ አለማድረጉን ተችተው፤ ከኬንያ ውጥተው ወደ ሌላ ክፍለ ዓለም እንዳይሰደዱ ጥብቅ ክክትትል እንዲደረግባቸው የሚል ጠካራ ደብዳቤ ለወያኔው የወጭ ጉዳይ ምንግሥት መስሪያ ቤት  አስተላልፉ። መንግሥት ይህን የአቡነ ጳውሎስን መመሪያ ተቀብሎ ኬንያ ውስጥ በአቡነ መርቆሬዎስ ላይ ምን ያህል ክትትል እንዳደረገ  በማሰጃ የተደገፈ ነገር ባይታወቅም፤ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፤ ኬንያ መግለጫ ሰጥተዋል እዚያው መግለጫ በስጡበት ሀገር በጥገኝነት ይቀመጡ በሚል ምክንያት ተሸፍኖ ለደህንነታቸው ጥበቃ ለሰላምዊ አገልግሎታቸው ሲባል ወደ አሜሪካን ሀገር ስደታቸን እንዳያራዝሙ ማዕቀብ ተጥሎባቸው ብዙ ጊዜ ኬንያ ተጉላልተው ቆይተዋል።
በዚህን ግዜ ውስጥ በበርሃ ጉዛቸው ውስጥ በሹፌርነት እስከ ጠረፍ መዳረሻ ድረስ መኪና እየነዳ የረዳቸው ወጣት መሀሪ በበረሃው ጉዞ ላይ በወባ ተነድፎ ኑሮ ሀመሙ ሳይታውቅ ሥር ሰዶ ስለነበረ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየባቸው፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ይህ ሁሉ የሆነው በእኔ ሀበሳ ነው፤ ምነው እኔ ተቀምጨ እሱን አስቀደምክ በማለት መሪር ሀዘናቸውን ለፈጣሪ አሰሙ እጅግም አዘኑ።
ከጊዜ በኃላ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከአሜሪካን መንግሥት ጋር በአደረጉት ከፍተኛ መጻጻፍ፣ ድጋፎችን በማሰባሰብ፣ እንዲሁም  እነ ሊቀ ዲያቆናት ታደሰ በኃላም አባ ገብረሥላሴ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሊቀ ጳጳስ ከፍተኛ ተሳትፎ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የስድት ኑርዋቸው በአሜሪካን ሀገር ሆነ።

12ኛ/ ፓትርያርክ አይሰደድም የሚለውን የማኅበረ ቅዱሳንና የንስሐ አባቶቹ ስብከት፤

ስደት አስከፊ ነገር ነው። የክርስቲያን ተግባር ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም ቢይቻል መጋፈጥ አለዚያም አመች ቦታ ፍልጎ እራስን መሰወርና በመንፈሳዊ ኃይል በጽሎት ችግሩን ድል ማደረግ ነው። በቤተ ክርስቲያናቸን አስተምህሮ፤ በዘመነ አበው አበ ብዙኃን ፓትርያርክ አብርሃም ተስዷል፤ አንደኛ ስደት፦ እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ አባቱን እና የእናቱን ዕርስት የተውልድ ሀገሩን  ዑርን ትቶ ወደ ከንአን ተሰዷል። እግዚአብሔር ከናአንን ርዕስት አድርጎ ሰጠው። ሁለተኛ ስደት፦አብርሃም ከንአንን ድርቅ በመታት ጊዜ ወደ ግብጽ ተስዶ በዘመኑ ከነበረው ከፈሮን መንግሥት ጥገኝነት ጠይቋል፤ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከአብርሃም አይበልጡም ተሰደዋል።
ሙሴ በግብጽ ሀገር  በስደት በፈሮን የባርነት ቀንበር ውስጥ እየማቀቁ ይኖሩ ከነበሩት ከናአንናዊያን የተወልደ ነው፤ በአጭሩ ሊቀ ነበያት ሙሴ ስደተኛ ሆኖ ያደገ ነው። ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ አይበልጡም ተሰደዋል።
ንጉሥ ሄሮድስ በክርስቶስ ልደት ዘመን ተነስቶ ለመንግሥቱ ሰግቶ ለሥጋው አድልቶ ሕጻናትን በፈጀ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እናቱ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ዩሴፍን ጨምሮ ያንን ክፉ ቀን ለማሳለፉ ወደ ግብጽ ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው ጨካኙ ንጉሥ እስኪሞት ድረስ የስደት ንሯቸውን ገፍተዋል፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከነሱ እጅግ ያነሱ በመሆናቸው ተሰድዋል።
ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ባልታውቀ ምክንያት ከደርግ ከእስር ቤት አምልጠው ለመሰደድ  በራሳቸው የግል ገንዘብ ባሰሩት ጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ግቢ ውስጥ ተደብቀው ሳሉ የራሳቸው ዘመድ የሆኑ ተንኮለኞች ጠቆማ አሳያዟቸው እንጅ ከጠላት ለማምለጥ ክፉ ቀንን ለማሳለፉ ስደትን ምርጫ አድረገው ነበር። ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የበለጠ ኃይል የላቸውም።
ኮምኒዝም እራሻን ባጥለቀለቀ ጊዜ እንደ ወያኔ ያሉ ጨካኞች  ስታሊናውያን የራሻን አርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በጠላትነት ፍርጀው ፓትርያርኩ ቅዱስ ኽርቨን በመኪና እየጎተቱ የቅዱስነታቸው አካላት ተቆራርጦ እንዲሞት አድርገዋል። በዚህ ምክንያት ብዙ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ስደት አድርገው ቅዱስ ሲኖዶስ አቋቁመው በስደት ሀገር ቤተ ክርስቲያናቸውን ሲጠብቁ ምዕመናኖቻቸውን ሲያጽናኑ ሲጸልዩ ቆይተው፤ ክርስቲያኑ መሪ የአሁኑ ቭላደሜር ፑቲን የሀገሪቱ መሪ ሆነው ሲመረጡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ ወደ ሀገራቸው እራሻ በክበር እንደተመለሱ ቤተ መንግሥቱና ቤተ ክህነቱ እንደታረቁ የቅርብ ጊዜ የታሪክ ትውስታችን ነው።
ከዚህ አንጻር እጅግ በተሳሳተ በተዛባና በወረደ የአስተሳሰብ ጭቃነትና ደካማነት የታሪክ ቅሌት በተመሠረተ ጽንሰ ሐሳብ  አዕማሯቸው በጠባብ ጎሰኝነት በሰከረና በተበከለ፤ የተሟላ ወደብ ዓለምን የሚያጓጓ መልካአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ተረዳደቶና ተዛዝኖ የሚኖር የታፈረ የተከበረ ነጻ ሕዝብ ያላትን ኢትዮጵያን ለማፈርስ ፣ ከሁሉም ወገኖች ጋር ተሳስቦ ያለውን አካፍሎ የሚኖረውን አማራውን እና ከዓለም በፊት ቀድማ ድኅነት ክርስቶስን የሰበከችውን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ተቀዳሚ ጠላት አድርገው የተነሱ ጨካኝ የትግራይ ጎረምሶች ሲያዋክቧቸው የስድብ ናዳ ሲያውዱባቸው ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ሕይዎታቸውን ለማትርፍ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ መሰደድ ችግሩ ምን ላይ ነው። በዚህ በኩል ብዙ ከማለት ይልቅ ከላይ እስከ ታች የሰፈረውን በመገምገም ክተገዥነት ነጻ የሆነ በጎ ህሊና ያለው አንባቢ የአዕምሮ ዳኝነት እንዲሰጥ እድሉን እንሰጣለን።

13ኛ/ በስደት ያለው የቅዱስ ሲኖድስ መቋቋም ሕጋዊነትና አስፈላጊነት፤

ከላይ በስፋት እንደተገለጸው ቅዱስ ፓትርያርኩ መንፈሳዊ ተልዕኳቸውን ለመወጣት የአካልም የመንፈስም ብቃት ሳይጎድላቸው ከጌዜው ጋር በተጣመሩ አድመኞች እና ጠመንጃ በታጠቁ የወያኔ ኃይሎች ግፊት ተገደው መልቀቃቸውንና ለስደት መዳረጋቸው ማስታወቃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ አይወርዱም ብለው የሚቃወሙ ሊቃነ ጳጳሳት እነሱም የሚደገፍ ምዕመናን እስካሉ ድረስ  ፓትርያርኩ ቅዱስ ሲኖዶስ የማቋቋም፣ ሊቃነ ጳጳሳት የመሾም መብቱና መንፈሳዊ ክህነታዊ ሥልጣኑ የተጠበቀ ነው። ምክንያቱም ሕገ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ሀገር በአንድ ዘመን ሁለት ፓትርያርክ አይኑር፤ ከኖረም ሥልጣኑ ለመጀመሪያው ይጽና ይላልና።
ከቤተ ክርስቲያን ልዕልና በአለፈ የሀገርን ክብር የሚጥስ፣ ወደብ የሚዘጋ፣ ሕዝብን ከሕዝብ  በጎሳ ከፋፍሎ የሚያጋጭ፣ ፍርድ የሚያጓድል ፍትህ  ርዕትዕ የሚያዛባ፣ በሃይማኖት ጣልቃ የሚገባ፣ ታሪክን የሚነቅፍ፣ ሕዝብን ለስደትና ለመከራ የሚዳርግ፣ የሀገር ገንዘብ እየመዘበረ በጉቦና በሌብነት አሮንቃ እስከ አንገቱ ድረስ የተዘፈቀ እራሱን  መንግሥት ብሎ ሰይሞ ሲነሳ ይህ ሰይጣናዊ ተግርባር በመሆኑ ከንደዚህ ዓይነት መሪር አገዛዝ የሰንሰለት እስራት ተላቆ፤ ግፍና መከራ ለሚደርስበት ሕዝብ በንጹሐን ደም ለምትታጠብ ሀገር ነጻ ሆኖ መጸለይ፣ እወነቱን እወነት ሀሰቱን ሀሰት እያሉ ያለሰቀቀን የሚመሰክር ቅዱስ ሲኖድስ መመሥረቱ ወቅቱን የዋጀና እጅግም አስፈላጊ መሆኑን የታመነና አሳማኝ ሕጋዊነት ያለው ተግባር ነው።
ስለዚህ የስደት ሀገር ሲኖዶስ መቋቋም ከፍተኛውን አስተዋጽዖ ያደረጉት ታላቁ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ቀዳማዊ ሊቀ ጳጳስ ምን ያህል አርቆ አሳቢ እንደሆኑ፤ በልዩ ፍጥነት እንዴት የወያኔን አፍራሽነትና ጠባብነት እንደገመገሙትና እንደታገሉት በዚህ አጋጣሚ ደግመን ደጋግመን እንናደንቃለን።
ታላቁ ፐሮፌሰር አሥራት ወልደ ኢየሱስ ትውልድ ገዳይ በማለት የሚጠሩት ወያኔን፤  በፈጠራ ላይ በተመሠረተ ወንጀል አማራን ጠላት አድርጎ የገባ መሆኑን በመረዳት አስቀድመው መላው አማራ ድረጅት በማለት በረኽኞች በጀምላ ሊያጠፉት የተነሱበትን ሴራ አስቀድሞ በማጤን አማራ ተብሎ የሚጠራውን ሁሉ ከሃገሩ መሬት ላይ እንዳይጠፋ ለመታደግ ሕይዎታቸውን አሳልፈው እንደሰጡ ሁሉ፤ ቤተ ክርስቲያንኗን እና ምዕመናኑን ለመታደግ ስደተኛውን ለማጽናናት፣ በየቀኑ በግፍ የሚገደሉትን ዜጎች ጽሎተ ፍትሐት ለማድረግ፣ መሪር በሆነ አገዛዝ በሰንሰለት ታስረው ለሚማቅቁት ዜጎች ለመጸለይ፤ በጠቅላላው በሀገርና በወገን ላይ የሚደርሰውን በደል ለማጋለጥ ብፁዕነታቸው አቡነ መልከጼዴቅ  በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራ በስደት ያለውን ቅዱስ ሲኖድስ ለማቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸው ሐዋርያዊ ብቃታቸውን እና ጥንካሪያቸውን ያስመሠከረ ሲሆን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ዘመነ ፕትርክና ሐዋርያዊ ጉዞ ሳይቋረጥ በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ ውስጥ መከራን፣ ጽርፈትን፣ አድሎንና ስደትን  ተቋቁሞ ሰላሳ ዓመት ሙሉ የዘለቀ እረጅሙ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን የፓትርያርክነት መዋዕለ ዘመን መሆኑን የሚያስተጋባ  እና እጅን ያለመስጠት የአርበኝነት ታሪክ የደም ወርስ የሚያረጋግጥ ተግባር ነው።
ይህን ስንል በሀገር ውስጥ ላለው ቅዱስ ሲኖድስ የሐዋርያዊ  ተግባር መንፈሳዊ  የክህነት አገልግሎትን ዝቅ ለማድረግ አሳንሶ በአድሎ መድሎት ለመለካት ሳይሆን፤ ወይም ደግሞ  በሀገር ውስጥ ባለፈው ሃያ አምስት ዓመት የቤተ ክርስቲያንዋ ሐዋርያዊ ጉዞ መንፈሳዊ የክህነት አገልግሎት ተቋርጣል ብሎ ህሊና የሌለው ጭፍን ፍርድ ለመፍረድና ዋጋ ለማሳጣት አይደለም። ለቤተ ክርስቲይኗ በሁለት ሲኖዶስ እንድትከፈል ያደረገው ሀገሪቱን የከፈለው ሕዝቡን በጎሳና በቋንቋ የሸነሸነው የወያኔ መንግሥት በቀጥታ ጣልቃ ገብነትና የእሱ ተባባሪዎች አድመኞች መሀል ሰፋሪዎችና ጊዜ የሰጣቸው ሊቃነ ጳጳሳት ጭምር ቤተ ክርስቲኗን ለአደጋ እንድትጋለጥ ዋና ምክንያት መሆኑናቸውን መቶ በመቶ ከማረጋገጥ በተጨማሪ ቀኖናዊ ያልሆነ ከጋሀነብም ከገነትም ከጽድቅም ከሀጥያትም የተለየሁኝ ነኝ የሚል «ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» የሚባል በእንቅርት ላይ ጀሮ ድግፍ የጥፋት መነገድ  መፍጠራቸውን ለማስገንዘብ ጭምር ነው።

14ኛ/ ከሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶሳት አይደለንም የሚሉ መሀል ሰፋሪዎች ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን ፣

በመሠረቱ የቀኖና ቤተ ክርስቲያንን «ገለልተኛ» አድርጎ ማቋቋም በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን ከሚለው የቀደሙት ሊቃውንት የሃይማኖት አባቶች ድንጋጌ መወጣት፣  ከማኅበረ ሐዋርያት፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌ፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን የማፈንገጥ ክህደት የማይተናነስ ቤተ ክርስቲያን የመናድና ከተዋሕዶ የማስወጣት ተግባር ነው።  ተዋሕዶን በምት ሰብክ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ላይ ገለልተኛ የሚል እራስ አገዝ የግል ሱቅ በደረቴ ከፍቶ በክህነት ስም ቤተ ክርስቲያንን የማጎሳቅቆልና ተከታዮችን ማባዘን መከፋፈል ተግባር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በጉበታቸውና በዕውቀታቸው ሠርቶ መብላት ኑሮዋቸውን መግባፍት ያቅታቸው ዋልጌዎችና ሰነፎች ትምህርት በሌለው የመንደር ውሻ ባልጮከበት ክህነት ስም በግሪክ ሱቲ ተሸፍነው ቤተ ክርስቲያን በራሳቸው ፈቃድ እየከፈቱ እንደ መዥገር ተጣብቀው ደም የሚመጡበትና የሚበለጽጉበት መንገድ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድርዋል ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለውም በዚሁ መልኩ በረቀቀ ስልት ገብቶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመዘብር ጥገኛ ተውሳክ ነው።
በመህኑም ይህን የራስ አገዝ ቤተ ክርስቲይና ማቋቋም የጀመሩት ብፁዕ አቡነ ጳውሎስና ብፁዕ አቡነ ማትያስ ናቸው። ሁለቱም ከማኅበረ ሲኖድስ እርቀው ከአስር ዓመታት በላይ ሲኖሩ ማንም የማይገባባቸው እራሳቸው በራሳቸው የሚያዙበት አቢያተ ክርስቲያናት ይመሩ ነበር። ቀጥሎም አቡነ ገብርኤል ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ተጣልተው አሜሪካን በቆዩበት  ዘመን ልደታ የምትባል ቤተ ክርስቲያን በግላቸው አቋቁመው ቆይተዋል። ይህ በሊቃነ ጵጵሳቱ የተጀመረው እራስ ገዝነት ማዕረገ ሊቀ ጳጳስነት ስለያዙ  የሚጸልዩበት ቤተ መቅደስ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ነው ብለን የቅንነት ምክንያት  ሰጥተን ልናልፈው ብንችልም፣ ሥሪቱ ግን መጥፎ በመሆኑ ቀስ በቀስ ሥር እየሰደ  መጥቶ ለብለብ ያለች ክህነት እየያዙ ቆብ እየጫኑ ቀሚስ እያጠለቁ  በየምክንያቱ ወደ አሜሪካን  የሚሰደደ  አጋሜዶ ሁሉ ጥራዝ  ነጠቅ አንደበቱን በድፍረት ሞረድ እየሳለ በለቃውንቱ መድረክ ላይ ካባ ለብሶ እየተንጠለጠለ ቤተ ክርስቲያን ታልባ የማትነጥፍ ጥገት መሆንዋ በማስመሰል ብቻ  የስለት ገንዘቡን ሙጥጥ አድርገው እየበሉ ብዙዎች ሲሆኑ፤ በመጨረሻ እጅ መንሻ  እያደረጉ እስከ ሊቀ ጳጵስነት  ደረጃ የደረሱም እንዳሉ ይታውቃል። የቀድሞው አባ መላኩ የአሁነ አቡነ ፋኑኤልን በማስረጃነት ማቅረቡ ተገቢ ነው።
ከዚህም አልፎ ቀን ጎሎባቸው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጥሶ ቀኖና ፈርሶ ሕጋዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እያሉ በስደት ሀገር ቅዱስነታቸው በሚመሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ተዋቅሮ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና የሀገር አንድነትን ከማስጠበቅ ይልቅ፤ የማስመሰያ ካባና የተምጻዳቂነት የፈጠራ ፍልስፍና ተጠቅሞ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በተዋሕዶ መድረክ የማይታውቅ አባቶች ያላስተማሩት በትውፊት ያልቆየ፣ ያልተዘገበና ያልተነገረ ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያ እያሉ ያቋቁማሉ ይዘርፋሉ ያዘርፋሉ።
ሆኖም እነዚህን ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን ታቦታተ ሕግ  በዶላር ድጎማ  እየተገዙ እየባረኩ የሚለግሱ ከላይ በሰባተኛው ርዕሰ አንቀጽ ከተዘረዘሩት መካከል ከወያኔ እና ወያኔ ካነሳቸው ዘመንተኞች ጋር በማበርና በመቀናጀት ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን ከመንበረ ክብራቸው ያፈናገቀሉ የገፉ መሀል ሰፋሪ አድመኞችና ዛሬ ስለጉድ የሚሰብኩ እራሳቸው ተመጻዳቂ ጉዶች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል።
ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በወጭ ሀገር በየፍርድቤቱ በግለሰብ ደረጃ ለእኔ ይገባኛል እያሉ መጠነሰፊ ገንዘብ ለሕግ ማስፈጸሚያ እያፈሰሱ ቤተ ክርስቲያንን የሚያንገላቱ፤ ምዕመናኑን የሚያጎሳቁሉና ከእምነት ጎዳና የሚያስወጡ፤ በጎሳ የሚደራጁና ቤተ ክርስቲያንን ከመዝረፍ ሕዝቡን ከመከፋፈል በስተቀር ምክንያት የሌላቸው ወያኔ ሀገሪቱን ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያፈርስ ገለልተኛ ነን እያሉ በሚቀልዱ ለቤተ ክርስቲያንን መዳከም ይበልጥ የሚፋጥኑ የሁለት ዓለም ስደተኞች  በእምነት ስም የግል ጥቅምን የሚያሳድዱ አፍራሾች መሆናቸውን መረዳት ተገቢ ነው።

15ኛ/ የብፁዕ ወቅዲስ አቡነ ጳውሎስ ህልፈተ ሕይዎት፤ የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዝማሬ፤

ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በወያኔ ሙሉ ድጋፍ በመሀል ሰፋሪ አድመኞችም አስተዋጽዖ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን አፈናቅለው፣ በኋላም ወደ ሌላ ክፍለ ዓለም ከመሄዳቸው በፊት እስከ ኬንያ ድረስ መንግሥት ሂዶ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲውስድ ደብዳቤ በመጻፍ ሕይወታችውን ሁሉ ለማስጠፋት ደባ የፈጸሙ አባት ናቸው።
አቡነ ጳውሎስ በዘመናቸው በአዲስ አበባ ከተማና በአካባቢው እንዲሁም በሌሎችም አህጉረ ስብከት ብዙ አቢያተ ክርስቲያንት ታንጸዋል፤ የቤተ ክርስቲያኑ መንበረ ፓትርያርክ ሕንጻና የቤተ ክህነት አስተዳደር ጽፈት ቤት ደረጃውን የጠበቀ ሕንጻዎችን ተገንብተዋል፤ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መልሶ መቋቋምም የመሳሰሉት እጅግ የሚመሰገኑ የሥራ ፍሬዎች ናቸው።
ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ  ጥሩ ቅዳሴ የመቀደስ ችሎታ ያላቸው፣ አማርኛ አሳምረውና አስረግጠው በኃይለ ቃል አስደግፈው በብቃት አንዳንድ ጊዜም በአሽሙር መልክ መናገር መተንተን የሚችሉ፣ የተዋጣለት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ ያላቸው፣ ሆኖም አንድ ጊዜ ከጀመሩ መቋጫ የሌላቸውና ነገር አራዛሚ ሲሆኑ፤ በቤተ ክርስቲያንዋ መንፈሳዊ ዕውቀት የጠለቀ ትምህርት የሌላቸው እንዲያውም የቤተ ክርስቲያኒቱን ልሳን የሆነውን ግዕዝ ስለማይውቁ በየክብረ በዓሉ የሚፈሰውን የሊቃውንት ቅንያት ተርጉመው መረዳት አይችሉም እየተባሉ በሊቃውንቱ ዘንድ ይተቻሉ። መጋቤ ምስጢር ወልደሩፋኤል ለምስክርነት ቢጠሩ የጽሑፍን እውነታ ይበልጥ ያጠናክረዋል።
በዘመናቸው ከሾሟቸው ከሃምሳ በላይ የሚደርሱ ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ወደ ሰላሳ ስምንት የሚደርሱት ተሻሚዎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው። የትግራይ ተወላጆች ሆነው ሳለ አማርኛ በመናገራቸው የአማራው ተወላጆ ነን በማለት የሕይዎት ታሪካቸውን እያሠሩ በአማራ ስም ሊቀ ጳጳስ ሆነው የሚያገለግሉም ይገኙበታል። በገንዘብ አህያ ሊሸከመው የማይችል የገንዘብ ኃይል በእጅ መንሻ ማዕረገ ክህነቱን ያገኙም እንዳሉም ከላይ በስፋት ተጠቅሷል።
የወያኔ መንግሥት እንደሚያደርገው ሁሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም በቤተ ክርስቲያኗ ገንዘብ በትግራይ ክፍለ ሀገር በአክሱም የከሳቴ ብርሃን  በድግሪ ደርጃ የሚያስመርቅ  እንዲሁም በመቀሌ  በዲፕሎማ ደርጃ የሚያስመርቅ ሁለት መንፈሳዊ ኮሌጆችን አስገንብተዋል። በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ማብቂያ ላይ ለጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች በሚል ስም ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የተሰብሰበ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብና ሁለተኛ ተለባሽ ከምዕመናን የተሰብሰብ ከሥር ሺህ የሚጠጋ ነብሰ ወከፍ ልብስ ለትግራይ ገበሬዎች እንዲከፋፈል አድርገዋል።
በሌላ በኩል በዝመናቸው ሰባት ሚሊዮን የቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮች የት እንደደረሰ መረጃ የለም። ለዚህ እሳቸውም በሳቸው የሚመራው ቅዱስ ሲኖድስም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን አንገቴን እሰጣለሁ የሚለው ነጋድራስ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ሸክም  የሰጠው ማብራሪያ አይታወቅም። ሆኖም  መረጃው የተሟላና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም የወያኔ መንግሥት እስታስቲክስ መስሪያ ቤት ከሁለት ሚሊዮን ተኩል በላይ በአማራው ክክል የሚገኙ ዜጎች መጥፍታቸውን ጠቁሟል። ሌሎች የመረጃ ምንጮች እንደ ዘገቡት  እስከ አምስት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱት መንግሥት ባሰማራቸው ካድሬዎች በየጊዜው በልዮ ልዩ ምክንያቶችና ዘዴ ሆን ተብሎ ደብዛቸው የጠፋው በአብዛኛው የቤተ ክርስቲይኗ ተከታዮች መሆናቸውን በአጽንዖት ሲጠቁሙ፤ ቤተ ክርስቲያኗ ቀድሞ ከነበራት ሃማሳ ሚሊዮን ተከታይ አባላት ሰባት ሚሊዮን የሚደርስ የምዕመናን ቁጥር ቀንሶ እንደተገኘ ተረጋግጧል።
አቡነ ጳውሎስ በአዲስ አበባ በደብረ ሰላም ቅዱስ  እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ታቦት በቆመበት እርሳቸው ባሉበት ባህታዊ ፈቃደ ሥልሴ በአጃቢዎቻቸው ተገድልዋል በመባል በሰፊው ይተቻሉ። በታላላቅ አድባራት ብዙም መንፈሳዊ ዕውቀት ያላካበቱ የትግራይ መነኮሳትን እየጠሩ በመሾም ገንዘብ ያስመዘብራሉ በመባል ይታማሉ። እንዲሁ በምንቸገረኝ በቀጥታ ከዲቁና ወደ ቅስና የገቡትም በደጋፊነት ስም ብቻ አለቃ በማድረግ አቢያተ ክርስቲይናቱን እንዳስበዘብዙ እሮሮ ይሰማል።
በሥልጣን በመታበይ በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እጅግ በጣም ከልክ ባለፈ በመዝመንመን እንዲያውም ጽድቅ በምድር ላይ ተደስቶ መኖር ነው ብለው የሚያምኑ እኪአስመስላቸው ድረስ፤ የወጪ ሀገር ገንዘቦችን በከፍተኛ አኅዝ ከማካበት በላይ፤ በእጃቸው የሚይዟቸው በንጹሕ የወርቅ ክምር የተቀረጹ መስቀላት፣ በየጊዜው የሚቀያይሯቸው ውድ የነጭ ሐር አልባሳት፣ በወርቅ የተጠለፉ ልብሰ ተክህኖዎች፣ በየዓመቱ ለበዓለ ሲመታቸው ክብር የሚፈሰው ቢራና ውስኪ፣ የሚቆረጠው ጮማ፣ የሚቆረሰው ኬክ፣ እይታሸገ  የእንግዳ መቀበያ እየተባለ የሚሰጠው ገንዘብ በቅርብ ለተመለከተ ሰው እኒህ አባት ምን ያህል ጨካኝ ቢሆኑ ነው በልመና በእንባ  በስለትና በጸሎተ ፍትሐት በሙዳዮ ምጽዋት በተሰብሰበ የቤተ ክርስቲያን  ገንዘብ እንደዚህ የሚንደላቀቁ በሚል ምድራዊ ድሎትን በከፍተኛ ድረጃ ማፍቀራቸው ከቤተ ክርስቲያንዋ ሐዋርያዊ ተልዕኮ፤  በባዶ እግራቸው ወጥተው ወርደው ቤተ ክርስቲያንዋን ካቀኑ ደጋግ አበው ድካምን የዘነጋ እና የማይዛመድ ለሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳት የድሎት ሕይዎትንና ንዋይን በእጅጉ የማፍቀር አርአያ የሆኑ መንፈሳዊ የአባትነት ድርሻቸውን አወዛጋቢና ለከፍተኛ ትችት የተጋለጠ እንደሆነ በብዙ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል።
ቤተሰቦቻቸውን በሙሉ ድርጅት በመክፈት፣ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ በእያንዳንዱ የቤተ ክርህነቱ መሥሪያ ቤት በመሰግሰግ ከነበረባቸው ድህነት አላቀዋቸዋል። ሁሉም የሥጋ ዘመድ ቤተ ሰቦቻቸው በትግራይም ሆነ በአዲስ አበባ እጅግ በተደንደላቀቀ ኑሮ ደርጃ አስተማማኝ በሆነ የደወዝ ሥራ ቅጥር ውስጥ ይገኛሉ።
የወያኔ ካድሬዎችን በመጥራት ተቃዋሚ ሊቃነ ጳጳሳትን ማረፍያ ቤታቸውን በማሰበር አስደብድበዋል። አባ ኃይለ ኢየሱስ በኋላም በተንኮል አቡነ መልከጼዴቅ የተባሉና በወያኔ ታፍነው ተወስደው በደረሰባቸው ከፍተኛ እንግልትና ድብደባ፤ ቁስሉ ወደ ካንሰር ተቀይሮ ለሕይዎታቸው ህልፈት ምክንያት እንደሆነ የመጨረሻ የኑዛዜ ቃል የተቀበሉ አባቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
እንደዚሁም እጅግ በበረታ ሁኔታ የተቃውሟቸውን ሊቃነ ጳጳሳትን በተለይም የብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን  ስም የሚያጠፋ መጽሐፍ በማጻፍ፤ ለጽሐፊው ደመወዝ ቀጥረው በቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ ቤት ሰጥተው እያኖሩ ማታ ማታ «እንዲህ ብለህ ጻፍ» እያሉ እያዘዙ ከአንድ መንፈሳዊ አባት የማይጠበቅ ከፍተኛ የስም ማጥፋት መጽሐፍ አጽፈው እራሳቸው በቢሯቸው ውስጥ ሲያሰራጩ አይተው የታዘቡ ሰዎች በሐዘኔታ ያስታውሱታል። በጠቅላላው በተቃወማቸው ሰው ላይ ያላቸው በቀልና ጭካኔ ከቶ ወደር የለውም እየትባሉ በብርቱ ይወቀሳሉ።
ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው ድርጅትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከመንግሥት ጋር  ባላቸው ቀረቤታ  አንጻር በመነጋገር ቤተ ክርስቲያንን ተጠግቶ በስሟ ያካበተውን መጠነ ሰፊ በሚሊዩኖች የሚቆጠር ንብረትና ገንዘብ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ካዝና አስገባ የሚል ትእዛዝ እንዳይመጣበት በመሥጋት ያቀርብ የነበረው ከፍተኛ ገጸ በረከትና እጅ መንሻ መጠነ ሰፊ ነበር እንዲሁም ለመልአእክት ከሚሰጠው ምስጋና ባልተናነሰ ያደርግ የነበረው ክብር  እና አጀብ ቀላል ግምት የሚሰጠው አልነበረም።ይህም በቤተ ክርስቲያን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ በረቀቀ ስልት ገንዘብ እንዲሰበስብ  የካህናትን መቁንን እንዲጋራ አረንጓዴ መብራት ሆኖለት ቆይቷል።
በዕለተ ሞታቸው ቀን ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሚባሉ ሊቅ ሞት ትልቅ መጽሐፍ ነው የሚያነበው ሰው ግን የለም ብለው እንዳስተማሩ፤ ሞት በድሎትና በገንዘብ ብዛት ተታሎ ስለማይቀር ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በከፍተኛ ደረጃ ያከማቹትን ገንዘብና ንብረት በአግባቡ ሳይሰብሰቡት ለቤተ ክርስቲያንም ሳይመልሱት በልተውም አብልተውም ሳይጨርሱት፤ በመልስ ዘናዊ ተከሻ በማሀል ሰፋሪዎች አመጽ እና ዘመን በቀናቸው ሰዎች ድጋፍ የመንፈስ ቅዱስ ወንድማቸውን አፈናቅለውና አሳደው አወዛጋቢ በሆነ መንገድ ከተሾሙበት እጅግም ከሚያፈቅሩት የኢትዮጵያ አርቶድክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክነት ከንዘብ ሊያድነው ሥልጣን ሊመክተው በማይችል እጅግ ከባድ በሆነ ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ እግዚአብሔር ነብሳቸውን በገነት ያሳርፍልን።
ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበረ ክብራቸው ተግፍተው በተለይም አሜሪካን ከገቡ በኋላ ከሰው ጋር የሚገናኙበት ጊዜ እጅግ የተወሰነ፣ የሚመገቡትም እጅግ የተመጠነ ትዕርምቱንና ጸሎቱ ላይ እጅግ ትኩረት አድርገው ነበር;፡ ሰው ለማነጋገር እንኳን ጊዜ ጠብቆ ካልሆነ በስተቀር እጅግ ብትህውናው ተጭኗቸው ነበር። ሆኖም ሰው መሆን አለና  መለስ ዜናዊን ተከትሎ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ዜና ዕረፍት ሲሰሙ« ገንዘብም ፣ ሥልጣንም ጠፊ ነው፣ ሰውም ንብረቱም ኃላፊ ነው ዓለምም እንደዚሁ ከንቱ ጠፊ ነው በሚል በሀዘን የተሞላ፣ በሊቅነት ዜማ የተራቀቀ በመንፈሳዊነት ክብር የትዋበና መንፈስን የሚነካ መዝሙር አሰሙ።
ሰዎች ስለምን አቡነ መርቆሬዎስ የማይናገሩት? እያሉ ይጠይቃል፤ ነገር ግን ይህ መንፈሳዊ መዝሙር በሊቃውንት አንደበት በአንድምታ ትርጉም ቢተነተን ምስጢሩ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ባህር ነው። የሚያስተላልፈውም መልዕክት ከባድ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን የሊቃውንት ትምህርት ቤት ያደጉ ሊቃውንት ብዙ የመናገር ሳይሆ ብዙ የማዜምና ብዙን በአጭሩ ቃላት የመግለጽ ባህሪ አብሯቸው በማደጉ ነው።
ይህ መዝሙር የሚያስተላልፈው መልዕክት  በጥቅሎ ለዚህ ለሚያልፈው ገንዘብ ሥልጣን ድንገት እንደጠዋት ጤዛ ለሚጠፋው የሰው ሕይዎትና ጊዝያዊ ዓለም እኔን አሳደዳችሁኝ፤ ሌሎችንም አሳደዳችሁ አፈናቀላችሁ ገደላችሁ አስገደላቸሁ ከፈላችሁን ከፋፈላችሁን፤ እናንተ የያዛችሁት ሥልጣን ያላችሁ ገንዘብ እናንተም እራሳችሁ ያላችሁበትን ተድላና ዓለማዊ ደስታ ጥላችሁ ማለፋችሁን አልተረዳችሁም አላውቃችሁም ዘንግታችሁ ነበርና ለማለት ነው።

16ኛ/ የብፁዕ አቡነ ናትናኤል አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆኖ መመረጥ፤ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ስልክ መደወል፤

የቀድሞ ስማቸው መምህር አባ መዓዛ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በቅድስት ሥላሴ ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ  ጋር  በምክትል ሊቀ ሥልጣናትነት አባቴ መዓዛ  እየተባሉ በተወዳጅነት በአንደበተ ርዕቱ ሰባኪነት ያገለገሉ፤ የአርሲ ሀገረስብከታቸው በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እንደተሰጣቸው ሳይነሳ ተወደው እስከ እስከ ወሪደ መቃብር ድረስ የቆዩበት በመሆናቸው ቅዱስነታቸውን አዘውትረው ከማስታውስ በተጨማሪ፤ ያላቸው አመለካከት ሚዛናዊ ነበር። ከብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ  እረፍት በኋላ ከውጪው ሲኖድስ ጋር በተደረገው የርቅ ውይይት ጋር በተያያዘ፤ ለቅዱስነታቸው አቡነ መርቆሬዎስ ስልክ ደውለው፤ «ቅዱስ አባታችን በቃ ተለያይተን ቀርን» በማለት መንፈሳዊ ስሜታቸውን እንደገለጹ ውስጥ አዋቂ ሰዎች ካፍለውናል።
የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ ሀገር የመመልስ ጉዳይ በቅንነት የተመለከቱት ቢሆንም፤ በመሀል ሰፋሪ አድመኞች፣ በወያኔ ካድሬዎች፣ የነጋድራስ ማኅበረ ቅዱሳን ጣልቃ ገብነት የነገር ሽረባ በውስጥም በውጭም ባለው የፓለቲካ ውሽንፍር ከአረጋዊነት እድሜያቸው ጋር ተብትቦ ስለያዛቸው ውስጣዊ ፍላጎታቸውን በውሳኔ ክመስጠት ይልቅ በተጽኖ፤ ለስደስተኛ ጊዜ በተጽኖ የፓትርያርክ ምርጫውን ማስፈጸም ግዴታ ሆነባቸው ብዙም ሳይቆዩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ ብፁዕ አባታችንን በገነት ያሳርፋቸው።

17ኛ/ የፕረዘዳንት ግርማ ወልደ ገዎርጊስ ደብዳቤ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ፣

የፐረዘዳንት ግርማ ወልደ ጊዎርጊስ ደብዳቤ ለቅዱስነታቸው፤ እርሱ መድኅኒዓለም ክብሩ ከፍፍ ይበል የቅዱሳኑ አማላጅነት ከሁሉ በላይ ይብለጥ እንጅ፤  ለኢየሱስ እርስቶስ፣ እናቱ ቅድስት ድንግርል ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ  ቅዱስ ገብኤል ያስተላልፈውን መልክት ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። መልአኩ ገብርኤል ለቅዱስ ዮሴፍ እንዲህ አለው «ዮሴፍ ሆይ ልጁንና እናቱን ሊገድል የሚፈልገው ንጉሥ ሄሮድስ ሞትዋልና  እናቱንና ልጁን ይዘህ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለስ የሚለው በየዕለቱ የሚጸለይ በመሆኑ ይህን የሚዘነጋ ማንም የለም።
ፕረዘዳንት ግርማ ወልደ ጊዎርጊስም ደብዳቤ ትክክለኛ ትርጉም በጥላቻና በክፋት የተነሱበዎት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋልና ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሆይ አራተኝው ሕጋዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በመሆነዎ አብረዎት የተሰደዱትን ሊቃነ ጳጳሳት አስከትለው ወደ ሀገርዎ ኢትዮጵያ ይግቡ ይመለሱ የሚል ነው።
ጎሰኛው ወያኔ ሙሉ ለሙሉ ከሚቆጣጠረው መንግሥት፣ ከጫካ ጀምሮ በአምራነታቸው በሚጠላቸው በግፍ ካሳደዳቸው  ላፈናቀላቸው የወያን ወጥመድ አልፎ ይህ ደብዳቤ ለብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ይደርሳል ብሎ ማሰብ ከአንበሳ ጉረሮ ያመለጠውን ዳንኤልን፣ በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ያደረውን የዮናስን ያክል ተአምር ነው።
የፕረዘዳንት ግርማ ወልደጊዎርጊስ ጥሪ መሠረት  ወያኔ ትግስት ኑሮት ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ  ወደ ሀገር ቤት የመግባት እድል ቢኖራቸው ኖሮ፤ የፕረዘዳንቱ አስተሳሰብ የሰፋና በፓለቲካው መድረክ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሊያመጣ በዲያስፓራው የፓለቲካ ውሽንፍር ላይ ጫና ሊያሳድር ከመቻሉም በላይ ወያኔም አለዝቦ ስልጣኑን ለማቆየት አስትዋጽዖ ያደርግለት ነበር ይገመታል ። ግን ሥልጣን በማይጠቅመው፣ዘረፋ በማይሰለቸው ከአፍንጫና በክነፈር መካከል ካለችው ክፍተት ባነሰ የጠበበ ከሚያስበው ወያኔ ይህን መጠበቅ አይቻልም፤ ከዝንብ ማር እንደመጠበቅ ይቆጠራል።
የሚገርመውና የሚደንቀው ይህን ደብዳቤ መሠረት አድርገው ገና ለገና ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ በሚል በእጃ አዙር የመሀል ሰፋይ ንስሐ ልጆች የሆነው ገለለተኛውና ማኅበረ ቅዱሳን ሳይቀር፤ ቅዱስ አባታችን አያሳፍሩንም እንዴት በወያኔ ተታለው ይገባሉ እያሉ በየሚዲያው ያስተጋቡት የነበረውን በቅርብ እንታዘብ ነበር።
በሌላ አቅጣጫ በወቅቱ አቃቢ መንበር የሆኑት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ለቅዱስ ፓትርያርኩ ያላቸው ቀና አመለካከት በጥሩ ሚዛን ላይ የሚገኝ መሆኑን ያጠኑት መሐል ሰፋሪዎች እንዲሁም የትግራይ ተወላጆች አንዳንድ ጳጳሳትና መስሎ አዳሪዎች በተለይም የነጋድራስ ማኅበረ ቅዱሳን ጮሌዎች አራጋቢነት፤ እንዴት መንግሥት በሃይማኖት ሃይማኖት በመንግስት ጣልቃ አይገባም እየተባለ ፕረዘዳንቱ በሲኖዶስ ሥልጣን ጣልቃ ይገባሉ። ተድፍረናል በማለት አረጋዊዩን አባት ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ማዋከብና አምስት ብለን እንደገና አራት አንልም የሚል እጅግ መናኛ የሆነ ሕጻናት የማያስቡት የቁጥር ስሌት ውስጥ የገቡ ለቤተ ክርስቲያና አንድነትና ለመንጋው ያልተጨነቁ ነገር ግን የቁጥር መወጣትና መወረድ ያሳሰባቸው አስመሳይ ጳጳሳት ጭምር ነገሩን ያጣምሙት ጀመር።
ከዚያም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ለፕረዘዳንት ግርማ ወልደጊዎርጊስ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ጥሰው በሲኖዶስ ስልጣንና ተግባር ጣልቃ ገብተዋል በማለት እንዲቆጡ አደረጓቸው። ይህ ብቻ ሳይሆ የወያኔ ካደሬ በሙሉ በፕረዘዳንቱ ላይ ማንዣበብ ጀመረ።  ግርማ ወልደጊዎርጊስም ደነገጡ ተሳስቻለሁ፤ ያሳሳቱኝ፤ መከረኛ ጎንደሬ እነ ኢንጅነር አራጋው ጥሩነህ ናቸው ብለው የጻፉትን  ደብዳቤውን አንስቻለሁ ብለው ቃላቸውን አጠፉ፤ አይፈርድባቸውም። ደብዳቤያቸው ግን ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል።
በነገራችን ላይ ኢንጅነር አራጋው ጥሩነህ ከካንናዳ መንግሥት ዕርዳታ ጠይቀው የለገዳዲን ውሃን አስገድበው የአዲስ አበባ ከትማን የወሃ አቅርቦት እጥረት ያቃለሉና በካናዳ መንግሥት የተሸለሙ ሀገራቸውን በከፍተኛ የሲቪል አገልግሎት በብቃት ያገለገሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሲሆኑ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በድንገት በሞት ተለይተዋል፤ የአገልጋያችን ነፍሳቸውን ይማር።

18ኛ/ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስን ላይ አድማ ያስነሱ የገፍና ያፈናቀሉ አባቶችና ባልጊዜዎች የመጨረሻ እጣ ፋንታ፤

መቸም ሰው ይሙት አይባልም። በሞትም መሳለቅ አይገባም። ሞት ሁላችንም ተራ ጠብቆ ይጠራል፤ ያን ጊዜ ከሞት ጥሪ ከቶ የሚያመልጥ ማንም የለም። ነገር ግን ሰው ከመሆን አንጻር ከጠላትና ከክፉ አድራጊ ከጨካኝና ከአድመኞች በፊት ለመሞት ማንም አይፈቅድም። ይከውም በሰው ኃይልና ጉልበት የሚሆን ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ሆኖም አባቶቻችን ከጠላቴ በፊት አትግደለኝ እያሉ ይጸልያሉ።
የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ሞት የተመኙ ወያኔዎች፣ መሀል ሰፋሮዎች ማኅበረ ቅዱሳን፣ የወያኔ ጀሮ ጠቢ ካድሬዎች እጅግ ብዙ ናቸው። ሆኖም «የጻድቅ ሰው ጸሎቱ የበረታ ኃይል አላትና»፤ ቅዱስነታቸው ከመንበረ ክብራቸው የገፉ ያደሙ ያሳደሙ አፈናቅለው የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትና የዘመኑ ቱባ ባለሥልጣናትን የመጨረሻ እጣ ፋንታ እንመለክታለን፤ በአንጻሩም ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የስደት ዘመናቸውን ባርኮ የፓትርያርክ ሐዋርያዊ ተጋብራቸው ሳይቋረጥ፤ይህን ታአምር ለምን ሊያሳያቸው ንደፈገ መጨረሻውን መከታተል መልካም ነው፤ ለማኝናውም ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ስሞች እና የመቸረሻ እጣ ፋንታቸውን ይመልከቱ።

1ኛ/ ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ምንስትር የነበር፤ ለወያኔ አሥራ ስድስት ዓመት ታግሎ ከወያኔ ጋር ተጣልቶ አሥራ ስድስት ዓመት የታሠረና ከሥልጣን የተሰናበተ በቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና ውስጥ ጣልቃ መግባቱን አምኖ ለቅዱስ ፓትርያርኩ መሰደድ ለቤተ ክርስቲያን ከሁለት መከፈል እጁ እንዳለበት ወኪ ሊንክ በሚባለው ታማኝ የዓለም መረጃ መዝገብ ያሰፈረው ቃል፤  አሳዳጁ ተሰዳጅ ሆኖ አሁን በስደት አሜሪካን ሀገር የሚኖር፤
2ኛ/ መምህር ሀብተማርያም ተድላ በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆርረዎስ ላይ በግፍ አድማ አድርገው ካፈናቀሉት መካከል ዋናውና ቀንደኛው ሲሆኑ በኃላ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ተጣልተው ያለደመወዝ ከመንገላታታቸውም በተጨማሪ ልጃቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተልይቶ አቡነ ጳውሎስን ተቃውመዋል ተብሎ በየተኛው አድባራት የቀብር ቦታ እንዳያገኝ ተደርጎ በራሳቸው ሀገር ዜግነታቸው ተገፎ የልጃቸውን ሬሳ ይዘው  የሚቀብሩበት አጥተው ሙሉ ቀን መንከራተታቸው በስፈሩት ቁና መሰፈር፤
3ኛ/ ክንፈ ገብረመድኅን የወያኔ የሀገር ውስጥ ጽጥታና የደህንነት ኃላፊ የነበረ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ስልክ እየደወለ ሲያዋክብ የነበረ በኋላ በእነ መለስ ዜናዊ የተቀነባበረ ስልት የተገደለ፤
4ኛ/ ሀያሎም አርአያ የወያኔ የመከላከያ ጀነራል የነበረ፤ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ስልክ እየደውለ ሲያስፈራራና ሲያሳቅቅ የነበረ በኋላ በሻቢያና በመለስ ዘናዊ የተቀነባበረ ስልት የተገደለ፤
5ኛ/ ብፁዕ አቡነ መቃሬዎስ ድሮም ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን፤ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ በዘመንተኛ ትግሬነታቸው ተመክተው በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ላይ አድማ የቀሰቀሱ የመሩ ያፈናቀሉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ፤
6ኛ/ ብፅዕ አቡነ ማቴዎስ የማሀል ሰፋሪው ቁንጮ ድሮም ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን እርምጃ ይወሰድባቸው ብለው የፈርሙ፤ በብፁዕ ውቅዱስ ስቡነ መርቆረዎስ ላይ በግቢ ገብርኤልና በበዓታ ለማርያም ገዳማት የሚገኙ ካህናትን ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጡ ያሳድሙ የነበሩ ለፓትርያርክ ስልጣን እንደጎመጁ ግን ሳያገኙጥ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ፤
7ኛ/ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆርሬዎስ ላይ አድማ ያደረጉ አቃቤ መንበር ሆነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አወዛጋቢ በሆነ መንገድ ያስመረጡ ወደ ሀገራቸው ኤርትራ ሁደው ብዙም ሳይቆዩ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ፤
8ኛ/ መለሰ ዘናዊ ጠቅላይ ሚኒስተር ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መንበራቸውን ለቀው ከቤተ ክህነቱ ግቢ እንዲወጡ መመሪያ እየሰጠ ሲያዋክብ የነብረ በከፍተኛ ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ፤
9ኛ/ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፤ ዘመኑን ተመክተው የቆብ ወንድማቸውን የሃማኖት አባታቸውን ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በግፍ አፈናቅለው አወዛጋቢ በሆነ መንገድ ፓትርያርክ የሆኑ በከፍተኛ ህመም ተይዘው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ፤
10ኛ/ብፁዕ አቡነ ሰላማ በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ላይ የአድማ ከዳሚ መሀል ሰፋሪ የነብሩ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ፤
11ኛ/ አባ ኃይለ ኢሱስ በኋላ አቡነ መልከጼዴቅ፤ ፓትርያርኩን ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስን ለማውገዝ ወደ ላይ የተንጠራሩ፤ በኋላም አቡነ ጳውሎስን ይቃውማሉ በሚል በወያኔ ታፍነው ተወስደው ተደብድበው በመጨረሻም ለከፍተኛ ህመም ተዳርገው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ፤
12ኛ/ መምሬ ፍስሐ ተበጀ/መምሬ ወርቁ/ የመሀል ሰፋሪው ክፍል በብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ላይ የሀሰት ክርስ ለወያኔ ያቀረበ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ያለጡረታ የተሰናበተ፤
እግዲህ የብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መሮሬዎስ ከልደት ጀምሮ እስክ ፓትርያርክ እስከ መመረጥ ድረስ ለኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰጡት አገልግሎት የደርሰባቸው መገፋት መፈናቀል መከራና እንግልት እንዲሁም ተአምራት ሁሉ እወነተኛው ታሪክ ከዚህ በላይ በአጭር በአጭሩ ለአንባቢ ምቹ በሆነ መልኩ ቀቧል። እውነቱን ለመረዳት ቅን ልቦና አስተዋይ ሕሊና ይጠይቃል።  እግዚአብሔር ቅን ልቦን ለሁላችንም ያድለን፤ በሰው ላይ ክፉ ከማድረግ ይሰውረን አሜን። ታሪክ ሁሉንም እየተከተለ ይዘግባል። እውነትን ማንም ደብቆ አያስቀራትም። እወነቱን እወነት ሐሰቱን ሃሰት ብሎ መመስከር የሃማኖት ግዴታ ነው። ከዚያ የወጣ ግን የሰይጣንና የመልክተኞቹ መሆኑን በቅድሱ መጽሐፍ ተዘግቧል፤ በሊቃውንት አንደበት ተሰብኳል።  ሁላችንም የእውነት ሰዎች ያደርገን፤ የአባቶቻችን በከት ይድረሰን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

አሜን ወአሜን!