06 Sep, 2017

ውድነህ ዘነበ

የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከዓመት ከመንፈቅ በኋላ ወደ ሁለት አኃዝ ተሸጋገረ፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ ባወጣው የነሐሴ ወር መረጃ፣ የዋጋ ግሽበቱ 10.4 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት አብዛኛዎቹ ወራት በነጠላ አኃዝ የተጠናቀቁበት እንደ ነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከጥር 2008 .. እስከ መጋቢት 2009 .. ባለው ጊዜ ግን የዋጋ ግሽበቱ በአብዛኛው መካከለኛ በሚባል የነጠላ አኃዝ ደረጃ የቆየ መሆኑም የሚታወስ ነው፡፡ በጥር ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 10.2 በመቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከመጋቢት 2009 .. ወደዚህ ግን የግሽበት ምጣኔው ድጋሚ ማንሰራራት ጀምሮ በመጋቢት፣ በሚያዝያ፣ በግንቦትና በሰኔ 8.58.68.7 እና 8.8 በመቶ በቅደም ተከተል ሆኖ በዝግታ እየጨመረ መቆየቱን የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል፡፡

ባለፈው ወር ማለትም በሐምሌ 2009 .. ባለፈው ዓመት ጋር ያለውን የንፅፅር የዋጋ ግሽበትን የሚለካው (Headline Inflation Rate) በአንዴ 9.4 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ድንገተኛ ማሻቀብ በመቀጠል የነሐሴ ወር ደግሞ የሁለት አኃዝ ድንበሩን መሻገር ችሏል፡፡ ነገር ግን ጥር 2008 .. ባለሁለት አኃዝ የዋጋ ግሽበት ተመዝግቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ለተከሰተው የዋጋ ንረት መንስዔው ምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ እንደሆነ ኤጀንሲው ይፋ አድርጓል፡፡

ማክሰኞ ዕለት በተጠናቀቀው ነሐሴ ወር የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት 13.3 በመቶ ተመዝግቧል፡፡ ይህም ከሐምሌ ወር ጋር (12.5 በመቶ) ሲነፃፀር በ0.8 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

በምግብ ዋጋ ላይ የታየው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ባለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱን የመታትን የድርቅ አደጋ አመላካች ለመሆኑ የሚከራከሩ እንዳሉ ሁሉ፣ በአንፃሩ ድርቁ አምራች አካባቢዎችን ባለማጥቃቱ ከዚያ ጋር አይያያዝም የሚሉም አሉ፡፡

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ 7.1 በመቶ የዋጋ ግሽበት የተከሰተ ሲሆን፣ ይኼም ከሐምሌ ወር ጋር ሲነፃፀር (5.9 በመቶ) 1.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የዋጋ ግሽበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ከተፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡ በተለይ ከሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የዋጋ ግሽበትን ሊፈትናት ችሏል፡፡ በወቅቱ የነበሩት ትንታኔዎች ተፈጥሮአዊ የሆነው የፍላጎትና የአቅርቦት መዛነፍ የሚያስከትለው የዋጋ ግሽበት ባሻገር፣ የኢኮኖሚው የገንዘብ አቅርቦት መጠንም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደነበረው ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የበጀት ጉድለት አሸፋፈን በዋናነት የሚጠቀስ ጉዳይ ነበር፡፡ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገለጻ ከሆነ፣ የበጀት ጉድለት ከብሔራዊ ባንክ በሚወሰድ ቀጥተኛ ብድር ሲሸፈን ማለትም በተለምዶው ‹‹ገንዘብ ማተም›› የሚሉት ዓይነት አሸፋፈን በእጅጉ የዋጋ ግሽበትን የማባባስ ዕድል አለው፡፡

መንግሥት የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ግሽበት በሚያስከትል ደረጃ ያለመሆኑን በመግለጽ የሚከራከር ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱ ደግሞ የበጀት ጉድለት ቢያንስ ከአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት (GDP) ከሦስት በመቶ ያልበለጠ መሆን እንዳበት ይመክራል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በቁጥጥር ሥር የዋለው የዋጋ ግሽበት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው የሞኒተሪ ፖሊሲ ውጤቶች ለመሆናቸው፣ መንግሥት ብቻ ሳይሆን እንደ አይኤምኤፍ ዓይነት ተቋማት ይመሰክራሉ፡፡

በተለይ የገንዘብ ተቋማቱን ምክር ተከትሎ ባንኩ ‹‹ቤዝ መኒ› ወይም ‹ሪዘርቨ መኒ› የተሰኘውን የገንዘብ አቅርቦት መለኪያ የሞኒተሪ ፖሊሲው ልጓም አድርጎ መጠቀም ከጀመረ በኋላ፣ ግሽበቱን መቆጣጠር መቻሉን የገንዘብ ተቋማት በዝርዝር ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡   

anon

ሪፖርተር