Wednesday, 06 September 2017 13:43

ጸጋው መላኩ

  በያዝነው 2009 .ም እና ከዚያ በፊት የነበሩ በርካታ የኢኮኖሚ ፈተናዎች በቀጣዩ አዲስ ዓመት 2010ም ጭምር የሚቀጥሉ ይመስላል። ባለፉት ዓመታት ከነበሩት በርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት የመሰረታዊ ፍጆታዎች አቅርቦት መፍትሄ አለማግኘት፣ ድርቅና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዋነኝነት ሊታዩ የሚችሉ ናቸው። 

መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች

መንግስት እጥረት የሚታይባቸውን እንደ ስኳርና ዘይትና ዱቄት የመሳሰሉት መሰረታዊ ሸቀጦች በራሱ በመንግስት አቅራቢነት በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል እንዲቀርቡ ማድረግ ከጀመረ ከአምስት ያላነሱ ዓመታት አልፈዋል።

በእርግጥ ከዘይትና የስንዴ ዱቄት ምርት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የሸቀጥ መደብሮች ያሉ ቢሆንም የስኳር ጉዳይ ግን አሁንም በመንግስት ጥብቅ የቁጥጥር ስርዓት ውስጥ ያለ ነው። በእርግጥ ነው የመጀመሪያው አምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲቀረፅ የስኳሩ ዘርፍ ፕሮጀክቶች በእቅዱ አጋማሽ ተጠናቀው የሀገር ውስጥ ፍጆታን ሙሉ በሙሉ ከመሸፈን ባለፈ በኤክስፖርት ግብይት በሚያስገኙት ገቢ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ ይደግፋሉ የሚል ሀሳብ ነበር። ሆኖም አሁን ባለንበት የሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን አጋማሽ ወይንም ከመጀመሪያው እቅድ ሰባት ዓመታት በኋላ ሀገሪቱ ስኳርን ኤክስፖርት ማድረግ ይቅርና ከውጪ በማስገባት ላይ ትገኛለች። ዛሬም ድረስ ዜጎች የስኳር ፍጆታቸውን የሚያገኙት በኮታ ነው። ይህ አሁን ልንሰናበተው ቀናት በቀሩት 2009ኝም ጭምር እየታየ ያለ በመሆኑ በመጪው 2010ም የሚቀጥል መሆኑ ጥርጥር የለውም። ከዓመታት በፊት በሀገሪቱ የተለያየ አቅጣጫ የተጀመሩት የስኳር ፕሮጀክቶች ዛሬም ተጠናቀው የስኳር የኮታ እደላን መታደግ አልቻሉም።

 የድርቅ ፈተና እና መጪው ዓመት

 ድርቅ የኢትዮጵያ ፈተና መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆረዋል። የክረምቱ የዝናብ ስርጭት ሁኔታ የተሻለ መሆኑ ቢነገርም አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ዘጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የቅርብ መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቱ ከገጠማት የድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ልዩ ልዩ ድጋፎችን ሲያገኝ ቢቆይም፤ የተገኘው ድጋፍ ግን ከችግሩ ስፋት አንፃር ሲታይ በቂ ሊባል የሚችል አልነበረም።

 ይህም በመሆኑ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት መንግስት እስከ 7 መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ተገዷል። ይህም በልማት ፕሮጀክቶች ላይ፤ እንደዚሁም በአጠቃላይ አኮኖሚው ላይ የፈጠረው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኢትዮጵያ በድርቅ በምትጠቃባቸው ጊዜያት ሁሉ ለድርቅ ተጠቂዎች ከፍተኛ እርዳታ በማቅረብ የምትታወቀው አሜሪካ ቀደም ሲል የነበራትን ቁርጠኝነት ማሳየት አልቻለችም።

 ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ሀገሪቱ ቀላል የማይባል የእርዳታና የእገዛ ገንዘብን ለመቀነስ እንቅሳቀሴ ከጀመረች ዋል አደር ብላለች። ኢትዮጵያ “ፊድ ዘ ፊውቸር” ተብሎ በሚጠራው የአሜሪካ የእርዳታ ፕሮግራም ታቅፋ ሰፊ ድጋፍ ስታገኝ ብትቆይም የትራምፕ አስተዳደር ለዚህ ፕሮግራም ይመደብ የነበረውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር በጀት በግማሽ እንዲወርድ ያደረገው መሆኑን የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያመለክታል። ኢትዮጵያ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የነበራት የ78 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታ ፈንድ ድርሻም የዚሁ ቅነሳ ሰለባ እንደሚሆን ይሄው ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

 ይህ ብቻ ሳይሆን የትራምፕ አስተዳደር ለታዳጊ ሀገራት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርገውን የዩ.ኤስ.ኤይድ በጀትንም የሚቀንስ መሆኑ በመታወቁ ድርቁ በመጪው አዲስ አመትም ጭምር የሚቀጥል ከሆነ ዜጎችን በመታደጉ በኩል ከኢትዮጵያ መንግስት ብዙ የሚጠበቅ ይሆናል።

 የዩ.ኤስ.ኤይድ አዲሱ ኃላፊ ሚስተር ማርክ ግሪን በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በተገናኙበት ወቅትም የድርቅ ተጠቂ ዜጎችን ህይወት በመታደጉ በኩል ከኢትዮጵያ መንግስት ብዙ የሚጠበቅ መሆኑ እንደገለፁላቸው የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

  ኃላፊው ለዚሁ የረድኤት ስራ የኢትዮጵያ መንግስት እስከ ዛሬ ከነበረው የገንዘብ መጠን የተሻለ በጀት እንዲመደብ የጠየቁ መሆኑን ይሄው ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል። አሁን ባለው ሁኔታ ቀደም ሲል በድርቅ የተጠቁትን ወገኖች ለማገዝ ተጨማሪ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን በመጪው 2010 .ም ደግሞ ምን አይነት ሁኔታ እንደሚኖር አይታወቅም።

 ሆኖም አሁን ካለው አጠቃላይ ሁኔታ ሲታይ የድርቁ ሁኔታ የቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መንግስት ፈተና ሆኖ ይቀጥላል። ከረድኤት ድርጅቶች ምላሽ አናሳነት ጋር በተያያዘም ከኢትዮጵያ መንግስት ብዙ የሚጠበቅ በመሆኑ መንግስት የተወሰነ በጀቱን ለእርዳታ በማዋል የሚቀጥል ከሆነ የልማት በጀት ወደ ፍጆታነት የሚቀየር በመሆኑ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት ብቸኛ አማራጭ የግብርናውን ዘርፍ ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የመስኖ ስራን ማስፋፋት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቢቆይም ይህ ጉዳይ እስካሁን ድረስ መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም።

                   የውጭ ምንዛሪው ፈተና

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ አሁንም በችግርነት ተንከባለው ወደ ሚቀጥለው ዓመት መሸጋገራቸው አይቀሬ ከሆኑት ፈተናዎች ውስጥ ሌላኛው አንኳር ችግር የውጭ ምንዛሬው እጥረት ነው። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለኢትዮጵያ አዲስ ባይሆንም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ከፋይናስ ጋር በተያያዘ በተባባሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የተካሄደው ስብሰባ ያመለክታል። የዚህ ችግር ዋነኛ መንስኤም የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ መሄዱ ነው።

በሀገሪቱ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በተለይ ከቱሪዝም ይገኛል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተፈለገው መጠን እንዳይሄድ አድርጎታል። ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም አሁንም ቢሆን እዚህ እና እዚያ የሚታዩት አለመረጋጋቶች ወደ ቀጣዩ ዓመት የሚሸጋገሩ ከሆነ የሚጠበቀው የቱሪስት ቁጥር በተፈለገው ደረጃ እንዳይገኝ የሚያደርገው ይሆናል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሀገሪቱ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በባንኮችና በጥቁር ገበያው ያለው የዶላር ምንዛሪ ክፍተት እየሰፋ ነው።

ስንድቅ