በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት የሚመራው ልዩ ጦር ጥቃቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ተነገረ፡፡ በክልሉ ፕሬዚዳንት ትዕዛዝ እና በህወሓት ውሳኔ ሰጪነት የሚመራው ልዩ ኃይሉ፣ ትላንትና በቦረና ዞን ጫሙኪ በተባለ ቀበሌ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል፡፡ ልዩ ጦሩ ከዚህ ቀደም በምስራቅ ሐረርጌ ልዩ ስሙ መኢሶ በተባለ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የጥቃት መዳረሻውን በማስፋት በቦረና ዞን ከአስር በላይ ሰዎችን ገድሏል፡፡ የቆሰሉ መኖራቸውንም መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ፣ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል  ፖሊስ፣ ግዛቱ ባልሆነው የኦሮሚያ ክልል ድንበር ዘልቆ በመግባት የሶማሌ ክልል ባንዲራን አውለብልቧል፡፡ በዚህም የተነሳ በተፈጠረው ግጭት ልዩ ኃይሉ በከፈተው ተኩስ ከአስር በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ሌሌች በርካቶችም ቆስለዋል፡፡ ጦሩ በንጹሃን ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ወደ ሶማሌ ክልል መመለሱንም መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ትላንት በተቀሰቀሰው ግጭት የተነሳም አካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንደራቀው የሚናገሩት የዓይን እማኞች፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የሚፈጸምባቸው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደጨመረ ተናግረዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ትላንትና ከለሊቱ 11 ሰዓት ላይ በባሌ ዞን የከፈተውን ጥቃት ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች የመልስ ምት እንደሰጡት የተገለጸ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች የፖሊስ አባላት መካከልም ረዥም ሰዓት የፈጀ የተኩስ ልውውጥ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ዜና፤ በኦሮሚያ ባሌ ዞን የሶማሊ ክልል ልዩ ጦር በከፈተው ጥቃት አራት ሰዎች መሞታቸውን እና ሌሎችም መቁሰላቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል እየተደረገ ያለው ግጭት ‹‹ከሌላ ሀገር ጋር የሚደረግ ጦርነት ይመስላል፡፡›› ሲሉ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ በምስራቅ ሐረርጌ ሜኢሶ ያለው ውጥረት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

ዜናው የቢቢኤን ነው::