ከገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየተደራደሩ የሚገኙ 12 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመደራደሪያ ሐሳባቸውን በጋራ ለማቅረብና ለመደራደር ወሰኑ፡፡

አሥራ ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ለመደራደር መወሰናቸውን ያስታወቁት ሐሙስ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የየፓርቲዎቹ ተወካዮች፣ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽሕፈት ቤት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡

በዚህም መሠረት በዚህ ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ድርድር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ከኢዴፓ፣ አቶ ሙሉጌታ አበበ ከመኢአድ፣ እንዲሁም አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ከአንድነት ዋና ተናጋሪዎች እንዲሆኑ መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሁለተኛው ዙር ድርድር የሚደረግበት አጀንዳ ደግሞ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ 532/99 ነው፡፡ ድርድሩ ለሕዝብና ለአገር የሚበጅ፣ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ የሚሰጥና የዴሞክራሲ ምኅዳሩን የሚያሰፋ፣ እንዲሁም ለውጥ ሊያመጣ የሚችልና ጠብ የሚል ድርድር እንዲከናወን በማሰብ አሥራ ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሰበሰባቸውን፣ የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ አመልክተዋል፡፡

‹‹ለሕዝቡም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ሒደት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣና ተፈጻሚ እንዲሆን ለመታገል ነው የተሰባሰብነው፤›› በማለት አክለዋል፡፡

‹‹ለብዙ ወራት ከመንግሥት ጋር ከፍተኛ ድርድር ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ይህ ድርድር በተለያዩ ቡድኖች ተከፍሎ ምናልባትም ለውሳኔ ሰጭነት ወይም ለመግባባት ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ የቆየ ነበር፤›› በማለት የገለጹት ደግሞ፣ የኢዴሕ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሐየ ናቸው፡፡

‹‹ምንም እንኳ እኛ አንድ ዓይነት አመለካከት ወይም ሐሳብ ቢኖረንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሦስት ወይም በአራት ቡድን መከፋፈላችን ድርድሩ ጎታች ባህሪ እንዲኖረው አድርጎት ነበር፡፡ ስለዚህ እርሱን እንደ ትልቅ ትምህርት ወስደን ተሰባስበንና አንድ ሆነን ሐሳባችንን ጨምቀን፣ በአንድ ድምፅ ማስገባት ይሻላል የሚለው ላይ ተሰማምተናል፤›› ብለዋል፡፡

የተሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ 111 አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ችግር አሉባቸው ያሏቸውን 25 አንቀጾች ነቅሰው ማውጣታቸውን አቶ ትዕግሥቱ አስረድተዋል፡፡

በእነዚህ 25 አንቀጾች ውስጥ ደግሞ 45 ንዑስ አንቀጾች እንዲሁ ተለይተው መውጣታቸውን ገልጸው በዚህም መሠረት 28 አንቀጾች እንዲሻሻሉ፣ 9 አንቀጾች እንዲሰረዙ፣ እንዲሁም ስምንት አዳዲስ አንቀጾች በአዋጁ እንዲካተቱ ማስገባታቸውን አስረድተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ እንዲሰረዙ የጠየቋቸው አንቀጾች የምርጫ ቦርድ አባላትን፣ የቦርዱ ሥልጣንና ተግባራትን፣ የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች አሿሿምና ተጠሪነት፣ የምርጫ ክልሎችን፣ በልዩ ሁኔታ ስለሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ለዕጩነት ስለሚያበቁ መመዘኛዎች፣ የዕጩዎችን ብዛት ስለመለየት፣ የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ የማይደረግባቸው ቦታዎችና የምርጫ ታዛቢዎችን የተመለካቱ እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አሥራ ሁለቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሆነው በሚያቀርቡት ጥያቄና ድርድር ዴሞክራሲ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከንድፍ ተላቆ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የሕዝቦች ባህል እንዲሆን፣ የፖለቲካ ተሳታፊዎች በነፃነት በአደባባይ እንዲንቀሳቀሱና እንዲታዩ የሕግ ከለላ እንዲደረግ፣ ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲተገበር፣ እንዲሁም የታፈኑ ሐሳቦች ያላንዳች መሰናክል በሕዝብ ውስጥ እንዲንሸራሸሩ ለማስቻል ተስፋ አድርገዋል፡፡

ከገዥው ፓርቲ ጋር በጋራ ለመደራደር የወሰኑት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሰያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ)፣ የመላው ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦሕዴፓ)፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት)፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴሕ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) እና የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ወሕዴፓ) ናቸው፡፡

ምንጭ   –    ኢትዮጵያን ሪፖርተር