September 10, 2017 

 ቆንጅት ስጦታው

ኢትዮጵያ ሰላም ከሌላቸው ሀገራት ተርታ ተሰለፈች

BBN
በህወሓት የምትመራው ኢትዮጵያ ሰላም ከሌላቸው ሀገራት ተርታ ተሰለፈች፡፡ ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም በተደረገ ጥናት ሰላም እና መረጋጋት ከሌላቸው የዓለም ሀገራት 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ደረጃዋ ለውጥ አሳይቶ 15ኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ መቻሏን አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡ በዩናይት ስቴትስ በተደረገ አንድ ጥናት ላይ እንደተጠቆመው ኢትዮጵያ፣ ከቅርበ ጊዜ ወዲህ ሰላም እና መረጋጋት እየራቃት እንደመጣ ካስመዘገበችው የደረጃ ሰንጠረዥ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ህወሓት ሀገሪቱን ከቀድሞ ስርዓት ከተረከበ በኋላ፣ የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከትቱ ጉዳዮች ሲከሰቱ መቆየታቸውን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ አሁን ያለችዋ እና በህወሓት የምትመራዋ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ብዙም ርቀት በሌለው የሰላም ማጣት ርቀት ላይ እንደምትገኝ ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ጥናቱ ለሀገራቱ ደረጃ የማውጣት ስራ ሲሰራ መሰረት ያደረገው፣ ጥናት በተደረገባቸው ሀገራት ያለውን የስራ አጥነት ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ደረጃ እና በሀገራቱ ውስጥ ያለውን የግጭት አዝማሚያ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በዚህም መሰረት ጥናት ከተደረገባቸው 178 የዓለም ሀገራት ደቡብ ሱዳን አንደኛ ደረጃ ስትይዝ፣ ሶማሊያ ደግሞ 2ኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ ማዕከላዊ አፍሪካ 3ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሱዳን በበኩሏ አምስተኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ ኢትዮጵያ 15ኛ ኬንያ ደግሞ 22ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጡ በ2017 የተካሔደው ጥናት አመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የስራ አጥነት ችግር በመሸሽ በርካታ ወጣቶች በባህር እና በየብስ ሀገር ጥለው መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡ እንዲሁም ስርዓቱ በየቀኑ አደገ የሚለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚም የተወሰኑ ሰዎችን በተለይም የስርዓቱን ሰዎች ብቻ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በተለያዩ የሐገሪተ ክፍሎች ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ያልተረጋጋ ሀገራት ተርታ ሰንጠረዥ ውስጥ እንድትመደብ አብቅቷታል፡፡