September 4, 2017

የወያኔ ባለሥልጣናት አዲስ አመት አከባበርን በማስመልከት የፍቅር ቀን፣ የምናምን ቀን እያልን እናከብራለን ሲሉ ነገሩ ጭንቀት የወለደው እንደሆነ ቢገባኝም በመላ አገሪቱ የተቀሰቀሰውን ቁጣ ለማብረድ ለተወሰኑ ቀናት የማስመሰል ድራማቸውን ሊያሳዩን ነው ብዮ ገምቼ ነበር። ለካ ለማስመሰልም ትንሽም ቢሆን ብልጠትና ማስተዋልን ይጠይቃል። የፍቅር ቀን ሊያከብር የተዘጋጀ ቡድን፤

 

ያሬድ ኃይለማርያም ለ7 ዓመታት ያህል ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ካውንስል ጋር አብሮ የሠራና የኖቬምበር 1 እማ 2ቱን ጭፍጨፋ ተከትሎ ከሃገር ብዙ ምስጢሮችን ይዞ በመውጣት ለአውሮፓ ሕብረት ያቀረበ ነው። – በምን ሂሳብ ነው ስለ ፍቅር ተቀኚውን የጥበብ ሰው ቴዲ አፍሮን በማንኛውም መድርክ ላይ እንዳይጫውት የሚያግደው? – ሕዝብ የወደደውንና ያነገሰውን ሰው መውጫ መግቢያ የሚያሳጣ ፈሪና እኩይ ቡድን እንዴት አድርጎ ነው አዲሱን ዓመት የእርቅና የሰላም የሚያደርገው – በአንድ የጥበብ ሰው ሥራ ውስጥ የተገለጹና የሕዝብን ስሜት የኮረኮሩ አገራዊ ጉዳዮችን መልስ መስጠት ቢያቅተው እንኳ ባላየ ማለፍ ያቃተው ደንባራ ቡድን እንዴት አድርጎ ነው ከሕዝብ የተነሱበትን እጅግ ውስብስብና ከባድ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚቻለው? – የፍቅር መልዕክተኛ ከሆነው ከቴዲ አፍሮ ጋር መታረቅ ያቃተው ቂመኛና ዘረኛ ቡድን በድርጀት ደርጃ ከተደራጁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቁጭ ብሎ በቅን ልቦናና በሆደ ሰፊነት ለመደራድር እንዴት ይቻለዋል? የወያኔ ባለሥልጣናትም ሆኑ የሥርዓቱ ደጋፊዎች ግራ የተጋቡ ስለመሆኑ ብዙ ምልክቶች እየታዩ ነው። ለዚህ አንዱ ማሳያውም የቴዲና የወያኔ ጸብ ነው። ለማከብረውና ለምወደው ቴዲ ግን ያለኝ መልዕክት፤ እንተ የአንድ የራስህን ብቻ ሳይሆን የሚሊዮኖችን ድርሻ ጨምረህ የዜግነት ድርሻህን ተወጥተሃል። ፍቅርን፣ ፍትህን፣ ሰላምን፣ አብሮነትንና ኢትዮጵያዊነትን ሰብከሃል፣ አስተምረሃል፤ ከዛም አልፈህ ዋጋ ከፍለህበታል። ቀሪው እዳ የኛ ነው። ይብላኝ ለኛ በፍርሃት ተተብትበንና የዜግነተ እዳችንን ተሸክመን ለምንዞረው ሰው መሳዮች፣ ወየው ለኛ የአንተን የፍቅር ዜማዎች እየሰማን ለዳንኪራ ከመመቻቸት ባለፈ አብረንህ በአደባባይ ለመቆም መንፈሳዊ አቅም ላጣነው፣ ይብላኝ ለኛ ቤተ አይማኖቶችን መደበቂያ ዋሻ አድርገን ከሰባኪ የኃይማኖት መሪ እስከ ተሰባኪ ምህመን ልባችንን በጥላቻ አጨልመንና ስለ ፍቅርና ፍትህ አብረን መቆምና መዘመር አቅቶን፤ ክፋታችንና ፍርሃታችንን በነጭ አልባሳት ሸፍነን እዘጌሩን ልንደልል ሌት ተቀን ደፋ ቀና ለምንለው፤ ይብላኝ ለኛ ለተማርነው፤ በቆጠርነው ቀለም ልክ ፍርሃትና ጨለምተኝነት በደም ስራችን ለሰረጸው፤ ፍርሃታችንን ዝም አይነቅዝም በሚል ፈሊጥ ሸፍነን አገርና ሕዝብ እንደ ወያኔ ባለ እኩብ ቡድን እጅ ወድቀው ሲሰቃዩ እያየን እውቀታችንን ሆድ ከመሙያና የራሳችንን ምቾት ከማደላደል እንዳይዘል አድርገን ሰው መሳይ በሸንጎ ለሆነው፤ ይብላኝ ለኛ ለፖለቲከኞች፤ በሰላሳ የደርጅት ዋሻዎች ውስጥ መሽገን የቃላት ቦንብ እርስ በራሳችን ላይ እያዘነብን ጥላቻን፣ ዘርኝነትንና ቂምን እያራባን ከየመጽሃፉ በቃረምናቸው የፖለቲካ አስተሳሰቦች ስንራቀቅ፣ ስንራገጥ፣ ስንቧደን፣ ስንፋለስ፣ በህልም ስንነግስ፣ ስናነግስ፣ በእውን ስንሳደድ፣ ስናሳድድ፤ አገርና ሕዝብ ለውርደት የዳረግን፤

ይብላኝ ለኛ የቴዲን የፍቅርና የሰላም ዘፈኖች ለዳንኪራና ለብሶት መግለጫ ያህል ከማንጎራጎር አልፈን እያንዳንዳችን በሙሉ ልብ የፍቅር፣ የሰላም፣ የፍትህና የነጻነት አዝማሪዎች የሆንን እለት እኩይ የሆኑት አፋኖችና አንባገነኖች እንደ ጨው ይሟሟሉ።

አንባገነንነትም በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ የሚሆንበት ጊዜም እሩቅ አይሆንም። ያኔማ እንኳን የዘፈን መድብል ይቅርና የዛሬዎቹን ግፈኞችና አፋኞች የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅር እያስተማረ ያስመርቃቸዋል። ለዛ ያብቃን! እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! ለኛም ልቦና ይስጠን!