September 11, 2017

“አዲስ አመት”ን በናዚ ካምፕ

(ጌታቸው ሺፈራው)

ነሃሴ 28/2008 ዓም የቂሊንጦ እስር ቤት ከተቃጠለ በሁዋላ ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ እስረኛውን ወደ ዝዋይና ሸዋ ሮቢት መጫን ተጀመረ። እስረኛው ላይ እሩምታ ሲተኩሱ የቆዩት የቂሊንጦ ፖሊሶችን ተክተው ፌደራል ፖሊሶች እስረኛውን እያረጋጉ ነው። የእስር ቤቱ ፖሊሶች የጥበቃ ማማ ላይ ሆነው መትረየስና ክላሽናቸውን እስረኛ ላይ አነጣጥረዋል። እስረኛው የጩኸት ድምፅ ባሰማ ቁጥር ለመተኮስ ይቁነጠነጣሉ። የእስር ቤቱ ፖሊሶች ከዛ በፊት ከእነሱ ጋር የተጋጨ፣ ወይንም በእስር ቤቱ አስተዳደሮች የተጠቆረ እስረኛን እያዳፉ በቃጠሎው እጃቸው አለበት ወደተባሉ እስረኞች ጋር ያሰልፋሉ። አብዛኛዎቹ በቃጠሎው ምንም ተሳትፎ የሌለውን እስረኛ እየደበደቡ የነበሩት ያለ መፈተሽ መብታቸውን ተጠቅመው ሲጋራ፣ ስልክና ሌሎች ቁሳቁሶችን በውድ ዋጋ ወደ እስር ቤት የሚያስገቡ ፖሊሶች ናቸው። ከማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች በተሻለ የፌደራል ፖሊስ አባላት እስረኛውን ያረጋጉ ነበር። የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች እንዳሳዩት ፀባይ አብዛኛው እስረኛ ሊረሸን እንደሚችል ሁሉ እስከማሰብ ደርሷል።
ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ 18 መኪና እስረኛ ወደ ዝዋይ ተጫነ። አብዛኛው እስረኛ ልብሱን ተቀምቷል። መደረብ አይቻልም ተብሎ ካናቴራና ቁምጣ ብቻ ያደረገው ብዙ ነው። ወደ አዳራሽ ያልገባውና ዶፍ ዝናብ ሲወርድበት የቆየው ብቻ በዝናብ የበሰበሰ ልብሱን አልተቀማም። ዝዋይ እኩለ ሌሊት ላይ ስለደረስን መኪና ውስጥ ለሁለት ለሁለት በካቴና እንደታሰርን እንድናድር ተደረገ። ጠዋት እንደታሰርን ከመኪና ወርደን ተሰልፈን ተፈተሽን። ብር፣ በሶ፣ ክኒንና ሌሎች እስረኛው የያዛቸው ነገሮችን ቀምተው ቆርቆሮ በቆርቆሮ የተሰሩ ሰፋፊ አዳራሾች ያሉት ግቢ ውስጥ ገባን። በዚህን ወቅት ፌደራል ፖሊሶች ለዝዋይ ማረሚያ ቤት ፖሊሶች አስረክበውን የሄዱ ሲሆን የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች እስረኛው በተንቀሳቀሰ ቁጥር ለመተኮስ ይቃጣቸዋል። ዱላ የያዙት ለመደብደብ ይቋምጣሉ። ከቂሊንጦ አዛዦች በተነገራቸው መሰረት ወደ ግቢያቸው የሚገባው እስረኛ ሁሉ ሰው ገድሎና አቃጥሎ የመጣ ነው ብለው አስበዋል። እስረኛው ቁሳቁሱን ለምን እንደሚቀማ ሲጠይቅ እንኳ የሚሰጠው መልስ ” ሰው ከእነ ነፍሱ አቃጥለህ መጥተህ!” የሚል ነው።

በካቴና እጥረት ምክንያት ካልታሰሩት እድሜያቸው ገፋ ያሉ ግለሰቦች ውጭ አብዛኛው ለሁለት ለሁለት በካቴና ተቆራኝቷል። የእስኛውን ሰልፍ ከእስረኛው በትንሽ የሚያንሱ ፖሊሶች አጅበውታል። መሳርያ የያዙት ራቅ ብለው በጥንቃቄ ቆመዋል። ባለዱላዎቹ ምክንያት ፈጥረው ” ፍጠን፣ ለምን ታየኛለህ፣ ምንድን ነው ያወራኸው………” የሚሉ መደብደቢያ ምክንያቶችን እየፈለጉ በእስረኛው ላይ መከራ ያወርዳሉ። ተመድበን የገባንባቸው ቤቶች ፍራሽ የላቸውም። ባዶ ወለል ላይ ካስቀመጡን በሁዋላ ከቂሊንጦ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ መፈፀም ጀመሩ። በርካታ ወታደር አስገብተው እስረኛውን ምክንያት እየፈለጉ ይደበድባሉ። ቂሊንጦ ታስሮ ዝዋይ እስኪደርስ ካቴናው እየጠበቀበት ” አላሉልኝ እጄ አበጠ” ብሎ በትህትና የጠየቀ እስረኛ ” ሰው በቁሙ አቃጥለህ መጥተህ !” ተብሎ ይደበደባል። ወይንም ይበልጡን ያጠብቁበታል። “ለምን?” ብሎ የሚጠይቅ ፖሊሶች ይረባረቡበታል። በርከክ ያለ “በቂጥህ ቁጭ በል”፣ ነጠላ ጫማው ላይ የተቀመጠ ” ባዶው ላይ ተቀመጥ” ተብሎ ዱላ ይወርድበታል።

የተመደብንበት አዳራሽ ቦዶ ወለል ስለሆነ የምንተኛው ባዶ ቀዝቃዛ ሊሾ ወለል ላይ ነው። በቁምጣና በካናቴራ የወጣ እስረኛ ከዚህ ወለል ላይ ኩርምት ብሎ ከመተኛት ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም። ቢበርደው፣ ቢቆረጥመው አለመተኛት አይቻልም። አለመተኛት ወንጀል ነው። በፖሊሶቹ ትርጓሜ መሰረት የማይተኛ ሊያመልጥ ነው። በመሆኑም ቀዝቃዛው ወለል ላይ ተጋድሞ ጣራ ጣራውን ያየ፣ ቁጭ ያለ፣… … ያልተኛን እስረኛ ፖሊሶቹ መሰላል ላይ ወጥተው በቀዳዳው ሲነጋ የሚደበደብበት መለያ ቁጥር ሰጥተውት ይሄዳሉ። አንተ 1፣ ጥግ ላይ ያለኸው አንተ 2……… ብለው ከአስር በላይ እስረኛን ቁጥር ጠርተውበት ይሄዳሉ። የቤት ሀላፊ ብለው ያስቀመጡት ሰው እነዚህን እስረኞች እንዲያስታውስ ይነገረዋል። ጠዋት ፖሊስ መጥቶ ቁጥሮቹን ሲጠራ ቁጥር የተጠራበት እስረኛ መውጣት ግዴታው ነው። ቅጣቱ እንዲቀልለት። ግን ዝዋይ ቀላል የሚባል ቅጣት የለም። የዝዋይ ፖሊሶች ለእስረኛው በተደጋጋሚ የሚጠይቁት “ቂሊንጦ እንዴት ወታደራዊ ቅጣት አትቀጡም?” የሚል ነው። እስረኞች ላለመደብደብ ቂሊንጦ ወታደራዊ የሚባል ቅጣት የለም ስለሚሉ ፖሊሶቹ ይገርማቸዋል። መርህ የተጣሰ ይመስላቸዋል። በዚህ መሰረት እነሱ መርህ ብለው ያስቀመጡትን ወታደራዊ ቅጣት ይቀጣሉ። ሲቪሉን እስረኛ!

የቤቶቹ ደረጃ ከአንድ ሜትር በላይ ነው። አጥፍቷል የተባለን እስረኛ እግሩን ደረጃው ላይ ይሰቅልና እጆቹን መሬት ላይ አድርጎ “ፑሽ ሀፕ” ስራ ይባላል። ወገቡን፣ ቁርጭምጭሚቱን፣ ጭኖቹን በዱላ ይቀጠቀጣል። ከዱላው በተጨማሪ በጥያቄ ያዋክቡታል፣ ይስቁበታል። ተሰብስበው። “ኩላሊት፣ ጉበት፣ የወገብ በሽታ…………” አለብኝ ቢል የሚሰማው የለም። አቧራ ላይ እየተንከባለለ ፖሊሶች እየተከተሉ ይደበድቡታል። አቧራው ላይ ሲደበደብ በባልዲ ውሃ እየተደፋበት ነው። ልብሱን ቀይር ተብሎ ከፖሊስ ይሁንታ እስኪሰጠው በድረስ መቀየር አይችልም። ሻወር የሚታሰብ አይደለም። እስረኞች በጅምላ በሚደበደቡበት ጊዜ መሬት ላይ ተኝተው አንደኛው የሌላኛውን እግሮች ውስጥ አንገቱን አስገብቶ (በሌላኛው እግሮች ታንቆ) እግሮቹን ይይዛል። ያነኛውም እንዲሁ። ሲደበደቡ አንዱ የሌላውን እግር ይዞ አንዴ አንዱ ከላይ፣ ያነኛው ከታች እየሆኑ እየተገለባበጡ ይደበደባሉ። ከዱላ ለማምለጥ ቶሎ ቶሎ መገለባበጥ አለባቸው። በወገብ ሩጫ ነው። ከላይ የሆነው ሲደበደብ ራሱን ለመደበቅ ተጓዳኙን ከላይ አድርጎ ከስር መሆን አለበት። ግን ተጣማሪውም ተገልብጦ እሱ ከላይ ያደርገዋል። ማኮብኮብ የሚባለው ትንሹ ቅጣት ነው።

በአንድ ካቴና ሁለት ሰው ይተሰራል። በአንድ ካቴና የአንዱ ሰው እጅና የሌላኛው እግር ሲታሰር ያየሁት ግን ዝዋይ ቀወጣት ቤት ብቻ ነው። እጁ ከሌላኛው እግር ጋር የታሰረው ግለሰብ የተጓዳኙ እግር ድረስ ዝቅ ብሎ መሄድ አለበት። እግሩ ከሌላኛው እጅ ጋር በካቴና የታሰረው ግለሰብ ደግሞ የራሱንም የተጓዳኙንም ካቴና ላለማጥበቅ በጥንቃቅ፣ ተጓዳኙን እየጠበቀ መንኳተት አለበት። ሲተኙም አንዱ የሌላኛውን እግር ታቅፎ ነው። እንዲህ ታስረውም ይደበደባሉ። ሲወራጩ ካቴናው እግርና እጃቸውን ይመላልጠዋል። ይህን በደል ያየ ሀገር በቅኝ ግዛት ውስጥ እንዳለች ይረዳል። ዜግነቱን እንደተቀማ ይገባዋል። ባይተዋርነቱን ያውቀዋል። የገዥዎቹን ጭካኔ ጥግ ይለካል። እስር ቤቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ አሳሪዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ይጠራጠራል!

ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆኑት አዳራሾች ሌሊት እጅግ ቀዝቃዛ ቀን ደግሞ ሀሩር ናቸው። ሌሊት ብርዱን መከላከል የሚያስችል ብርድ ልብስና አንሶላ ይቅርና ከካናቴራቸው በላይ የሚደረብ ሸሚዝ የሌላቸው ብዙዎች ስለሆኑ ደንዝዘው ያድራሉ። የቀን ሀሩሩን እንዲብስ ቤቶቹ ተዘግተው ይውላሉ። በዝዋይ ሙቀት ከቀኑ 6 ሰዓት ላት ሜዳ ላይ መቀመጥ ከቤቱ ሙቀት አንፃር ገነት ነው። እስረኛን እያራሱ ለመደብደብ ባልዲ ሙሉ ውሃ ሲደፉ እየዋሉ ለሙቀቱ ማስታገሻ ግን በቀን ሁለቴ ብቻ አንድ አንድ ኩባያ ውሃ ያድላሉ። ይህም የማይገኝበት ጊዜ አለ።

የቂሊንጦ ቃጠሎ የተከሰው በአተት ሰበብ ምግብ በመከልከሉ ነው። አተት ያመጣል የተባለው ደግሞ ቤተሰብ ተጠንቅቆ አዘጋጅቶ ለእስረኛ በሚያመጣው ምግብ ነው። ዝዋይ ግን ለመታጠቢያ ይቅርና ለመጠጥ የሚሆን ውሃ ስላልነበረ እስረኛው የሚመገበው እጁን ሳይታጠብ ነበር። በአንድ ቤት ለታፈነ 285 እስረኛ ሶስት ሽንት ቤት፣ ሌሊት ሌሊት ለተወሰነ ሰዓት ብቻ ውሃ የሚፈስባት ባንቧ እና አንድ ሻወር ቤት አለ። ውሃ ስለሌለና በእስረኛው ብዛት ምክንያት ሽንት ቤቶቹ ሞልተው የእግር መረገጫ እንኳን የላቸውም። ዝዋይ ከገባን ከአንድ ቀን በሁዋለ እስረኛው ያመልጣል ተብሎ ነጠላ ጫማ ስለተቀማ ሽንት ቤት የሚገባው ባዶ እግሩን ነው። ሶፍትና ወረቀት የለም። በውሃ መጠቀም እንዳይቻል ውሃ የለም። እስረኛው ከእነዚህ እስር ቤቶች ተጠቅሞ እጁን ሳይታጠብ ይበላል። ሁለት ሰው በአንድ ካቴና ስለታሰረ አብሮ የታሰረውን ቁጭ ብሎ ሽንት ቤት ማስጠቀም ግዴታ ው። ተቆራኝቶ ስለታሰረ ተገላብጦ መተኛት አይቻልም። ወደ ዝዋይ ከተወሰድን በሁዋላ ለ10 ቀናት ሙሉ ባዶ ወለል ላይ ነበር የተኛነው። በዚህ 10 ቀን ውስጥ አብዛኛው እስረኛ በአንድ ካቴና ሁለት ሰው ታስሮ ነበር የሰነበተው። በውሃ ቀጠነ ሰበብ መሬት ላይ እየተንከባለለና ውሃ እየጠማው ግን ውሃ እየተደፋበት እየተደበደበ ነበር።

ከኢትዮጵያ እስር ቤቶች መካከል በክፉነቱ የሚነሳው ማዕከላዊ ነው። ዝዋይ ግን ማዕከላዊን ያስንቃል። ያስናፍቃል። ማዕከላዊ የሰቆቃ እስር ቤት ቢሆንም ቢያንስ እጅን መታጠብ ይቻላል። በሳምንት አንድ ጊዜ ሻወር አለ። በዛ ስቃይ ውስጥ መጫወት፣ ማውራት፣ ስቃይን ለማቃለል መዝፈንና መሳቅም ይቻላል። ዝዋይ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ወንጀል ናቸው። ያስደበድባሉ። ዝዋይ ኢትዮጵያውያን አለን የለንም ብለው የሚጠራጠሩትን ሀገር እንደተቀሙ የሚያረጋግጡበት የስቃይ ቤት ነበር። ከአንድ አመት በፊት እንዳየሁት።

በወቅቱ በእስረኛው ላይ ይህ ሁሉ በደል እንዲፈፀም የሚያስተባብረው በግምት 55 አመት ገደማ የሚሆነው የህወሃት ታጋይ ነበር። ይህ ግለሰብ ገና ወደ ግቢው ስንገባ ድምፁም ከፍ አድርጎ “አሁን ዲሞክራሲ ስለሰፈነ ነው እንጅ ደርግ ቢሆን በቀጥታ ይረሽናችሁ ነበር።”! እያለ እያስደበደበ ያስገባ ነበር። እሱም ካቴና ጠበቀብኝ ያለውን ደብድቦ ይበልጥ አጥብቆት ይሄዳል። በየ ቀኑ እየመጣ ለማምለጥ የሚሞክር ካለ በጥይት እንደሚመታ ዝቶ ይሄዳል። አንድ ቀን በቆርቆሮው ቀዳዳ ወደ ውጭ እየያዩ ነው የሚያድሩት የሚል ሪፖርት ይደርሰዋል። ወደ ግቢው ስንገባ ” ደርግ ቢሆን በቀጥታ ይረሽናችሁ ነበር”! ያለው ታጋይ በዚህ ቀን ” አመልጣለሁ ብትል አስር አስርክን አንድ ቤት እያስገባሁ ነው የምረሽንህ!” ነበር ያለን። እሱ እንዳለው ደርግ። ግን ባለፈው አመት እንዳየሁት ዝዋይ የባዕድ እስር ቤት ነው። ካምፕ። በፊልም እንደምናየው የጀርመን ካምፕ። የናዚ!

አዲስ አመትን በዚህ ካምፕ ውስጥ የሰው ልጅ አቧራ ላይ እየተንከባለለ ውሃ እየተደፋበት፣ ምን አልባት ወራሪዎች “ባርያ” ብለው በአፍሪካውያን እንዳደረጉት እግርና እጅ ታስሮ እየተደበደበ ነበር ያሳለፍነው። ያን የመከራ ጊዜ ሳስብ ይህን የሚፈፅመው አገዛዝ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የናዚ ካምፖች እንዳሉ ህሊናዬ ይነግረኛል። ስቃይና ሰቆቃ የሚደርስባቸው፣ በሀገራቸው ባይተዋር የሆኑ ድምፅ አልባዎች፣ ከደብዳቢዎቹና ከእነሱ ውጭ ምን እየተፈፀመባቸው እንዳለ ማንም የማያውቅላቸው ኢትዮጵያውያን ይህን ቀን በተመሳሳይ ስቃይ እያሳለፉ እንደሆነ ይሰማኛል! ይህ የሚያበቃበት የኢትዮጵያ አዲስ አመት፣ አዲስ ዘመን መቼ ይሆን? እጅግ እናፍቀዋለሁ! ለዛ አዲስ አመት ያብቃን!