September 11, 2017

የ፪ሺህ፲ ዓመተ ምሕረት አዲስ ዘመን ቃለ ምዕዳን!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ ። አሜን ።

በሀገራችን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም የምትገኙ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ፥ ማኅበረ ካህናት ፥ ምእመናንና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ! እግዚአብሔር በቸርነቱ እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ ፪ሺህ፲ ዓመተ ምሕረት አደረሳችሁ ።

 

ዓመተ ምሕረት ማለት የይቅርታ ፣ የምሕረትና የትድግና ዓመት ፥ ዘመን ፥ ወቅት ማለት ነው ። ዓመተ ምሕረት የዓመተ ፍዳ ፥ የዓመተ ኩነኔ ተቃራኒ ነው ። በቤተ ክርስቲያናችን ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለው ዘመን ዓመተ ኩነኔ ዓመተ ፍዳ እየተባለ ይጠራል ። ምክንያቱም ሰው የፈጣሪውን ትእዛዝ ተላልፎ ከፈጣሪው ጋር በጣላቱ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ተፈርዶበት ስለ ነበር ነው ። በርደተ መቃብር ላይም ርደተ ሲኦል ተወስኖበት ነበር ። በመሆኑም ይህ ከባድ ዘመን ሰው በሥጋውም በነፍሱም የተቀጣበት ዘመን ስለ ሆነ ዓመተ ኩነኔ ይባላል ። የእግዚአብሔር ፍርድም ለዲያብሎስ ባርነት ስለዳረገው ሥጋውን በመቃብር ተቆራኝቶ ፣ ነፍሱን በሲኦል ረግጦ ይገዛው ፣ ያሰቃየውም ስለ ነበር «ዓመተ ፍዳ» ይባላል ። ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ፍጹም ሰው በመሆን ይህን ሁሉአስቀርቶልናል ። ይህም ሊሆን የቻለው የሰውን በደል በመስቀል ላይ ተሸክሞ ፣ ሞትን በሞቱ ደምስሶ ፣ ስለ ሰው ሕይወት ሕይወቱን ክሶ የሰውን ልጅ ነጻ ስላወጣው ነው ። ስለዚህ ነበር ወንጌልን ሲሰብክ «ለድሆች ወንጌልን … ለታሰሩትም መፈታትን ፥ ለዕውሮችም ማየትን ፥ እሰብክ ዘንድ ፣ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ ፥ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል» ያለው። (ሉቃ 4 ፥ 19) ።

ክብር ይግባውና ዓመታችንን ዓመተ ምሕረት አደረገው ፤ የቁጣንና የፍዳን ዓመት አሳለፈልን ። አሁንም ለሕገ እግዚአብሔር የሚታዘዙ መሪዎችና ሕዝቦችን ካፈራን ዓመታችን በእውነት ዓመተ ምሕረት ይሆናል ። ያ ካልሆነ ግን በቁጣ

 

«ለታሰሩትም መፈታትን ፥ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ ፣ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ ፥ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል» (ሉቃ 4 ፥ 19) ።

ዓመት እንድንኖር ልንገደደ እንችላለን ። አገራችን ኢትዮጳያ ሥጋዊና መንፈሳዊ ነጻነቷ የተጠበቀላት አገር ነበረች ። በዚህ ወቅት ግን ዜጎቿ በመላው ዓለም ተበትነው የውርደትንና የመከራን ኑሮ እንዲገፉ ተደርጓል ። በአገራችን በኢትዮጵያ የሚኖሩትም በችግር አለንጋ እየተገረፉ ፣ ሰብአዊ መብታቸውን ሳይቀር እየተገፈፉ በእስራትና በሞት ጥላ የሚኖሩ ጥቂቶች አይደሉም ። ስለዚህ ዓመታችን ዓመተ ምሕረት ሁኖ እንዲቀጥል ፤ ሰው እርስ በእርሱ ሊተዛዘን ፣ ሊረዳዳ ፥ ለተጠቁት ነጻነት ፣ ለታሰሩት መፈታት ፣ ሊታወጅላቻው ይገባል ።

መንፈሳዊ ነጻነት የሰብአዊ ማንነታችን ነጻነት መገለጫ ነው ። ሥጋዊ ነጻነትም የመንፈሳዊ ነጻነት መገለጫ ነው ። ስለዚህ የሕዝባችን መንፈሳዊና ሥጋዊ ነጻነት አባቶቻችንና እናቶቻችን ጠብቀው እንዳቆዩን እኛም ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ሰላም ፣ የመብት እኩልነትና አብሮነት ተግተን ልንሠራ ይገባናል ።

እንደሚታወቀው ዓመታት ፥ አውራኅ ፥ ሳምንታት ፥ ዕለታት ፥ ሰዓታት ሁሉ የእግዚአብሔር ገንዘቦች ናቸው ። እግዚአብሔር እድሜንና ዘመንን የሰጠን እንድንጠፋፋ ሳይሆን እንድንተባበርበት ነው ። እንድናንስ ሳይሆን እንድናድግበት ነው ። አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን እያሳለፈች እስከዚህ ዘመን ደርሳለች ። የወደፊቱን እርምጃዋን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ስለ ሆነ ሁላችንም ቅድስት አገራችንን በጸሎት ልናስባት ይገባል ። የተራቡትን ፥ የታረዙትን ፥ በግፍ የታሰሩትን ፥ የተጨነቁትን በምንችለው ሁሉ ልንረዳቸው ይገባል ።

የተከበራችሁ በሀገራችን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም የምትገኙ የመፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ! አዲሱ ዓመት የምሕረት የይቅርታ የሰላም የአንድነት ዓመት ይሆን ዘንድ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ፥ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ጸልዩ ። እንደሚታወቀው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምን አንድነትን ተርቧል ፤ ልጆቻቸው በእስራት የሚንገላቱባቸው ወላጆች ፣ ወላጆቻቸው በጨላማ ቤት የተጣሉባቸው ልጆች ፣ በእስር ቤት ልዩ ልዩ ግፍ የሚፈጸምባቸው የሕሊና እስረኞች ፣ በልቅሶ በኀዘን ተውጠው አዲሱን ዓመት ሲያሳልፉ ማየትና መስማት ያሳዝናል ። ስለዚህ እስረኞችን በመጠየቅ ፣ ወላጅ ያጡ ልጆችን በመጎብኘት ፣ የተራቡትን በማብላት ፣ ተስፋ የቆረጡትን በማጽናናት አዲሱን ዓመት ልናከብረው ይገባል ። አምላካችን ለሕዝቡ የሚራሩ መሪዎችን እንዲያስነሣ ተግቶ መጸለይና መሥራት የሁሉም ሕዝብ ድርሻ መሆኑን አምነን እግአብሔር በፍትሕ በርትዕ ኢትዮጵያን እንዲጎበኛት ተግተን እንጸልይ ።
እግዚአብሔር አዲሱን ዓመት ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነጻነትና በክብር የሚኖርበት ፣ የሰላም ፥ የፍትሕ ፥ የአንድነት ዓመት ያድርግልን ።

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !

አባ መርቆሬዎስ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

15521Orchard Drive Bowie MD 20715 Phone:(301) 262-3031