13 Sep, 2017 By ዘመኑ ተናኘ

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር  ነገሪ ሌንጮ (/) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች የተነሳው ግጭት ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት ቢሆንም አሁን ግን ቆሟል፡፡

የዚህ ችግር ዋነኛ መንስዔ ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ እየተጣራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ለዚህ ችግር መንስዔ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ነው የተባለውን ለማጣራት መንግሥት ባደረገው ጥረት ይህ ኃይል እንዳልሆነ የክልሉ መንግሥት መናገሩን ጠቅሰዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ማክሰኞ መስከረም 2 ቀን 2009 .. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዚህ ግጭት ላይ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ሦስት ናቸው፡፡ እነሱም የሶማሌ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል፣ የሶማሌ ክልል የሚሊሻ አባላትና ከሶማሊያ ሪፐብሊክ የመጡ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በተለይም የሶማሊያ ዜግነት ያለው ሹኔኬኖ አብዲ የሚባል ሰው በግጭቱ መሀል መያዙንና ይህም በወቅቱ ከተያዙ ሰዎች ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አቶ አዲሱ፣ ‹‹ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያሉ አስተዳደራዊ ወሰኖች የግጭት መነሻ እንዳይሆኑ ስንሠራ ቆይተናል፤›› ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር ያለውን አስተዳደራዊ ግጭት ለመፍታትም በ1997 .. በሁለቱ ክልሎች መካከል ተደርጎ በነበረው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2009 .. በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካይነት ከ85 በመቶ በላይ ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን ማካለል መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

ሁለቱ ክልሎች በመቀራረብ የነበሩ ችግሮችን ፈትተው በጋራ በመሥራት ላይ እያሉ በድጋሚ ግጭት መቀስቀሱን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡ ቦረናና ሞያሌ በሚባል ወረዳ በተለምዶ ጫሙክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተነሳው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም መከሰቱን አስታውቀዋል፡፡

አቶ አዲሱ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ሕዝቡን አስተባብሮ ራሱን እንዲከላከል እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እንዲከላከል ብቻ ሳይሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት ጋር በመገናኘት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህንን ግጭት ከአስተዳደራዊ ወሰኑ ጋር የማያያዝ ነገር አለ፡፡ ሁለተኛ ግጭቱ የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት አድርጎ የማየት ነገር አለ፤›› ያሉት አቶ አዲሱ፣ እነዚህ ሁለቱ ጉዳዮች እጅግ የተሳሳቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ አብሮ የኖረና አሁንም ድረስ አብሮ እየኖረ ያለ በመሆኑ፣ በሕዝቦች መካከል ግጭት እንደሌለና ወደፊትም እንደማይኖር እምነታቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በኦሮሚያ ክልል በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁለቱ ክልሎች መካከል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጡት መግለጫ፣ የችግሩ ምንጭ የሶማሌ ልዩ ኃይል ነው ብለዋል፡፡ ፓርቲዎቹ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ)፣ የኦሮሞ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦአዴፓ)፣ የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ)፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር (ኦነአግ) እና የኦሮሞ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ (ኦነብፓ) ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀና በወታደራዊ ፓትሮል ተሽከርካሪዎች የሚታገዝ የሶማሌ ልዩ ኃይል ባዶ እጁን በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ሚሊሻ ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ዕልቂት እያደረሰ መሆኑን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡

ግጭቱ በሕዝብ መካከል እንዳልሆነ የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፣ ይህን ችግር እያደረሰ ያለው የሶማሌ ልዩ ኃይል በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እያደረገ ነው ያሉትን ድርጊት ‹‹ያልታወጀ ጦርነት›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ፓርቲዎች የንብረትና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውና ለሞቱ ወገኖች አጥፊው ወገን ተገቢው ካሳ እንዲከፍልና በሕዝቦች መካከል ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲወርድ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ማክሰኞ ምሽት ማተሚያ ቤት ከመግባታችን በፊት በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ ሐረርጌና በምሥራቅ ሐረርጌ አንዳንድ አካባቢዎች የተቃውሞ ሠልፎችና ግጭቶች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስላደረሰው ጉዳት ግን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ 

Author

anon