September 14, 2017

 

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ክፍል አንድ

መነሻ

ኢትዮጵያ ሃገራችን ከሌሎች አገሮች የምትለይባቸው፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚያኮሩ የታሪክ ሂደቶች፤ ቅርሶች፤ እሴቶች እና ልምዶች አሏት። ኢትዮጵያን ከሌሎች አገሮች የሚለያት ምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ታዛቢዎች የተለያዩ መልሶች ይሰጡታል። ለምሳሌ፤ ይህች አገር የምትታወቀው በድህነት፤ በረሃብ፤ በምግብ ጥገኝነት፤ በየእርስ በርስ ጦርነት ነው የሚሉ ብዙ የውጭ አገር ታዛቢዎች አሉ። ሌሎች የአገር ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃን፤ በተለይ እንደ ህወሓት ያሉ ጠባብ ብሄርተኞች ደግሞ ይህች አገር የመቶ ዓመታት ታሪክ ያላት፤ “የብሄሮሮች እስር ቤት ናት” ይላሉ።

የእኔ መሰረታዊ ሃሳብ ሌሎች በሚሰብኩት ላይ አይደለም። በእኔ ጥናትና እምነት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች የምትለይባቸው፤ እኔ የምኮራባቸው የሚከተሉት ናቸው፤

ኢትዮጵያ የሰው ልጆች የተፈጠሩባት አገር (The Origin of Humanity) መሆኗ፤
ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ከተመሰረቱባቸው፤ እንደ ቻይና ካሉ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ፤
ኢትዮጵያ የራሷ ፊደልና የቀን መቁጠሪያ መለያዎች ያሏት አገር መሆኗ፤
እንደ ጀርመኒ፤ ዩናይትድ ኪንግደም፤ ኢታሊ ያሉና ሌሎች የአውሮፓ መንግሥታት ብሄራዊ አንድነት መስርተው በመንግሥትነት ከመታወቃቸው በፊት ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ፤ የባህር በር ጨምሮ፤ ሰፊ መልክአ ምድር፤ የአስተዳደር ስነ ስርዓትና መንግሥት የነበራት አገር መሆኗ፤
ኢትዮጵያ ከመጀመሪያዎቹ የክርስትና ኃይማኖትን ከተቀበሉ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗና ከራሷ ባህል ጋር ያዛመደች (Indiginous and Unique) ያደረገች መሆኗ፤
የነቢዩ ሞሃመድ ተከታዮች በሃገራቸውና በቤታቸው በእምነታቸው ጸንተው ለመኖር አፈና፤ ጭቆና፤ ድብደባ፤ እስራት፤ ግርፋትና ሌላ ስቃይ ሲደርስባቸው ባህሩን ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ሲሰደዱ የኢትዮጵያ ንጉሥ፤ መንግሥትና ሕዝብ በደስታ ተቀብሎና መጠጊያ ሰጥቶ ያስተናገደባት አገር መሆኗ፤

“ሶስተኛ ዓለም” ብለው አውሮፓዊያን የሰየሙት፤ በተለይ ከበርሊን ጉባኤ በኋላ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ለራሳቸው የንግድ፤ የገበያ፤ የተፈጥሮ ኃብት፤ የኢኮኖሚ እድገት ምሰሶዎች የበላይነት፤ የገቢና የኑሮ መሻሻል፤ የሕዝብ መኖሪያ ስርጭት መስፋፋት፤ የባህር በር፤ የባህልና ሌላ የበላይነት ስርጭት (Diffusion of cultural, religious, linguistic, artistic and other supremacy) ጥቅም ሲሉ አፍሪካን ሲሻሟት፤ ሲቀራመቷትና የግል ኃብታቸው ሲያደርጓት፤ በሕዝቦቿ አንድነትና ጀግንነት ኢትዮጵያ ነጻነቷን ያስከበረችአገር መሆኗ፤

ምንም እንኳን በቴክኖሎጅ፤ በዘመናዊ ኢኮኖሚ ልማት፤ በምግብ ዋስትናና በሌሎች የእድገትና ልማት መስፈርቶች ኋላ ቀርና ድሃ ናት ብትባልም፤ ይህች የጥቁር ሕዝቦች “የነጻነት መዲና፤ እና አንዲት ደራሲ “የአንድነት ብርሃን” ብላ የሰየመቻት አገር ነጻ ላልወጡ የአፍሪካ አገሮች ካላት ዝቅተኛ ገቢና ባጀት እየቀነስች ለጥቁር አፍሪካ ታጋዮች (ደቡብ አፍሪካ፤ ዚምባብዌና ሌሎች)፤ ለወጣት የአፍሪካ ተማሪዎችከፍተኛ አስተዋፆ ያደረገች አገር መሆኗ፤

የአፍሪካ አገሮች ነጻነት ከወጡ በኋላ አቅማቸው እንዲጠነክር፤ በዓለም ተደማጭነት እንዲኖራቸው፤ ተደጋግፈው ነጻነታቸውን እንዲያስከብሩ በማሰብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (The Organization of African Unity/OAU) እንዲመሰረት ማድረጓና አዲስ አበባ የአፍሪካዊያን “መናገሻ ከተማ” እንድትሆን መሬት የሰጠች አገር መሆኗ፤

የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ፈርሶ የተካውን የተባበሩት መንግሥታትን በጠንካራ ዲፕሎማሲ ተሳትፎ እንዲመሰረት ካደረጉት መስራች አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ፤

የተባበሩት መንግሥታት በኮሪያና በኮንጎ ባደረገው “የጋራ ደህንነት” ጦርነት ስመ ጥሩ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን መኮንኖችንና ወታደሮችን ያሰለፈች፤ ዝናን የተቀዳጀት አገር መሆኗና፤

ምንም እንኳን የተለያዩ በደሎችና ግፎች መካሄዳቸው ባይካድም፤ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ስብጥር ሕዝብ በአንዲት የጋራ ድንኳን (ቤት) የታቀፈና የተሳሰረ በመሆኑ (Diverse Population) የተለያዩ ብሄሮችና ኃይማኖቶች፤ የተለያዩ ባህሎችና ልምዶች የጌጣችንና የጥንካሬያችን መሰረት መሆናቸውን ያሳየች፤ በአብዛኛው “የኢትዮጵያ ልጆች” የብሄርና የኃይማኖት ጥላቻችን ጫና ተቋቁመው፤ የጨዋነትን ባህል ተቀብለው፤ ዜጎቿ ተከባብረው የሚኖሩባት    አገር መሆኗ ይገኙበታል።

እነዚህና ሌሎች እሴቶች፤ ጥሪቶች፤ ልምዶች፤ ማህበረሰባዊ ኃብቶች (Social Capital Assets) ለአገራችን ለኢትዮጵያ ቀጣይነትና ለ105 ሚሊየን ሕዝቧ ዘላቂና ፍትሃዊ እድገት መሰረት ናቸው የሚል እምነት አለኝ። እነዚህ የሃገራችን የጥንካሬ ምሰሶዎች ለእድገት ወሳኝ ከመሆናቸው ባሻገር ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶች እንዳትጠቃ ይረዷታል። እነዚህን ጥሪቶች ከናቅናቸው ማንም አያከብረንም። ሕዝቡን ከሕዝቡ ጋር እንዲናከስ ካደረግነው እነዚህ የጋራ ጥሪቶች ይባክናሉ። የቻይናና የደቡብ ኮሪያ ወዳጆቸ እንደነገሩኝና እኔም እንደማምነው፤ የራሱን ታሪክ ያላከበረን ሕዝብ ማንም አክብሮት አያውቅም።

ህወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫነው በቋንቋና በብሄር ልዩነቶች ላይ የተመሰረተው የክልል ሕገ መንግሥትና የፌደራል አስተዳደር፤ የአገራችንን ረዥም ታሪክ “ሰው ሰራሽ” ነው በሚል ብሂል ተነስቶ ለሃገራችን ዘላቂነት፤ ግዛታዊ አንድነት፤ ነጻነት፤ ደህንነትና ሉዐላዊነት ጠንቅ ሆኗል። ኢትዮጵያ ረዥምና የሚያኮራ ታሪክ የላትም የሚለው ፈጠራ የሌለ የታሪክ ምርመራ እንዲደረግ፤ ኢትዮጵያ የሚለው ስመ ጥሩ የአገር ስም በሌላ፤ ለምሳሌ “ኩሽ” በሚለው እንዲቀየር የተቀነባበረ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ አጥፊዎች ሴራ በተቀነባበረ መልኩ እየተካሄደ ነው። ይህ ሴራ ወደየት እንደሚያመራ ለመተንበይት ሳይንቲስት መሆንን አይጠይቅም።

የዚህ ትንተናና ትችት ዋና ይዘት የእኛ፤ በተለይ የአገር ወዳዶች፤ የእርስ በርስ መጠላለፍና መጋጨት ኢትዮጵያ ፈጽሞ እንድትጠፋ ለሚፈልጉና ለሚመኙ የውጭ ኃይሎች መጋቢ ሆኗል የሚል ነው። በተጨማሪ፤ ብሄርን ከብሄር ጋር፤ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ጋር በማጋጨትና ሲፈልግ ደግሞ የሌለ ብሄርንና ቋንቋን ፈልፍሎ የሚፈጥረው ህወሓት የቆመበት ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን እንደ ሃገርና መላው ሕዝቧን እንደ አንድ ሕዝብ ማገልገል አለመሆኑን ያለፉት 27 የስልጣን ዓመታት ይመሰክራሉ። ይህ የስታሊንን “የብሄር ጥያቄ” በተወላገደ፤ በተዛባና አግባብ በሌለው መልኩ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫነበት ዋና ምክንያት በብሄር ጭቆናና ነጻነት ስም የህወሓትን የበላይነት ለማጠናከር፤ የመሬት ነጠቃውንና የትግራይን ክልል መስፋፋት ዓላማ ስኬታማ ለማድረግ ነው።

ይህ የጠባብ ብሄርተኛና ጎጠኛ ቡድን እንዳለ ሆኖ፤ ለአገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪዎች ነን የምንለው የተቃዋሚው ክፍል አባላት አሁንም መልስ የምንሰጠው ለህወሓት አጀንዳ ነው (We continue to react to the TPLF agenda and fail to respond to Ethiopia’s crisis in a sustainable and proactive manner). እኔን በጣም የሚያሳስቡኝ ብዙ ብሄራዊ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ፤ በየጊዜው የሚነሱትን የጋራ ብሄራዊ ችግሮች በወዳጅነት፤ በመልካም ጉርብትና፤ በመደጋገፍ፤ በመቻቻል በድርርድና  በውይይት ይፈታ የነበረው የኢትዮጵያ ታላቅ ሕዝብ ዛሬ እርስ በርሱ እንዲጋጭ፤ እርስ በርሱ እንዳይተማመን፤ እርስ በርሱ እንዳይደጋገፍ፤ እርስ በርሱ ተወያይቶ ችግሮቹን እንዳይፈታ፤ የጋራ አገሩን ተባብሮ እንዳይጠብቅ እያደረግነው ነው። እኛ ራሳችን ከህወሓቶች መለየት መቻል አልብን።

ህወሓት የኢትዮጵያ ሕዝብ እርጋታ እንዲኖረው ተመኝቶና ሰርቶ አያውቅም። Waves በተባለው መጽሃፌ በመረጃ እንዳሳየሁት፤ ይህ ቡድን የሚገዛበት ዘዴ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በመከፋፈልና በማጋጨት ነው። It keeps Ethiopians in suspense by creating perpetual uncertainity about the future. ሕዝብ የሚመጣው ምን እንደሚሆን የማያውቅ ከሆነ ያለው ወይንም የአሁኑ አገዛዝ ከማናውቀው ይሻል ይሆናል (የባሰ አታምጣ) ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ይገባል።  የዚህ የመንፈሳዊና የማህበረሰባዊ እርጋታ አለመኖር ዋና ትሸካሚና ዋጋ ከፋይ የሆነው የአማራው ብሄር ነው።

ህወሓት ስልጣን ከመያዙና ስልጣን ከያዘ በኋላ በጎንደሬውና በሌላው የአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸማቸውን ድርጊቶች ብንመረምር፤ በጎንደር ክፍለ ሃገር በወልቃይት፤ በሰቲት ሁመራ፤ በጠለምትና ሌሎች ቁልፍ ናቸው ብሎ በገመታቸው ቦታዎች ሁሉ ጥናቶች አካሂዷል። አቋሞች ወስዷል። የጎንደሬው ነዋሪ ሕዝብ የሚከፋልበትን ሁኔታዎች አመቻችቶ ነበር። የጎንደር ድንበር፤ የቅማንት፤ የወልቃይት፤ የላሊበላ፤ የዋልድባና ሌሎች የወደፊት የካርታ አቀራረጽ ጥያቄዎች ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም። በእነዚህ አካባቢዎች ብዙ ንጹህ ጎንደሬዎች ተገድለዋል፤ እንዲሰወሩ ተደርገዋል፤ ተሰደዋል፤ መሬታቸውን ተቀምተዋል። በመሃል አገር፤ በደቡብ፤ በኦሮምያና በሌሎች ክልሎች በህወሓት ቀስቃሽነት ብዙ አማራዎች ተጨፍጭፈዋል። የአማራ ብሄር አባላት ከጉራ ፈርዳ፤ ከጋምቤላና ከቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ እንዲሰደዱ ተደርጓል።

የጎንደር/ቤጌምድር ክፍለ ሃገር የሚታወቀው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አስተጋጅ በመሆኑ ነው። ቤተ ኢዝራኤል፤ ቅማንት፤ አማራ፤ አገውና ሌሎች ተጋብተው፤ ተዋልደው፤ ተጉራብተውና ተደጋግፈወ የሚኖሩበት ክፍል ሃገር ነው። ቅማንቱና አማራው አንድ ባህል፤ አንድ ኃይማኖት፤ አንድ ቋንቋ ወዘተ ይጋራል። ተጎራብቶ ይኖራል። ዛሬ ህወሓቶች የጠነሰሱትና ስኬታማ ለማድረግ ያቀዱት ጎንደሬው፤ በተለይ አማራው የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት እንዳይሆን ነው። ወንድማማች፤ እህትማማች የሆነው የቅማንትና የአማራው ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲገዳደልና ለህወሓቶች የመሬት ነጠቃና የትግራይ መስፋፋት እቅድ በሮች እንዲከፍት ወይንም እንዲያመቻች እየተደረገ ነው። ይህ በጎንደሬው ላይ የሚደረግ የህወሓት ሴራ ለኢትዮጵያ ህልውና፤ ዘላቂነት፤ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት፤ እርጋታ፤ ሰላም፤ ዘላቂና ፍትሃዊ እድገት ጸር ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሊቃወሙት ይገባል።

በእኔ ጥናትና እምነት ኢትዮጵያ ብትፈራርስ የሚጎዳው አንድ ብሄር ወይንም አንድ ኃይማኖት አይደለም። ሁሉም የብሄር አባላት፤ ሁሉም የልዩ ልዩ ኃይማኖት አባላት፤ ሁሉም መደቦች ይጎዳሉ። የመቶ ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ይከሰታል። የተገገኘው የእድገት ውጤት ይወድማል። አይቮሪ ኮስትን፤ ኢራክን፤ ሶሪያን፤ ሊቢያን፤ አፍጋኒስታንን፤ የመንን፤ ሌባኖንንና ሌሎችን በእርስ በርስ ጦርነት የመከኑና የደቀቁ አገሮች ታሪክ መመራመሩና ትምኅርት መሸመቱ ይበጃል እላለሁ።

ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በመከፋፈል፤ በማጋጨትና በማጣላት የሚሸመት የፖለቲካ ስልጣንና የኢኮኖሚ የበላይነትአጥፊ መሆኑን ብዙ ተመራማሪዎች ተችተውታል። ለግል፤ ለቤተሰብ፤ ለቡድን፤ ለፓርቲ፤ ለጎሳና ለሌላ ወገናዊ ጥቅም ተብሎ ሕዝብን ከሕዝብ፤ ኃይማኖትን ከኃይማኖት መለያየት (Divide and Rule or Divide and Conquer or Divide and Exploit or Plunder) ለተወሰነ ጊዜ የበላይነት እንደሚያስገኝ፤ ለኃብት ማካበቻ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል የአፍሪካ አገሮች ታሪክ ይነግረናል። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጫነው የአገዛዝ ሸክምልክ የቅኝ ገዥዎችን የሚመስል ስርዓት ኢትዮጵያን ፈጽሞ ወደሚያጠፋበት ደረጃ እያመራት ነው። ለምሳሌ፤ በወልቃይት ጠገዴ፤ በጋምቤላ፤ በዖሞ ሸለቆ፤ በኦጋዴን፤ በአዲስ አበባ፤ በኦሮምያና በሌሎች ቦታዎች የሚካሄደው የተፈጥሮ ኃብት ነጠቃ፤ ባለቤትነት ፉክክርና በአንድ አንድ አካባቦዎች የእርስ በርስ ጦርነት ሕብረተሰቡን እያመሰው ነው።

በመሬት ነጠቃ፤ ቅርሚትና ቅጥ ያጣ ሽሚያ ማን ይጠቀማል? ማን ይጎዳል? ብለን ብንጠይቅ የሚጎዳው ተራው ኢትዮጵያዊ ነው። የሚጠቀሙት የውጭ ኃይሎችና የአገር ውስጥ የጠባባ ብሄርተኛ የጥቅም ነጋዴዎች፤ በተለይ የህወሓት ባለሥልጣናት፤ አባላትና ታማኞች ናቸው።

የተፈጥሮ አደጋዎችና ሰው ሰራሽ ቀውሶች ለኢትዮጵያ ቀጣይነት አደጋዎች ናቸው።

የአንድ አገር ቀጣይነት ታሪክ ከአገር ወዳድ አመራር ጋር፤ ከፍትህ-ርትህ ጋር፤ ከፍትሃዊ እድገት ጋር፤ ከሕግ የበላይነት ጋርና ከእውነተኛ፤ ሕዝብን የስልጣኑ ባለቤት ካደረገ አገዛዝ (Governance) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ይህ ሲሆን ሁሉም የሃገሩ ባለቤትነት ስሜት ይኖረዋል። ለሃገሩ የሚቆረቆር ሕዝብ ጠላትን አያስገባም። አንዱ ሌላውን ካገለለ፤ አንዱ ሌላውን ከጨቆነ፤ አንዱ ሌላውን ከኮነነ፤ አንዱ የሌላውን የተፈጥሮ ኃብት ነጥቆ ለራሱ ካደረገ ወዘተ ግን የጋራ አገር የሚባል ጉዳይ ደብዛው ይጠፋል። የእርስ በርስ ጦርነትና እልቂት አይቀርም። ገዢው ፓርቲ የፈለገውን ያክል ወታደራዊ ኃይል ተጠቅሞ ጭፍጨፋና አፈና በተራው ሕዝብ ላይ ቢያካሂድ ሰላም አይኖርም፤ እርጋታ አይኖርም። እድገት አይታሰብም።

ዛሬ በኢትዮጵያ በመሬት ላይ የሚታየው የፖለቲካ ሁኔታ ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር–ለምሳሌ፤ ከድርቅ ረሃብ፤ ከድህነት፤ ከአገር ውስጥ የሕዝብ ፍልሰት፤ ከተስቦ በሺታዎች ወዘተ—ጋር ሲደማመር ኢትዮጵያን ወደማይመለስ ውድቀት እንድታመራ ያደርጋታል። ይህ፤ ከመጥፎ አገዛዝ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ የሚታየው ክስተት ምንን ያንጸባርቃል? ብየ ራሴን ስጠይቅ መልሱ ሆነ ተብሎ የተጸነሰውና ሊቆም የማይችል የሚመስለው የብሄር የማንነት ጥያቄ እየተስፋፋና እየከረረ መሄዱን ያሳያል የሚል ይሆናል። የማንነት ጥያቄ፤ ለምሳሌ የቋንቋ፤ የኃይማኖት፤ የሞያና ሌላ ምንም አያከራክርም። በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የተለየ የሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ሁኔታ አለ። ለምሳሌ፤ ይህ መሬት የእኔ እንጅ የአንተ አይደለም፤ መለስ ዜናዊ እንደተናገረው የእኔ “ብሄር እንቁ ወይንም ወርቅ ነው።” የእኔ ኃይማኖት ከአንተ ኃይማኖት ይበልጣል፤ ይቀድማል። ከአንተ ጋር የምጋራው ታሪክ የለኝም  ወዘተ።

የማንነት ጥያቄ የፖለቲካ ስልጣንና የጥቂቶች የኃብት ማካበቻ ጥያቄ እየሆነ ሲሄድ መቆሚያ የለውም። ዛሬ አዲስ የጎሳና የብሄር ማንነት እየተፈለፈለ ከቀብሩ እንዲወጣ ይደረጋል። ማንነት በተዛባ መልኩ ሲቀርብ፤ ከሌላው ጋር መለያ፤ ሌላውን ማግለያ፤ የግጭቶች መነሻና መድረሻ ይሆናል። ሩዋንዳን ወደ እልቂት ያመራት ይኼው የተለጠጠ የማንነት ጥያቄ ነው። እኛ ገና ከዚህ እልቂት አልተማርነም!!

ይህ ሆነ ተብሎ ጥልቀትና ስፋት እንዲያገኝ የተደረገው የጎሳና የኃምኖት ማንነት ሂደት፤ ኢትዮጵያዊነት የሚለው መለያችን ፈጽሞ እንዲጠፋና ኢትዮጵያዊያን እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ የኦጋዴን ሶማሌዎች ከኦሮሞው ወገኖቻቸው ጋር፤ የአማራ ብሄር አባላት ከትግራይ ብሄር ወገኖቻቸው ጋር እንዲጋጩ ተደርጓል። በጎንደር የተከሰተው ሕዝባዊ አመጽ እየተባባሰ በመሄዱ የተነሳ ህወሓት የመሬት ነጠቃ ዓላማውን ስኬታማ ለማድረግ በሚል “የከፋፍለህ ግዛው” ጥበብ የቅማንት ብሄረሰብ ከአማራው የተለየ መሆኑን፤ ወልቃይት ጠገዴ ከሰፊው የጎንደር አማራ ሕዝብ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን እያስተጋባው ነው። ማንኛውም የወልቃይት፤ ማንኛውም የቅማንትና ሌላ ከፋፋይና የመሬት ነጠቃ ስተራተጂ የሚጸነሰውና የሚቀየሰው መቀሌ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። አዲስ የወልቃይት ታሪክ ተጸንሶ የሚሰራጨው ከዚሁ ክልል ነው። ኢላማው የአማራው ብሄር በሙሉ የተፈጥሮ ኃብት እንዳይኖረው ለማድረግ ነው።

ህወሓት አንዱን የጎንደር መለያ የሆነውን “የዳሸንን ተራራ የትግራይ አካል ነው” ብሎ ካሪኩለም አውጥቶ ሕዝብ ሲነሳበት ከሳበው ወዲህ ምንም ሊታመን የሚችልበት ሁኔታ የለም። ዋልድባና ላሊበላ የትግራይ አካል ነው ቢል ምን ያስደንቀናል? ይህ ቡድን በጎንደርና በሌላው ሕዝብ ላይ የሚያደርገው ሴራ ሊያሳስብንና ሊያንቅሳቅሰን ይገባል የምልበት ዋና ምክንያት አብዛኛዎቻችን አሁንም ከእንቅልፋችን ስላልነቃን ነው።

ችግሩ እኛው ነን
ችግሩ ህወሓት ብቻ አይደለም። ህወሓት የተቋቋመው ለጎንደር ወይንም ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም አይደለም። ህወሓት የተመሰረተው ለራሱና ለቆመለት ለትግራይ ብሄር ጥቅም ነው። በተመሳሳይ፤ የፌደራሉ መንግሥት አስታራቂ በመሆን ፋንታ ሁኔታውን የሚያባብስ ተቋም ሆኗል። ምክንያቱም፤ የፌደራሉን መንግሥት ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው ህወሓት ነው። ስለሆነም፤ የፌደራሉ መንግሥት የህወሓት መሳሪያና መገልገያ ነው።

ዲሞክራሲ የሚለው ቃል በኢትዮጵያ “ዋጋ ቢስ፤ ትርጉመ ቢስ” እንዲሆን ያደረገው ህወሓት ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በሕግ የበላይነት አያምንም። ሊያምንም አይችልም። በሕግ የበላይነት ካመነ ራሱን ያጋልጣል። ምዝበራ ለማካሄድ አይችልም። ግዙፍ ኃብት እየሰረቀ ለማሸሽ አይችልም። ሌብነት፤ ባለጌነት፤ ጉቦ፤ ሕዝብን ማጉላላት፤ አድልዎና ሙስና ከቁንጮው ሊወገድ ያልቻለበት መሰረታዊ ምክንያት አገዛዙ በሕግ የበላይነት ስለማያምን፤ ሕዝብ የፖለቲካው ስልጣን ባለቤት ስላልሆነ ነው። ኢትዮጵያና ሕዝቧ ተቆርቋሪ የላቸውም ብየ የምከራከረው ለዚህ ነው።

እኔን የአገር ውስጥ ሁኔታ ብቻ አያስጨንቀኝም። ዞሮ ዞሮ የአገር ቤቱ ሁኔታ ህብረት ካለ መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ። ሆኖም፤ ሌላ ልንክደው የማንችለው፤ ግን የማንነጋገርበትና የማንተቸው ክስተት አለ። ይኼውም፤ ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶችና በውስጥ ተገንጣይ ኃይሎች እየደማች መሆኗን ነው።

ይኼን አበይት ጉዳይ ለምን እንሸሸዋለን?

በሌላ አነጋገር፤ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ፤ ሆነ ተብሎ በተቀነባበረ በውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶችና በአገር ውስጥ ጠባብ ብሄርተኞች “ድርድር” መሳይ ሴራ “የተለያዩ አገሮች የሚገኙባት መልክዓ ምድር ናት” የሚለው ሰው ሰራሽ ታሪክና ብሂል ስር ሰዶባታል። ዘጠኝ ክልሎች፤ ዘጠኝ አገሮች!!!

በአጭሩ፤ ተገንጣይ ኃይሎችና የውጭ አጋሮቻቸው የሚሉት እንዲህ ነው። ኢትዮጵያ “የኢትዮጵያዊያን የጋራ አገር አይደለችም! ኢትዮጵያዊነት በአማራ ገዥዎች ተቀነባብሮ በሌሎች ብሄሮች ላይ የተጫነ የቅኝ ገዥዎች ታሪክ እንጅ የጋራ ብሄራዊ የዜግነት መለያችን አይደለም! ኢትዮጵያ የብሄሮች እስር ቤት ናት!! እነዚህና ሌሎች የፈጠራ ዜናዎችና አዲስ ታሪኮች ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት መርሆዎች ናቸው። አገር አፍራሾች ናቸው። ጠብ ጫሪዎች ናቸው። ጸረ እድገት ናቸው። ጸረ ሰላም ናቸው። ጸረ እርጋታና ጸረ ሕዝብ ናቸው። ለእውነተኛ ዲሞክራሳዊ ስርዓት ምስረታ ማነቆና ተግዳሮት ናቸው። ለኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች መግቢያ ወንፊቶች ናቸው። ይኼን በሚመለከት ብዙ ምርምርና ጥናት ያደረገውን የPaul Collierን መጻህፍት፤ በተለይ “Understanding Civil War: volume 1, Africa. ኮሌ በማያሻማ ደረጃ የእርስ በርስ ጦርነት ለአፍሪካ አገሮች ድህነት፤ ኋላ ቀርነት፤ መፈራረስና ጥገኝነት መሰረት መሆኑን በመረጃ አሳይቷል። ብዙ የተገነጠሉ አገሮች ለድህነትና ለተከታታይ መፈራረስ እንደተጋለጡ መረጃዎች አሉ።

የቀድሞዋ ዩጎስላቪያ ምሳሌ ናት። ኢስት ቲሞርም እንደዚሁ። በደቡብ ሱዳን የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ሕዝቡን ሊወገድ ለሚችል የረሃብ፤ የስደት፤ የበሽታ፤ የጥገኝነት፤ የእርስ በርስ እልቂት አደጋዎች አጋልጦታል። ይህ በኢትዮጵያ አይከሰትም የምንል ተሳስተናል፤ ሊከሰት ይችላል። በየቦታው የተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት ማየት አግባብ አለው።

ተገንጣዮችን ወደ ጎን ትተን በኢትዮጵያ ቀጣይነት፤ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነጻነት እምነት አለን ብለን አፋችን ከፍተን የምንናገረው ይህችን የጋራ አገራችን ከመፈራረስ ለማዳን ምን እየሰራን ነው?

መልሱን ለአንባቢ እተወዋለሁ።

ኢትዮጵያ ሃገራችን አሁንም ብዙ ተቆርቋሪዎች፤ ብዙ አገር ወዳዶች አሏት። ማንን ጠቅሸ ማንን ልተወው? ከዚህ ትንተና ጋር የሚዛመድ ጽሁፍ ሳገኝ ግን ላልፈው አልፈልግም። ልጠቅስ የፈለግሁት ኢትዮጵያዊቷ አገር ወዳዷ ወይዘሮ ከበቡሽ ተስፋየ የተባለች ደራሲ“ቴዲ አፍሮ” የዘፈነውን የአገር ፍቅር ዘፈን መንፈስ የሚያንጸባርቅ፤ በሁለት ገጾች ያበረከተችንን ግጥም ነው። ይህ ጽሁፍ ወደ መጽሃፍ ቢለወጥ አንድ ስንክሳር ይወጣዋል። ደራሲዋን በጣም እያመሰገንኩ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይኼን የእሷን ድርሰት እንዲያሰራጨው፤ እንድታሰራጨው አደራ አላለሁ።

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር
ትልቅ ነበርን ትልቅ ያሉን፤
ነፃ ህዝብ በነፃነት የከበርን፤
የሰው ልጆች አሃዱ የፍጥረታት መጀመሪያ፤
የአንድ እናት ልጆች የድንቅነሽ ዝርያ፤
በአንዲት ድንኳን ስር ተሰልፈን፤
ለኣንድ ሰንደቅ አላማ በአንድነት የዘመርን፤
ቀይ የቀይ ዳማ ጠይም ጥቁር ኢትዮጵያዊ የብሄሮች ጥምር፤
ባለአገር ባለፊደል፤ ባለባህል፤ ታሪክ ያለን…….
በአንድ ድንክ አልጋ እንዳሸን ወተን ገብተን፤
የምንቦርቅበት የወል ቤት የነበረን……
በዕውቀት በጥበብ የላቀው፤
ትውልድ ምን ይላል ወገኔ ስደት የተመቸው፤
መቼ ነው ሮጦ ለወገኑ የሚደርሰው፤
ዛሬ ተባብሮ ነገ የሚያፈርሰው፤
የት አለ ያትውልድ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ያሉት፤
የአበው ምሳሌ በክቡር በጨዋነት አንድ አድርገው ያሳደጉት!!
ማነው ጎበዝ የአያቱን ጋሻና ጦር የታጠቀ፤
የእምዬን ቃልኪዳን እምነትዋን የጠበቀ፤
ፍርድ አወቅ ትውልድ ጥፋተኛ ከሳሽ፤
የወገኑን ዕምባ የሚያብስ ደም መላሽ፤
በቃለ መሃላ የአንድነትን ብርሃን በኢትዮጵያ ላይ የሚፈነጥቅ፤
ማነው ጎበዝ ወገን አንገቱን ሳይደፋ ያለፍርሀት ያለጭንቀት ዜጋዋ ሀሳቡን በነፃነት የሚገልጥባት በሐቅ?
ፍትህ የነገሰባት፤ የዜጎች እኩልነት የተረጋገጠባት፤
ሁሉም እንደችሎታው ሰርቶ የሚያድርባት፤
የጋርዮሽ ባህልና ታሪክ  የሚጋሩባት፤
የጎሳ አጥር ፍርሶ የአንድነት ግንብ የሚገነባባት፤
እጅ ለእጅ ተያይዞ አንዲት ኢትዮጵያን የሚገነባ፤
ማነው? ደፋር ለአገሩ ቃል የሚገባ!!!”

ይህች እህታችን በሚቀሰቅስ ቋንቋ ያቀረበችውን ሃሳብ፤ ምክር፤ ጥያቄና ተግዳሮት ረጋ ባለ አአምሮ አስበንበት እስኪ ከአሁን በኋላ ለአዲሱ ዓመት፤ በአዲስ መንፈስ፤ በአዲስ ቆራጥነት፤ በአገር ወዳድነት፤ በብሄራዊ መግባባትና በዜጎች ትሥስር አስፈላጊነት አምነን፤ አፋኙን፤ ጨቋኙንና መዝባሪውን አገዛዝ አስወግደን፤ ሕዝብን የስልጣኑ ባለቤት በሚያደርግ፤ በሕግ የበላይነት፤ በፍትህ-ርትህ፤ በእውነተኛ የብሄሮችና የዜጎች እኩልነት፤ በዘላቂና ፍትሃዊ እድገት በሚያምን ዲሞክራሳዊ ስርዓት ለመተካት እንወስን።

አገር እየፈረሰች፤ ሕዝብ እያለቀሰና ልጆቹን ለስደት እየዳረገ፤ ቢያንስ ስምንት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን በረሃብ እየተሰቃዩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙስናና ከአገር ከሕግ ውጭ በሚወጣ ግዙፍ ኃብት እየደማ “አዲስ ዓመት” ለማክበር ህሊናችን መፍቀድ የለበትም። በዚህ አዲስ ዓምት የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ብንወስን ራሳችን አክብረን የዓለም ሕዝብ እንዲያከብረን ለማድረግ እንችላለን።

የአስተሳሰብ ለውጥ ካላደረግን ራሳችን በታሪክ ተጠያቂዎች መሆናችን አይቀርም።
የአስተሳሰብ ለውጥ አይቻልም የሚሉ ብዙ ናቸው። ሆኖም፤ አይቻልም ከሚሉት ይልቅ መጭውን ወይንም የወደፊቱን ዓለም ሁኔታ የሚለውጡት የአስተሳሰብ ለውጥ ይቻላል የሚሉት ናቸው።

ይህን ክፍል ለማጠቃለል ሁለት በመሬት ላይ የታዩ ምሳሌዎችን ላቅርብ።

አንድ፤ የጎንደር ሕዝብ እንደ ብረት በጠነከረ ሕብረት ዳር እስከ ዳር ተነስቶ በህወሓት/ኢህአዴግ አልገዛም ሲል የምግብ እጥረት ተከሰተ። በተለይ የተጎዱት በከተማ የሚኖሩ የቀን ሰራተኞች ነበሩ። ይኼ ደፋርና ጀግና ሕዝብ ችግሩን እንዴት ይወጣው ይሆን? እያልን የምንጨነቅ፤ በስደት የምንኖር ኢትዮጵያዊያን እንነጋገር ነበር። እኛን ቀድመውን የሄዱት ወገኖቻችን ያደረጉት አስደናቂ ስራ የሚከተለውን ይመስላል። ሕዝቡ ተነጋግሮ ትንሽ ያለው ምንም ለሌለው መስጠት ግዴታው ነው የሚል መርህ ተከተለና ለወገኖቹ ደረረሰላቸው። ይህን የተቀደሰ ስራ ስኬታማ ያደረጉት ወጣቶች ነበሩ። አንዲት ጀግና ጎንደሬ–ስሟ “የእኔ አበባ” ነው ሲሉ ሰምቻለሁ– እንጀራ ይዛ ለሌላቸው ምግብ ስታቀርብ የወያኔ አልሞ ተኳሾች ገደሏት። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ቁርስ እነጀራ ለተራቡ መስጠት ወንጀል ነው። ያስገድላል።

በዚህ አዲስ ዓመት ይህችን በለጋነቷ የተቀጨችና ታሪክ የሰራች ጀግና እህታችን ሳስታውስ ለጎንደር ሕዝብ ያለኝን አድናቆትና አክብሮት እየገለጽኩ ወጣቱን ትውልድ አደራ የምለው ይህችን ወጣት አትሩሳት ነው።

ሁለት፤ ህወሓት በጎንደር ሕዝብ፤ በተለይ በአማራው ሕዝብ ላይ ጦርነት ካወጀ አስርት ዓመታት አልፈዋል። አዲሱን ዓመት የሚያከብረው ለብዙ ሽህ ዓመታት በወንድማማችነት፤ በእህትማማችነት ማህበረሰባዊ ትሥስር (Social cohesion) ፈጥሮ፤ ተከባብሮ፤ ተዋልዶ፤ አንድ ባህል፤ አንድ ቋንቋ፤ አንድ አስተሳሰብ፤ አንድ ኃይማኖት ወዘተርፈ ተከትሎ የሚኖረውን የአማራና የቅማንት ሕዝብ፤ የጋራ ጠላቱን ትቶ እርስ በርሱ እንዲጫረስ፤ መሬቱን ተነጥቆ የተፈጥሮ ኃብት ድሃ እንዲሆን፤ እንዲሰደድ፤ ክብሩና ነጻነቱ እንዲገፈፍ፤ ለህወሓቶች የመሬት ነጠቃና የትግራይ መስፋፋት እቅድ ሰለባ እንዲሆን እየተደረገ ነው።

በጥቂት ቀናቶች ውስጥ ለቅማንት ብሄር የሚሰጠውን መሬት ለማጽደቅ ሬፈረንደም ይካሄዳል የሚል የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ህወሓት በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢህአዴግና “የአማራው ክልል” አስተዳደር ወስነዋል። የብሄር ተኮሩ አገዛዝ እድሜውን የሚያራዝመውና መሬቶችን የሚነጥቀው ሕዝብን ከሕዝብ በመለያየትና በማጋጨት ስለሆነ ይኼን ተንኮል የሚያውቀው የአማራውና የቅማንቱ ሕዝብ ሴራውን እያጋለጠው ነው።

ወጣት ጎንደሬዎች በየአካባቢው እየተዘዋወሩ የህወሓት ታዛዦችንና የተወሰኑ ለግል ጥቅማቸውና ለዝናቸው የቆሙትን “የቅማንት ሕዝብ” ተቆርቋሪዎች እያጋለጧቸው ነው።

የቅማንት ጥያቄ ከሕዝባዊው አመጽ በኋላ ለምን እንደ አዲስ ጉዳይ ብቅ አለ?

ከዚህ በፊት በሰፊ ጥናት፤ ምርምርና መረጃ እንዳሳየሁት “የቅማንት ጥያቄ” እንደ አዲስ ዓመት ስጦታ ለጎንደርና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረበበት መሰረታዊ ምክንያት የወልቃይት ጉዳይ እንዲረሳ፤ ሕዝቡ እንዲዘነጋው ለማድረግ ነው። አሁን ከቅማንት ጥያቄ ጋር አብሮና ተሳስሮ የሚካሄደው የውስጥ ደባ ከዚህ በፊት ከጎንደር/ቤጌምድር፤ ከወሎ፤ ከጎጃም የተነጠቁት መሬቶች የታላቋ ትግራይ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ፤ ወልቃይት ጠገዴ ቢያንስተከፋፍሎ ወደ ትግራይ ክልል እንዲጠቃለል ለማድረግ፤ የቅማንቱና የአማራው ዝብ እርስሕዝብ እንዲከፋፈል ለማመቻቸትና የትግራይ ክልል የበላይነቱን እንዲይዝ ለማድረግ ነው።

ልጠቅሰው የምገደደው አስኳል ጉዳይ፤ ይህን ሴራ የተረዳው የጎንደር ወጣት ትውልድ ተጻራሪውን እያደረገ መሆኑን ነው። ይህ ወጣት ትውልድ የሚለው እንዲህ ነው። “አማራውና ቅማንቱ አንድ ሕዝብ ነው። የሚጸሉየው በጋራ፤ የሚናገረው ቋንቋ የጋራ፤ አለባበሱ ተመሳሳይ፤ የሚያለቅሰውና የሚዘፍነው በአንድ ላይ፤ በአንድ ቋንቋ፤ የሚለብሰው ተመሳሳይ” እያለ ነው። በቅማንቱ ስም የሚነግዱት ጥቂት የቅማንት ተወላጆች ብቻ አይደሉም። ህወሓት የትግራይ ሰርጎ ገቦችን በየቦታው አስማርቶ ድምጽ እንዲሰጡ፤ እንዲቀሰቅሱ እያደረገ ነው። ሬፈረንደም ሲካሄድ እነሱ ከፍተኛውን ድምጽ እንደሚሰጡ ለመገመት አያስቸግርም።

በዚህ አዲስ ዓመት ጎንደሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እንዲያስቡበት የምጠይቀው ህወሓቶች የሚያደርጉት የተለመደ የከፈፍለህ ግዛው ስልት አሁንም ጎንደሬው ተከፋፍሎ እርስ በርሱ እንዲጋጭ፤ ጎደሬው ምንም እርጋታና ሰላም እንዳይኖረው ነው። በህወሓቶች ስሌት አማራውን፤ በተለይ ጎንደሬውን እርጋትና ሰላም መንሳት ለትግራይ ክልል “ተሃድሶ” ወሳኝ ነው። ቅማንቱ ከአማራው የተለየ ኑሮ የለውም፤ አማራው ከቅማንቱ የተሻለ ኑሮ አይኖርም። ሁለቱም የህወሓት ተጠቂዎች ናቸው።

በትምህርት፤ በጤና አገልግሎት፤ በመገናኛ፤ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፤ በምግብ ዋስትና፤ በመጸዳጃ፤ በተማ መስፋፋት፤ በአካባቢ እንክብካቤ (ለምሳሌ በዛፎች ተከላ፤ በውሃ ማቋት) ቅማንቱና አማራው ከትግራይ ሕዝብ ኋላ ቀር ነው። ጎንደሬው በሙሉ (ምንም ብሄር ሳይለይ) አሁን ባለበትም ሁኔታ ቢቀጥል ከትግራይ ክልል ሕዝብ ኑሮ ጋር ሊመጣጠን የሚችልበት ሁኔታ የለም። ምክንያቱም፤ የኢትዮጱያን የልማትና የድጎማ ባጀት በሙሉ የሚቆጣጠረው ህወሓት ነው። ህወሓት ከጎንደር የተፈጥሮ ኃብት፤ ለም መሬት ሲነጥቅና ወደ ትግራይ ክልል ሲያጠቃልል ሁኔታው እየተባባሰ ይሄዳል ማለት ነው።

ህወሓት መሬት ሲነጥቅና መሬት እየሸነሸነ “ለቅማንት ይሰጥ” ሲል ማን ይጠቀማል?

የመጀመሪያው ተጠቃሚ ወያኔ/ህወሓትና የትግራይ ክልል ነው፤

በተጨማሪ፤ የተማሩና ለህወሓት ታዛዢ የሆኑ ጥቂት ቅማንቶችና አማራዎች መጠቀማቸው አይቀርም።
አብዛኛው የቅማንትና የአማራ ጎንደሬ ግን በጣም ይጎዳል። ለቅማንትና ለጎንደር አማራ ወጣት ትውልድ የምመክረው እንዲህ የሚል ነው። ጎንደሬው እርስ በርሱ ከተጣላና እልቂት ከመጣ ሁለቱም ወገኖች ተጠቂ ይሆናሉ። በቅማንት ላይ የሚከተለ እልቂት የአማራው እልቂት ነው። በአማራው ላይ የሚካሄድ እልቂት የቅማንት እልቂት ነው። ወያኔ እርስ በርሳችን አጋጭቶ መግቢያውን እንዳመቻቸ ማወቅ አግባብ አለው።

በመጨረሻ፤ በቅማንቱና በአማራው መካከል የሚፈጠር እልቂት በቀላሉ አይፈታም። ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። በህወሓቶች ስሌት በጎንደሬው መቃብር ላይ ታላቋን ትግራይን ከመሰረትን ማንም አይነካንም የሚል ህልምና ቅዠት አለ። ህወሓት ለዘላለም ኢትዮጵያን ሊገዛ እንደማይችል በሌሎች ትንተናዎች ላይ በመረጃ አቅርቤአለሁ።

ይህን ክፍል ለመደምደም፤ ቅማንቶች ራሳቸውን ባያታልሉ ጥሩ ነው። በተመሳሳይ የጎንደር አክራሪ አማራዎችም መቻቻልን መምረጥ ግዴታቸው ነው። ህወሓቶች ከስልጣን ሲወገዱ አብሮ የሚኖረው ሕዝብ አማራው፤ ቤተ ኢዝራኤሉ፤ ቅማንቱ፤ ጎንደሬነቱን የተቀበለው ትግራዩ፤ አገውና ሌላው ነው። የሚመረጠው ጎንደሬነትና ኢትዮጵያዊነት ይሆናል ማለት ነው።

““““““““““““““““““““““““““““““““

ክፍል ሁለት፤ “የራሳችን ጠላቶች ራሳችን ነን” የሚለው በሳምንት ውስጥ ይለቀቃል።

የደራሲው መብት የተጠበቀ ነው (All Rights reserved)