September 16, 2017

ቆንጅት ስጦታው

በኦሮሚያ ክልል አወዳይ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ከ32 የማያንሱ የኦጋዴን የሱማሌ ክልል ተወላጆች ተገድለዋል

(ምንሊክ ሳልሳዊ ) ፦ እሳቱ ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ ሊበቃ ይገባል ። በውስጥም በውጪም በስሜትና በቁጭት የሚራገቡ ጉዳዮች ሀገርን ለአደጋ አጋልጠው ሕዝብን ዋጋ እያስከፈሉት ነው ።የጎሳ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ ውጥረት አስከትሏል ። ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችው የዘር ፖለቲካ በአፍሪካ ያልተደፈረ በአለም ያልታየ እጅግ አደገኛ በመሆኑ የሀገሪቷን ሰላም በተደጋጋሚ እያናጋው ነው ። መንግስት የፖለቲካ ቁማሩን እየተበላ ነው ። ውጤቱም ስህተትን እያስከተለ ነው ። የጎሳ ፖለቲካው ድንበር ለማስመር ደፋ ቀና ሲል በሚፈጥረው ችግር ከፍተኛ ሕዝቦ እየሞተ ነው ። በኦሮሞና በሱማሌ ሕዝቦች መካከል የተነሳው ግጭት የዚህ ፌዴራሊዝም አስከፊ ውጤት ነው ።

የዘር ፖለቲካ መጨረሻው ይህው ነው የዘር ፍጅቱ በሁለቱም በኩል እየተካሄደ ነው ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አወዳይ አካባቢ ከ32 የማያንሱ የኦጋዴን የሱማሌ ክልል ተወላጆች በአካባቢው በንግድና በተለያዩ ሁኔታዎች ለረጅም ጊዜ የኖሩ ንፁሃን የኦጋዴን ተወላጆች ተገድለዋል ። ከዚህ በታች የምታዩት ምስል በትላንትናው እለት በኦጋዴን ውስጥ የቀብር ስነስርዓት ሲፈፀም ነው ። የኦጋዴን ወንድሞቻችን በደረሰባችሁ ሃዘን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልቡ ተነክቷል እግዚአብሔር ያፅናችሁ። ሁሉንም ይበቃል ልንላቸው ይገባል ።