ዛጎል ዜና – በሚያስገርም እና በሚያሳዝን መልኩ የሶማሌ ክልልና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት ፌስ ቡክን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚያካሂዱትን ንትርክ እንዲያቆሙ መታዘዛቸው ተገለጸ። የሁለቱ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች አንዱ ሌላውን ተከትሎ የሚወራወሩት መግለጫ ” አይ መንግስት” የሚል ሃዘን የተሞላበት አስተያየት ሲሰጥበት ነበር። በተለይም የሶማሌ ክልል ከመስመር የወጡ ሃረጎችን እና ፍረጃዎችን በማካተት ሲያሰራጭ የነበረው መግለጫ እጅግ የወረደ እንደነበር በስፋት አስተያየት የተሰጠበት እንደነበር የሚታወቅ ነው።

Image may contain: one or more people, sky and outdoor

ሕዝብ ትዝብቱን ከሰጠና ሁለቱ አካኦች መስመር ለቀው በቃላት ሲሞሻለቁ ዝምታን የመረጠው ኢህአዴግ ዛሬ በዶክተር ነገሪ ሌንጮ አማካይነት በሰጠው መግለጫ ሁለቱ አካላት ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። ዶክተር ነገሪ እንዳሉት ማስጥንቀቂያው የተጠው በአቶ ሃይለማሪያም በኩል በስልክ ነው።

” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱንም አካላት በስልክ አገኝተዋቸዋል” ያሉት ነገሪ ሌንጮ ፣ ድርጊቱን ሃላፊነት የጎደለው፣ ችግሩን የሚያባብስና በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንን ነው ያስረዱት።

ለአገር ውስጥ የኢህአዴግ ሚዲያዎች መግለጫ የሰጡት የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትሩ ለተጠየቁት ሲመልሱ ብዙም መረጃ ያላቸው አይመስልም። ወይም የሚያውቁትን ለመናገር ጥንቃቄ ሲያበዙ የተምታታባቸው ይመስላሉ። የግጭቱ መንስኤ የህዝብ ለህዝብ ችግር እንዳልሆነ፣ የወሰን ችግሩም ቢሆን በስምምነት የተቋጨ መሆኑንን ያመለከቱት ነገሪ ሌንጮ ” ምክንያቱን በውል አይታወቅም” ሲሉ ተደምጠዋል። አያይዘውም ” እየተጣራ ነው” ብለዋል።

ከቀናት በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ እሳቸውን ጠቅሶ ገጭቱ ሙሉ በሙሉ በቆሙን ቢገልጽም፣ በዛሬ መግለጫቸው ” ግጭቱ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ዋለ ያለ ሰው የለም” ብለዋል። ሆኖም የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ ሙሉ በሙሉም ባይሆን አሁን ችግሩን ከክልሎቹ ሃላፊዎች ጋር በመሆን መቆጣጠሩን አመልክተዋል።

ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ መፈናቀሉን ያልሸሸጉት ሃላፊው የቀውሱ መንስኤእየተጣራ መሆኑን ከማስረዳት ውጪ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ፍንጭ እንኳን አልሰጡም። በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት መግለጫ ሲሰጡ የነበሩት ዶከተር ነገሪ በተደጋጋሚ ” የአንድ ሰው እንኳን ህይወት ሊያልፍ አይገባውም” በሚል ሃዘናቸውን ከመግለጻቸው ውጪ፣ እንደ ተቆጣ አገር አስተዳዳሪ አስረግጠው ከወከላቸው ክፍል ሕዝብን ግራ ከመጋባት የሚያላቅቅ ነገር አልተናገሩም።

ይህን ያህል ሰው ሲሞትና፣ በአገሩ ሰው መታወቂያው እየታየ እንደ ባዳ ሲባረር ዝም ብሎ የተኛው ኢህአዴግ በዚህ ጉዳይ ባህሉ ባይሆንም ሊያፍር በተገባ ነበር ሲሉ በርካቶች አስተያየት እየሰጡ ነው። ድሆች እድሜ ልካቸውን ከኖሩበት ቀዬ እየተዘረፉ ሲፈናቀሉ ” የኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል ዳንኪራ ላይ የነበረው ኢህአዴግ ቁብም አልሰጠውም ሲሉ ሰለባዎች ተናግረዋል። ኢህአዴግ መቀመጫን በሚፈታተን ጉዳይ ላይ ብቻ ያለ የሌለ አቅሙን ከመጠቀም ውጪ ለዜጎች መጎሳቀል ዳተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ የሚከሰስበት ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል።

አማራ መሆን ነውር ሆኖ ህጻናት ሳይቀሩ እንደ ወራሪ ሃይል ተቆጥረው ሲባረሩ የተወሰደ ርምጃ አልነበረም። ንጹሃን ገደል ሲጣሉ፣ ሲዘረፉ እና አዛውንቶች በመጦሪያ ዘመናቸው ባዶ ቀርተው መውደቂያ በማጣት ሲያነቡ የደረሰና ያስቆመ አካል የለም። ይህንን የሚያስታውሱ ወገኖች ዛሬ የሆነውን በማሰብ የነገ ተስፋቸው የተሟጠጠ ያህል እየተሰማቸው እንደሆነ እየገለጹ ነው።

አንድ አገር እመራለሁ የሚል አካል፣ 50 ሺህ ሰዎች በጭነት መኪና እየተጋዙ ሲባረሩ፣ ተገን ይሆነናል በሚሉት የመከላከያ ሰራዊት ፊት ሲረገጡና ሲገደሉ ከማየት በላይ አሳፋሪና ልብ የሚሰበር ጉዳይ የለም ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰለባዎች፣ ምን እየሆነ እንደሆነ እንደማይገባቸው በይፋ በቪኦኤ ተናግረዋል።

Image may contain: 2 people, crowd

ሰዎች ከጠመንጃ ውርደው በገጀራ ሲቆራረጡ፣ ሞተው ሲቃጠሉ፣የጎረቤት አገሮችን ሰላም አስከብራለሁ የሚለው ኢህአዴግ የት ነበርኩ ብሎ ለዳተኝነቱ ማስረጃ እንደሚያቀርብ መገመት እንደሚያዳግት አብዛኞች ይስማማሉ። በተግባር አርንቋ ውስጥ የወደቀውና ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ያለው ኢህአዴግ ይህንን ሁሉ እያየ ወደ አገራዊ እርቅ የማይሄድበት ምክንያት ምን እንደሆነ በትንሹ ማሰብ ለሚችሉ ሁሉ ግራ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ የአብዛኞች እምነት ነው።

Image may contain: indoor

በጎንደር አስር የማይሞሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ተፈናቀሉ በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል ለነበረው “ኢህአዴግ” ሌላው ህዝብ ሆኖ የመታየቱ ጉዳይ አነጋጋሪም አተያያቂም መሆኑንን የሚጠቁሙ ክፍሎች፣ የተቃዋሚ ሃይሎችም በተመሳሳይ ይህንን እልቂት እያዩ፣ የወደፊቱን በመገመት፣ የጋራ ግብ አስቀምጠው በህብረት ለመስራት መስማማት አለመቻላቸው ከኢህአዴግ በላይ የሚያስጠይቃቸውና ከንቱዎች የሚያሰኛቸው ነው። በሌላም በኩል ” ተቀጣሪ ” ሆነው የሚያገለግሉት ሰዎችም የወገኖቻቸውን ደምና አጥንት እየተመገቡ የሚኖሩ፣ ከሰው ደረጃ የወረዱ እንስሶች ተደርገው ሊታዩ እንደሚገባ በማህበራዊ ገጽ ላይ በብዛት ትችት እየቀረበ ነው።

ፎቶ ፌስ ቡክ

BYON