September 18, 2017

(EMF) ሰባት የቅማንት ቀበሌዎች አማራ መሆናቸውን በሰጡት ድምጽ ሲያረጋግጡ፤ አንድ ወረዳ የራስ አስተዳደር መምረጡን ደብርሃን ድረገጽ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

12 የሰሜን ምእራብ ጎንደር ቀበሌዎች እንዲካሄድ የተወሰነው የ “አማራ ወይንም ቅማንት” ህዝበ ውሳኔ በሕዝብ እንቢተኝነት በ4ቱ ቀበሌዎች ሊካሄድ ባለመቻሉ በስምንት ቀበሌዎች ብቻ በመደረጉ የሚታወስ ነው።

ትላንት እሁድ ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ በ 8 ቀበሌዎች ሲካሄድ የዋለው “የሕዝበ ውሳኔ” ምርጫ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት የተጠናቀቀ ሲሆን ለዚህ “ሕዝበ ውሳኔ” ዜጎች በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ውቴቱ በትላንት ምሽት የታወቀ ቢሆንም የምርጫ ቦርዱ በይደር አሳልፎታል።

የህወሃት መንግስት በጎንደር አማራ እና ቅማንት በማለት ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ለመከፋፈል ያቀደው ሴራ በሕዝብ ድምጽ ይክሸፍ እንጂ በህወሃት የተፈጠረው እና ለህወሃት የሚያገለግለው የምርጫ ቦርድ እንደተለመደው ውጤቱን ይገለብጠው ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።

የቅማንት ሕዝብ ያለፍላጎቱ ይህንን “ሕዝበ ዉሳኔ” እንዲሰጥ መደረጉ በራሱ፣ በህወሃት እና በብአዴን ባለስልጣናት የተዶለተ “የራስ አስተዳደር” ሴራ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ሕዝብ የዘረኞቹን ሴራ በድምጹ አክሽፎ በማንነቱ ላይ ወስኗል። ኮሮጆ የመገልበጥ አባዜ ያለው የምርጫ ቦርድ የሕዝቡን ድምጽ እንደገና ሊሰርቅ ቢሞክር አካባቢው ለከፍተኛ ብጥብጥ እንደሚዳረግ ሕዝቡ እየገለጸ ነው።