በሰሜን ጎንደር በተካሄደው ሕዝበ-ውሳኔ ተታፊዎች
አጭር የምስል መግለጫ በሰሜን ጎንደር የተካሄደው ሕዝበ-ውሳኔ ተታፊዎች

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በአራት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ የስምንት ቀበሌ ነዋሪዎች በቅማንት ራስን በራስ የማስተዳደር ወይንም እስካሁን በነበረው አስተዳደር ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ሕዝበ-ውሳኔ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም አካሂደዋል።

ህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም )እንዴት ይካሄዳል?

የኢህአዴግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ሕዝበ-ውሳኔዎች የተካሄዱ ሲሆን የመጀመሪያውና እስካሁን በአነጋጋሪነቱ የሚነሳው ኤርትራን ከኢትዮጵያ ተለይታ ሃገር የመሆን ጥያቄ የወሰነ ነው።

በተለይም ብሄርን መሠረት ካደረገው የፌደራሊዝም ሥርዓት ጋር ተያይዞ ለማንነታቸው ዕውቅና ይሰጠን የሚሉ እንዲሁም የአስተዳደር ድንበሮችን ለመለየት እና ነዋሪዎች ወደየትኛው አስተዳደር መካለል እንደሚፈልጉ ለማወቅ ሲባሉ የተካሄዱ አሉ።

እነዚህም ሕዝበ-ውሳኔዎች የኢትዮጵያ ምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 መሠረት አድርገው ይካሄዳሉ።

የህግ ምሁሩና በፌደራሊዝም ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረጉት አቶ ውብሸት ሙላት እንደሚሉት በሕዝበ-ውሳኔው መሠረት አብዛኛው ወደ መረጠው አስተዳደር ይጠቃለላል።

“ይህ እንግዲህ በህዝቦች መካከል ሊፈጠር የሚችልን ግጭት ለማስወገድ ህገ-መንግስታዊ መፍትሄ ነው” ይላሉ።

የቅማንት ዝበውሳኔ ምንድን ነው?

እንደ አቶ ውብሸት አባባል የቅማንት ሕዝበ-ውሳኔ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ውሳኔዎች ይለያል ።

እንደምክንያት የሚያስቀምጡትም በአንድ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአስተዳደር ወሰኖችን ለመለየት የተዘጋጀ መሆኑንና እንደ አዲስ የሚመሰረትን የአስተዳደር አካል ለመወሰን ሲባል የሚደረግ መሆኑን ነው።

”ከዚህ ቀደም ቀበሌን፣ ወረዳን ወይም ዞንን እንደ አዲስ ለማዋቀር በአካባቢው የሚኖረውን ማህበረሰብ ፍላጎት ለማወቅ ሲባል ሕዝበ-ውሳኔ ማደረግ አልተለመደም” ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ አቶ ውብሸት እንደሚሉት በ1999ኙ የሕዘብና የቤት ቆጠራ ላይ የቅማንት ማህበረሰብ ራሱን ችሎ ባለመቆጠሩ እና በሌሎችም ምክንያቶች የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ተነስቶ በ2007 ዓ.ም የአማራ ክልል ምክርቤት ‘ማንነቴ ይታወቅልኝ’ ያለውን ማህበረሰብ ሕዝበ-ውሳኔ ሳያደርግ በራሱ እውቅና ሰጥቷል።

እስካሁን የተደረጉ ዝበውሳኔዎች

በተለይም በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የተለያዩ ሕዝቦችና ብሄሮች አንድ ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ የሕዝበ-ውሳኔ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ።

ብሄርን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ቋንቋን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ግጭቶችን እያስከተሉ የሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል።

በሃገሪቱ ውስጥ ከተደረጉት ህዝበ ውሳኔዎች አንዱ የስልጤ ማህበረሰብ ማንነቴ ይታወቅልኝ የሚለው አንዱ ነው።

የስልጤ ህዝብ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ሥር የነበረ ሲሆን የተለያዩ ግጭቶችና ክርክሮችን ተከትሎ ሕዝበ-ውሳኔ ተደርጓል።

ይህም ውሳኔ የስልጤ ዞን እንዲመሰረትና ራሳቸውንም እንዲያስተዳድሩ አስችሏቸዋል።

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የተደረገውም ሕዝበ-ውሳኔ ከ400 የሚበልጡ ቀበሌዎችን ያሳተፈ ነው።

ሕዝበ-ውሳኔው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቀበሌዎች በኦሮሚያ አስተዳደር ሥር እንዲጠቃለሉ የተወሰነበት ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ኮንሶን፣ ደራሼን፣ ቡርጂንና አማሮን በአንድ ዞን ለማካተት በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ግጭት ተነስቶ የነበረ ሲሆን የክልሉ መንግሥትን በመቃወም ሕዝበ-ውሳኔ እንዲደረግ ከፍተኛ ጥያቄ ቀርቦ ነበር ።

በአንድ ዞን መጠቃለሉ ከፍተኛ የሆነ የበጀት መቀነስና ቀውስ ስለሚያደርስም ነበር ተቃውሞው የቀረበበት።

ዝበ ውሳኔ ምን ተፈቷል?

ምንም እንኳን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሕዝበ-ውሳኔዎች ቢደረጉም ውጤታቸው ግን እንደታሰበው አይደለም።

አቶ ብውሸት እንደዋና ማሳያነት የሚያነሱት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ተደርገው የነበሩትን ሕዝበ-ውሳኔዎች ባለማክበር በየጊዜው የተፈጠሩት ግጭቶችን ናቸው።
“ሕዝብ ከወሰነም በኋላ መልሶ ግጭት ሲከሰት እየተስተዋለ ነው። ለዚህ ደግሞ በአጠቃላይ የሕዝበ-ውሳኔ ሂደትና ከህጉ ጋር የሚያያዙ ችግሮች አሉ። እነዚህን መቅረፍ እስካልተቻለ ድረስ በትክክል እንዲመቱ የታሰቡትን ግብ ላያሳኩ ይችላሉ” ይላሉ።
ከነዚህም ጥንቃቄ ከሚያሻቸው ነገሮች ውስጥ ሕዝበ-ውሳኔዎቹ ፍትሃዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ስለሕዝበ-ውሳኔው ለሚመለከታቸው ሁሉ ተገቢውን ትምህርት መስጠትና ክርክሮች መደረግን የተመለከቱ ይገኙበታል ብለዋል።

http://www.bbc.com/amharic/41306705

SOURCE    –   BBC /amharic