ምርጫው አማራና ቅማንት አንድ ይሁን አይሁን አልነበረም! ምርጫው ከርስት የመነቀልና ያለመነቀል ነበር!

ትናንት “እቤታችሁ ዋሉ፤ አትምረጡ” ያሉትም ሆኑ ዛሬ “ቅማንት አማራ ነኝ ብሎ መርጧል” እያሉ ያልነበረና ያልተፈጠረ ተረት የሚያወሩት እኩል እንቅፋቶች ናቸው። እነዚህን ሁለቱንም አዘናጊ አካላት እንዲታረሙ መምከር ያስፈልጋል።
በተለይ ይሄ ዛሬ ብቅ ያለው የወላዋይ ድምጽ በጣም አሳፋሪ ነው። ቅማንት ለመምረጥ በቅማንትነት ተመዝገቧል። አማራ በአማራነት ለመምረጥ ተመዝግቧል። ምዝገባው ላይ አብላጫው ድምጽ የአማራው ነበር። ይሄ አብላጫ ድምጽ በምርጫው አሸንፏል። ነገር ግን ወላዋዮች አዲስ ተረት መፍጠር ይዘዋል።

የዚህ ተረት ታሰበበትም አልታሰበበበትም ጎጅ ጎን አለው። ነገ ከነገ ወዲያ ዛሬ የተሸነፈው የቅማንት ኮሚቴ “ድምጼን ለአማራነቴ ሰጥቸ ነው እንጅ አሸንፍ ነበር፤ ስለዚህ ምርጫ እንደገና ይደረግልኝ” እንዲል በር የሚከፍት ነው።
ለቅማንትነቱ የመረጠን የትግሬ ወዶገብ የቅማት ኮሚቴ ያላደረገውን ለአማራነት መርጧል እያሉ ማቆላጳጰስ ወላዋይነት ብቻ ነው። የአማራና ቅማንትን አንድነት በዚህ አይነት ተረት ማምጣት አይቻልም። ቀድሞም ህዝቡ አንድ ነበር፤ ደጋግመን ተናግረናል። ነገር ግን ይሄንን ቅዱስ የአንድት መንፈስ በመጣስ በአማራው ህልውና ላይ ቢላ ይዞ የሚዘዋወር የቅማንት ኮሚቴ መጣ።

ይሄንን ለመቀልበስ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ መረጠ፤ እንቅልፉን ሳይተኛ ድምጹን ጠበቀ፣ በህወሀት የቀረበለትን መደለያ ከአማራነቴ አይበልጥብኝም ብሎ ውድቅ በማድረግ ርስቱን አስከበረ። በዚህም ቁርጠኝነቱ ለምርጫ የተዘጋጀውን እና መላውን አማራ ለማፈናቀል እቅድ የነበረው የቅማንት ኮሚቴ በምርጫው ተሳተፈ፤ በድምጽ ብልጫ ግን በሰፊው ተዘረረ። ከዚህ ውጭ የሌለ ነገር ማራገብ ወላዋይነት፣ አስመሳይነት ወይም ከሀዲነት ነው። ህዝቡ ገና ተሰልፎ የዋበለበት እግሩ ህመም ሳይለቀው፤ እንቅልፍ ሳይተኛ ያደረበት ራሱ እየዞረበት ባለበት ሰአት፤ የትግሉን ፍሬ ሰርዞ ያልነበረ ተረት መደላለዝ ክህደት ነው።

ይሄንን ግጭት ያስወገደውና አንድነቱን ያመጣው ይሄ ቅማንት አንድነትን መረጠ የሚለው ተረት ሳይሆን አማራው በነቂስ ወጥቶ መምረጡ ብቻ ነው። መሬት ላይ የሌለን ነገር በተረት አንድ ነን ማለት ለኢትዮጵያም አልበጃት። እንዲህ አይነቱ የሽፍንፍን ጉዞ ነው አገሪቷን መሰረቷን የናደው።

በ12 ቀበሌዎች ለምርጫ የተመዘገበ ህዝብ ከ95 በመቶ በላይ አማራ ሲሆን እጅግ ያነሰው ቁጥር ቅማንት ነበር፡፡ የአሁኑ ውጤትም የሚያሳየው ያንን ቀድሞ የታወቀ ቁጥር ነው፡፡ አንዱም ምርጫ 100 ለ 0 አልተጠናቀቀም፡፡ ይልቅም አማካዩ የምርጫ ውጤት 95 ለ 5 አካባቢ ነው፡፡ ይህ ውጤት አማራና ቅማንት አንድ ይሁን ወይስ አይሁን አልነበረም፡፡ ይህ ምርጫ አማራ ከርስቱ ይነቀል ወይስ ርስቱን ያስከብር የሚል ነበር፡፡ ስለዚህ የውጤቱ እውነታ አማራው በነቂስ ወጥቶ በመምረጡ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው ቅማንቶች ማሸነፍ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ አማራ በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች አማራው ሊያሸንፍ ግድ ነው፡፡ ውጤቱ የተመዘገበው የቅማንት ቁጥር ለአማራነት እንደመረጠ አያሳይም፡፡ የተመዘገበ ቅማንት ለአማራነት መምረጥ እና አለመምረጡን የምናረጋግጠው ያለ ህዝበ ውሳኔ በተከለሉት 42 ቀበሌዎች ውስጥ በቀጣይ በሚደረገው ህዝበ-ውሳኔ ላይ ነው፡፡

ወገናችን በአደባባይ ወጥቶ ርስቱን አስከብሯል፡፡ ህዝብ ደግሞ በሰአታት ልዩነት ይሄንን ድል ሌላ ገጽታ ሰጥቶታል፡፡ ይሄ ህዝብ በራሱ ልጆች እንዲህ እየተካደ ነው እዚህ የደረሰው እኮ፡፡ ቅማንት ነኝ ብሎ የመረጠ ህዝብ እንደሌለ ማስመሰሉ ራስን ማሞኘት ነው፡፡