By ዮሐንስ አንበርብር 

16 Sep.2017

የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ከኳታር መንግሥት ጋር በፈጠሩት ግጭት ምክንያት ጫና የተፈጠረበት አልጄዚራ በኢትዮጵያ ቢሮውን ከፈተ፡፡
አልጄዚራ የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮውን የከፈተው በአዲስ አበባ ስናፕ ፕላዛ ሕንፃ ላይ ሲሆን፣ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችም በይፋ ምረቃው በተከናወነበት ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ተገኝተዋል፡፡
የቀድሞ የአልጄዚራ ዘጋቢ በኋላም የቱርክ የዜና ወኪል (አናዶሉ) የአዲስ አበባ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ መሐመድ ጠሃ ተወከል ለአዲስ አበባ የአልጄዚራ ቢሮ ዳይሬክተርነት ተመድበዋል፡፡
አቶ መሐመድ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናዋ የጎላ በመሆኑ የቢሮው መከፈት ለአልጄዚራ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ከዜና ዘገባዎች በተጨማሪ ዶክመንተሪ ፊልሞችን በአፍሪካ ኅብረት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያና አካባቢዋ ላይ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኳታር እንዲሁም የኳታሩ የሚዲያ ተቋም አልጄዚራ በጠብ የተቃኘ የኋላ ታሪክ እንዳላቸው ይታወሳል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2008 የኢትዮጵያ መንግሥት በኳታር የሚገኘውን ኤምባሲውን በመዝጋት አምባሳደሩን ጠርቶ ነበር፡፡ በወቅቱ የተሰጠው ምክንያትም የኳታር ወታደሮች በሶማሊያ የሚገኘውን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት በመወገን የኢትዮጵያ ወታደሮችን ወግተዋል፣ አልጄዚራ በተደጋጋሚ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የሚያቀርበው ዘገባ ጨለምተኛ ነው የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ይህንን የኢትዮጵያ ወቀሳ መሠረተ ቢስ እንደሆነ በወቅቱ የገለጸችው ኳታር፣ ተመሳሳይ ዕርምጃ በመውሰድ የኢትዮጵያ ኤምባሲዋን መዝጋቷ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በ2010 በለንደን በተደረገው የሶማሊያ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ጉባዔ የኳታር አሚርና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተገናኝተው ችግሩን ፈትተዋል፡፡
ከወራት በፊት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው የባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች ጥምረት ከኳታር ጋር ግጭት ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ጥምረት ውስጥ የሚገኙት ባህሬን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ግብፅ እንዲሁም ሳዑዲ ዓረቢያ ኳታር አሸባሪዎችን በገንዘብና በመሣሪያ እንደምትደግፍና አካባቢውንም እየበጠበጠች ነው በሚል ወቀሳ የአየር ትራንስፖርትና ማዕቀቦች መጣላቸው ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም ኳታር ከእነዚህ አገሮች ጋር ግንኙነቷን ለማደስ ከፈለገች አልጄዚራ እንዲዘጋ መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡
በዚህ ግጭት ሳቢያ የባህረ ሰላጤው አገሮች በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ አገሮች ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ ጫና እያደረጉ ነበር፡፡

Source   –   Ethiopian Reporter