18Sep, 2017

ነአምን አሸናፊ

ሰማያዊ ፓርቲ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መስከረም 28 ቀን 2010 .. ለማድረግ ባቀደው ሰላማዊ ሠልፍና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት፣ በሐራምቤ ሆቴል ጠርቶት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ባልታወቀ ምክንያት መከልከሉን አስታወቀ፡፡

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፓርቲው በወቅታዊና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ለመስጠት ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 .. ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም፣ የፓርቲው ኃላፊዎች ሥፍራው ሲደርሱ የሆቴሉ ኃላፊዎች መግለጫውን መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውላቸዋል፡፡

በጉዳዩ ግራ የተጋቡት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችም መግለጫውን ለመስጠት ለሆቴሉ ክፍያ የፈጸሙበትን ደረሰኝ በማሳየት ማብራሪያ ቢጠይቁም፣ የሆቴሉ ኃላፊ ምንም ዓይነት ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት  የፓርቲው አመራሮችና የሆቴሉ ኃላፊዎች ለአንድ ሰዓት ያህል ክርክር ቢያደርጉም፣ የሆቴሉ ኃላፊዎች በአቋማቸው በመፅናታቸው ፓርቲው መግለጫውን በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽሕፈት ቤት ለማድረግ መገደዱን አስታውቋል፡፡

በመኢአድ ዋና ጽሕፈት ቤት የተሰጠውን መግለጫ የመሩት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አበበ አካሉና የጥናትና ስትራቴጂ ኃላፊው አቶ አሮን ሰይፉ ናቸው፡፡

‹‹በሐራምቤ ሆቴል የጠራነው ጋዜጣዊ መግለጫ መከልከሉ ሥርዓቱ ምን ያህል አፋኝ እየሆነ እንደሄደ ያሳያል፡፡ መንግሥት ከዚህ ቀደም ከተፈጠረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምንም ዓይነት ትምህርት አለመውሰዱን በትክክል የሚያሳይ ነው፤›› ሲሉ አቶ አሮን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው ስብሰባውን ለማድረግ ለሆቴሉ 4,400 ብር ከፍሎ እንደነበር ገልጿል፡፡ አቶ አሮን፣ ‹‹ይኼ ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ ስብሰባ አይደለም፡፡ አንድ ፓርቲ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ ይኼን ማድረግ አለመቻል ደግሞ አፈናው ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ሁኔታ ቢያሟሉም ጋዜጣዊ መግለጫውን ከመስጠት መከልከላቸውን ያወሱት አቶ አበበ፣ ከክልከላው ጀርባ ማን እንዳለ ለማወቅ መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት መስከረም 28 ቀን 2010 .. ለማድረግ ስላቀደው ሰላማዊ ሠልፍ ከመግለጽ በተጨማሪ፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መሀል የተፈጠረው ግጭት ለአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ከመሆኑ አንፃር የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን አግባብ እንዲያመቻችም ጠይቋል፡፡

Author

anon