19Sep, 2017

ዘመኑ ተናኘ

ለዓመታት በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ አሸባሪ ቡድኖችን ሲደግፍና ሲያስታጥቅ እንደቆየ የሚነገርለት የኤርትራ መንግሥት፣ በአሁኑ ወቅት የሥጋት ምንጭ የማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2009 .. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ የኤርትራ መንግሥት አሁን የሥጋት ምንጭ የማይሆንበት ደረጃ ላይ ቢደርስም ዓለም ተለዋዋጭ ከመሆኗ አንፃር አሁን ካለው ሁኔታ ጋር የሚመጥን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መከተል ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ ለመከተል መወሰኑን ያስታወቀ ቢሆንም፣ ይኼ አዲስ ፖሊሲ ምን እንደሆነና መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን እንደማይታወቅ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡ አዲሱ ፖሊሲ ለሕዝብ ሳይገለጽ ረዥም ጊዜ ሊወስድ የቻለው አዲስ ሥልት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን በተመለከተ ሦስት ፖሊዎችን ሲከተል መቆየቱንም አብራርተዋል፡፡ እነዚህም ውስጣዊ አቅምን በማጠናከር የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን እንዳይተነኩስ ማድረግ፣ ሁለተኛው ከማተራመስ ባህሪው እንዲወጣ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወንና አስፈላጊ ሲሆን ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ የሚባሉት መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በ2010 .. በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታካሂደውን የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኗን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች በተወከሉ ሚሲዮኖችና በዋናው መሥሪያ ቤት በሚገኙ የሥራ ሒደቶች አማካይነት የተቀናጀ ጥረት በማድረግ፣ አገራዊ ተልዕኮን ለመወጣት የተጠናከረ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

2010 .. ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጥቅሟና መብቷ እንዲጠበቅና በሌሎች መንግሥታት እንዲከበር ማድረግ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ቅርበት እንዲጠናከር መሥራት፣ ከሌሎች መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርጋቸውን ግንኙነት ማስተባበር፣ የዳያስፖራውን ተሳትፎና መብት ማረጋገጥ፣ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው በኩል ኢንቨስትመንት መሳብና ሌሎች ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡

2009 .. በተከናወነው ሥራም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን፣ ውክልናን በማስፋትና አጋርነቶችን በመመሥረት በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ተደማጭነት ለማሳደግና ጥቅሟን ለማስጠበቅ የሚያስችል ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ኅብረትን ጉባዔ ሁለት ጊዜ በማስተናገድ በመጀመርያው 43፣ በሁለተኛው ደግሞ 24 ፕሬዚዳንቶች፣ በድምሩ 67 ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ከ20 ሺሕ በላይ እንግዶች የፕሮቶኮል ድጋፍ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

... መስከረም 12 ቀን 2017 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በኒውዮርክ እንደተጀመረ ያስረዱት አቶ መለስ፣ በዚህ ሳምንት በሚካሄደው ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደሚገኙና ጉባዔውን በሊቀመንበርነት ይመሩታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

ዘመኑ ተናኘ‘s blog

Author

anon