September 19, 2017

ቆንጅት ስጦታው

በሊሙ የዐማራ ተወላጆች ንብረታችን እየወደመ ጥበቃ የሚያደርግ የሕግ ከለላ አጥተናል አሉ፤

ብራና (መስከረም 9 ቀን 2009)፤ በጂማ ዞን ሊሙ ገነትና ሊሙ ኬሳ አካባቢ ከመስከረም መባቻ ጀምሮ የዐማራ ተወላጆች ንብረትና ምርት እየወደመ እንዳለ ተወጎጂዎች ዛሬ ለብራና ሚዲያ ተናግረዋል፡፡

ንብረታቸው በጅምላ እየወደመባቸው እንደሆነ የሚናገሩት በስልክ ያነጋገርናቸው ዐማሮች አካባቢውን በአስቸኳይ ለቀው ካልወጡ እንደሚገደሉም ጭምር ተነግሯቸዋል፡፡ ተጎጂዎች እንደሚሉት ሕይወታችን ለማዳን ልጆቻችንና አቅመ ደካማዎችን ለማስወጣት ስንፈልግ ደግሞ መውጫ መንገዶች ታጥረው መንቀሳቀስ አልቻልንም ብለዋል፡፡

በርካታ የዐማራ ተወላጆች በሊሙ ልዩ ቦታው ሰርጤ በተባለው ቀበሌ በአንድ ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ከወረዳው የመጣ ፖሊስ ምንም እርዳታ ሳያደርግ ተመልሶ ሒዷል ተብሏል፡፡ ከንብረትና ቤት ቀጥሎ እነረሱን እንደሚገድሏቸው እየተነገራቸው ዙሪያቸው ታጥሮ ያሉት የዐማራ ተወላጆች በአስቸኳይ ሊያስቆም የሚችል ኃይል ካልደረሰ እንደ 1999ኙ ዓይነት ዕልቂት ሊከሰት ይችላል ብለዋል፡፡