19 ሴፕቴምበር 2017

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በአራት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ የስምንት ቀበሌ ነዋሪዎች በቅማንት ራስን በራስ የማስተዳደር ወይንም እስካሁን በነበረው አስተዳደር ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ሕዝበውሳኔ መስከረም 7 ቀን 2010 .ም አካሂደዋል።

ህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም )እንዴት ይካሄዳል?

የኢህአዴግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ሕዝበውሳኔዎች የተካሄዱ ሲሆን የመጀመሪያውና እስካሁን በአነጋጋሪነቱ የሚነሳው ኤርትራን ከኢትዮጵያ ተለይታ ሃገር የመሆን ጥያቄ የወሰነ ነው።

በተለይም ብሄርን መሠረት ካደረገው የፌደራሊዝም ሥርዓት ጋር ተያይዞ ለማንነታቸው ዕውቅና ይሰጠን የሚሉ እንዲሁም የአስተዳደር ድንበሮችን ለመለየት እና ነዋሪዎች ወደየትኛው አስተዳደር መካለል እንደሚፈልጉ ለማወቅ ሲባሉ የተካሄዱ አሉ። እነዚህም ሕዝበውሳኔዎች የኢትዮጵያ ምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 መሠረት አድርገው ይካሄዳሉ። የህግ ምሁሩና በፌደራሊዝም ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረጉት አቶ ውብሸት ሙላት እንደሚሉት በሕዝበውሳኔው መሠረት አብዛኛው ወደ መረጠው አስተዳደር ይጠቃለላል። ይህ እንግዲህ በህዝቦች መካከል ሊፈጠር የሚችልን ግጭት ለማስወገድ ህገመንግስታዊ መፍትሄ ነውይላሉ።

የቅማንት ሕዝበውሳኔ ምንድን ነው?

እንደ አቶ ውብሸት አባባል የቅማንት ሕዝበውሳኔ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ውሳኔዎች ይለያል ። እንደምክንያት የሚያስቀምጡትም በአንድ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአስተዳደር ወሰኖችን ለመለየት የተዘጋጀ መሆኑንና እንደ አዲስ የሚመሰረትን የአስተዳደር አካል ለመወሰን ሲባል የሚደረግ መሆኑን ነው። ከዚህ ቀደም ቀበሌን፣ ወረዳን ወይም ዞንን እንደ አዲስ ለማዋቀር በአካባቢው የሚኖረውን ማህበረሰብ ፍላጎት ለማወቅ ሲባል ሕዝበውሳኔ ማደረግ አልተለመደምይላሉ። ከዚህም በተጨማሪ አቶ ውብሸት እንደሚሉት በ1999ኙ የሕዘብና የቤት ቆጠራ ላይ የቅማንት ማህበረሰብ ራሱን ችሎ ባለመቆጠሩ እና በሌሎችም ምክንያቶች የማንነት ይታወቅልኝ ጥያቄ ተነስቶ በ2007 .ም የአማራ ክልል ምክርቤት ማንነቴ ይታወቅልኝያለውን ማህበረሰብ ሕዝበውሳኔ ሳያደርግ በራሱ እውቅና ሰጥቷል።

እስካሁን የተደረጉ ሕዝበውሳኔዎች

በተለይም በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የተለያዩ ሕዝቦችና ብሄሮች አንድ ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ የሕዝበውሳኔ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ። ብሄርን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ቋንቋን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ግጭቶችን እያስከተሉ የሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል። በሃገሪቱ ውስጥ ከተደረጉት ህዝበ ውሳኔዎች አንዱ የስልጤ ማህበረሰብ ማንነቴ ይታወቅልኝ የሚለው አንዱ ነው። የስልጤ ህዝብ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ሥር የነበረ ሲሆን የተለያዩ ግጭቶችና ክርክሮችን ተከትሎ ሕዝበውሳኔ ተደርጓል። ይህም ውሳኔ የስልጤ ዞን እንዲመሰረትና ራሳቸውንም እንዲያስተዳድሩ አስችሏቸዋል።

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የተደረገውም ሕዝበውሳኔ ከ400 የሚበልጡ ቀበሌዎችን ያሳተፈ ነው። ሕዝበውሳኔው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቀበሌዎች በኦሮሚያ አስተዳደር ሥር እንዲጠቃለሉ የተወሰነበት ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ኮንሶን፣ ደራሼን፣ ቡርጂንና አማሮን በአንድ ዞን ለማካተት በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ግጭት ተነስቶ የነበረ ሲሆን የክልሉ መንግሥትን በመቃወም ሕዝበውሳኔ እንዲደረግ ከፍተኛ ጥያቄ ቀርቦ ነበር ። በአንድ ዞን መጠቃለሉ ከፍተኛ የሆነ የበጀት መቀነስና ቀውስ ስለሚያደርስም ነበር ተቃውሞው የቀረበበት።

በሕዝበ ውሳኔ ምን ተፈቷል?

ምንም እንኳን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሕዝበውሳኔዎች ቢደረጉም ውጤታቸው ግን እንደታሰበው አይደለም። አቶ ብውሸት እንደዋና ማሳያነት የሚያነሱት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ተደርገው የነበሩትን ሕዝበውሳኔዎች ባለማክበር በየጊዜው የተፈጠሩት ግጭቶችን ናቸው። ሕዝብ ከወሰነም በኋላ መልሶ ግጭት ሲከሰት እየተስተዋለ ነው። ለዚህ ደግሞ በአጠቃላይ የሕዝበውሳኔ ሂደትና ከህጉ ጋር የሚያያዙ ችግሮች አሉ። እነዚህን መቅረፍ እስካልተቻለ ድረስ በትክክል እንዲመቱ የታሰቡትን ግብ ላያሳኩ ይችላሉይላሉ። ከነዚህም ጥንቃቄ ከሚያሻቸው ነገሮች ውስጥ ሕዝበውሳኔዎቹ ፍትሃዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ስለሕዝበውሳኔው ለሚመለከታቸው ሁሉ ተገቢውን ትምህርት መስጠትና ክርክሮች መደረግን የተመለከቱ ይገኙበታል ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች