Skip to content
የተረጅዎች ቁጥር አስደንጋጭ ወደ ሆነ ደረጃ ማደጉም አሳሳቢ እየሆነ ነው።
ግጭቶች የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ቁጥር ይጨምራሉ ከሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰነው የኦሮሚያ ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከሚንቀሳቀስ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው በዞኑ ከ116 ሺህ በላይ ሰዎች በድንበር ግጭት ምክንያት ተፈናቅለዋል። ግጭቶቹ ለ66 የጤና እና ለ41 የትምህርት ተቋማት ሥራ መቋረጥ ምክንያት እንደሆኑም መረጃው ያሳያል።
መቀመጫውን በጄኔቫ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መቆጣጠሪያ ማዕከል (አይዲኤምሲ) እንደሚለው እ.ኤ.አ 2017 የመጀመሪያ አጋማሽ በኢትዮጵያ 213 ሺህ አዳዲስ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሉ። ይህም ከግጭት ጋር በተያያዘ ከሚኖሩበት ወይንም ከሚሰሩበት ቀዬ የለቀቁ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ቁጥር ከ588 ሺህ በላይ ያደርሰዋል።
በተለይም በ2007 ዓ.ም እና በ2008 ዓ.ም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተነሱት ተቃውሞችና ግጭቶች ለተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር ምክንያት ሳይሆኑ እንዳልቀረ ይቆጠራል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የወርሃ ሐምሌ ሪፖርት እንደሚያስረዳው ድርጅቱ በ544 የተፈናቃዮች ጣቢያዎች ውስጥ ባደረገው ቅኝት ከ1 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በሶማሌ ክልል ይገኛሉ። ድርቅና ግጭት ከቀዬ ለመፈናቀል ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ይላል ሪፖርቱ።
ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ በተለይም ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ ለተፈናቀሉ 800 ሺህ ገደማ ስደተኞች መጠለያ ሰጥታለች። በሌላ በኩል የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ሰነድ አልባ የሆኑ የሌላ አገር ዜጎች አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ያስተላለፈውን መመሪያ ተክትሎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዕጣ ሲያነጋግር ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ከባለፀጋዋ ሳዑዲ ለማስወጣትና ወደ አገራቸው ከተመለሱም በኋላ በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይገልፃል። እስካሁንም 70 ሺህ ያህል ዜጎች መመለሳቸው ተዘግቧል።
በቅርቡ ሳዑዲ ለሰነድ አልባ ሰራተኞች የሰጠችውን አገሪቱን ለቆ የመውጫ የምህረት ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜ ማራዘሟን ተከትሎ ተጨማሪ ሰዎች የሚመለሱ ከሆነ፤ እነርሱን የማቋቋሙ ኃላፊነት በአገሪቷ ጫንቃ ላይ የሚደረብ ሌላ ፈተና ይሆናል።
Like this:
Like Loading...