(Hara ZeTewahido) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን፣ በያዝነው 2010 ዓ.ም. መባቻ፣ በአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ ማስተላለፍ የጀመረው ፕሮግራም ሥርጭት፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ በሰጡት ትእዛዝ ታገደ፡፡

 

ፓትርያርኩ ትእዛዙን የሰጡት፣ ባለፈው ሰኞ፣ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ ሲሆን፤ ጽ/ቤቱም፣ ዛሬ፣ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ከቀትር በኋላ ይመለከታቸዋል ለተባሉት አካላት ትእዛዙን በማስታወቅ ተፈጻሚ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ለአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ፣ ለኮሚዩኔኬሽ ጉዳዮች ጽ/ቤትና ለፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር በአድራሻ የተጻፈው የእገዳው ትእዛዝ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎትና የአስተዳደር መምሪያ፣ የብሮድካስት ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ በግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉ ተገልጿል፡፡

ይኸው የፓትርያርኩ የእገዳ ትእዛዝ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት ቦርድ፣ ባለፈው ዓመት ጳጉሜን፣ የማኅበሩን የቴሌቭዥን ፕሮግራም እንደማያውቀው በመግለጽ የጻፈላቸውን ደብዳቤ መነሻ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡

የማኅበሩ የአሌፍ ቴሌቭዥን ፕሮግራም፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ያሳለፈውን ውሳኔ መተላለፉን የገለጹት ፓትርያርኩ፤ እንቅስቃሴው “ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ” በመኾኑ በአስቸኳይ እንዲቆም መመሪያ መስጠታቸውን ጠቅሷል፡፡

ቀደም ሲል፣ ለኢቢኤስ ቴሌቭዥን ድርጅት፣ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም.፣ ከቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሳይሰጣቸውና ሳያሳውቁ፣ በስሟ፣ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ፕሮግራም ስለሚያስተላልፉ ሕገ ወጥ ተቋማትና ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ድርጅቶች ተመሳሳይ ውሳኔ መተላለፉን በማውሳት፣ አኹንም ይኸው ተፈጻሚ እንዲኾን አሳስቧል፡፡ ለወደፊቱም እንዲህ ዓይነት ሚዲያዎችና ፕሮግራሞች ለዘለቄታው እንዳይመጡ በጥብቅ አስጠንቅቋል፡፡

ፓትርያርኩ ለሰጡት የእገዳ ትእዛዝ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ይጥቀሱ እንጅ፤ የውሳኔውን አፈጻጸም የመከታተል ሓላፊነት ያለበት ቋሚ ሲኖዶሱ አጀንዳውን ውድቅ እንዳደረገባቸው ይታወሳል፡፡

ባለፈው ሳምንት ዓርብ፣ ፓትርያርኩ፣ የማኅበሩ ፕሮግራም እንዲታገድ ይወሰንልኝ፤ በማለት በአጀንዳ ቢያቀርቡም፣ የማኅበሩ ተወካዮች በቤተ ክህነቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ ከመጠቀም ይልቅ ወደ ሌላ ለመሔድ ስለተገደዱበት ኹኔታ ተጠርተው ማብራሪያ እንዲሰጡ፤ ጉዳዩም ለቤተ ክርስቲያን በሚጠቅም አኳኌን በምክክርና ውይይት እንዲፈታ ያቀረበላቸውን አካሔድ ፈቃደኛ ባለመሆን ነው፣ በራሳቸው የእገዳ ትእዛዙን የሰጡት፡፡

ማኅበሩ፣ ከቤተ ክህነቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአየር ሰዓት በመግዛትና ውል በመግባት ለማገልገል ብቻ ሳይኾን፤ ድርጅቱን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ለማጠናከር በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄና ልመና አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ትምህርተ ወንጌልን በዘመናዊ መገናኛ ዘዴዎች እንዲያስፋፋ ሙሉ እውቅና በተሰጠው መተዳደርያ ደንቡ የተጣለበትን ሓላፊነት ለመወጣት ሌላ አማራጭ ለመፈለግ መገደዱን በዋና ጸሐፊው በኩል በሰጠው ምላሽ አስታውቋል፡፡ አገልግሎቱንም በደንቡ መሠረት ለዓመታት ሲሰጥ የቆየው በመኾኑ፣ “ለእያንዳንዱ አገልግሎት ፈቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልገው” አስረድቷል፡፡ ዕውቅና ከሌላቸው ተቋማትና ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ድርጅቶች ጋራ በመደመር ፕሮግራሙን ለማገድ የሚተላለፍ ውሳኔም ተቀባይነት እንደማይኖረው አስገንዝቧል፡፡

ፓትርያርኩም፣ ከቤተ ክህነቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአየር ሰዓት እንደማይሰጠውና ከሌላ አካል የአየር ሰዓት በመግዛት መጠቀም እንደሚችል፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደረጃ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለቀረበላቸው ጥያቄ ቁርጥ ምላሽ የሰጡበት በመኾኑ፣ ደግሞ መጠየቁ አስፈላጊ እንዳልኾነ አስረድቷል፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ቋሚ ሲኖዶስ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ መሠረት በማድረግ ጉዳዩን በምክክር ለመፍታት ያስቀመጠውን አቅጣጫና የራሳቸውን ቃል ጭምር በመፃረር የሰጡት ትእዛዝ ተደርጎ እንደሚታይ ተገልጧል፡፡

በብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ የአየር ሰዓት ሽያጭ አሠራር መሠረት፣ የማኅበሩን ጥያቁ ተቀብሎ ከማስተናገድ ይልቅ፣ በአሉታዊ ምላሾችና የአድርባይነት አካሔዶች ማጓተትንና ማሰናከልን የመረጠው፣ ሥራ አስኪያጁ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልም፣ የታወቀበትን ምቀኝነትና ተንኮል የተሞላበትን ገብጋባ ሰብእናውን ያረጋገጠበት ኾኗል፡፡

ከድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቤ ሊቀ ጳጳስና ከምክትላቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ፣ አጀንዳውን በተነሣሽነት ከማቅረብ ጀምሮ ፓትርያርኩን በማስጠናትና በመገፋፋት፤ ለብሮድካስት ኤጀንሲና ለተለያዩ የመንግሥት አካላት፣ አፍራሽና ሐሰተኛ መረጃን በመስጠት(የአለፍ ቴሌቭዥን ጣቢያን በአሸባሪነት መወንጀል ሳይቀር) ማስፈጸሙም ታውቋል፡፡

“በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በማንኛውም መልኩ የሚተላለፉ ሚዲያዎችን ለመቆጣጠር ፈቃድ ተሰጥቶኛል፤” እያለ የሚሹለከልክበትን የአድርባይነት አሠራሩን ግን፣ በውግዙ አሰግድ ሣህሉ የኑፋቄ ቴሌቭዥን ላይ አላሳየውም ነበር፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን፣ የሙከራ ሥርጭት ማስታወቂያ እስቲነቃ ድረስ!!