ወያኔ ፀረ ሀገር ወይም ፀረ ኢትዮጵያ፣ ፀረ ሕዝብ፣ ፀረ ሰላም፣ ፀረ አንድነት፣ ፀረ ስምምነት፣ ፀረ ፍቅር በሆነው የሀገርን ክብር፣ ፍቅርና ምንነት ከዜጎች አእምሮ አጥፍቶ ጠባብነትንና አደገኛ የጥላቻ የመንፈስን በተካው ጎሳን መሠረት ያደረገው የፌዴራል (የራስገዝ) የአሥተዳደር ሥርዓቱ የክልሎችን ድንበር እንዲህ እንደሰሞኑ ዓይነት ግጭት ማስነሣት በፈለገ ጊዜ ለግጭት ማስነሻነት እንዲያገለግለው ሆን ብሎ ሒደቱን ሳያጠናቅቅ በውዝፍ የተወውን አወዛጋቢ የድንበር ጉዳይን መንስኤ አድርጎ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሞ ብሔረሰቦቻችን መካከል ግጭትና የእርስበእርስ ፍጅት በማስነሣት ወያኔ እያየነውና እየሰማነው እንዳለነው ለዚሁ ጉዳይ አስቀድሞ አሠልጥኖ ያዘጋጃቸውን የኢትዮጵያ ሶማሌን ወታደሮች አሠማርቶ ሰፊ ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግ ከ50 በላይ ወገኖቻችን እንዲገደሉ ከሰባ ሽህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው፣ ከየመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡

ወያኔ ኦሮሚያ ክልል ብሎ የሚጠራው ክልል ክልላዊ መንግሥት ቃለ አቀባይ እንዳሉት እንዲያውም በሕዝብ ላይ ጥቃት ከፈጸሙት የሶማሌ ታጣቂዎች መሀከል የጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ወታደሮች ጭምር መሳተፋቸውን ከተማረኩት ወታደሮች የመታወቂያ ወረቀት ማረጋገጣቸውን ቃለ አቀባዩ ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ (ነጋሪተ ወግ) ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡

ለመሆኑ ወያኔ ይሄንን ግጭት የቀሰቀሰበት ምክንያት ወይም ዓላማ ምንድን ነው?

ወያኔ ይሄንን ጎሳን ወይም ብሔረሰብን መሠረት ያደረገ ግጭት የቀሰቀሰበት ሁለት ዐበይት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ወያኔ እንደብሔረሰብ አማራን ትምክህተኛ ነው ብሎ እንደሚያምነው ሁሉ ኦሮሞን ደግሞ እንደብሔረሰብ ጠባብ ነው ብሎ እንደሚያምን የምታውቁት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ሕዝባዊ ዐመፁ ወይም ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ ወዲህ ይሄንን አመለካከቱን እንደነ ዐባይ ፀሐዬ ባሉ ባለሥልጣናቱ በኩል በአደባባይ በመናገር አስተሳሰቡን ግልጽ አድርጓል፡፡ በመሆኑም በተለይ በአሁኑ ሰዓት ስር ሰዶ ያለውን ኦሮሚያ ለኦሮሞ!” የሚለውንና የአዲስ አበባ ከተማን ያልተሸራረፈ የባለቤትነት መብት!” ጥያቄን የሚያነሡትን ይህ ጠባብና አደገኛ አስተሳሰብ ያለባቸው ኦሮሞዎች እንደሚያስቡት ኦሮሞ አፈናቃይ፣ አባራሪ ብቻ ሳይሆን ተፈናቃይና ተባራሪም መሆኑን በማሳየት ያበጠ አስተሳሰባቸውን አስተንፍሶ እንዲታረሙ እንዲተው ለማድረግ አስቦ ሲሆን፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወይም አስቀድሞ ወዳጆቹ በነበሩና በሚረዱ በሚደግፉት ምዕራባውያን ዘንድ ወያኔ በአሁኑ ሰዓት ያለው ተቀባይነትና ክብር እግጅ በማሽቆልቆሉ፤ ከዚህም አልፎ እነኝሁ ምዕራባውያት አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ወያኔ ከተቃውሞው ጎራ ጋር የግድ እንዲስማማ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩበት በመሆኑ እሱ ባሻው መስመር እንጅ ፈጽሞ ሊያደርገው የማይፈልገውን ስምምነት ከተቃውሞው ጎራ ጋር እንዲያደርግ ጫና እንዳይፈጥሩበት፣ እምቢ ሲላቸው ደግሞ እነኝሁ ምዕራባውያን ሌላ ወያኔ የማይፈልገውን አማራጭ እንዳያስቡ እኔን እነካለሁ ብትሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በእርሱ አፋጅቸ ምሥራቅ አፍሪካን አደገኛ ወደሆነና ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ እዘፍቀዋለሁ!” ብሎ ለማስፈራራት ነው እንዲህ በግልጽ ልክ በሩዋንዳ የዛሬ 24 ዓመት ከ800 ሽህ በላይ የሚሆኑ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች እንዲፈጁ የሩዋንዳው ራዲዮ ሚሌ ኮሊንስ አድርጎት እንደነበረው ሁሉ የኛዎቹ የሁለቱ ክልል መንግሥታትም የብዙኃን መገናኛዎቻቸው አንዱ ሌላውን እንዲያጠፋ ወይም እንዲያጠቃ የሚቀሰቅሱ መልእክቶችን እያስተላለፉ ግጭቱ እንዲባባስ በማድረግ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቀውና እንዲደነግጥ የተደረገው፡፡

ይሄንን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያነሣሁትን ነጥብ ገልብጠው ማለትም በተቃራኒው የሚመለከቱት ወገኖች አሉ፡፡ ወያኔ እንዲህ ዓይነቶችን ግጭቶች የሚቀሰቅሰው እኔ ከሌለሁ ሀገሪቱ ወደ የእርስበርስ ግጭት ትገባለች!” የሚል መልዕክት ለምዕራባውያኑ በማስተላለፍ ድጋፋቸውን እንዳያቋርጡበት፣ አመኔታቸውን እንዳያጎሉበት ለማድረግ ነው እንዲህ ዓይነት ግጭቶችን የሚቀሰቅሰው ይላሉ፡፡ ይሄ አስተያየት የምዕራባውያንን አቅምና በሀገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ ያገናዘበ አስተያየት አይደለም፡፡

ምዕራባውያኑ ማናችንም ወያኔን ከምናውቀው በላይ ብጥር ምንጥር አድርገው ያውቁታል፡፡ በሀገሪቱ የትኛውም ጫፍ ላይ በየዕለቱ የምትደረግ እያንዳንዷ ስውር ድርጊት ሁሉ ከእነሱ ዕይታ ውጭ አይደለችም፡፡ ይሄንን ለመረዳት የዊኪሊክስን መረጃዎች መለስ ብላቹህ ማሰቡ ወይም ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት ሳይቀር የሚያውቁበት ሁኔታ ሁሉ አለ፡፡ በመሆኑም ወያኔ እነኝህን ግጭቶች እንዲከሰቱ የሚያደርገው እሱ ከሌለ ሀገሪቱ ወደ ቀውስ እንደምታመራ ለማስገንዘብና ለዚህች ሀገር መረጋጋት የእሱ መኖር የግድ አስፈላጊ መሆኑን እንዲረዱ ለማድረግ ሳይሆን እሱ እንዳይኖር የሚያደርግ አንዳች ዓይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ጨርሶ እንዳያስቡት ቢያስቡ ግን እንዲህ ዓይነቱን ቀውስ ቀስቅሶ አጥፍቶ እስከመጥፋት ድረስ የማይመለስ መሆኑን እንዲረዱ ለማድረግ ነው፡፡ ሰሞኑን ፈጽሞ ተጠያቂነት በሌለው መልኩ የቀሰቀሰውን ግጭት በዚህ ደረጃ በግልጽ የቀሰቀሰበት ሁኔታ የሚያረጋግጠው ሀቅ ይሄንን ነው፡፡ ምዕራባውያኑ እንዲህ በግልጽ መነበብ የሚችልን ነገር ማንበብ የሚሳናቸው ሆነው ነው ወይ ገልብጠው የሚያነቡት?

በአንደኛ ደረጃ ላይ ወደ ጠቀስኩት ወያኔ ይሄንን ግጭት ወደ ቀሰቀሰበት ምክንያት ልመለስና ይህ ምክንያት ትክክልና መወሰድ ያለበት የማስተማሪያ እርምጃ የሚመስላቹህ ወገኖች ካላቹህ አንድ ነገር እንድታስቡ እጠይቃለሁ፡፡ ሲጀመር እነኝህን ማለትም ኦሮሚያ ለኦሮሞ ብቻ! ፣ አዲስ አበባ የእኛ ነች ለእኛ ትሰጠን!” የሚሉትንና የመገንጠል ዓላማን የሚያራምዱትን ጽንፈኛና አደገኛ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ማን እንዲህ ፀረ ኢትዮጵያ፣ ፀረ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ፀረ ኢትዮጵያዊ ማንነትና ፀረ ሌላ ጎሳና ብሔረሰብ በተለይ አማራ አድርጎ ማን ቀረጻቸውና ነው? ይሄንን የቁቤ ትውልድተብሎ የሚጠራውን በአብዛኛው ክፉኛ የተመረዘ ትውልድ ጠፍጥፎ እንደሚፈልገው አድርጎ ይሄው ትውልድ ስለኦሮሞ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረውና ለበቀልም እንዲነሣሣ ሐሰተኛ ታሪክ በመፍጠር ጥላቻንና ቂም በቀልን የሚያነሣሣ ዘግናኝ ሐውልት ገንብቶ በመቀስቀስ ጭምር አስወጡ ግደሉ!” እየለ መርዞ የፈጠረው እራሱ ወያኔ አይደለም ወይ?

አዲስ አበባ የኛ ናት ትሰጠን! ፣ እንገነጠላለን!” ምንትስ ማለታቸውም ወያኔ ሕገ መንግሥት በሚለው ፀረ ሕዝብ፣ ፀረ ኢትዮጵያ ሰነዱ ላይ ባሰፈረው የብሔር ብሔረሰብ መብት ብሎ ሰጠኋቹህ!” ያላቸውን መብት ነው የጠየቁት፡፡ ታዲያ ወያኔ የዘራውን ቢያጭድ ምኑ ነው የሚገርመው? ለዚህም ነው የዚህን ጽሑፍ ርእስ ወያኔ የኦሮሞን ሕዝብ ምን አድርግ ነው የሚለው?” በማለት የጠየኩት፡፡ እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው እርሱ እራሱ ነውና፡፡ እንዲህ አድርጎ ከቀረጻቸው በኋላ ደግሞ እንደተቀረጹት ሆነው ሲያስቡ ወያኔ ጠባብ ምንትስ እያለ ለመክሰስ የሞራል (የቅስም) ብቃትና መብት ይኖረዋል ወይ? ነው የኔ ጥያቄ፡፡

በጣም የገረመኝ ነገር ደግሞ ወያኔ በጠ/ሚ ተብየው በኩል የሁለቱንም ወገኖች ባለሥልጣናት ሰብስቦ ከአሁን በኋላ አንደኛቹህ በሌላኛቹህ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ብታደርጉ፣ በየብዙኃን መገናኛዎቻቹህ ጥቃት እንዲፈጸም ብትቀሰቅሱ በሕግ ተጠያቂ ትሆናላቹህ!” በማለት ስንት ወገኖቻችን ያለቁበትንና የተፈናቀሉበትን ጉዳይ የልጆች የሕፃናት ጥል አድርጎት ቁጭ ማለቱ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ አቁሙ!” ከተባለ በኋላም መጠቃቃቱ ተስፋፍቶ መቀጠሉ ነው፡፡ ወያኔ እንግዲህ ጠርቶ አቁሙ!” ማለቱ እንዴት ዝም ብሎ ይመለከታል?” የሚል ጉርምርምታና ክስ በሕዝቡ ዘንድ እንዳይነሣ ለመከላከል መሆኑ ነው፡፡

ወገኖቸ ሆይ! እነኝህ ወያኔ ክልል የሚለው የሀገሪቱ ክፍል ባለሥልጣናት ታጣቂዎቻቸውን አንደኛው በሌላኛው ላይ ማዝመታቸው ከታወቀ፣ በብዙኃን መገናኛዎቻቸው ሳይቀር ሕዝባቸውን አንዱ ልላውን እንዲያጠቃ መቀስቀሳቸው ከታወቀ ከዚህ በላይ ወንጀል ምን አለና ነው ሰዎቹን በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ሲገባ እንደ ሕፃናት ፀብ በምክርና በተግሳጽ ለማለፍ የተፈለገው? ይሄ የዘር ልዩነትን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም ወንጀል እኮ አይደለምና ወንጀሉ ለተፈጸመበት ሀገርና ሕዝብ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ቢሆን እኮ ይሄ ወንጀል በሰው ልጆች ላይ ከሚፈጸሙ የወንጀል ዓይነቶች የመጨረሻው ወንጀል እኮነው፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ይሄንን የሚያክልን ግዙፍና እጅግ አደገኛ ወንጀል ወያኔ የሕፃናት ፀብ ያህል አቅሎ ሊያይ የቻለው? ለምን እንደሆነ ልንገራቹህ? ድርጊቱ የተፈጸመው ወይም የተቀሰቀሰው ከወያኔ በወረደ ትዕዛዝ ሆን ተብሎ በመሆኑ የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ለፍርድ ማቅረብ አይፈልግም፡፡

እነኝህ ግጭቱን የቀሰቀሱት አካላት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለፍርድ ይቅረቡ!” ተብሎ ቢጠየቅና ቢቀርቡ የዚህ ቀውስ አስኳሉ ወያኔ መሆኑ በግልጽ ስለሚታወቅ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቢጠይቅ እንኳ ወያኔ ይሄ እንዲሆን ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡ ይሁንና ወያኔ ፈቀደም አልፈቀደ፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሩዋንዳ ላይ ባሳየሁት ቸልተኝነትና መዘናጋት ያ ሁሉ ዘግናኝ እልቂት በመፈጸሙ ተጸጽቻለሁ!” የሚለው ነገር እውነት ከልብ ከሆነ ተመሳሳይ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ በአስቸኳይ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡

ከሀገር ውጭ ያላቹህ ኢትዮጵያንም በተለይም ምሁራን ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በማሳሰቡ፣ በማስጠንቀቁ ረገድ ጊዜ ሳታጠፉ በተለያየ መንገድ እንድትረባረቡ አበክሬ አሳስባለሁ፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይሄንን ጉዳይ በቸልታ ተመልክቶ ይሄንን ማድረግ ካልቻለና እርምጃ ሳይወስድ፣ ጫና ሳያሳድር በዝምታ ካለፈው ኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ የዘር ፍጅት እንዲቀሰቅስ ፈቃድ እንደሰጠና እንደተስማማ፣ ከወያኔ ጎን እንደቆመ ይቁጠረው! ፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንዳችም እርምጃ ሳይወስድ ቢቀር መፈጠሩ ለማይቀረው በዓለማችን ታይቶ ለማይታወቀው የእርስበእርስ የዘር ፍጅት ዋነኛው ተጠያቂ እሱ ራሱ እንደሚሆን ያለ የሌለ ኃይላቹህን አሟጣቹህ በመጠቀም እንድታሳውቁልን ከኢትዮጵያ ውጭ ያላቹህትን ኢትዮጵያንን አጥብቄ አሳስባለሁ!!!

ከዚህ ቀደም ምዕራባውያኑ ከሩዋንዳው የዘር ፍጅት ሦስት ዓመታት አስቀድሞ ወያኔ ኦነግና ደጋፊዎቻቸው ዛሬ ኦሮሚያ ብለው በሚጠሩት የሀገራችን ክፍል አማራን ከሕፃን እስከ እናቶችና አሮጊት ሽማግሎች ድረስ እያሰሱ በመፍጀት የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸማቸውን እያወቁ አንዳችም ነገር ትንፍሽ ሳይሉ አይተው እንዳላዩ አልፈዋል፡፡ በተለይም አሶሳ ላይ ኦነግና ሸአቢያ በተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ድርጅት እጅ የነበሩትን ጨምሮ አማራ የተባለን ሁሉ ልቅም አድርገው ሲፈጁ የተባበሩት መንግሥታት ወኪሎች በዓይናቸው ዓይተው የነበረ ቢሆንም ድርጊቱን ለማጋለጥና ለማውገዝ ግን አንድም ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ ይሄንን አደገኛ ስሕተት ፈጽሞ እንዳይደግሙት በቻልነው መንገድ ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ከሀገር ውጭ የምትኖሩ ወገኖቻችን ሆይ! የፈለገ ነገር ይሁን እዚህ ላይ አስከፊው ቀን ከመምጣቱ በፊት መሥዋዕትነት መክፈል ይኖርባቹሀል! ይሄ ጉዳይ እኮ የእያንዳንዳቹህ ወላጆች፣ ቤተሰብ ዘመዶች፣ ወገንና ሀገር ጉዳይ እንጅ የሌሎች ጉዳይ እኮ አይደለም! ታዲያ እንዴት የዚህን ያህል ደንዝዛቹህና ፈዛቹህ ለሌሎች ጉዳዮቻቹህ ቅድሚያ በመስጠት በዝምታ ታዩናላቹህ? ከዚህ በላይ ምን ዓይነት የማንቂያ ደወል ነው የምትፈልጉት? እባካቹህ የሆነ ነገር አድርጉ??? በሰይጣኑ፣ በአረመኔውና በድንቁርናው ተወዳዳሪ በሌለው ወያኔ እጅ እንዳለን እያወቃቹህ እባካቹህ ለቅጽበት እንኳ አትዘናጉብን???

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com