27 Sep, 2017

ዮሐንስ አንበርብር

ከጎረቤት ሶማሌላንድ ሦስት ሺሕ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መፈናቀላቸው ተሰማ፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልላዊ መንግሥታት የጋራ ድንበር አካባቢ በሚኖሩ የኦሮሞና የሶማሌ ተወላጆች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ፣ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል ሲፈናቀሉ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ይኖሩ የነበሩ ሶማሌዎችም ተፈናቅለዋል፡፡

የሁለቱ ብሔሮች ተወላጆች ግጭት ድንበር ዘሎ ኢትዮጵያ ከሕግ በመለስ እንደ አገር ዕውቅና በሰጠቻት ሶማሌላንድ ውስጥ የሚኖሩ ከሦስት ሺሕ በላይ ኦሮሞዎችም መባረራቸውን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ ነገሪ ሌንጮ (/) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የተፈናቀሉት የኦሮሞ ተወላጆች በአሁኑ ወቅት ቶጎ ውጫሌ በሚባለው የኢትዮጵያ ድንበር እንደሚገኙና ወደ ኦሮሚያ ክልል በመግባት ላይ ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የክልሉ ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ከፍተኛ አመራሮች በዚህ ግጭትና ተፈናቃዮችን በመቀበል ላይ ከሕዝብ ጋር በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው እየመከሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (/) በጉዳዩ ላይ ከሶማሌላንድ መንግሥት ኃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሚኒስትሩ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመዘዋወርም የተፈናቀሉ ወገኖችንና የአገር ሽማግሌዎችን እንዳነጋገሩ የሪፖርተር መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር የመሥራት መብታቸውን መንግሥት እንደሚያረጋግጥላቸው ለተፈናቃዮቹ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ የፌዴራል መንግሥት ከሁለቱ ክልሎች አመራሮች ጋር ሆኖ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ማስታወቃቸው ተሰምቷል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ መንግሥት ካሁን በኋላ ግጭቶች እንዳይቀሰቀሱ የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ መናገራቸው ታውቋል።

Author

anon

ዮሐ