መስከረም 27 2017

በታዋቂው የግጥምና የቲያትር ደራሲ በአቶ ጌትነት እንየው የተደረሰው የቴዎድሮስ ራዕይ የሚባለውና፣ በጣይቱ ማዕከል ተዘጋጅቶ እ. አ በ15.09.2017 ዓ.ም በበርሊን ከተማ ሊታይ የበቃው ቲያትር በበርሊንና አካባቢው የሚኖሩንና፣ ከሌላም የጀርመን ግዛት የመጡ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ የሳበ እጅግ ግሩም ቲያትር ነው። በጣይቱ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር፣ በወይዘሮ አለምፀሃይ ወዳጆ አቀነባባሪነትና ዋና ግንባር ቀደምትነት ተዘጋጅቶ የቀረበው የቴዎድሮስ ራዕይ የሚባለው ቲያትር ወቅታዊ ብቻ ሳይሆን የዘለዓለማዊነት ባህርይ እንዳለው የቲያትሩን ሂደት ለተመለከተና ለተከታተለ ሊገነዘብ ይችላል።

እንደሚታወቀው አፄ ቴዎድሮስ በተለይም የሰሜኑ ክፍል የኢትዮጵያ ግዛት ለስልጣኔና ለዕድገት ሳይሆን በስልጣን ጥማት ተሳክረው አካባቢዉን ወደ ጦርነት አውድማነት የለወጡትን መሳፍንቶች አንድ በአንድ እያሉ ድል ካደረጉ በኋላ የተሰበጣጠረዉን ኃይል በመሰብሰብና በአንድ ማዕከላዊ ግዛት ስር እንዲተዳደር በማድረግ ህዝቡን የዘመኑ ስልጣኔ ቀማሽ ለማድረግ የተነሱ በጊዜው የተገለጸላቸው ታላቅ ንጉስ ነበሩ።  ከቲያትሩ እንደተመለከትነውና፣ ስለሳቸውም ታሪክ አንዳንድ የታሪክ አዋቂዎች በጻፉት መሰረት፣ አፄ ቴዎድሮስ መሳፍንቱን ድል እየመቱ ሲመጡ ያልተጠበቀ ሁኔታ በመፈጠሩ በፊዩዳላዊ ባህል የሚዝናኑትና፣ ንጉስ ወይም መሳፍንት መሆን ለጥቂቶች ብቻ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ፀጋና፣ ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ተደርጎ በሚመለክበት አገር ውስጥ ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል  መጥትው የንጉሰ-ነገስትን ማዕረግ መቀዳጀታቸው መሳፍንቱን ያስቆጨና ያንበረከከ ታሪካዊ ድርጊት ነው።

ከቲያትሩ ክንዋኔ እንደምንገነዘበውና በእርግጥም በድርጊት እንደተረጋገጠው አፄ ቲዎድሮስ በ19ኛው ከፍለ-ዘመን በተለይም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ግዛት ተንሰራፍቶ የነበረውን ፊዩዳላዊ ስርዓትና፣ ፈጠራና ዕድገት እንዳይኖር ህዝቡን አንቆ የያዘውን ኋላ-ቀር አኗኗርና ብዝበዛ በመገንዘብ እንዲወገድ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቆርጠው የተነሱ ታላቅ መሪ ናቸው። የንጉሰ-ነገስትነት ማዕረግነትንም ከተጎናጸፉ በኋላ በአገሪቱ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ተስፋፍቶ የሚገኘውን የባሪያ ንግድ እንዲቆምና፣ በአምላክ ምስል የተፈጠረ ሌላውን አምሳያውን የመሸጥና እንደ ዕቃ የማየት መብት እንደሌለው በአዋጅ ያበስራሉ፤ እንዲከለከልም ያደርጋሉ። ምንም ዐይነት የተገለጸለት ምሁራዊ እንቅስቃሴ በማይታወቅበት አገር ከአንድ ንጉስ ይህ ዐይነቱ ሰውን እንደ ዕቃ የመሸጡ ተግባር እንዲከለከል መደረጉ ከፍተኛ የሆነ ፓለቲካዊ ትርጉም እንዳለው መገንዝብ ይቻላል።  አፄ ቴዎድሮስ ከዚህም አልፈው በመሄድ በየቤተክርስቲያኑ ደጃፍ ላይ የሚንቀዋለለውንና ፣ ስራ ፈት መነኩሴ ቆቡን ሲቀድና ሲሰፋ ይውላል  ተብሎ የሚጠራውን መነኩሴና ደብተራ  ከስራ ፈትነትና ከነገር ተብታቢነት ባህርይዉ እንዲላቀቅና ወደ ስራ ዓለም እንዲሰማራ በማድረግ አዲስ የስራ ባህል በዚህ የህብረተሰብ ክፍል ጭንቅላት ውስጥ ሰርጎ እንዲገባ የመጀመሪያውን ሙከራ ያደርጋሉ። በተጨማሪም በቤተክርስቲያ ስር የተያዘውን ጦም የሚያድር መሬት ለመንጠቅ ይሞክራሉ፤ ለገበሬው እንዲከፋፈል ወይም ራሱ ደብተራው እንዲያርስበት በማድረግ የቤተክርስቲያንን ርዕዮተ-ዓለማዊ የበላይነት ለመስበርና ሁሉም እንደየችሎታውና እንደየሙያው በስራ ዓለም በመሰማራት ለአገር ዕድገት አስተዋፅዖ እንዲያበረክት የመጀመሪያዉን እርምጃ ይወስዳሉ።  አንድ ሰው በመቀመጡና በመለመኑ፣ ወይም በየጊዜው ቤተክርስቲያን በመሄድና በመጸለዩ ሳይሆን ማንነቱ የሚታወቀው፣ በስራ ብቻና፣ ስራም ዋናው የሀብትና የዕድገት ምንጭ መሆኑን በአዋጅ ያበስራሉ። አፄው እንደታላላቅ ኢኮኖሚስቶች፣ „ስራና የተለያየ የሙያ ዐይነት መዳበርና መስፋፋት ዕውነተኛ የህብረተሰብ ሀብትና የዕድገት ምንጭ መሆናቸውን የገባቸው ለመሆኑ ከቲያትሩና በእርግጥም ከወሰዱት እርምጃ መረዳት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ስር-ነቀል አዋጃቸውና ተግባራዊ ወደ ማድረግ የጀመሩትም ልዩ ልዩ አዋጅ በመሳፍንቱና በቀሳውስቱ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት እንዳልቻለና ከፍተኛ ተቃውሞም እንዳስከተለ ከቲያትሩም ሆነ ከታሪክ ማህደር መረዳት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ተቃውሞና በቀሳውስቱና በመሳፍንቱ ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘው ዕርምጃና፣ በንጉሱ ላይም የሚወራው የጥላቻ ዘመቻ እሳቸውን እንዳስቆጣቸውና፣ ቀሳውስቱና መሳፍንቱም፣ እንደዚሁም ህዝቡ ዋና ምኞታቸውንና ህልማቸውን ባለመረዳቱ ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ እንደከተታቸውና ወደማይሆን እርምጃ እንዲያመሩ እንዳስገደዳቸውና፣ ኃይላቸውም እንደበታተን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳበረከተ ከቲያትሩና እሳቸውም ከደረሰባቸው ብስጭት መረዳት ይቻላል። በዚህ ዐይነት የትንቅንቅ ሁኔታ ውስጥ በሚገኙበት ወቅት ከልብ የሚያፈቅሯቸውና የምኞታቸውና የህልማቸው ተጋሪና አማካሪያቸው ውድ ባለቤታቸው ንግስት ተዋበች  ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ። በሀዘን ላይ ሀዘን ይታክልባቸዋል።

አፄ ቴዎድሮስ የአገራቸው ኋላ-ቀርነት የሚያስቆጫቸው መሪ ብቻ ሳይሆኑ፣  በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና ህዝቡን ሊያስተሳስር የሚችል የመገናኛ መንገድ ከሌለና፣ ህዝቡንም የሚጠቅም ዕድገት ዕውን እስካልሆነ ድረስ  አንድነትና ጥንካሬ ሊኖር እንደማይችል በመገንዘባቸው ሰለጠነ ከሚባለውና፣ የክርስትናን ሃይማኖት ከተቀበለው የአውሮፓ አገዛዝ፣ በተለይም ታላቋ ብሪታንያ ተብላ ከምትታወቀውና ከምትጠራው አገርና ከንጉስ ቪክቶሪያ ጋር የደብዳቤ ግኑኝነት ይፈጥራሉ። በሁለቱ የክርስቲያን አገዛዞች ዘንድም መቀራረብ እንዲኖርና፣ በዚህም አማካይነት ስልጣኔን ለማግኘት የሚችሉ መስሏቸው ለታላቋ ብሪታኒያ ንግስት፣ ለንግስት ቪክቶሪያ ህዝባቸውን የሚያስተምርላቸውን  ኢንጂነሮች፣ ቴክንሺያኖችና ሳይንቲስቶች እንዲላኩላቸው ደብዳቤ ይጽፋሉ። ከንግስት ቪክቶሪያና ከአማካሪዎቻቸው ለአፄ ቴዎድሮስ የተላኩላቸው የቴክኖሎጂ አስተማሪዎች ሳይሆኑ መጽሀፍ ቅዱስን የሚስብኩ በመሆናቸው በዚህ የታላቋ ብሪታንያ ንግስትና አማካሪዎቻቸው ድርጊት ከፍተኛ ብስጭት ይደርስባቸዋል፤ ብስጭታቸውም ወደ ቁጣነት በመለወጥ ወደ ማይሆን፣ ለሳቸው ህይወትና ለአገራቸው አንድነት ወደሚያሰጋቸው እርምጃ ላይ ያዘነብላሉ።  በንግስት ቪክቶሪያና በአማካሪዎቻቸው የተላኩትን ቀሳውስት በማሰር መድፍ እንዲሰሩና ብረት እንዲያቀልጡ ያስገድዷቸዋል። በተጨማሪም የእንግሊዝን ተጠሪዎቿንና ሌሎች የአውሮፓን ዲፕሎማቶች በማሰር ለዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት መሻከር ዕምርታ ይሰጡታል።  ይህ ዐይነቱ የአፄው ድርጊት ሲሰማ ታላቋ ብሪታንያ አንድ የጥቁር ንጉስ ደፈረኝ በማለት የሌለና ያለ ኃይሏን በማዘጋጀት በጄኔራል ናፒር የሚመራ በጊዜው ወደ 60 ሺህ የሚጠጋ ወታደር ከሰላሳ ሺህ ዝሆኖች፣ ፈረስ ወይም በቅሎ ጋር በመላክ በአፄው ላይ ጦርነት ታውጃለች። ይህ ዐይነቱ ዘመቻ ለአፄ ቴዎድሮስ ያልጠበቁትና፣ አንድ የሰለጠነና የክርስትናን ሃይማኖት የሚከተል መንግስት ሊያደርገው ይችላል ብለው የሚያስቡት ነገር አልነበረም። በተጨማሪም የእንግሊዝ መንግስት ኢትዮጵያን ለመውረር ካሰፈሰፈው የቱርክ ወራሪ ጦር ጋር ሲመሰጣጣርና አሻጥር ሲሰራ ይደርሱበታል። ይህም ጉዳይ እጅግ ያሳዝናቸዋል፤ ያበሳጫቸዋልም።  በእሳቸውም ዕምነት ማንኛውም የሰለጠነ፣ ወይም በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተራመደና፣ በተለይም ደግሞ የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበለና ዕምነቱ ያደረገ አገዛዝ ለሌላው የክርስትናን ሃይማኖት ዕምነቱ ላደረገ አገርና አገዛዝ ስልጣኔን የሚያካፍልና፣ በችግርም ጊዜ የሚደርስለት መስሎ የሚታያቸው ነበሩ። ይህንን የመሰለው የአፄ ቴዎድሮስ ዕምነትና አመለካከት ግን በአውሮፓ የፖለቲካ ፍልስፍና ውስጥ የሌለና፣ በተለይም ህብረ-ብሄራዊ አገዛዝ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የበላይነትን በተቀዳጀበትና የበላይነት ስሜት ባየለበት ዘመን ሊስራ የሚችል ጉዳይ አልነበረም። ይህ ዐይነቱ የአፄው አስተሳሰብና አመለካከት የጊዜውን የምሁር ኃይል ክፍተት የሚያሳይ በመሆኑ የግዴታ የየዋህነት ፖለቲካ እንዲያራምዱ አስገድዷቸዋል። ከዚህም በላይ ታላቋ ብሪታንያንና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በኢንዱስትሪ አብዮት እየመጠቁ ሲመጡ የግዴታ የጥሬ-ሀብት ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ ርስ በራሳቸው ፉክክር የሚያደርጉበት ወቅት በመሆኑ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን ወደ በዝባዥነት የሚለውጡበት ዘመን እንጂ ስልጣኔን ወደዚህ አህጉር የሚያስፋፉበትና እኩልነትን የሚያጸድቁበት ዘመን አልነበረም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እንግሊዝ በጊዜው ብቸኛዋ ኃያል መንግስት መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በጊዜው ብቅ ያሉት ምሁሮቿ ባዳበሩት አዳዲስ ቲዎሪዎች መሰረት እንዴት አድርጋ የተወሰነውን ዓለም በቁጥጥሯ ስር ለማድረግና ጥሬ-ሀብቶችን ለመበዝበዝና በዚያው መጠንም ፀረ-ዕድገትን ለማስፋፋት የሚያስችሏትን ማንኛውንም ዐይነት የምሁር ተንኮል የምትሸርብበትና የምታስፋፋበት ወቅት ነበር። ከአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እነ አዳም ስሚዝና ሪካርዶ ባፈለቁትና ባዳበሩት ዓለም አቀፋዊ የስራ-ክፍፍልና ነፃ ንግድ አማካይነት መሰረት በተለይም የጥሬ-ሀብት ያላቸው አገሮች በዚሁ ሙያ ብቻ እንዲሰለጥኑና፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ማህብረሰብና ጠንካራ ህብረ-ብሄር እንዳይገነቡ የተጠነሰሰበት የሴራ ዘመን ነበር። ለእንግሊዝና በኋላ ብቅ ላሉት ፈረንሳይና ጀርመን ይህ ዐይነቱን የበላይነትን መቀዳጀትና በሌላ ህዝቦች ላይ ጭነት በማድረግ ሀብታቸውን መበዝበዝ ብቸኛውና አማራጭ የሌለው መንገድ ነበር። ለሌሎች አገሮች የስልጣኔን ፈር ማሳየት ማለት በራሴ መሳሪያ መልሳችሁ ውጉኝ እንደማለት ስለሚቆጠር፣ በተለይም እንግሊዝ እንደ አፄው ታታሪና ስልጣኔን የሚፈልግ የተገለጸለት አገዛዝ ሲነሳ ህልሙን መቅጨት ዋናው ፍልስፍናዋ ነበር። በመሆኑም በናፒር የሚመራው ጦር ዋና ዓላማው ይህንን የስልጣኔ ናፍቆትና ህልም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ከጥቁር አዕምሮ ውስጥ በመደምሰስ ተገዢ ማድረግ ነው።

አፄ ቴዎድሮስ ከውስጥ በተነሳባቸው ተቃውሞና ለእንግሊዝ ባደሩ መሳፍንትና ንጉስ በመከዳትና የእንግሊዝም ጦር ሰተት ብሎ እንዲገባ መንገዱን በማሳየት ለመቋቋም የማይችሉ መስሏቸው ሲታያቸውና እጅግም የሚወዱት ገብርዬ በጦር ሜዳ ላይ መሰዋቱን ሲሰሙ እጄን ከምሰጥ ይልቅ መሞትን እመርጣለሁ በማለትና በጸና ዕምነታቸው በማመን ህልማቸውን ዕውን ሳያደርጉ ራሳቸውን ይገድላሉ። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን የገደሉበት ዘመን በ1868 ዓመተ-ምህረት ጃፓን በሜጂ ዲናስቲ አማካይነት የዘመናዊነትን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና በምትልበት ወቅት ነበር። ይህ ሁሉ የሚያስተምረን ምንድነው? በጊዜው ብሄራዊ ስሜቱ ያልዳበረ፣ አገርና ህብረተሰብ፣ እንደዚሁም ደግሞ ህዝባዊ ነፃነትና ስልጣኔ ማለት ምን ማለት እንደሆኑ ባልገባው ህዝብና፣ በተለይም ደግሞ የነቃ የህብረተሰብ-ኃይል በሌለበት አገር ውስጥ አንድ የተገለጸለት መሪና ጥቂት ተከታዮቹ ብቻ ብዙም መራመድ እንደማይችሉ ነው ሁኔታው የሚያረጋግጠው። ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ የተነሱት ታላቅ መሪ የአፄ ምኒልክም ህልም ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባርነት ለመመንዘር ያልተቻለውና፣ አገራችን በጸና መሰረት ላይ እንድተገነባ ማድረግ ያልተቻለው ሰፋ ብሎ የሚገኝ የተገለጸለትና የስልጣኔን አርማ አንግቦ የሚጓዝ ህብረተሰብአዊ ኃይል(Social Force) ባለመኖሩ ነው። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመንና፣ በተለይም ባለፉት አርባ አመታት በአገራችን ምድር ውስጥ የሚፍተለተለውና ህዝባችንን አስሮና አንቆ የያዘው ጉዳይ ይህ ዐይነቱ የስልጣኔ ጥም ያለው የከበረ ኃይል ባለመኖሩ ነው። በተለይም የውስጥ ኃይሎች ሳይገለጽላቸውና በከፍተኛ የምሁር ንቃተ-ህሊና ሳይታጠቁ የሚያደርጉት የፖለቲካ ትንቅንቅ አገራችንና ህዝባችንን የማይወጡት ማጥ ውስጥ እንደከተታቸው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ የህዝባችን፣ በተለይም የምሁሩና ፖለቲከኛ ነኝ ባዩ ዝቅተኛ የሆነ ንቃተ-ህሊና ያረጋግጣሉ።

በአጭሩ የቴዎድሮስ ራዕይ ተብሎ የሚጠራው ቲያትር ተዋናይነትን በተካኑ በቂ ችሎታ ባላቸው፣ ቴዎድሮስን መስሎ በሰራው ትሁቱና ወጣት ተዋንያን በሱራፌልና፣ ካሜሩንን መስሎ በሰራው እጅግ በሚያስደንቅ አነጋገሩና አቀራረቡ የታላቋን ብሪታንያን ስም እየደጋገመ በማንሳት አፄ ቴዎድሮስን እንዲናደዱ ባደረገው ታላቅ ተዋንያን ተስፋዬ ሲማ የተሰራ ቲያትር ነው። ማለት የሚቻለው ሁሉም ተዋንያን በተመደበላቸው ቦታ ችሎታቸውን ያሳዩበትና፣ በተቻለ መጠንም ቲያትሩ ዓለም አቀፋዊ ስታንደርድን ጠብቆ የተሰራ ነው ማለት ይችላል። በዚህ አጋጣሚ የቴዎድሮስን ህልምና ምኞት የምትተርከውና በግልጽና በጠራ አማርኛዋ ሁኔታውን ለተመልካቹ የምታቀርበው ወይዘሮ አለምፀሀይ ወዳጆ የቲያትር ችሎታዋን ያረጋገጠችበት ቦታ ብቻ ሳይሆን፣ ከቲያትሩና ከሷም ትርካ ለመረዳት እንደሚቻለው ታላቋ እህታችን የቱን ያህል የአገርና የህዝብ ፍቅር እንዳላት ነው መረዳት የሚቻለው። ጤንነቱንና ብርታቱን እንዲሰጣት እንመኝላት።

በተረፈ ይህ ዐይነቱ በእነዚህ ዐይነት ታላላቅ ተዋንያን የሚከናወነው ቲአትር የቱን ያህል በተመልካቹ ጭንቅላት ውስጥ ሰርጎ በመግባት ለስልጣኔ እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው እንደሚችል መረዳቱ ከባድ ነው። ለማለት የሚቻለው የአብዛኛው አድማጭ ወይም ተመልካች ተመስጦው ይበልጥ በአፄው ጀግንነትና የአንድነት ፈላጊነት ላይ ብቻ ያዘነበለ ነው የሚመስለው። በትዕይንቱ ላይ ያልቀረበው አፄው በጊዜው ያነሱት የነበረው የጠነከረ ድርጅትና የሚከተላቸው ህዝብ ያለመኖር፣ በተለይም ደግሞ ለአንድ አገር ዕድገትና አንድነት መሰረቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ሁለ-ገብ ዕድገት አስፈላጊነታቸው ጎልቶ ባለመውጣቱ የታዳሚውን አስተሳሰብ የበለጠ በጀግንነታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩር ሊያስገድደው ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል። ያም ተባለ ይህ፣ ይህ ዐይነቱ ቲያትር ወቅታዊና፣ ከቲያትሩም እንደታየው የማይተባበር፣ በፕሪንስፕልና በዕምነት የማይመራ፣ ለህሊናው ተገዢ ያለሆነ የህብረተሰብ ኃይል ባየለበት አገርና፣ ከመደማመጥ ይልቅ ወደ ጠብ በማምራት አንዱ ሌላውን በሚንቅበትና በሚያንቋሽሽበት አገር ውስጥ ምንም ዐይነት ስራ መስራት እንደማይቻል ነው ቲያትሩ የሚያስተምረን። የቲያትሩም ዋና መልዕክት፣ በአንድ በኩል ወደ ኋላ ተመልሰን የታሪክን አስቸጋሪ ሂደትና፣ በተገለጸላቸውና ባልተገለጸላቸው ኃይሎች መሀከል የነበረውን ትንቅንቅ እንድንቃኝ የሚጋብዘን ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ወደፊት እንድናይና አገራችንን የሳንይስና የቴክኖሎጂ፣ የጥበብና የስነ-ጽሁፍ፣ ባለቤት ማድረግ እንዳለብንና፣ ይህ ራዕይ ዕውን እስካልሆነ ድረስ ዕውነተኛ ህዝባዊ ነፃነት ሊሰፍን እንደማይችል ነው። ስለሆነም የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን እየተሰመጣጠሩ የጨለማውን ዘመን እንዳያረዝሙብን ከፈለግን በንቃትና በታታሪነት መስራት እንዳለብን ነው የቲያትሩ ደራሲና ተዋንያኑ እንድናስብ የሚጋብዙን። ስለዚህም የቲአትሩ መልዕክት የሚሆን የማይሆን መሰናክል በመፍጠር የህዝብን ሰቆቃ አናብዛው፤ የስቃዩንም ዘመን አናርዝምበት ነው የሚለን። በተጨማሪም ሰለጠነ በሚባለው ዓለም አንታለል፤ በአንድ አገር ውስጥ ዕድገት ሊመጣና አንድነትም ሊጠንክር የሚችለው በራስና በህዝብ ላይ ብቻ ከፍተኛ ዕምነት ሲጣል ነው። የቲያትሩ መልዕክትም ይህ ነው።

ከዚህ በተረፈ ይህ ዐይነቱ ቲአትር በርሊን ከተማ መጥቶ እንዲታይ ላደረጉት የኢትዮ-በርሊን በህግ የታወቀ ማህበር(Ethio Berlin e.V.) ኃላፊዎችና አባሎች፣ እንዲሁም ዝግጅቱ ድምቀት እንዲኖረው ደፋ ቀና ላሉት እህቶቻችንና ወንድሞቻቸን ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል እላለሁ። በተጨማሪም በጥቂት ሰዓታት ልምምድ ብቻ ካለብዙ ዝግጅት ቲያትሩን በማጀብ ድምቀት ለሰጡት የበርሊን ተዋንያን ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል። ቲያትሩ ካለቀ በኋላ የኢትዮ-በርሊን አባሎች፣ በተለይም ውድ እህቶቻችን ምሽቱ በጥሩ ሁኔታ እንዲከናወንና እንድንዝናና ብዙ ነገሮች አዘጋጅተው በማቅረብና የቲአትሩንም ተዋንያን ለማስደሰት በመቻላቸውና ብዙ ነገሮችን ረስተን ጥሩ እንቅልፍ እንዲወሰድን ለማድረግ በመብቃታቸው በዚህ አጋጣሚ ምስጋናዬ ይድረሳቸው እላለሁ። ብዙ ትዝታዎችን ቀስቅሰውብናልና።

 

                                                                              ፈቃዱ በቀለ ከበርሊን ከተማ

                                                                             fekadubekele@gmx.de