የአገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ክልሎችና በሕዝቦች መካከል እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መፍጠር አለመቻሉን፣ ሰሞኑን ይፋ የሆነ የዓለም ባንክ ጥናት አመለከተ፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት አሥር ዓመታት ባለ ሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዘገቧን፣ ከዚያ ቀደም በነበሩ ዓመታት በታዩ መነቃቃቶች እ.ኤ.አ. በ2000 የነበረው 55.3 በመቶ የድህነት መጠን፣ እ.ኤ.አ. በ2011 ወደ 33.5 በመቶ ማውረድ እንዳስቻለ ይገልጻል፡፡

ይህም ማለት በአሁኑ ወቅት ከሚገመተው 100 ሚሊዮን የአገሪቱ ሕዝብ ውስጥ 33 በመቶ የሚሆነው ከድህነት ወለል በታች ማለትም በቀን ከ1.9 ዶላር በታች ገቢ እንደሚያገኝ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ ቢሆንም በዓለም ባንክ ጥናት መሠረት፣ አሥር በመቶ የሚሆኑት በመጨረሻው እርከን ላይ የሚገኙ ድሆች ዕለታዊ የፍጆታ መጠን ከማደግ ይልቅ አሽቆልቁሏል፡፡

ጥናቱ እንደሚያመለከተው፣ የድህነት መጠኑ በታሪካዊ አመጣጣቸው ወደኋላ ቀርተዋል በሚባሉት የሶማሌ፣ የአፋር፣ የጋምቤላና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ ይህ ቢሆንም በታሪካዊ አመጣጣቸው ወደኋላ ያልቀሩት በተለይም በኦሮሚያና በደቡበ ክልሎች የድህነት መጠናቸው ሰፊ መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል፡፡

በዓለም ባንክ ከፍተኛ ኢኮኖሚስት የሆኑት ማይክል ጊገር፣ የልማት እንቅስቃሴው ሁሉንም የአገሪቱ አካባቢዎችና ነዋሪዎች ያካተተ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በድሆችና በማደግ ላይ ባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል የሚታየው የኢኮኖሚ ርቀት መጥበብ እንደሚገባው፣ በማደግ ላይ ወደሚገኙ አካባቢዎች የሚያደርሱ የመንገድ መሠረተ ልማት ሽፋኖች በሚዛናዊነት መስፋፋት እንደሚገባቸውም በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡
የዓለም ባንከ እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት የመደበ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይህንን ቀላል ብድርና ዕርዳታ መጠቀም የምትችለው በክልሎችና በሕዝቦች መካከል እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ስትችል መሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ምንጭ     –   Home